የቅድመ ውሳኔን (ቀዷ ወል-ቀደር) ጽንሰ ሃሳብ በተመለከተ ክፍል -3

2,241 Views

በአቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡

በሁለት ተከታታይ ክፍሎች ከስድስቱ የእምነት ማእዘናት አንዱ የሆነውን በቀዷ ወል-ቀደር ማመንን አስመልክቶ ሊነሱ የሚችሉ ብዥታዎችን በአላህ ፈቃድ ለማጥራት የተወሰነ ሙከራ ተደርጓል፡፡ በነዚህ ሁለት ተከታታይ ክፍሎች ውስጥም፡-

ሀ/ ሰው ነጻ ፈቃድ ያለው ፍጡር መሆኑን፣ በተሰጠው የሰውነት መሳሪያ ተጠቅሞ የሚፈልጋቸውን ነገራት ያለምንም አስገዳጅ ኃይል ሊፈጽም እንደሚችልና፡ በነዚህም ስራዎቹ ምክንያት ኃላፊነትን ወስዶ በመጨረሻው ዓለም ተጠያቂ እንደሚሆን፡ የሰራው መልካም ከሆነም ጌታው በመልካም ምንዳውን (ደሞዙን) እጥፍ ድርብ አድርጎ እንደሚሰጠው፡ የሰራው መጥፎ ከሆነ ደግሞ የጌታው እዝነት ካልደረሰው በስተቀር በእሳት እንደሚቀጣው ተመልክተናል፡፡

ለዚህም ሀሳብ አጋዥ ይሆነን ዘንድ፡ ስድስት የሰውነት ተቀዳሚ ብልቶችንና (ክፍለ-አካላትን) ፍላጎት የሚባለውን እንደ ምሣሌ ጠቅሰን በህይወታን ውስጥ የምንተገብርባቸውን ነገራት አንስተን አይተናል፡፡ ከዚህ በኋላም ‹‹እኔ ነጻ ፈቃድ የሌለኝ ፍጡር ነኝ!›› በማለት ለምንሰራው ጥፋት በቀደር ማሳበብ አግባብ አለመሆኑን አውቀናል፡፡

ለ/ በመቀጠልም ነገራት ሁሉ ቀድመው ከተወሰኑ፡ የኛ ልፋት ትርጉሙ ምንድነው ታዲያ? ለሚሉት፡ ምላሻችን፡- የኛ ልፋት ትርጉሙና ዓላማው፡- የጌታችንን ትእዛዝ፡ በታዘዝነው መሰረት ፈጽሞ መገኘትና እንዲሁም የነጌውን ዓለም የአላህን ውድ ስጦታ ‹‹ጀነትን›› ተስፋ ማድረግ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡

ሐ/ አያይዘንም ቀዷ ወል-ቀደር ማለት፡- በዓለማችን የሚከናወን የማንኛም አካል ክንዋኔ፡ ቀድሞውኑ አላህ ዘንድ የታወቀ፣ በለውሐል መሕፉዝ ላይ የተጻፈ፣ ከአላህ ፈቃድና ይሁንታ እንዲሁም ከቁጥጥሩ ሊወጣ የማይችል ነገር መሆኑን አምኖ መቀበል ማለት ነው የሚል ትርጉምን ተመልክተናል፡፡

