የቅድመ ውሳኔን (ቀዷ ወል-ቀደር) ጽንሰ ሃሳብ በተመለከተ ክፍል -6

1,293 Views

አቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡

ዛሬ በአላህ ፈቃድ የምንመለከተው ደግሞ ‹‹አላህ የፈለገውን ይመራል፣ የፈለገውን ያጠማል›› በሚለው ነጥብ ዙሪያ ይሆናል ኢንሻአላህ፡፡
በዚህ ሀሳብ ዙሪያ የሚናገሩ የቁርኣን ክፍሎች ብዙ ናቸው፡፡ መልእክታቸውን በመረዳት ዙሪያ ግን መስመር የሚስት አልለ (አላህ ያሳወቀው ሲቀር)፡፡ አንዳንድ ሰውም የፍትሕ ጥያቄ ያነሳል፡፡ እንዲህ ሲልም የተቃውሞ ጥያቄ የቀርባል፡- የሂዳያ ነገር ‹አላህ ካልሻ በስተቀር› በሚለው ሀሳብ በሩ የተዘጋና የተቆለፈ ሁኖ እያለ፡ እንዴት የሂዳያውን መንገድ ማግኘት ይቻላል? አንድ ሰው አላህ ልቡን ካሸገውና በአይኑ ላይ መጋረጃን ካደረገበት እንዴት የሐቅን መንገድ ማግኘት ይችላል? የሚል፡፡

ለዚህ ጥያቄ መጠነኛ ምላሹን እንመልከት፡-

1ኛ/ በአላህ ቃል ውስጥ ‹‹አላህ የፈለገውን ይመራል፣ የፈለገውን ያጠማል›› የሚለው አንቀጽ፡ ልክ ‹‹አላህ የፈለገውን ይምረዋል፣ የፈለገውን ደግሞ ይቀጣዋል›› እንደሚለው አንቀጽ ነው፡፡ እነዚህ አንቀጾች ሀሳባቸው ጥቅላዊ ነው፡፡ ‹የፈለገውን› በሚል ሀሳብ ተገለጹ እንጂ፡ እነማናቸው ምሪትን የፈለገላቸው? ጥመትንስ የሻላቸው? የሚለው አልተብራራም፡፡ ስለዚህ ከጥቅላዊ ሀሳብ ተነስተን ስህተት ውስጥ ከመውደቃችን በፊት፡ ይህን ጥቅላዊ ሀሳብ ተፈጻሚነቱ በነማን ላይ እንደሆነ ሊያብራሩ የሚችሉ ሌሎች ዝርዝር ሀሳቦችን ከቃሉ ላይ መፈለግ አለብን፡፡ ቁርኣንን ቁርኣን ያብራራዋልና!!፡፡

” لِلَّهِ مَا فِي السَّمَاوَاتِ وَمَا فِي الْأَرْضِ وَإِنْ تُبْدُوا مَا فِي أَنْفُسِكُمْ أَوْ تُخْفُوهُ يُحَاسِبْكُمْ بِهِ اللَّهُ فَيَغْفِرُ لِمَنْ يَشَاءُ وَيُعَذِّبُ مَنْ يَشَاءُ وَاللَّهُ عَلَى كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ” سورة البقرة 284

“በሰማያት ውስጥና በምድርም ውስጥ ያለው ሁሉ የአላህ ነው፡፡ በነፍሶቻችሁ ውስጥ ያለውን ብትገልጹ ወይም ብትደብቁት አላህ በርሱ ይቆጣጠራችኋል፡፡ ለሚሻውም ሰው ይምራል፡፡ የሚሻውንም ሰው ይቀጣል፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡ ” (ሱረቱል በቀራህ 2፡284፣ 3፡129፣ 5፡18፣ 5፡40፣ 29፡21፣ 48፡14)፡፡

በነዚህ ስድስት የቁርኣን አንቀጾች ውስጥ ‹‹ለሚሻውም ሰው ይምራል፡፡ የሚሻውንም ሰው ይቀጣል›› የሚል ተመሳሳይ ሀሳብ አልለ፡፡ በሌላ የቁርኣን ክፍል ላይ ደግሞ፡- አላህ በክህደትና በሽርክ ተግባር ላይ እያለ፡ ያለ ተውበት የሞተን ሰው በፍጹም እንደማይምረው ይናገራል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በአላህ ላይ ጽኑ እምነት ያለውንና አመስጋኝ የሆነን ሰው እንደማይቀጣው ይገልጻል፡፡ ቃሉ እንዲህ ይነበባል፡-

