የተረሳው መንፈስ ቅዱስ

843 Views

እንደ ክርስቲያኖች እምነት መሠረት ከሥላሴ አካላት ውስጥ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ እንደ አብና ወልድ እኩል መለኮታዊ ስልጣን ያለው አምላክ ነው ብለው ያምናሉ። እንዳለመታደል ሀኖ ግን መንፈስ ቅዱስ የሚገባውን ያክል ቦታ አልተሰጠውም። አንዳንዴም እንዴውም ሌሎች አካላት ሁሉ ተጠቅሰው እሱ ሲረሳ እንታዘባለን። እንዴው መንፈስ ቅዱስ አምላክ የተባለው ሁሉ “አምላክ ሁለት ነው” እንዳይባል ተብሎ ብቻ የኃለኛው ጉባኤ የጨመረው ይመስላል። ይህንን ጥርጣሬ እስኪያረጋግጥልን ድረስ መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያኖች ልብም ሆነ በመጽሀፍ ቅዱስ ከአብና ወልድ ጋር እንኳን እኩል የማይታወስ ባይተዋር ተደርጓል። ማቴዎስ በወንጌሉ እንዲህ ማለቱ ተፅፏል፦

“ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም።”
— ማቴዎስ 11፥27

በዚህ ምስል ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ተቆርጦ ቀርቷል። በአንቀፁ ላይ ተቆርጦ መቅረቱ ብቻ ሳይሆን የመለኮታዊነቱ ፅንሰሀሳብም ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ምክንያቱም በዚህ አንቀፅ መሠረት ስለ አብ የሚያውቀው ወልድ ብቻ ሲሆን ስለወልድም የሚያውቀው አብ ብቻ ነው። ማርክ ግሪሰርና ባልደረቦቹ በህብረት ባዘጋጁት “Reconsidering the Cornerstone of the Christian Faith” በተሰኘው መጽሀፍ ገፅ 584 ላይ ይህንን አስመልክቶ እንዲህ ይላሉ፦

“መንፈስ ቅዱስ በትክክል ራሱን የቻለ አካል ከነበረና ከሶስቱ አካላት የተለየ አምላክ ከነበረ (በዚህ ንግግሩ መሠረት) ወይ ኢየሱስ ያንን አያውቅም ነበር ማለት ነው፤ አልያም ለመንፈስ ቅዱስ በሚሰጠው ክብር ዙሪያ ቋሚ መርህ አልነበረውም ማለት ነው” (1)

የማቴዎስ 11፥27ን መልዕክት አስመልክቶ ክርስቲያኖች የሚከተሉት ሁለት ምርጫዎች ይኖሯቸዋል፦

1- ሥላሴ እውነት ነው፤ መንፈስ ቅዱስም ከሥላሴ አካላት ውስጥ አንዱ የሆነ አምላክ ነው። ነገር ግን ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን አስመልክቶ በሚናገራቸው ንግግሮች ውስጥ ቋሚነት/Consistency/ የለም። እሱን በተመለከተ የሚያውቀው አብ ብቻ እንደሆነ ሲናገርም አማኙን አታሏል ማለት ነው።

2. ኢየሱስ በማቴዎስ ወንጌል ንግግሩ ቋሚ መርህን ካንፀባረቀና አታላይም ካልነበር መንፈስ ቅዱስ አምላክ አልነበረም፤ ሥላሴም ፈጠራ ነው ማለት ነው።

ሀሳቡን ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ በሚከተለው መንእሳዊ አመክንዮት ተነስተን በአጭር ሲሎጂዝም እናስቀምጠው፦

ምንስኤ 1፦ ሥላሴ ሶስት አካላት ሲሆኑ እያንዳንዱ አካል በራሱ ምሉዕ የሆነ እውቀት ያለውና አንድኛው ስለ አንድኛው እርስበርስ የሚተዋወቅ ነው።

ምንስኤ 2፦ ሦስተኛው አካል ማለትም መንፈስ ቅዱስ እንደ ማቴዎስ 11፥27 ገለፃ መሠረት ስለ አብና ወልድ የሚያውቀው ነገር የሌለ ሲሆን ተነጥሎ ባይተዋር ተደርጓል።

መደምደሚያ፦ መንፈስ ቅዱስ አምላክ አይደለም፤ ሥላሴም መሠረተ ቢስ አስተምህሮ ነው።

ስኮት ሐንና ኩርቲስ ሚች አዲስ ኪዳንን ባብራሩበት ስራቸው የማቴዎስ 11:27ን አንቀፅ ሲያብራሩ፦

“አብና ወልድ የተገለፁበት እውቀት በሥላሴ አማካኝነት አንድ የሆኑበት እውቀት ነው። ይህም ማለት የተጋሩት መለኮታዊ እውቀት የተጋሩትን መለኮታዊ ባህሪን ይጠቁማል” (2)

በዚህ ገለፃ መሠረት መንፈስ ቅዱስ ከዚህ ክብር ገሸሽ ተደርጓል። በትክክልም መልዕክቱ ስለመለኮታዊ አንድነት ከሆነ “በብቻ” ሳይታጠር ሶስተኛው አካል መንፈስ ቅዱስም አብሮ መጠቀስ ነበረበት። ይህ አንቀፅ የመንፈስ ቅዱስን የተረሳ ማንነት ከማጋለጡም በላይ አስተምህሮ- ሥላሴን ቅርቃር ውስጥ የከተተ የኢየሱስ ንግግር እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል።

◾️ማስታወሻዎች

[1] Graeser, M. H., Lynn, J. A. & Schoen (2010). One God & One Lord: Reconsidering the Cornerstone of the Christian Faith. Indiana: Spirit & Truth Fellowship international. p. 584

[2] Hahn, S. & Mitch, C. (2010). Ignatius Catholic Study Bible: New Testament. San Francisco: Ignatius Press. p. 26

(የሕያ ኢብኑ ኑህ)