መ/ በመጨረሻም ታዲያ ሁሉ ነገር ቀድሞ የታወቀና የተጻፈ ከሆነ፣ እንዲሁም ጊዜው ደርሶ በተግባር እውን ሲሆን በአላህ ፈቃድ እንጂ ያለ እርሱ ፈቃድ ሊሆን አይችልም ከተባለ፡ እኛ ነጻ ፈቃድ አለን ማለቱ ምን ትርጉም አለው? የሚለውን የፍትሕ ጥያቄ አንስተን፡ በምላሹም፡- አላህ ነገራትን አስቀድሞ አወቃቸው፡ እንዲሁም በለውሐል መሕፉዝ ወስኖ ጻፋቸው (እንዲጻፍ አዘዘ) ማለት፡ የሰውን ነጻ ፈቃድ በምንም መልኩ ትርጉም አልባ የሚያደርግ አይደለም፡፡ ይልቁኑ ይህ ሰው የተባለው ፍጥረት ዛሬ ላይ በዚህች ምድር ተገኝቶ በተሰጠው ነጻ ፈቃድ የፈለገውን ነገር ማድረጉን፡ እሱን የፈጠረው አምላክ አላህ ግን ዓለማትን ከመፍጠሩ በፊት ቀድሞውኑ ያወቀውና በለውሐል መሕፉዝ ላይ ያሰፈረው እንደሆነና፡ ይህም (የጌታችን ዕውቀት የሰውን ስራ መቅደሙ) አላህን በእጅጉ የሚያስከብረው፡ ምን አይነት ሁሉን ዐዋቂ ጌታ አምላክ እንደሆነ በማሰብ ‹ሱብሐነከ ረቢ!› በማለት ሊወደስ የሚገባው መሆኑን፡ በደካማው ፍጡር (መምህር) የተማሪዎቹን የፈተና ውጤት ከፈተና በፊት መገመት መቻሉ የአስተማሪውን ጉብዝና የሚያሳይ እንጂ የሚያስወቅሰው እንዳልሆነ በምሣሌ አይተናል፡፡

ሠ/ ለዛሬ ባሸጋገርነው ጥያቄ ደግሞ፡- እንግዲያውስ ሰው ነጻ ፈቃድ ያለው ፍጡር ከሆነ፡ የፈለገውን ነገር ሁሉ በራሱ ፈቃድ ብቻ ነው የሚያከናውነው ማለት ነውን? የሚለውን ጥያቄ አንስተን፡ ምላሹን በቀጣዩ ተባብለን ነበር፡፡ ዛሬ ላይ በአላህ ፈቃድ ደርሰናልና አልሐምዱ ሊላህ፡፡ ምላሹን ይከታተሉ፡-

ሰው የሚከውናቸው ተግባራት በራሱ ነጻ ፈቃድ ብቻ ነው ወይስ ተገዶ? የሚለውን በአግባቡ ለመረዳት፡ ቀዷ ወል-ቀደር በሰው ሕይወት ውስጥ ጊዜው ደርሶ እውን ሲሆን (ሲከሰት) በስንት አይነት መንገድ እንደሚከሰት ማየቱ ለመልሱ አጋዥ ይሆናል፡፡ እንደኛ ሙስሊሞች መረዳት፡- ቀዷ ወል-ቀደር በሰው ሕይወት ውስጥ የሚከሰተው በሁለት አይነት መንገድ ነው፡፡ እነሱም፡-

ሀ. ያለ ሰው ነጻ ፈቃድና ጣልቃ ገብነት
ለ. በሰዎች ነጻ ፈቃድና ሰበብ መሰረት

ሀ. የሰው ምርጫ የሌለበት፡- ይህ አይነቱ የቀደር ክፍል፡ የሰዎችን ምርጫ ያላካተተ፡ በጉዳዩ ላይ ሰዎች ምንም አይነት ጣልቃ ገብነት ወይንም ድርሻ የሌላቸው፡ ወደውና ፈቅደው ሳይሆን፡ ተገደውና ከአቅማቸው በላይ ሆኖ የሚከሰት (የሚሆን) የቀደር ክፍል ነው፡፡ ለምሣሌ፡-
መወለድና መሞት፣ የጾታ ጉዳይ (ወንድ ወይም ሴት መሆን)፣ የቁመት መርዘምና ማጠር፣ የመልክ መቅላትና መጥቆር፣ ሙሉ ጤናማ አካል ይዞ መወለድና አካለ ጎዶሎ መሆን፣ እንዲሁም የመሳሰሉት፡፡