” إِنَّ اللَّهَ لَا يَغْفِرُ أَنْ يُشْرَكَ بِهِ وَيَغْفِرُ مَا دُونَ ذَلِكَ لِمَنْ يَشَاءُ وَمَنْ يُشْرِكْ بِاللَّهِ فَقَدِ افْتَرَى إِثْمًا عَظِيمًا ” سورة النساء 48
“አላህ በርሱ ማጋራትን በፍፁም አይምርም፤ ከዚህ ሌላ ያለውንም (ኀጢአት) ለሚሻው ሰው ይምራል። በአላህም የሚያጋራ ሰው ታላቅን ኀጢያት በእርግጥ ቀጠፈ።” (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡48፣ 4፡116)፡፡

ጌታ አላህ በዚህ አንቀጽ ስር ‹‹በርሱ ማጋራትን በፍፁም አይምርም!›› በማለት ከነገረን፡ ያለ ተውበት የሞተ ሙሽሪክ (አጋሪ) የሆነ ሰው ‹ለፈለገው ይምራል› የሚባለው ውስጥ አይካተትም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም እሱ ምሕረት አልባ ነውና፡፡

አንቀጹ ይቀጥልና ደግሞ ‹‹ከዚህ ሌላ ያለውንም (ኀጢአት) ለሚሻው ሰው ይምራል›› በማለት፡ ከሺርክ ውጪ የሆኑትን ኃጢአት የፈጸመ ሰው፡ ተውበት ሳያደርግ ቢሞት ጉዳዩ ወደ አላህ ይመለስና፡ አላህ ከፈለገ ሊምረው፡ ካልፈለገ ደግሞ የኃጢአቱን ያህል ይቀጣዋል ማለት ነው፡፡ በዚህም ሰበብ ሺርክን ያልፈጸመና በትክክለኛው የተውሒድ እምነት ላይ ሆኖ የሞተ ሰው ከዘላለም ቅጣት የሚድን ይሆናል ማለት ነው፡፡

” مَا يَفْعَلُ اللَّهُ بِعَذَابِكُمْ إِنْ شَكَرْتُمْ وَآمَنْتُمْ وَكَانَ اللَّهُ شَاكِرًا عَلِيمًا ” سورة النساء 147
“ብታመሰግኑና ብታምኑ፣ አላህ እናንተን በመቅጣት ምን ያደርጋል? አላህም ወሮታን መላሽ አዋቂ ነው።” (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡147)፡፡

በዚህ አንቀጽ ስር ‹‹ብታመሰግኑና ብታምኑ፣ አላህ እናንተን በመቅጣት ምን ያደርጋል?›› በማለት፡ ከኃጢአት ተግባር በተውበት የተመለሱ፡ በእምነታቸው የጸኑና ጌታቸውን ያመሰገኑ ሰዎችን አላህ እንደማይቀጣቸውና እነሱንም በመቅጣት የሚጠቀመው ነገር እንደሌለ ይገልጻል፡፡ ይልቁኑ እሱ አላህ የባሮቹን መልካም ስራ የማያባክን፡ እጥፍ ድርብ አድርጎ በመልካሙ ወሮታን የሚመልስ አምላክ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

ከዚህ በመነሳት፡- የእምነትና የምስጋና ሰዎች ‹የሚሻውንም ይቀጣል› የሚለው ውስጥ እንደማይካተቱ መረዳት እንችላለን ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም አላህ፡- ከኃጢአቱ በተውበት ተመልሶ በእምነቱ የጸናና ጌታውን ያመሰገነን እንደማይቀጣው ተናግሯልና፡፡

አጠቃላይ ሀሳቡ፡- ‹‹አላህ የፈለገውን ይምራል፣ የፈለገውን ይቀጣል›› የሚለውን ጥቅላዊ ገለጻ፡ በሌላ ቦታ ከተዘረዘሩ ዝርዝር ገለጻዎች ጋር በማዛመድ፡ ለቅጣትና ለምህረት የተገቡት እነማን እንደሆኑ መረዳት ይቻላል ማለት ነው፡፡ ወደ ‹ማጥመምና መምራት› ሀሳብ ደግሞ በቀጥታ እንሂድ፡-

