የቅድመ ውሳኔን (ቀዷ ወል-ቀደር) ጽንሰ ሃሳብ በተመለከተ ክፍል -10

1,332 Views

አቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56)፡ ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181)፡ የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

በቀደር ማሳበብ ይቻላልን?

አንዳንድ ሰዎች ለጥፋታቸው ተውበት ከማድረግ ይልቅ በቀደር ያሳብባሉ፡፡ እንዲህ ሲሉም ይደመጣሉ፡- ይህ ተግባር ቀድሞውኑ በኛ ላይ ተጽፎብን ነበር፡፡ እኛ ደግሞ ከተጻፈው መውጣት ስለማንችል ለዛ ነው የፈጸምነው!፡፡ ለዚህ የተሳሳተ ምክንያት ምላሹም በአላህ ፈቃድ የሚከተለው ይሆናል ኢንሻአላህ፡፡

1ኛ/ አላህ ምድራዊ ሲሳያችንን ቀድሞ ወስኖታል፡፡ እሱ ባወቀውና በወሰነው ልክ ተቀምጧል፡፡ ከዕውቀቱ ሊወጣ የሚችል አዲስ የሆነ ‹ጉርሻ› እንኳ የለንም፡፡ ከመሆኑም ጋር ስራን እንድንሰራና ሪዝቃችንን እንድንፈልግ አዞናል፡፡
ምድራዊ ቆይታችንን (ዕድሜ) መልአኩ በእናታችን ማኅፀን ጽንስ እያለን እንዲጽፍና እንዲወስን ከአላህ ዘንድ ታዟል፡፡ አላህ ዘንድ ከታወቀውና ከተጻፈልን ዕድሜ ውጭ የምንኖረው ትርፍ ጊዜ የለንም፡፡ ከመሆኑም ጋር እራሳችንን ከአደጋ እንድንከላከል፣ ለጉዳት ከሚዳርጉ ነገራት እንድንርቅ፣ ስንታመምም መድኃኒትን እንድንጠቀም ታዘናል፡፡

እንደዚሁም ፍጻሜአችን ምን እንደሆነ አላህ ዘንድ የታወቀና ተወስኖ የተቀመጠ ነገር ነው፡፡ ከዚህም ጋር የአላህን ትእዛዝ አክብረን በመልካም ስራ ላይ እንድንገኝ እና እራሳችንን ከኃጢአት እንድናርቅ፡ ኃጢአት ላይ በወደቅን ጊዜ ደግሞ በተውበት እንድንመለስ ታዘናል፡፡
እንግዲያውስ ለሚሰራቸው ክፉ ተግባራት በቀደር የሚያሳብበውን ሰው፡- ለምን በሪዝቅህና በጤናህስ ጉዳይ ቀደርን አታሳብብም? ድኃ መሆንህ ቀደር ከሆነ፡ ይህን ድኅነትህን በሐብት ለመቀየር መስራቱ ምን ያደርግልሀል? መታመምህ ቀደር ከሆነ፡ በጤና ለመቀየር በማሰብ በየፋርማሲውና ክሊኒኩ፡ ላይ ታች ማለቱ ምን ይጠቅምሀል? በማለት ልንጠይቀው ይገባል፡፡
ሲሳይን በመፈለግ በአላህ እገዛ ድኅነትን በሐብት መለወጥ ከተቻለ፣ መድኃኒትን በመጠቀም በሽታን በጤንነት መቀየር ከተቻለ፣ ታዲያ ኃጢአትንስ ተውበት በማድረግና አላህን ይቅርታ በመጠየቅ ወደ ሐሰናት መቀየር አይቻልምን? አንዱን በሌላው ለመተካት መልፋት በሪዝቅና በጤና ጉዳይ ብቻ ነው ያለው ማው? ኃጢአት መስራቴ ቀደር ነው ብለህ የምታመካኝ ከሆነና ተውበት ለማድረግ የማትጥር ከሆነ፡ ቀዷ ወል-ቀደር ኃጢአት ላይ ብቻ አይደለምና፡ ድኅነቴም መታመሜም ቀደር ነውና በሐብትና በመድኃኒት ልለውጠው አልችልም ብለህ እጅ ስጥና አርፈህ ተቀመጥ! መባል አለበት፡፡ አንዱን ጥሎ ሌላውን ጥሎ አይሰራምና፡፡ ደግሞስ ኃጢአት መስራትህ ቀደር መሆኑን ማን አሳወቀህ? ሳትሰራው በፊት ተነግሮህ ነበርን? ስለዚህ በማናውቀው የገይብ ጉዳይ ጣልቃ ገብተን ለጥፋታችን በቀደር ማሳበቡ አይበቃልንም፡፡ በሌላ ጥፋት ድጋሚ ሊያስጠይቀን ይችላልና፡፡

