የቅድመ ውሳኔን (ቀዷ ወል-ቀደር) ጽንሰ ሃሳብ በተመለከተ ክፍል -9

1,266 Views

አቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56)፡ ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181)፡ የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

መምህሩና ተማሪው፡-

ከዕለታት በአንዱ ቀን ተማሪው መምህሩ ፊት ቆመና፡- ክቡር መምህር ሆይ! አንዳንዴ እንግዳ አስተሳሰብ በህሊናዬ ብቅ ይላልና፡ መፍትሔ ካገኘሁ በማለት ለእርስዎ ማቅረብን ወደድሁ፡፡ እሱም፡- አምላካችን አላህ ለተወሰኑ ሕዝቦች ሰዓዳህ (ዘላለማዊ ደስታን) ለተቀሩት ደግሞ ‹ሸቃዋህ› (ዘላለማዊ ስቃይን) ለምን ወሰነ? ለምን ዘላለማዊ ደስታን (የጀነት መሆንን) ብቻ አላደረገም?
ለምን ጀነትና ጀሀነም እንዲኖሩ ፈቀደ? ለምን ጀነት ብቻ አልተዘጋጀምን?
አንድ የአላህ ባሪያ ጥመትና ዕድለ-ቢስነት ቀድሞ ከተወሰነበት፡ የሱ ጥፋት ምኑ ላይ ነው?
መምህሩ፡- ይህ ጥናት ከፈጣሪ ስራና ከፍጥረቱ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ በመሆኑም ከፍጥረቱ ጋር ከሚገናኘው (አንድ የአላህ ባሪያ ከሚለው) ጥያቄ እንነሳ፡፡ ለመረዳትም የቀረበ ይሆናልና፡፡ ቢስሚላህ….

1/ ሰው መልካሙን ከክፉ የሚለይበት አዕምሮ አለው፡፡ ይህ አዕምሮ በሃይማኖታዊ ግዳጅ ባለቤቱን የሚያናግረው ዋና የሰውነት ክፍል ነው፡፡ አዕምሮው የተሸሸገበት (ዕብድ) ወይም ለአካለ መጠን ያልደረሰ ህፃን ሃይማኖታዊ ግዳጅ አይመለከተውም፡፡

2/ ሰው ነጻ ፈቃድ አለው፡፡ አዕምሮ አለኝ የሚል ሁሉ ይህንን ሊቃወም አይችልም፡፡ ስለዚህም…
ሀ/ ይህ ሰው በምርጫው ይቆማል፣ ሲፈልግ ይቀመጣል፣ በፈቃዱ ወደፈለገው ስፍራ ይሄዳል ደግሞም ይመለሳል፣ ሲፈልግ ዒባዳህ ያደርጋል፡ ሲፈልግ ደግሞ ኃጢአት ላይ ይወድቃል፡፡ በዚህም ሰበብ ለጥፋቱ በቀደር ማሳበብ አይችልም ማለት ነው፡፡

ለ/ ይህ ሰው ለጥፋቱ በቀደር ከማሳበብ አላቆምም ካለና ለጥፋቱ ቀደርን እንደ ዑዝር የሚመለከት ከሆነ፡ በኃይለኛው እንመታዋለን፡ ደግሞም እናሳምመዋለን፡፡ ልክ ሲቆጣና ሲናደድ፡- እባክህ ዑዝር ስጠን! ባንተ ላይ ይህን እርምጃ የወሰድነው የቀደር ጉዳይ ሆኖብን እንጂ እኛ ፈልገን አይደለም፡፡ ልክ አንተ ኃጢአት ላይ ወድቀህ ቀደር ነው እንደምትለው ማለት ነው እንለዋለን፡፡ እሱም ምክንያታችንን ካልተቀበለ፡ እኛም፡- አንተ በአላህ ህግ ላይ ወሰን እያለፍህ እንዳትወቀስ በቀደር ማሳበብህ ትክክል ከሆነ፡ እኛስ ባንተ ክብር ላይ ወሰን ማለፋችንን በቀደር ብናሳብብ ለምን አትቀበለንም? ቀደር ከሆነ ሁሉም ቀደር ነውና! እንለዋለን፡፡ የዛኔም ለሁለተኛ ጊዜ ለሚሰራው ኃጢአት በቀደር ማሳበቡ ምክንያት እንደማይሆነው ይረዳል ማለት ነው፡፡