” وَلَوْ شَاءَ اللَّهُ لَجَعَلَكُمْ أُمَّةً وَاحِدَةً وَلَكِنْ يُضِلُّ مَنْ يَشَاءُ وَيَهْدِي مَنْ يَشَاءُ وَلَتُسْأَلُنَّ عَمَّا كُنْتُمْ تَعْمَلُونَ ” سورة النحل 93
“አላህም በሻ ኖሮ አንዲት ሕዝብ ባደረጋችሁ ነበር፤ ግን የሚሻውን ሰው ያጠማል፤ የሚሻውንም ሰው ያቀናል፤ ትሠሩት ከነበራችሁትም ሁሉ በእርግጥ ትጠየቃላችሁ።” (ሱረቱ-ነሕል 16፡93፣ 35፡8)፡፡

በዚህ አንቀጽ ስር ‹‹የሚሻውን ሰው ያጠማል፤ የሚሻውንም ሰው ያቀናል›› የሚል ጥቅላዊ ገለጻ አልለ፡፡ እነዚህን ጥቅላዊ ሀሳቦች በአግባቡ ለመረዳት፡ በጉዳዩ ዙሪያ የተነገሩ ዝርዝር ገለጻዎችን ከግምት ማስገባት አለብን፡፡ በሌሎች የቅዱስ ቁርኣን አንቀጾች ላይ አላህ መናፍቃንን፣ ከሀዲያንን፣ ከሐቅ የኮሩትን፣ ከእምነት በኋላ ወደ ክህደት የተመለሱትን፣ ከትእዛዙ አመጸኛ ሆነው ያፈነገጡትን እንደማይመራቸው ይነግረናል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ፡- በተውበት ወደሱ የተመለሱትን፣ በእምነታቸው የጸኑትን፣ ለትዛዙ ያደሩትን፣ በሱ መንገድ የታገሉትን እንደሚመራቸው ይነግረናል፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይነበባል፡-

” وَإِذْ قَالَ مُوسَى لِقَوْمِهِ يَا قَوْمِ لِمَ تُؤْذُونَنِي وَقَدْ تَعْلَمُونَ أَنِّي رَسُولُ اللَّهِ إِلَيْكُمْ فَلَمَّا زَاغُوا أَزَاغَ اللَّهُ قُلُوبَهُمْ وَاللَّهُ لَا يَهْدِي الْقَوْمَ الْفَاسِقِينَ ” سورة الصف 5
“ሙሳም ለሕዝቦቹ ሕዝቦቼ ሆይ! እኔ ወደ እናንተ የአላህ መልክተኛ መሆኔን በእርግጥ የምታውቁ ስትሆኡ ለምን ታሰቃዩኛላችሁ? ባለ ጊዜ (አስታውስ፤ ከውነት) *በተዘነበሉም ጊዘ አላህ ልቦቻቸውን አዘነበላቸው* አላህም አመጠኞችን ሕዝቦች አያቀናም።” (ሱረቱ-ሶፍ 61፡5)፡፡
‹‹*በተዘነበሉም ጊዘ አላህ ልቦቻቸውን አዘነበላቸው*›› የሚለው ላይ ያስምሩበት!!

” فِي قُلُوبِهِمْ مَرَضٌ فَزَادَهُمُ اللَّهُ مَرَضًا وَلَهُمْ عَذَابٌ أَلِيمٌ بِمَا كَانُوا يَكْذِبُونَ ” سورة البقرة 10
“በልቦቻቸው ውስጥ (የንፍቅና) በሽታ አለባቸው፡፡ አላህም በሽታን ጨመረባቸው፡፡ ለነርሱም ይዋሹ በነበሩት ምክንያት አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡10)፡፡

” سَأَصْرِفُ عَنْ آيَاتِيَ الَّذِينَ يَتَكَبَّرُونَ فِي الْأَرْضِ بِغَيْرِ الْحَقِّ وَإِنْ يَرَوْا كُلَّ آيَةٍ لَا يُؤْمِنُوا بِهَا وَإِنْ يَرَوْا سَبِيلَ الرُّشْدِ لَا يَتَّخِذُوهُ سَبِيلًا وَإِنْ يَرَوْا سَبِيلَ الْغَيِّ يَتَّخِذُوهُ سَبِيلًا ذَلِكَ بِأَنَّهُمْ كَذَّبُوا بِآيَاتِنَا وَكَانُوا عَنْهَا غَافِلِينَ ” سورة الأعراف 146