2ኛ/ ለሚሰራው ኃጢአት በቀደር የሚያሳብብ ሰው ከራሱ ሀሳብ ጋር የተምታታ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው አንድ ሌላ ሰው በራሱ ላይ ወሰን ቢያልፍበት፣ ንብረቱን ቢቀማው፣ ደሙን ቢፈሰው ወይም በክብሩ ቢሳለቅበትና ከዛም ይህ ወሰን አላፊው ሰው ለዚህ ግለሰብ፡- ይቅርታ! ይህን ሁሉ ያደረግሁብህ ፈልጌ ሳይሆን አላህ የወሰነብህ ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ እኔን እንዳትቆጣኝ ቢለው፡ ምክንያቱን ይቀበለዋልን? ወይስ የበለጠ ያስቆጣዋል? የወሰን አላፊውን ሰውዬ በቀደር ማሳበብ እንደ ዑዝር ካልተቀበለው፡ እንዴት ለራሱ ጊዜ በአላህ ህግ ላይ ወሰንን ሲያልፍ ቀደርን እንደ ዑዝር ማቅረብ ይፈልጋል? ይህ ከራስ ሀሳብ ጋር መጋጨት አይደለምን?

وقد ذكر أن أمير المؤمنين عمر بن الخطاب رضي الله عنه أتي بسارق فأمر بقطع يده، فقال السارق: مهلا يا أمير المؤمنين، والله ما سرقت إلا بقضاء الله وقدره، فقال عمر : ونحن نقطع يدك بقضاء الله وقدره. فاحتج عليه عمر بما احتج به هو على عمله السيئ. مجموع فتاوى ورسائل ابن عثيمين: الجزء الخامس 234.

አሚረል ሙእሚኒን ዑመር ኢብኑል-ኸጥጣብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ዘንድ አንድ ሌባ ተይዞ ቀረበ፡፡ እሳቸውም፡- “እጁን ቁረጡት! በማለት ትእዛዝ ሰጡ፡፡ ሰሪቂውም መላ ያገኘ መስሎት፡- ‹‹ያ አሚረል ሙእሚኒን እባክዎ ይረጋጉ! በጌታዬ በአላህ ይሁንብኝ እኔ የተቀደረብኝ (የተወሰነብኝ) ሆኖ እንጂ አልሰረቅሁም›› አለ፡፡ እሳቸውም፡- ‹‹እኛም እጅህን በተቀደረው (በተወሰነው) መሰረት እንቆርጠዋለን አሉት››” (መጅሙዕ ፈታዋ ወረሳኢል ሸይኽ ኢብኑ ዑሠይሚን ቅጽ 5 ገጽ 234)፡፡

3ኛ/ ሰዎች በፈቃዳቸው ለሚተገብሩት የኃጢአት ተግባር በቀደር ማሳበብ እውነት እና አግባብነት ያለው ነገር ነው ማለት፡ የአላህ ወዳጆችንና ጠላቶችን በእኩል ወደ ማየት ያመጣናል፡፡ አማኞችን ከከሀዲዎች ጋር ማመሳሰልን ያስይዘናል፡፡ የጀነት ሰዎችንና የጀሀነም ሰዎችን መለየት ያቅተናል፡፡ ምክንያቱም የአማኞች እምነትም ሆነ የከሀዲዎች ክህደት ሁለቱም ቀደር ነውና ስለሚባል፡፡ አላህ ግን በቃሉ እንዲህ ይላል፡-