• ለምን ወደዚህ ዓለም መጣህ? ተብለህ ብትጠየቅ ያንተ መልስ ምንድነው የሚሆነው? አይ! ያኛው ዓለም ስለሰለቸኝ ነው ብለህ ትመልሳለህን? ቀድሞውኑ የት ነበርክና? እንደዛውም የምትሞተውም ፈቅደህና ወደህ አይደለም፡፡ መፈጠርህን በገዛ ፈቃዱ ብቻ በማድረግ አንተን የሰራህና ያስገኘህ አምላክህ አላህ፡ ምድራዊ ቆይታህንም የሚወስነው እሱ ብቻ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ ያንተ ድርሻ የለበትም፡፡ መቼ እንደምትሞት የሚያውቀውና ወስኖም የሚጽፈው፡ ፈቅዶም የሚያደርገው እሱ ነው፡፡ እንዲህ ይላል ይህ አምላክህ፡-
“ሰዉ፣ ከአሁን በፊት ምንም ነገር ያልነበረ ሲኾን፣ እኛ የፈጠርነዉ መኾኑን አያስታዉስምን ?” (ሱረቱ መርየም 19፡67)፡፡
“ለማንኛይቱም ነፍስ በአላህ ፍርድ ቢሆን እንጅ ልትሞት አይገባትም፤ (ጊዜዉም) ተወስኖ ተጽፏል…” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡145)፡፡

• ደግሞስ ያንተና ያንቺ ጾታ ለምን ወንድና ሴት ሆነ? ተብላችሁ ብትጠየቁ፡ ምን ትመልሳላችሁ? አይ! ሆቢያችን (ዝንባሌያችን) ስለሆነ ነው ብላችሁ ትመልሳላችሁን? ቀድሞውኑ ወንድ ወይም ሴት መሆናችሁን ያወቃችሁት ባደጋችሁ ጊዜ እንጂ መች በተፈጠራችሁበት ሰዓት ሆነና? አምላካችሁ አላህ እሱ እንደሻው አድርጎ፡ አንቺን ሴት፡ አንተን ደግሞ ወንድ አድርጎ ፈጥሯችኋል፡፡ ቅዱስ ቃሉም እንዲህ ይላል፡-
“እርሱ ያ በማሕፀኖች ዉሰጥ እንደሚሻ አድርጎ የሚቀርጻችሁ ነዉ። ከርሱ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፤ አሸናፊዉ ጥበበኛዉ ነዉ።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡6)፡፡
“የሰማያትና የምድር ንግሥና የአላህ ነው፤ የሚሻውን ይፈጥራል፤ ለሚሻው ሰው ሴቶችን (ልጆች) ይሰጣል፤ ለሚሻውም ሰው ወንዶችን ይሰጣል። ወይም ወንዶችና ሴቶች አድርጎ ያጠናዳቸዋል። የሚሻውንም ሰው መካን ያደርገዋል፤ እርሱ ዐዋቂ ቻይ ነውና።” (ሱረቱ-ሹራ 42፡49-50)፡፡

• እንደዚሁም የመልኮቻችን መለያየት (ቀይ፣ ጥቁር፣ ነጭ…) የሰው ዘር መገኘት፡ በኛው ምርጫ የሚከናወን ሳይሆን፡ በአምላካችን አላህ ፈቃድና ፍላጎት ብቻ የሚሆን ነገር ነው፡፡ ይህም ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-

“ሰማያትንና ምድርንም መፍጠሩ፥ የቋንቋዎቻችሁና የመልኮቻችሁም መለያየት ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው፤ በዚህ ውስጥ ለዐዋቂዎች ታምራቶች አሉበት።” (ሱረቱ-ሩም 30፡22)፡፡

ሌሎችንም ምሳሌዎች በዛው መልኩ መመልከት ይቻላል፡፡ በጥቅሉ በዚህ አይነቱ የቀዷ ወል-ቀደር ክፍል ላይ የጌታችን አላህ መለኮታዊ ፈቃድና ፍላጎት ብቻ እንጂ፡ የሰው ነጻ ምርጫ ጣልቃ-ገብ አይደለም፡፡ ስለሆነም በዚህኛው ክፍል ለሚከሰት ማንኛውም አይነት ክስተት፡ ሰው ጌታው ዘንድ በኃላፊነት ተጠያቂ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሱ ድርሻ የለበትምና፡፡ ባይሆን ከሱ የሚጠበቀው፡ የአላህን ውሳኔ ወዶ መቀበል ነው፡፡ በጌታው ውሳኔ (ቀደር) ላይ ተቃውሞን እንዳያሰማ ነው፡፡

