ተኝቼ ፈጅር ሶላት አመለጠኝ!

1,594 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በኾነው
ክብርና ምሥጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ውዳሴና ሰላም የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለኾኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

1/ ሶላት በተግባር ከሚገለጹ የዒባዳህ (አምልኮ) ዘርፎች ውስጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሹ ነው፡፡ ከሶላት የሚበልጥ የዒባዳ ዘርፍ በኢስላም ውስጥ የለም፡፡ ሶላት በአላህና በባሪያው መካከል ያለ ብቸኛ የግንኙነት መስመር ነው፡፡ አንድ ሰው በሶላት ውስጥ ሆኖ ጌታውን ያወድሳል፣ ችግሩን በመግለጽ አላህን ይማጸናል፣ የኃጢአት ይቅርታን ይጠይቃል፣ የመጨረሻው ቤቱ እንዲስተካከል ዱዓእ ያደርጋል…፡፡ በቃ ሶላት ለሙስሊም ሁሉ ነገሩ ነው፡፡ ከዱንያ ጭንቆች፣ ከስራ ድካም ሁሉ የሚያርፈው ሶላት ውስጥ ሲገባ ነው፡፡

ሶላት በኢስላም ውስጥ ያለው ደረጃ እጅግ የላቀ መሆኑን ከሚያመላክቱት አንዱ የኩፍርና የኢማን መለያ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት ሶላትን የሚሰግድ ሰው ሙስሊም ሲሆን፡ የማይሰግድ ደግሞ ካፊር ይባላል ማለት ነው፡፡ ይህን የተመለከቱ ሐዲሦችን ቀጥለን እንይ፡-

ጃቢር ኢብኒ-ዐብዲላህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ሲሉ ሰማሁ አለ፡- “በሰውየውና በኩፍር መሐከል ያለው ነገር ቢኖር ሶላት መተዉ ብቻ ነው” (ሙስሊም)፡፡
የሐዲሡ መልእክት ሶላትን የተወ ሰው ወደ ኩፍር ለመግባት ምንም የሚቀረው ነገር የለም ነው፡፡ ሶላትን የተወ ጊዜ ከፈረ ማለት ነው፡፡ በሌላ ሐዲሥ ላይ ደግሞ መልክተኛው (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ይላሉ፡- “በኛና በነሱ (በሙሽሪኮች) መሐከል ያለው የቃል-ኪዳን ምልክት ሶላት ነው፡ የተዋትም ሰው በርግጥ ከፈረ” (ቲርሚዚይ)፡፡
ዐብዱላህ ኢብኑ-ሸቂቅ አል-ዑቀይሊይ (ረሒመሁላህ) እንዲህ አለ፡- “የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ባልደረቦች ሳይሰሩት መተውን እንደ ኩፍር የሚመለከቱት ነገር ከሶላት ውጪ ሌላ ነገር አልነበረም” (ቲርሚዚይ 2622)፡፡
ነገ የውሙል ቂያም የባሮች ሥራ በትክክለኛ ሚዛን ሲመዘን መጀመሪያ የሚመዘነው ከስራ ሶላት ነው፡፡ ሶላቱ ከተስተካከለ ሌላው ስራው ሁሉ ይስተካከላል፡፡ ሶላቱ ከተበላሸ ሌላው ስራ ሁሉ ይበላሻል፡፡ ይህ በመሆኑም ሶላት ላይ ልዩ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ማለት ነው፡-
‹‹የውሙል ቂያም ሰዎች ከስራቸው መጀመሪያ የሚተሳሰቡት ሶላታቸውን ነው፡፡›› (አቡ ዳዉድ 864)፡፡

