የቅድመ ውሳኔን (ቀዷ ወል-ቀደር) ጽንሰ ሃሳብ በተመለከተ ክፍል -4

1,213 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው

አቡ ሀይደር

ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡

” وَمَا تَشَاءُونَ إِلَّا أَنْ يَشَاءَ اللَّهُ رَبُّ الْعَالَمِينَ ” سورة التكوير 29
“የዓለማት ጌታ አላህ ካልሻም አትሹም” (ሱረቱ-ተክዊር 81፡29)፡፡

በዛሬው ክፍላችን በአላህ ፈቃድ የምንመለከተው፡ ባለፈው ክፍል ላይ ያነሳነውን ጥያቄ ነው፡፡ እሱም፡- ሰው የሚባለው ፍጥረት ነጻ ፈቃድ ያለው ፍጡር መሆኑን ከተስማማን፣ ደግሞም በፈቃዱ መልካምም ይሁን መጥፎ ስራዎችን መስራት ከቻለና፡ በነዚህም ስራዎቹ ኃላፊነትን ወስዶ በየውሙል ቂያም በአላህ ዘንድ ተጠያቂ ከሆነ፣ እንዲሁም ቀዷ ወል-ቀደር የሚባል ነገር በእምታችን ውስጥ ካለና፡ በዚህ ማመናችንም የአላህን ሁሉን አዋቂነት፡ የፍጥረተ ዓለሙን የበላይ ተቆጣጣሪነትና ገዢነት፡ እንዲሁም ከሱ ፈቃድና ይሁንታ ውጪ ሊከሰት የሚችል ነገር አለመኖሩን የሚጠቁም እንጂ፡ የሰዎችን ነጻ ፈቃድ የሚጋፋና ትርጉም አልባ የሚያደርግ አለመሆኑን ከተረዳን፣ ታዲያ ‹‹አላህ ካልሻላችሁ በስተቀር እናንተ አትሹም›› የሚለውን እንዴት ነው መረዳት ያለብን? የሚል ነበር፡፡ በአላህ ፈቃድ ምላሹን ይከታተሉ፡፡ አላህ ኸይሩን የተሻለውን ግንዛቤ ይለግሰን፡-

1/ ጥቅላዊ ማብራሪያ፡-

‹‹አላህ ካልሻ በስተቀር እናንተ አትሹም›› ማለት ሁለት መሰረታዊ ቁም ነገርን ያስጨብጠናል፡፡ የመጀመሪያው፡- ሰው መሻት (ፈቃድ) ያለው ፍጡር መሆኑን ሲሆን፡ ሁለተኛው ደግሞ፡- ይህ የሰው መሻት እውን የሚሆነውና የሚሳካው አላህ ሲሻለትና ሲፈቅድ ብቻ እንደሆነ ነው፡፡
እኛ በራሳችን ፈቃድ እንዲሆን የምንፈልገው ነገር በጠቅላላ የአላህ ፈቃድና ይሁንታ ካልታከለበት፡ ፈቃዳችን ትርጉም አልባ ነው የሚሆነው፡፡ ወደ ተግባር ሊቀየር አይችልም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም እራሳችንን ችለን ከጌታችን ተነጥለን የቆምን አካላት አይደለንምና፡፡ የኛነታችን ትርጉም ሁሉ ያለው በአላህ ‹‹ፈቃድ›› ውስጥ ነው፡፡ እኛ ሁሌም የሱ ጥገኞች ነን፡፡ ያሰብነው ነገር እንዲሳካ የኛ ጉጉት መኖሩ፡ የፈራነው ነገር እንዳይመጣ የኛ ሽሽት መገኘቱ፡ ብቻውን ውጤት መሆን አይችልም፡፡ የተፈለገውንም ነገር አያስገኝም፡፡ ከተፈራውም ነገር አያስጥልም፡፡