ሐ/ ይህን ሰው ና! ወደ መስጂድ ሄደን ለጌታችን እንስገድ! ብለን ስናዘው፡ በባዶ ተስፋ ላይ ሆኖ፡- አላህ እስኪያገራልኝ ጠብቁኝ፡ ሂዳያውንም እንዲወፍቀኝ በዱዓእ አግዙኝ ሊለን ይችላል፡፡ የዛኔም፡- የሂዳያ ጉዳይ እንደ ሪዝቅ ነው፡፡ ጌታ አላህ ሂዳያን ሰጪ እንደሆነው ሁሉ፡ ሲሳይን ሰጪም እሱ ብቻ ነው፡፡ እናማ፡ አንተ ምንም ሳትለፋ ቤትህ ተጎልተህ ሂዳያን ከአላህ በባዶ ተስፋ የምትጠብቅ ከሆነ፡ በል ሱቅህን ዝጋና ሳሎንህ ገብተህ ተቀመጥ፡፡ ሲሳዩ ራሱ ፈልጎህ አለህበት ቦታ እስኪመጣ ድረስ ጠብቀው እንለዋለን፡፡

እሱም በእምቢተኝነት ስሜት፡- ሲሳይን ለማግኘትማ የተወሰነ መልፋት አለብን፡ ሰበቡን ልናደርስ ግድ ነው ይለናል፡፡ እኛም የዛኔ፡- የአላህን ሂዳያ ለማግኘትም መንቀሳቀስና ጁህድ (ትግል) ማድረግ ግድ ነው እንለዋለን፡፡ አሁንም ለስንፍናው በሂዳያ አለማግኘት ከለላ ስር መሸሸጉ ምክንያት እንደማይሆነው ለሶስተኛ ጊዜ ይረዳል ማለት ነው፡፡

መ/ ይህን ሰው ደግመን እንዲህ እንለዋለን፡- አንተ በቀደር ታሳብባለህ፡፡ ሁሉም ነገር የሚሆነው በቀዷ ወል-ቀደር ነው ትላለህ፡፡ በጥቅሉ ልክ ነህ፡፡ እንግዲያውስ ይህን ፍም እሳት በእጅህ ያዘው! አላህ ወስኖብህ ከተቃጠልህም ትቃጠላለህ፡፡ ካልተወሰነብህ ደግሞ እሳቱ ምንም አያደርግህምና! እንለዋለን፡፡ እሱም እምቢ በማለት፡- ጥንቃቄ ማድረግማ የግድ ነው! ይለናል፡፡ እኛም የዛኔ፡- የአላህን ህግ ጥሰህ በቀደር ከማሳበብህ በፊት ኃጢአት ላይ እንዳትወድቅ ጥንቃቄ ማድረግም ግድ ነው እንለዋለን፡፡ በዚህ ሰበብም፡ ለጥፋቱ ቀደርን ማሳበቡ ልክ አለመሆኑን ለአራተኛ ጊዜ ይረዳል ማለት ነው፡፡

ሠ/ በድጋሚም እንዲህ እንለዋለን፡- ሰው በተፈጥሮው አደጋንና የሚጠላውን ነገር ከራሱ ላይ የሚከላከል ሆኖ የተዘጋጀ ፍጡር ነው፡፡ ለምሣሌ፡- መሪው የተበላሸ መኪና ሊገጨው ወደሱ ቢቀርብ፡ ምንም ሳያስበው እጁን በማንሳትና በመዘርጋት ከራሱ ላይ ለመከላከል ይሞክራል፡፡ ይህንን አደጋ ግን እጆች ለመከላከል ምንም አቅም ካለመያዛቸው ጋር!