2/ ሶላት እኛ በፈለግነው ቀንና ሰዓት የምንፈጽመው የአምልኮ ተግባር ሳይሆን፡ የተወሰነ ሰዓትና መጠን ያለው አላህ ባዘዘው መልኩ የሚፈጸም የአምልኮ ስራ ነው፡፡ ሶላትን ሰግዶ መገኘት ብቻ ሳይሆን፡ አሰጋገዳችንም እሱ እንዳዘዘን መተግበሩ በራሱ አላህን ከመገዛት የሚመደብ ነው፡-
“ሶላትንም በፈጸማችሁ ጊዜ ቆማችሁም ተቀምጣችሁም በጎኖቻችሁም ላይ ተጋድማችሁ አላህን አውሱ። በረጋችሁም ጊዜ ሶላትን (አሟልታችሁ) ስገዱ። ሶላት በምእመናን ላይ በጊዜያት የተወሰነች ግዴታ ናትና።” (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡103)፡፡

3/ ጌታችን አላህ በቅርኣኑ ‹‹አላህን የቻላችሁትን ያህል ፍሩት…›› ይላል (ሱረቱ-ተጋቡን 64፡16)፡፡ እሱ ጌታችን አላህም ለባሮቹ በጣም አዛኝ ከመኾኑ የተነሳ ‹‹አላህ ነፍስን ከችሎታዋ በላይ አያስገድዳትም›› ይላል (ሱረቱል በቀራህ 2፡286)፡፡ ከነዚህ ቁርኣናዊ ምክሮች በመነሳት፡ አንድ ሙስሊም የኾነ ሰው ፈጅር ሶላትን በወቅቱ ተነስቶ ለመስገድ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ፈጅር ለመነሳትም የሚያግዙ (ሰበብ የሚኾኑ) ነገራትንም መጠቀም ግድ ይኾንበታል፡፡ በሚተኛ ሰአት ቶሎ ብሎ በግዜ መተኛት፣ ከእንቅልፍ የሚቀሰቅሱ አላርሞችን መጠቀም፣ ሌሎች አብረውት የሚኖሩ ለፈጅር ሶላት የሚነሱ ወንድምና እሕቶች ካሉ፡ እነሱ እንዲቀሰቅሱት አደራ ማለት ይጠበቅበታል፡፡ ይህንና መሰል ሰበቦችን ተጠቅሞ ከመኝታው መነሳት ካልቻለና እንቅልፍ ካሸነፈው፡ እንቅልፉ ለሱ ዑዝር ነው፡፡ በነቃ ጊዜ ሶላቱን ይሰግዳል፡፡ ረሱል (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንደተናገሩት፡- “በእንቅልፍ ውስጥ ማጉደል የለም፡፡ ማጉደል ማለት በንቃት እያሉ ሌላ ሶላት እስኪገባ ሶላትን ከወቅቱ ማሳለፉ ነው” ብለዋልና፡፡ (ሙስሊም 1594)፡፡

ነገር ግን ያለ-ምንም ምክንያት አርፍዶ በለሊት እየተኛ፣ የማንቂያ ደውሎችን መጠቀም እየቻለ ሳይጠቀም ቢቀር፣ መንድምና እሕቶቹን እንዲቀሰቅሱት አደራ ማለት እየቻለ በቸልተኝነት ይተወውና ኋላ ላይ ሶላቱ ቢያልፈው ግለሰቡ ከተጠያቂነት አይድንም፡፡ ኃጢአተና ኾኗልና፡፡ ይህ ተግባር (ሶላቱን ከወቅቱ ማውጣት) ሁሌም የሚደጋገም ከኾነ ደግሞ፡ ግለሰቡን ከኢስላም አጥር ሊያስወጣው ሁሉ እንደሚችል የኢስላም ሊቃውንት ይገልጻሉ፡፡ (ፈታዋ ኑሩን ዐለ-ዶርብ፡ ጥራዝ 7፡ ገጽ 129-136)፡፡