ነገር ግን አላህ በራሕመቱ (በቸርነቱ) ኸይር ከሻልን፡ በጉጉታችንና በልፋታችን ሰበብ የተፈለገውን ነገር ያስገኝልናል፡፡ የፈራነውንም ነገር ያርቅልናል፡፡ በዛው ተቃራኒ በኃጢአታችን ሰበብ በዐድሉ (በፍትሐዊነቱ) ሊቀጣን ከፈለገ፡ የፈለግነውን ነገር በማስቀረት የፈራነውን ነገር እንዲደርስብን ያደርጋል፡፡ በዚህ ጥቅላዊ መልእክት ውስጥ እኛ ጉጉታችንና ልፋታችን ‹ሰበብ› መሆኑን መረዳት እንችላለን ማለት ነው፡፡ ሰበቡ ግን ወደ ውጤት የሚቀየረው አላህ ሲፈቅድና ሲፈልግ ብቻ ነው፡፡ man proposes and ALLAH disposes “ሰው ያስባል አላህ ይፈጽማል” እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ ያለሱ ፈቃድ እራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ ማንም ፍጥረት የለም፡፡ እንዴት ካሉም፡-

ሀ/ አላህ ብቻውን ፈጣሪ ነው፡፡ ከሱ ውጭ ያለው ‹ዓለም› በጠቅላላ ፍጥረት ነው፡፡ ካለመኖር መደመኖር የመጣ፣ ካልነበረበት ወደ መገኘት ዓለም የተሸጋገረ፣ ከባዶነት ወደ ቁስ አካልነት የተቀየረ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን አላህ ማንንም አላማከረም፡፡ ከማንም እርዳታ አልሻም፡፡ በራሱ ፈቃድና ፍላጎት ብቻ ነው የሚያደርገው፡፡ ቀጣዮቹ አንቀጾች ይህንን እውነት ያጎላሉ፡-

” قَالَتْ رَبِّ أَنَّى يَكُونُ لِي وَلَدٌ وَلَمْ يَمْسَسْنِي بَشَرٌ قَالَ كَذَلِكِ اللَّهُ يَخْلُقُ مَا يَشَاءُ إِذَا قَضَى أَمْرًا فَإِنَّمَا يَقُولُ لَهُ كُنْ فَيَكُونُ ” سورة آل عمران 47
“ጌታዬ ሆይ! ሰዉ ያልነካኝ ስሆን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል? አለች፤ ነገሩ እንደዚህሽ ነዉ፤ አላህ #የሚሻዉን_ይፈጥራል፤ አንዳችን በሻ ጊዜ ለርሱ ሁን ይለዋል ወድያዉኑም ይሆናል፥ አላት።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡47)፡፡

” لَقَدْ كَفَرَ الَّذِينَ قَالُوا إِنَّ اللَّهَ هُوَ الْمَسِيحُ ابْنُ مَرْيَمَ قُلْ فَمَنْ يَمْلِكُ مِنَ اللَّهِ شَيْئًا إِنْ أَرَادَ أَنْ يُهْلِكَ الْمَسِيحَ ابْنَ مَرْيَمَ وَأُمَّهُ وَمَنْ فِي الْأَرْضِ جَمِيعًا وَلِلَّهِ مُلْكُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَمَا بَيْنَهُمَا يَخْلُقُ مَا يَشَاءُ وَاللَّهُ عَلَى كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ ” سورة المائدة 17

“እነዚያ አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው ያሉ፣ በእርግጥ ካዱ፤ የመርየምን ልጅ አልመሲሕን እናቱንም በምድር ያለንም ሁሉ ለማጥፋት ቢሻ ከአላህ ማዳንን የሚችል ማነው? በላቸው። የሰማያትና የምድር የመካከላቸውም ንግሥና የአላህ ብቻ ነው፤ #የሚሻውን_ይፈጥራል። አላህም በነገሩ ላይ ቻይ ነው።” (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡17)፡፡

” اللَّهُ الَّذِي خَلَقَكُمْ مِنْ ضَعْفٍ ثُمَّ جَعَلَ مِنْ بَعْدِ ضَعْفٍ قُوَّةً ثُمَّ جَعَلَ مِنْ بَعْدِ قُوَّةٍ ضَعْفًا وَشَيْبَةً يَخْلُقُ مَا يَشَاءُ وَهُوَ الْعَلِيمُ الْقَدِيرُ ” سورة الروم 54
“አላህ ያ ከደካማ (ፍትወት ጠብታ) የፈጠራችሁ ነው፤ ከዚያም ከደካማነት በኋላ ኅይልን አደረገ፤ ከዚያም ከብርቱነት በኋላ ደካማነትንና ሺበትን አደረገ፤ #የሚሻውን_ይፈጥራል፤ እርሱም ዐዋቂው ቻዩ ነው።” (ሱረቱ-ሩም 30፡54)፡፡