ጌታዬ አላህ፡- ለምን ሰው አድርጎ ሰራኝ? ለምን ጾታዬ ወንድ ወይም ሴት ሆነ? ለምን ጥቁር አፍሪካዊ ሆኜ ተፈጠርኩ? እና የመሳሰሉ የቅሬታና የተቃውሞ ድምጾች በሀሳብም ሆነ በንግግር ፈጽሞ ከሱ ሊሰማ አይገባም፡፡ ባይሆን ከሱ የሚጠበቀው፡- አምላኬ አላህ ሆይ! እኔን ሰው አድርገህ፣ እንዲሁም ጾታዬን (ወንድ ወይም ሴት) እንዲሆን ፈቅደህ፣ በዘሬም ጥቁር ሰው ወይም ነጭ ወይም ቀይ አድርገህ ስለሰራኸኝ ከልቤ አመሰግንሀለሁ፡፡ ያንተንም ውሳኔ ወድጄ ተቀብያለሁ እንዲል ነው፡፡

ለ. የሰው ምርጫ ያለበት፡- በዚህኛው ክፍል ላይ ደግሞ፡ ጉዳዩ አሁንም ቀደር ሆኖ፡ ነገር ግን የሰው ነጻ ፈቃድ ጣልቃ-ገብነት ያለበት፡ ሰው ፈቅዶና መርጦ የሚተገብረው፡ ተገዳጅ ያልሆነበት የቀደር አይነት ነው፡፡ ለምሣሌ፡-

ከተፈቀዱ ነገራት፡- መብላት መጠጣት፣ መቆም መቀመጥ፣ መስጠት መቀበል፣ መሄድ መመለስ እና የመሳሰሉት፡፡
ከታዘዝናቸው ነገራት፡- ሶላት መስገድ፣ ረመዷንን መፆም፣ ዘካን ማውጣት፣ ሐጅ ማድረግና የመሳሰሉት፡፡
ከተከለከልናቸው ነገራት፡- መስረቅና መዋሸት፣ አስካሪ መጠጦችን መጠቀም፣ ዝሙት መፈጸምና የመሳሰሉት፡፡
በዚህ አይነቱ የቀደር ክፍል ላይ ሰው ነጻ ፈቃድ አለው፡፡ የፈለገውን መርጦ ለመተግበር፡ ያልፈለገውን ደግሞ ለመተው የሚያስችል ፈቃድና ውስን ኃይል ተሰጥቶታል፡፡ ስለዚህም በሚሰራቸው ስራዎች ሁሉ ኃላፊነትን በመውሰድ ነጌ በጌታው ዘንድ ስለ ስራው ተጠያቂ ይሆናል፡፡ በእምነትና በመልካም ተግባራት በርትቶ ከተገኘና በዛው ሁኔታ ከሞተ የጌታውን ራሕመት ጀነትን ይጎናጸፋል፡፡ በተቃራኒው በክህደትና በወንጀል ላይ ተዘፍቆ በዛው ሁኔታ ጌታውን ከተገናኘ፡ የጌታውን ቁጣ ጀሀነም እሳትን ይገባታል፡፡

በነዚህ ተግባራት ላይ እኛ ነጻ ፈቃድ ባይኖረን ኖሮ፡ ይህ ሐራም ነው አትቅረቡት! ይህ ደግሞ ሐላል ነው! ከፈለጋችሁ ተጠቀሙበት ካልሆነም ተዉት! ያኛው ደግሞ ዋጂብ ነውና እንደታዘዛችሁት ስሩ! ፈጽሙ! ብሎ ጌታችን ወደኛ ትእዛዝ ማስተላለፉ ምን ትርጉም ይኖረዋል? መጽሐፍት ከሱ ዘንድ የወረዱት፡ ነቢያት ከሰው ተመርጠው የተላኩት ፈቃድ የሌለውን አካል ለማናገር ነውን?