” أفنجعل المسلمين كالمجرمين * ما لكم كيف تحكمون ” سورة القلم 36-35
“ሙስሊሞቹን እንደ ከሐዲዎች እናደርጋለን? ለናንተ ምን (አስረጅ) አላችሁ? እንዴት ትፈርዳላችሁ።” (ሱረቱል ቀለም 68፡35-36)፡፡
“لا يستوي أصحاب النار وأصحاب الجنة أصحاب الجنة هم الفائزون” سورة الحشر 20
“የእሳት ጓዶችና የጀነት ጓዶች አይስተካከሉም፤ የጀነት ጓዶች እነሱ ምኞታቸውን አግኚዎች ናቸው።” (ሱረቱል ሐሽር 59፡20)፡፡

እውነታው ግን፡ ሰዎች አማኝና ከሀዲ ተብለው ለሁለት የተከፈሉት በተሰጣቸው ነጻ ፈቃድ፡ በቀረበላቸው ፈተናና እነሱም ባስመዘገቡት ውጤት ልክ መሆኑ ነው፡፡ አላህ ይህን ሁሉ ተግባር አስቀድሞ ማወቁና በለውሐል መሕፉዝ ወስኖ ማኖሩ፡ ማንም ሊያሳብብበት አይችልም፡፡ ቀድሞ የተጻፈው ምን እንደሆነ ማወቅ ስለማይችል፡፡ ደግሞም ቀድሞ የተጻፈው የሱን ነጻ ፈቃድ የማይጋፋ በመሆኑና፡ የቂያም ቀንም ፍርድ የሚሰጠው ሰውየው በሰራው እንጂ ቀድሞ በተጻፈው ባለመሆኑ ማለት ነው፡፡

4ኛ/ ቀደር ከሰዎች ጥፋት በፊት የቀደመና የተጻፈ መሆኑ፡ ለኃጢአተኞች ማሳበቢያ ምክንያት መሆን ቢችል ኖሮ፡ አላህ ከዚህ በፊት በኃጢአታቸው ሰበብ ያጠፋቸው የነቢያት ህዝቦችም ዑዝር ሊሆናቸው በቻለ ነበር፡፡ እነሱም በቅጣቱ በመጥፋታቸው ተበድለዋል ማለት ይቻል ነበር፡፡ እውነታው ግን እንደዛ ባለመሆኑ ጌታቸው አላህም አልበደላቸውም፡ ቀደርም ለነሱ መከላከያ ምክንያት ሊሆናቸው አይችልም፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-

” وما ظلمناهم ولكن ظلموا أنفسهم…” سورة هود 101
“እኛም አልበደልናቸውም፤ ግን ነፍሶቻቸውን በደሉ…” (ሱረቱ ሁድ 11፡101)፡፡
” فكلا أخذنا بذنبه..” العنكبوت: 40
“ሁሉንም በሐጢአቱ ያዝነው…” (ሱረቱል ዐንከቡት 29፡40)፡፡
ምንጭ፡- አል-በያን ፊ አርካኒል ኢማን ፡ሸይኽ አሕመድ ቢን መጅድ መኪይ ገፅ 469-471.

5ኛ/ ለማንኛውም አይነት የኃጢአት ተግባር ‹‹አላህ የቀደረብኝ ነው!›› ብሎ ማሳበብ ትክክለኛ ምክንያት

ነፍስ እንዴት ተውበት ያደረጋል? ከተውበት መስፈርቶችስ አንዱ ‹ነዳማህ› (ጸጸት) አይደለምን? አላህ ትክክለኛ ግንዛቤን ይወፍቀን፡፡

ወአኺሩ ዳዕዋና ዐኒል-ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