ለ/ አላህ በፍጥረተ ዓለሙ ላይ የነገሰ ብቸኛ ንጉስ ነው፡፡ ከሱ ውጭ ንጉስ የለም፡፡ ንግስና የሱ ብቻ ነው፡፡ ለሰዎችም ጊዜያዊ ንግስናን የሚሰጥ እሱ ነው፡፡ በመሆኑም የፈለገውን በመርዳት ያልቀዋል፡፡ የፈለገውን ደግሞ በማዋረድ ይቀጣዋል፡፡ እሱ አላህ የዓለሙ ንጉስ እስከሆነ ድረስ በንግስናው ግዛት ላይ ያለ ፈቃዱ አንዳች ነገር ሊከሰት አይችልም፡፡ ከቁጥጥሩ ውጪ የሚሆን አንዳችም ነገር የለም፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-

” يُسَبِّحُ لِلَّهِ مَا فِي السَّمَاوَاتِ وَمَا فِي الْأَرْضِ لَهُ الْمُلْكُ وَلَهُ الْحَمْدُ وَهُوَ عَلَى كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ ” سورة التغابن 1
“በሰማያት ውስጥ ያለው በምድር ውስጥ ያለው ሁሉ ለአላህ ያሞግሳል፤ #ንግሥናው_የርሱ_ብቻ ነው፤ ምስጋናም ለርሱ ነው፤ እርሱም በነገሩ ቻይ ነው።” (ሱረቱ-ተጋቡን 64፡1)፡፡

“…ذَلِكُمُ اللَّهُ رَبُّكُمْ لَهُ الْمُلْكُ لَا إِلَهَ إِلَّا هُوَ فَأَنَّى تُصْرَفُونَ ” سورة الزمر 6
“…ይሃችሁ ጌታችሁ አላህ ነው። #ሥልጣኑ_የርሱ_ብቻ ነው፤ ከርሱ ሌላ አምላክ የለም፤ ታዲያ ወዴት ትዞራላችሁ።” (ሱረቱ-ዙመር 39፡6)፡፡
” قُلِ اللَّهُمَّ مَال

ህዝቦቿ አጥፋውና፣ ሌላም ሌላም፡፡ ስለዚህ አላህ በጥበቡ የፈለገውንና የፈቀደውን ይሰራል፡፡ ከባሮቹም ፍላጎት ለፈለገው እውን በማድረግ ያሳካል፡ የፈለገውን ደግሞ ይከለክላል፡፡ ‹‹ወማ ተሸኡነ ኢልላ አን-የሻአላህ››!! (አላህ ቢሻላችሁ እንጂ አትሹም)፡፡

2/ አላህ የሰጠህን ነጻ ፈቃድ፡ በራሱ ፈቃድና ፍላጎት ስር በማድረግ አንተን መቆጣጠር መቻሉ፡ ያንተን ነጻ ፈቃድ ትርጉም አልባ አያደርገውም፡፡ ምክንያቱም፡- አንተ የተሰጠህ ነጻ ፈቃድ ብቻ ሳይሆን፡ ህያው መሆን፣ ማየት፣ መስማት መናገር…ጭምር ነው፡፡ ነገር ግን ህያው የሆንከው በአላህ ህያው አድራጊነት፣ ሰሚና ተመልካች የሆንከውም በአላህ የመስማትንና የማየትን መሳሪያ ሰጪነት፣ የተናገርከውም አላህ በፈጠረልህ ምላስ ነውና፡፡ የፈለገ ጊዜ እነዚህን መሳሪያዎች ከጥቅም ውጪ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ እንግዲያውስ፡- እኔ እራሴን ችዬ በራሴ ህይወት ከሌለኝ፣ በራሴ ሰሚና ተመልካች ካልሆንኩኝ ምኑን ህያው ተሰኘሁ? ምኑን ሰሚና ተመልካች ሆንኩት? ትላለህን? ያ ከሆነማ፡- እውርን ከተመልካች፣ ዲዳን ከተናጋሪ፣ ደንቆሮን ከአዳማጭ፣ ሙትን ከህያው በምን ልንለየው ነው?