ሰው አላህ ዘንድ ተጠያቂ የሚሆነው በዚህኛው የቀደር ክፍል ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያውን የቀደር ክፍል ወዶ ከመቀበል ውጪ ሌላ ነገር አልተጠየቀም፡፡ በራሱ ላይ ሊቀይረውም ሆነ ሊያስተካክለው የሚችለው ነገር የለምና፡፡ በሁለተኛው ክፍል ላይ ግን፡ ምንም ጉዳዩ ቀደር ቢሆንም የሱም ድርሻ ስላለበት በኃላፊነት ይጠየቅበታል፡፡ ጥቅምና ጉዳትንም ይጋራበታል፡፡
በነዚህ በሁለቱ የቀደር ክፍሎች መካከል ያለውን ልዩነት በአግባቡ አለመረዳት፡ ሰዎችን ለሁለት ተቃራኒ ስህተት ይዳርጋቸዋል፡፡

አንደኛው፡- ሁለቱንም የቀደር ክፍሎች በአንድ በመመልከትና ልዩነቱንም ባለማስተዋል፡ ሰው ለጌታው ውሳኔ ተገዳጅና ተጎታች ነው፡፡ የራሱ የሆነ ነጻ ፈቃድና ፍላጎት የሌለው፡ አየር ላይ እንደተንሳፈፈ ላባ፡ ንፋሱ ወደፈለገው አቅጣጫ እንደሚያሽከረክረው፡ ይህንንም ሰው ‹ቀደር› እንደ ሮቦት ያንቀሳቅሰዋል የሚል ድምዳሜ ላይ ይደርሳል፡፡
ከዚህ አስተሳሰብ በኋላ ለጌታው ትእዛዝ ከበሬታና ፍርሀት እንዲሁም ታዛዥነት አይኖረውም፡፡ ነፍሲያውና ሸይጧን በኃጢአት ላይ እንዲጨማለቅ ያደርጉትና፡ በስራው ተወቃሽ እንዳይሆን ደግሞ በቀደር እንዲያሳብብ ይገፋፉታል፡፡

ሁለተኛው፡- ይህም ክፍል፡ ሁለቱንም የቀደር አይነቶች በአንድ ይመለከታቸውና፡ ሰው ነጻ ፈቃድ የሌለው ፍጡር እንደሆነ አድርገው መግለጻቸውን በመውሰድ ግንዛቤው ይሳሳትና፡ ቀደርን ይክዳል ያስተባብላል፡፡ እንዲህም ይላል፡- ከአላህ ፍትሐዊነት አንጻር አብሮ ስለማይሄድ ሰውም ተበዳይ የሆነ ስለሚመስል ቀደር የሚባል ነገር የለም የሚል ክህደት ውስጥ ይገባል፡፡
እውነታው ግን ከሁለቱም ግሩፖች ውጪ ነው፡፡ ቀደር የሚባል ነገር አልለ፡፡ መኖር ብቻም አይደለም ከስድስቱ የእምነት ማእዘናት አንድ ማእዘን ነው፡፡ ሰውም ነጻ-ፈቃድ ያለው ፍጡር ነው፡፡ ሰው ምርጫ እንዳለው ለመረዳት ሸሪዓዊ፣ አእምሮአዊና ስሜታዊ ማስረጃዎችን በመጠኑ እንመልከታቸው፡-

ሀ/ ከሸሪዓ፡-

“በክት ፈሳሽ ደምም የእሪያ (አሣማ) ሥጋም በርሱ ከአላህ (ስም) ሌላ የተነሳበትም፤ የታነቀችም ተደብድባ የተገደለችም ተንከባላ የሞተችም በቀንድ ተወግታ የሞተችም ከርሷ አውሬ የበላትም (ከነዚህ በሕይወት ደርሳችሁ) ያረዳችሁት ብቻ ሲቀር ለጣዖታትም የታረደው… በናንተ ላይ እርም ተደረገ…” (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡3)፡፡