በባህር ላይ የሰመጠ ሰው፡ ምንም የዋና ልምድ ባይኖረውም፡ እራሱን ለማዳን ግን ይፍጨረጨራል፡፡ ይህ ሁሉ መፍጨርጨር እንደማያተርፈው ቢረዳም ማለት ነው፡፡ ታዲያ አዕምሮ አለኝ የሚል ሰው፡ አላህ በሰጠው ነጻ ፈቃድና ውስን ችሎታ ለምን የአኼራውን ስቃይ ከወዲሁ በኢማንና በመልካም ስራ ለመከላከል አይጥርም? ለምን ለጥፋቱ ወቃሽ እንዳይኖረው በቀደር ያሳብባል? እንለዋለን፡፡ ስለዚህ ለጥፋታችን ወቃሽ እንዳይኖረን በቀደር ማሳበብ የትም የሚያስሄድ አይደለም ማለት ነው፡፡ አምስተኛ ምላሽ ማለት ነው፡፡

ተማሪዬ ሆይ! ይህ እንግዲህ የፍጥረቱን ስራ በተመለከተ የዳሰስነው ክፍል ነው፡፡ ሰው ቀድሞ ከተወሰነበት ጥፋቱ ምንድነው? የሚለው የኃጢአተኞች ምሽግ እንጂ፡ የሙእሚኖች ንግግር አይደለም ማለት ነው፡፡ እነሱ አላህ ቀድሞ የጻፈባቸውን ስለማያውቁ፡ መልካም ከሰሩ፡ በአላህ ዕገዛና ተውፊቅ መሆኑን አውቀው ያመሰግኑታል፡፡ አጅሩንም ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ኃጢአት ላይ ከወደቁ ደግሞ፡ የነፍሲያቸው ድክመትና የሸይጧን ጉትጎታ መሆኑን ተረድተው፡ አላህ ይቅር ይላቸው ዘንድ በተውበት ይመለሳሉ፡፡

ከዛ ውጭ ተውበት በማድረግ ፈንታ ‹‹አላህ ወስኖብኛል›› በማለት ለመከላከያነት አያቀርቡም፡፡ መጥፎ ስራቸው የነሱ መሆኑን እያወቁ፡ አላህ ወስኖብኝ ነውና መቀጣት የለብኝም ካሉ፡ መልካም የሰራችሁትም አላህ ወስኖባችሁ ነውና በአኼራ አጅር ማግኘት የለባችሁም ሊባሉ ግድ ነው፡፡ ወል-ዒያዙ ቢላህ፡፡ አሁን የቀረው የፈጣሪን ስራ (ጀነት እና ጀሀነም) በተመለከተ ይሆናል፡፡ ምን መሰለህ….

አላህ ጥበበኛ ጌታ ነው፡፡ አል-ሐኪም በመባል በፍፁም ጥበበኝነቱ ይገለጻል፡፡ ጥበብ ደግሞ፡ ማንኛውንም ነገር ተገቢው ስፍራ ላይ ማስቀመጥ ነው፡፡ በመሆኑም፡ ከጌታችን ፍጹም ጥበበኝነት የተነሳ በሰዎች ዘንድ እምነትና ክህደት፡ ምሪትና ጥመት፣ ዕድለኝነትና ዕድለ-ቢስነት፣ ጀነት እና ጀሀነም እንዲኖር ፈቃዱ ሆነ ማለት ነው፡፡ የሰው አዕምሮ በዚህ ምድር ላይ እያለ ይህን ጥበብ ሚስጥሩን ሊያገኘውና ሊዘልቀው አይችልም፡፡ የጌታውን ፍትሐዊነት እና ፍፁም ጥበበኛነት የቂያም ቀን ግን ማወቁና መመስከሩ አይቀርም!፡፡ ዛሬ በዚህ ምድር ላይ ግን፡ ከአፈር የተፈጠረና ደካማ የሆነው ሰው እንዴት የአምላክን ጥበብ ሊደርስበት ይችላል ብለህ ታስባለህ?