4/ በእንቅልፍ ሰበብ የፈጅር ሶላት ያመለጠው ሰው፡ ፈጅርን መስገድ ያለበት፡ ወዲያውኑ እንደነቃ ነው፡፡ የዙህር ሶላት እስኪመጣ ወይንም የነገው ፈጅር እስሲገባ መጠበቅ የለበትም፡፡ ፀሀይ ከወጣች በኋላ ቢነቃ፡ ወዲያውኑ ተነስቶ ሶላቱን መፈጸም አለበት፡፡
አነስ ኢብኑ ማሊክ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዳስተላለፈው የአላህ ነቢይ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) እንዲህ አሉ፡- “አንድን ሶላት ከመስገድ የረሳ ሰው፡ ባስታወሳት ጊዜ ወዲያውኑ ይስገዳት፡፡ ከዚህ ውጭ ሌላ ከፍፋራህ (ማካካሻ) የላትምና፡፡ አላህም ‹‹ ሶላትንም (በእርሷ) እኔን ለማውሳት (ወይም ባስታወስካት ጊዜ) ስገድ፡፡›› ብሏልና” (ቡኻሪይ 597፣ ሙስሊም 684)፡፡

5/ ፈጅር ሶላትን በእንቅልፍ ወይንም በመርሳት ሰበብ ወቅቱ ካለፈ በኋላ ያስታወሰ (የነቃ) ሰው፡ ቅድሚያ ከፈርዱ በፊት ሁለት ረክዐህ የፈጅርን ሱንና ሶላት መስገድ ይችላል፡፡ በላጩም እሱ ነው፡፡ በተጨማሪም አዛንና ኢቃም ማለት፡ ድምጹንም ከፍ አድርጎ በመቅራት ሶላቱን መፈጸም ይችላል፡፡ ከአቢ ቀታዳህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው፡ ረሱሉላህ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በአንድ የለሊት ጉዞአቸው ላይ ከሶሓቦች ጋር ተኝተው፡ ሁሉንም ፈጅር አምልጧቸው፡ ፀሀይ ከወጣ በኋላ፡ በፀሀዩ ሙቀት ሰበብ ቅድሚያ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ይነቃሉ፡፡ በመቀጠልም ሶሓቦች በመደንገጥ ይነሳሉ፡፡ የተኙበትን ስፍራ ለቀው ይሄዱና ዉዱእ አድርገው ቢላልም (ረዲየላሁ ዐንሁ) አዛን ያደርግና፡ የአላህ መልክተኛም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሁለት ረክዐህ ሱንና ይሰግዱና በመቀጠልም ፈርዱን ሶላት ያሰግዳሉ፡፡ (ሶሒሕ ሙስሊም 1594)፡፡
(ሸይኽ ኢብኑ ባዝ፡ http://www.binbaz.org.sa/noor/6239 ፣ ሸይኽ ሷሊሕ አል-ሙነጂድ፡ https://islamqa.info/ar/209169 )፡፡

6/ ፀሀይ ልትወጣ አካባቢ ከእንቅልፉ የነቃ ሰው፡ ፀሀይ ወጥታ ከፍ እስክትል መጠበቅ የለበትም፡፡ ቶሎ ወደ ሶላቱ መቸኮል ነው ያለበት፡፡ እየሰገደ እንኳ በሁለተኛው ረክዐህ ላይ ፀሀይ ብትወጣ፡ የፈጅርን ሶላት ከፀሀይ መውጣት በፊት አንድ ረክዐህ ስላገኘ፡ ሶላቱን እንዳገኘ ይቆጠራልና፡፡ ቀሪዎቹን ረክዐዎች በቀጣዩ የሶላት ወቅት ውስጥ ቢሰግዳቸውም ማለት ነው፡፡

ከአቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ከሱብሒ ሶላት አንድ ረክዐን ከፀሀይ መውጣት በፊት ያገኘ ሰው፡ በርግጥም ሱብሒን አግኝቷል፡፡ ከዐሱር ሶላት አንድ ረክዐን

ፀሀይ ከመግባቷ በፊት ያገኘ (የሰገደ) ሰው፡ በርግጥም የዐሱርን ሶላት አግኝቷል” (ቡኻሪይ 579፣ ቲርሚዚይ 186፣ ኢብኑ ማጀህ 700)፡፡ ወላሁ አዕለም!!