ውርስና የቁርዓን ስህተት?

2,354 Views

ኢልያህ ማህሙድ

በአላህ ስም እጅግ አዛኝ እጅግ ሩህሩህ በኾነው እንጀምርና በመቀምቀሚያው ዘመን የመጨረሻ ነብይ ኾነው በተላኩ ሙሐመድ (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ላይ የአላህ ሰላምና እዝነት ይውረድ ብለን ቀጠልን፡፡ ወዳጄ እንደምን ከረሙ? ዛሬ በአላህ ፈቃድ ከላይ ርእስ ባደረግነው ላይ አንድ ሰው ቁርአን በግልጽ ተሳስቷል በሚል ከውርስ ጋር የተያያ ስሌት አምጥቶ “ ይህ እጅግ ግልጽ የኾነ ስህተት ነው፤ ፈጣሪ እንዲህ ዓይነት የኹለተኛ ክፍል ተማሪ የማይሰራውን እንኳን ስህተት ይሰራል ብሎ ማመን አይቻልም…ይህ ቁርአን በእርግጥም የፈጣሪ ቃል አለመኾኑን ያረጋግጣል…” ካለ በኋላ “ሙስሊሞች…ወደ ክርስቶስ ትመጡ ዘንድ የዘወትር ጸሎታችን ነው” ብሎ ወደ ራሱ ሃይማኖት ጋብዞናል፡፡ ወዳጄ እስኪ አብረን ስሌቱን እንስራና ማን ወደ ሃይማኖቱ መጋበዝ እንዳለበት በጋራ እንፍረድ!!!እንደ ኹሌውም በምንሰራው ስራ ኣላህ ኢኽላሱን እንዲለግሰን፣ ከታይታና ይስሙልኝ ከነፍስያም ግራሞት እንዲጠብቀን እንለምናለን፡፡

ሰውዮው ሲሞት ትቶት የሄደው የገንዘብ መጠን 48000፣ ለውርስ የቀረቡት የቤተሰብ አባላት ደግሞ እንደሚከተሉት ናቸው፡-
1. ሚስት
2. ሦስት ሴት ልጆች
3. እናትና አባት

ሚስት በዚህ አግባብ ትወርሳለች “ለናንተም ልጅ ባይኖራችሁ ከተዋችሁት ንብረት ለእነርሱ (ለሚስቶች) ከአራት አንድ አላቸው፡፡ ለእናንተም ልጅ ቢኖራችሁ ከተዋችሁት ንብረት ለእነርሱ ከስምንት አንድ አላቸው” አኒሳእ/12
ሴቶች በዚህ አግባብ ይወርሳሉ “ከሁለት በላይም የኾኑ ሴቶች ብቻ ቢኾኑ ለእነሱ (ሟቹ) ከተወው ረጀት (ድርሻ) ከሦስት ሁለት እጁ አላቸው፡፡ አንዲትም ብትኾን ለርሷ ግማሹ አላት፡፡” አኒሳእ/11
አባትና እናት በዚህ አግባብ ይወርሳሉ “ለአባትና ለእናቱም ለእርሱ ልጅ እንዳለው ከሁለቱ ለያንዳንዱ ከስድስት አንድ አላቸው፡፡ ለእርሱም ልጅ ባይኖረውና ወላጆቹ ቢወርሱት ለእናቱ ሲሶው አላት፡፡ ለእርሱም ወንድሞችና እኅቶች ቢኖሩት ለናቱ ከስድስት አንድ አላት፡፡” አኒሳእ 11
ከወንዶች ውርስ አኳያ መልክተኛው (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል “ ውርሶችን ለሚገባቸው አካላት አድርሱ፤ የተረፈ ካለ (ለመውረስ ከመጡት ወንዶች መካከል) በውርስ የበላይ ለኾነው ስጡ”

አኹን ወደ ማከፋፈሉ እንግባና ያሉትን ሕግጋት እንይ፡-

አስል 24
ሚስት (1/8) = 3
3 ሴቶች (2/3) = 16
እናት (1/6) = 4
አባት (1/6) እና የተረፈ ካለ = 4

ለእነዚህ ክፍልፋይ ቁጥሮች አካፋይ ኾኖ በጋራ የሚያገለግለው ቁጥር 24 ነው፡፡ይህንን በውረስ ሳይንስ “አስል” እንለዋለን፡፡ ይህ ማለት የሚወረሰው ንብረት ለ24 ይካፈላል ማለት ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን የእያንዳንዱን ሰው ድርሻ ከጠቅላላው 24 ላይ እያነሳን እናካፍል፡፡ ከላይ ሰንጠረዢ ላይ እንደምናየው ሚስት 3 እጅ (ከ24 ላይ1/8 ኛውን ስናነሳ ማለት ነው)፤ ሴቶቹ 16 እጅ፣ እናት 4 እጅ፤ አባትም 4 እጅ ይደርሳቸዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ድርሻቸውን ስንደምር 24 ሳይኾን 27 ይመጣል፡፡