እውነታው ግን ሰው፡- ህያው፣ ሰሚ፣ ተመልካችና ተናጋሪ ፍጥረት ነው፡፡ እነዚህን መገልሀያ መሳሪያዎች አላህ ስለሰጠው ማለት ነው፡፡ ልክ እንደዛው ነጻ ፈቃድ ያለውም ፍጡር ነው፡፡ አላህ ፈቃድ ያለው እንዲሆን አድርጎታልና፡፡ የሰውነት መሳሪዎችህን በፈለገው ግዜ መውሰድ እንደሚችለው ሁሉ፡ ፈቃድህንም እንደፈለገው መገደብ ይችላል!!

3/ አላህ በፈቃድህ ውስጥ ጣልቃ በመግባት እሱ የሻልህን ብቻ እንድታከናውን ማድረጉ ላንተ ካለው አዘኔታና ርህራሄም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም አንተ ነገሮችን በጠቅላላ በእቅድና በፕሮግራም ታስኬዳቸዋለህ እንጂ፡ ፍጻሜያቸው ምን እንደሆነ ቀድመህ አታውቅም፡፡ ሁሉን ዐዋቂ የሆነው ጌታህ ግን ላንተ በማዘን ፍጻሜው መራራ የሆነውን የስራ ጅምርህን፡ ጣልቃ በመግባት ከመነሻው ወይም ከመሀሉ ሊያከሽብህ ይችላል፡፡ አንተ ግን ይህ ሲነገርህ ልክ ፈቃድህ እንደቀበሌ ንግድ ፈቃድ የተሰረዘ አድርገህ ታስባለህ፡፡

ሶላቱል ኢስቲኻራህ የተደነገገበት አንደኛው ምክንያት ይህ አይደለምን? በመተውና በመፈጸም መሀል አጣብቂኝ ውስጥ ስንገባ፡ የቱን እንወስን ብለን ስንቸገር፡ የተሸለውን ለመምረጥ ባቃተን ጊዜ፡ ያ አላህ! እኔ መኃይም ስሆን አንተ ሁሉን ዐዋቂ ነህ፣ እኔ ደካማ ስሆን አንተ ሁሉን ቻይ ነህና ይህ ነገር ለዲኔም ሆነ ለዱንያዮ ከጠቀመኝ አሳካልኝ፡፡ ካልሆነም እኔን ከሱ ገለል አድርገኝና በምትኩ የተሻለ ስጠኝ! በማለት በህይወታችን ውስጥ ጣልቃ መግባቱን ወደን አልተቀበልንምን?

ከሷሊሖች አንዱ፡- በዱዓዎችህ በጣም የምትደሰተው መቼ ነው? በማለት ተጠየቀ፡፡ እሱም፡- አላህ የኔን ልመና ያልተቀበለኝ ጊዜ! በማለት መለሰ፡፡ ጠያቂዎቹም ተገረሙና፡- እንዴት እንዲህ አልክ? ሲሉት፡ ይህ ሷሊሕ ሰውም፡- እኔ ዱዓዬ ተቀባይነትን አግኝቶ ከተሳካልኝ፡ የፈለግሁት ነገር ሆነ ማለት ነው፡፡ ዱዓዬ መቅቡል ካልሆነ ግን አላህ ለኔ ያቀደልኝ ሌላ ነገር አልለ ማለት ነው፡፤ ከኔ ምርጫ የጌታዬ ምርጫ እጅጉኑ የተሻለ ስለሆነ በዚህ ነው የምደሰተው በማለት መለሰ፡፡ (መንቁል)፡፡ በአላህ ላይ ያለው ጥሩ ግምት ‹‹ሑስኑ-ዘን››!!
ወንድምና እህቶች ይን ነጥብ እራሱ በቀጣይነት ክፍል አምስት ላይ ከቀሪ ነጥቦች ጋር ይቀርባል ኢንሻአላህ፡፡
ወአኺሩ ዳዕዋና ዐኒል-ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