በዚህ አንቀጽ ውስጥ ጌታ አላህ በኛ ላይ እርም የተደረጉ የምግብ አይነቶችን ይዘረዝራል፡፡ ይህ በራሱ ምርጫ ያለን ፍጡር ለመሆናችን ትልቅ አስረጂ ነው፡፡ የፈለገውን ነገር በመምረጥ ለመያዝ ወይም ለመተው ፈቃድ የሌለውን አካል፡ እንዴት ይሄ ሐራም ነው! ይሄ ሐላል ነው ብለህ ህግ ትደነግግበታለህ? ከዛም ጌታ አላህ በመቀጠል በዚሁ አንቀጽ ስር እንዲህ ይላል፡-

“…በረኃብ ወቅት ወደ ኃጢያት ያዘነበለ ሳይሆን (እርም የሆኑትን ለመብላት) የተገደደ ሰውም (ይብላ) አላህ መሐሪ አዛኝ ነውና።” (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡3)፡፡

ይህ ሰው ከነዚህ ከተከለከሉት ነገራት (በድርቅ መከሰት) ለመብላት በተገደደ ጊዜ ግን መብላት እንደሚችልና አላህም በይቅርታ በማለፍ እንደ ኃጢአት እንደማይቆጥርበት ይገልጻል፡፡ ምክንያቱም ግለሰቡ ከፈቃዱና ከምርጫው ውጪ ነው፡፡ በረኃቡ ሰበብ እራሱን ከሞት ለመታደግ በወቅቱ ያንን ነገር ከመመገብ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረውምና፡፡

ነገር ግን ያለ-ምንም ረኃብና አስገዳጅ ሁኔታ ሳይፈጠር፡ መሐመድ ካፌ ገብቶ ቡናና ሻይ አዝዞ መጠታት እየቻለ፡ ወይዘሮ አለሚቱ መሸታ ቤት ሄዶ አስካሪ መጠጥ የሚጎነጭ ከሆነ፣ በሕረዲን ሬስቶራንት ገብቶ በአላህ ሥም የታረዱ የሐላል ከብት ስጋ አዝዞ መመግብ እየቻለ፡ ካሰች ምግብ ቤት ተጎልቶ የአሳማና የአላህ ስም ያልተወሳባቸው ሐራም ምግቦችን በማዘዝ የሚመገብ ከሆነ፡ በምርጫው ያደረገው ነውና ተጠያቂ ከመሆን አያመልጥም፡፡

ለ/ ከነጻ አእምሮ፡-
ማንኛውም ንጹህና ያልተዛባ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ሰው፡ ከሰውና ከዛፍ እንቅስቃሴ የሚፈጠሩ ነገራትን መለየት ይችላል፡፡ በኃይለኛ ነፋስ ሳቢያ፡ ከመሬት የተነሳ አቧራ በአፍንጫውና በአፉ ገብቶ ቢያጨናንቀው፣ ወይንም ንፋስ ያነሳው ድንጋይ ጭንቅላቱን ቢፈነክተው፣ ወይም በነፋሱ ሰበብ የተወዛወዘው የዛፉ ቅርፊት አይኑ ላይ ጌዚያዊ ህመም ቢያደርስበት፡ ይህ ሰው እውነት በአቧራውና በድንጋዩ እንዲሁም በዛፉ ቅርፊት ላይ ይቆጣልን? ለመበቀልስ ያስባልን? በፍፁም!!