ቁርአን ተሳስቷል ብለው የደመደሙ አካላት እዚህ ድረስ መጥተው ከዚያም ምን መደረግ እንዳለበት ሳያውቁ በቀጥታ በክፍልፋዩ የሚወረሰውን 48,000 ብር አባዙና 54,000 ብር ላይ ደረሱ፡-
ሚስት (1/8) ( 48,000)= 6000
ሴቶች (2/3)(48000)= 32000
እናት (1/6)(48000)=8000
አባት (1/6)(48000)=8000
———————–
ጠቅላላ ድምር = 54,000
—————————–
በኢስላም ውርስ ሕግ ንብረቱን ማከፋፈል ከመጀመራችን በፊት፣ “አስሉን” ለኹሉም ባለመበት ካከፋፈልን በኋላ የድርሻዎቹ ድምር ከ”አስሉ” እኩል ካልኾነ “ዐውል” የሚባል ሌላ ሒሳብ ውስጥ እንገባለን፡፡ ለምሳሌ እዚህ ጋር የኹሉንም ድርሻ (ሰህም) ስንደምር ሚስት (3) + ሴቶች (16) + አባት (4) + እናት (4) = 27 ይመጣል፡፡ ይህ ደግመ ከአስሉ (24) ይበልጣል፡፡ ስለዚህ “ዐውል” ስናደርገው አስሉ 24 መኾኑ ይቀርና 27 ይኾናል፡፡ ይህ ማለት ጠቅላላ ንብረቱ ለ24 መካፈሉ ይቀርና ለ27 ይከፋፈላል ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የምናደርገው በመጀመሪያው አስል (24) የደረሳቸውን ድርሻ(ሰህም) በ”ዐውሉ” ማካፈል ይኾናል፡-
ሚስት (3/27)፣ ሴቶች (16/27)፣ አባት (4/27)፣ እናት (4/27)
ይህ አዲሱ የዐውል ክፍልፋይ ኹሉም ወራሾች መጀመሪያ ከሚኖራቸው ድርሻ ዝቅ ብለው ያለምንም ሒሳባዊ ስህተት የሚካፈሉበት ሒደት ነው፡፡ ለምሳሌ ሚስትን በመጀመሪያው አስል (24) እናካፍላት ብንል ይደርሳት የነበረው 3/24 ነበር፡፡ ይህ ማለት ጠቅላላ ንበረቱ 24 ቦታ ተከፋፍሎ ለሚስት 3/24 ወይም 1/8 ው ይደርሳት ነበር ማለት ነው፡፡ በዐውል ሒሳብ ግን ከመጀመሪያው ዝቅ ብላ 3/27 ወይም 1/9 እንድትወርስ ይደረጋል፡፡
——————————
የመጨረሻው ሥራችን የሚኾነው በዐውሉ መስረት የደረሳቸውን ድርሻ በጠቅላላው ውርስ ገንዘብ ማባዛት ነው፡-
ሚስት (3/27) (48000) = 5333.33
ሴቶች (16/27) (48000) =28,444.44
አባት (4/27) (48000) = 7111.11
እናት (4/27) (48000) = 7111.11
———————–
ንዑስ ድምር = 47, 999.99~ 48,000
ወዳጄ ከላይ ያስቀመጥነው ሰንጠረዥ ላይ አባት ከድርሻው ባሻገር የተረፈ ካለ ይውስዳል እንዳልን ልብ ይሏል፡፡ ግን አብረን እንዳየነው ኹሉም ድርሻውን ከወሰደ በኋላ ምንም ትርፍ ብር ስለሌለ አባት መጀመሪያ በደረሰው ላይ ይጸናል፡፡
———————-
አኹን “ክርስቶስን” እንድንቀበል የጠሩን ወገኖች ኢስላም ምን ያህል ጥልቅ እምነትና ሳይንሳዊ እንደኾነ የተረዱ ይመስለኛል፡፡ ቀጥለን እኛም እስኪ እናንተው ያነሳችኋቸው ሰዎች 48000 ብር ለመውረስ ቢመጡ ከመጽሐፍ ቅዱስ አኳያ እንዴት እንደምታከፋፍሏቸው አሳዩን ብለን እንጠይቃለን፡፡
——————
«ጥራት ይገባህ፤ ከአስተማርከን ነገር በስተቀር ለኛ ዕውቀት የለንም፡፡ አንተ ዐዋቂው ጥበበኛው አንተ ብቻ ነህና»
አልበቀራህ/32
ቸር እንሰንብት