ተማሪውም፡- መምህር ሆይ! ምናልባት ይህ የአላህን ጥበብ በደካማው አዕምሮአችን ለማግኘት አይቻለንም! የሚለው ምላሾት፡ ትክክለኛውን መልስ ከማጣት የመነጨና ለመሸሽ የተደረገ ሙከራ ነው ብሎ ሰው አይገምተውምን? አለ፡፡
መምህሩም፡- ነገሩ እንደዛ አይደለም! ነገሩ ቀላልእንዲሆንልህ ምሣሌን ልስጥህ፡፡ አሁን አንተ የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ተማሪ ነህ፡፡ ስለ ሳይንስ፣ ስፖርት፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ እና መሰል የትምሕርት ዘርፎችን ትማራለህ፡፡ መምህርህ ከነዚህ ውስጥ አንዱን ላንተ ያስረዳህን የትምሕርት አይነት በመውሰድ፡ ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በማቅረብ ቢያስተምራቸው፡ አንተ ከመምህርህ የገባህን ያህል እነሱም ይረዱታል ብለህ ታስባለህ?
ተማሪው፡- በፍጹም!
መምህሩ፡- ለምን?
ተማሪው፡- አዕምሮአቸው ይህን የትምህርት ዘርፍ ለመረዳት ገና ስላልበሰለና ስላላደገ ነዋ!
መምህሩ፡- እንግዲያውስ እነዚህ ዛሬ መረዳቱን ያልቻሉት ተማሪዎች፡ ወደፊት የአንተ ዕድሜ ክልል ላይ ሲደርሱ፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ሲጀምሩና ከመምህራቸው ይህን ትምሕርት ቢማሩ፡ የዛኔ አንተ እንደተረዳኸው ወይም ካንተ በላይ የመረዳት አቅም አይኖራቸውምን?
ተማሪው፡- እንዴታ! ይኖራቸዋል እንጂ፡፡
መምህሩ፡- እነዚህ ተማሪዎች አንዱን የትምህርት ዘርፍ መርጠው በደንብ ካጠኑ ደግሞ፡ በኔ ዕድሜ ደረጃ ላይ ሲደርሱ፡ ከኔ የተሻለ ብቁ መምህር መሆን አይችሉምን?
ተማሪው፡- በደንብ ይችላሉ እንጂ!፡፡
መምህሩ፡- የምፈልገው ቦታ አምጥቼሃለሁና በል አድምጠኝ፡፡ ሰው ምድራዊ ዕውቀቶችን ለመቅሰም በልጅነት፣ በወጣትነትና በጎልማሳነት ዕድሜ ላይ ያለው ደረጃ ይህን ያህል የሚለያይ ከሆነ፡ እንግዲያውስ ደካማ በሆነው የሰው አዕምሮና፡ ፍፁም ጥበበኛ በሆነው አላህ መሀል ምን ያህል ልዩነት ሊኖር እንደሚችል ገምት እንግዲህ!፡፡
ተማሪውም፡- እጅግ በጣም አመሰግናለሁ መምህር! ከልቤ ላይ እየጎተጎተኝ፡ ማረፊያን አሳጥቶኝ ኢማኔን ሲፈታተነኝ የነበረውን ነገር በአላህ ፈቃድ አስወግደውልኛልና አለው፡፡
መምህሩም፡- ወደ እውነቱና ወደ ትክክለኛው መንገድ በራሕመቱ ለመራን ጌታ አልሐምዱ ሊላህ አለ፡፡
ምንጭ፡- አል-በያን ፊ አርካኒል ኢማን ፡ሸይኽ አሕመድ ቢን መጅድ መኪይ ገፅ 460-464
ወአኺሩ ዳዕዋና ዐኒል-ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