ምክንያቱም እነዚህ ነገራት የራሳቸው ፈቃድ የሌላቸው፡ ንፋስ በድንገት ከቦታቸው ያንቀሳቀሳቸው መሆናቸው ህሊናው ይነግረዋልና፡፡
ታዲያ ይህ ሰው በአንድ መንደር ሲያልፍ ደግሞ፡ አንድ በውፍረቱም ሆነ በቁመቱ ከሱ ጋር የሚተካከል የሆነ ሌላ መንገድ አላፊ ወደሱ ቢመጣና፡ በጥፊ በርግጫ እያጣደፈ ጉዳት ቢያደርስበት እንደ ቅድሙ የንፋስ አደጋ በዝምታ ያልፋልን? ወይስ በሰውየው ላይ እሱም ማንነቱን ለማሳየትና ለመበቀል ይታገላል? መልሱም፡- ይህን ጥቃት ከራሱ ላይ በቻለው መልኩ ለመከላከል ይታገላል፡፡ በወሰን አላፊው ሰውዬም ድርጊት ይቆጣል፡፡ ከቻለም ለመበቀል ይሞክራል ነው፡፡ ምክንያቱም ያ ወሰን አላፊ ሰውዬ ይህን እርምጃ የወሰደበት በፈቃዱና በምርጫው እንደሆነ ህሊናው ስለነገረው ነው፡፡

ሐ/ ከስሜት ህዋሳት፡-

ሁላችንም በነጻ ፈቃዳችን የምንተገብራቸው ነገራት እንዳሉ ሁሉ፡ እንዲሁም ያለ ፈቃዳችን ተገደን የምንሰራቸው ነገራት መኖራቸውን በውስጣዊ ስሜታችን እንረዳለን፡፡ ስንበላና ስንጠጣ በምርጫችን ስለሆነ በፈለግነው ጊዜ ማቆምና ማቋረጥ እንችላለን፡፡ ስንነሳና ስንቀመጥም እንዲሁ በፈቃዳችን ስለሆነ የፈለግነውን ቦታና የአቀማመጥ ሁኔታ እንመርጣለን፡፡

በዛው ተቃራኒ ደግሞ፡ ስናዛጋና ስናስነጥስ በፈቃዳችንና በምርጫችን ስላልሆነ፡ ለማዛጋትም ሆነ ለማስነጠስ ቦታና ሰዓት መምረጥ አንችልም፡፡ ሁኔታው እንዳይከሰትም ከራሳችን ላይ ማስወገድ አንችልም፡፡ የደም ዝውውር፣ የልብ ምትም ከዚሁ ምድብ ውስጥ ይካተታሉ፡፡ ማነው የልብ ምቱን በደቂቃ ክ 70 ወደ 35 ለመቀነስ የተወዳደረው? ማነው የደም ዝውውሩን በሰዓትና በቦታ ለመገደብ የጣረው?

ታዲያ ሰው ነጻ ፈቃድ የለውም የምንል ከሆነ፡ መብላትና መጠጣት፡ ከማስነጠስና ማዛጋት ጋር እንደ እኩል ይታያሉ ማለት ነው? መቆምና መቀመጥ ከልብ ምትና ከደም ዝውውር ጋር ይስተካከላሉ ማለት ነው?

ለማንኛውም ሰው ነጻ ፈቃድ ያለው ፍጡር ነው፡፡ አላህ የበለጠውን ሐቁን ይግለጽልን፡፡

5/ ስለዚህ ሰው ሁሉንም ነገር ሳይሆን በፈቃዱ የሚተግብረው፡ የተወሰኑ በራሱ ምርጫ የሚተገብራቸው ነገራት እንዳሉ አውቀናል ማለት ነው፡፡ በነዚህም ኃላፊነትን ወስዶ ይጠየቃል ተብሏል፡፡ እውነታው ይህ ከሆነ ‹‹አላህ ካልሻ በስተቀር እናንተ አትሹም›› ‹‹ብንሻ ኖሮ ነፍሱን ሁሉ ቅንነቷን በሰጠናት ነበር›› ‹‹አላህ የሻውን ይመራል፡ የሻውን ደግሞ ያጠማል›› የሚሉትን አንቀጾች፡ ‹እኛ በምርጫችን ነው ጥሩውንም ሆነ መጥፎውን የምንሰራው› ከሚለው አስተሳሰብ ጋር አብረን የምናያቸው? የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል፡፡ መልሱን በአላህ ፈቃድ በቀጣዩ ክፍል ኢንሻአላህ፡፡
ወአኺሩ ዳዕዋና ዐኒል-ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