“እነዚያን ያለ አግባብ በምድር ላይ *የሚኮሩትን* ከአንቀጾቼ በ እርግጥ አዞራቸዋለሁ፤ ታምርንም ሁሉ ቢያዩ፣ በርሷ አያምኑም ቅንንም መንገድ ቢያዩ መንገድ አድርገው አይይዙትም ግን የጥመትን መንገድ ቢያዩ መንገድ አድርገው ይይዙታል፤ ይኽ እነሱ በአንቀጾቻችን ስለ አስተባበሉና ከርሷም ዘንጊዎች ስለኾኑ ነው።” (ሱረቱል አዕራፍ 7፡146)፡፡

” كَيْفَ يَهْدِي اللَّهُ قَوْمًا كَفَرُوا بَعْدَ إِيمَانِهِمْ وَشَهِدُوا أَنَّ الرَّسُولَ حَقٌّ وَجَاءَهُمُ الْبَيِّنَاتُ وَاللَّهُ لَا يَهْدِي الْقَوْمَ الظَّالِمِينَ ” سورة آل عمران 86
“ከእምነታቸዉና መልክተኛዉም እዉነት መሆኑን ከመሰከሩ፣ የተብራሩ አንቀጾችም ከመጡላቸዉ በኋላ *የካዱን ሕዝቦች*፥ አላህ አንዴት ያቀናል! አላህ በዳዮችንም ሕዝቦች አያቀናም።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡86)፡፡

” فَبِمَا نَقْضِهِمْ مِيثَاقَهُمْ وَكُفْرِهِمْ بِآيَاتِ اللَّهِ وَقَتْلِهِمُ الْأَنْبِيَاءَ بِغَيْرِ حَقٍّ وَقَوْلِهِمْ قُلُوبُنَا غُلْفٌ بَلْ طَبَعَ اللَّهُ عَلَيْهَا بِكُفْرِهِمْ فَلَا يُؤْمِنُونَ إِلَّا قَلِيلًا ” سورة النساء 155
“ቃል ኪዳናቸውንም በማፍረሳቸው፣ በአላህም አንቀጾች በመካዳቸው፣ ነቢያትንም ያለ አግባብ በመግደላቸውና ልቦቻችን ሽፍኖች ናቸው በማለታቸው ምክንያት፣ (ረገምናቸው)፤ በውነቱ *በክሕደታቸው ምክንያት* አላህ በርሷ ላይ አተመ፤ ስለዚህ ጥቂትን እንጂ አያምኑም።” (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡155)፡፡

ሌሎች ብዙ ጥቅሶችንም ማቅረብ ይቻላል፡፡ ሰዎች ሐቅን ለመቀበል ባለመፈለጋቸው፣ በሐቅ ላይም በመኩራታቸው፣ ማስረጃው ከቀረበላቸው በኋላ አሻፈረኝ በማለታቸው፣ እምነትን በፈቃደኝነት ከተቀበሉ በኋላ በመካዳቸው፣ አስመሳይነት የተጠናወታቸውን ሰዎች አላህ የሚያጠማቸው ከሆነ፡ እንዲህ አይነቶቹ ሰዎች ‹‹የሚሻውንም ይመራል›› የሚባለው ውስጥ አይካተቱም ማለት ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ለምሪት የሚዳረጉትንም እንመልከታቸው፡-

” وَيَقُولُ الَّذِينَ كَفَرُوا لَوْلَا أُنْزِلَ عَلَيْهِ آيَةٌ مِنْ رَبِّهِ قُلْ إِنَّ اللَّهَ يُضِلُّ مَنْ يَشَاءُ وَيَهْدِي إِلَيْهِ مَنْ أَنَابَ ” سورة الرعد 27
“እነዚያም የካዱት፥ በርሱ ላይ ከጌታው ታምር ለምን አልተወረደም ይላሉ፤ አላህ የሚሻውን ያጠማል፤ የተመለሰውንም ሰው ወደርሱ ይመራል፥ በላቸው።” (ሱረቱ-ረዕድ 13፡27)፡፡

” شَرَعَ لَكُمْ مِنَ الدِّينِ مَا وَصَّى بِهِ نُوحًا وَالَّذِي أَوْحَيْنَا إِلَيْكَ وَمَا وَصَّيْنَا بِهِ إِبْرَاهِيمَ وَمُوسَى وَعِيسَى أَنْ أَقِيمُوا الدِّينَ وَلَا تَتَفَرَّقُوا فِيهِ كَبُرَ عَلَى الْمُشْرِكِينَ مَا تَدْعُوهُمْ إِلَيْهِ اللَّهُ يَجْتَبِي إِلَيْهِ مَنْ يَشَاءُ وَيَهْدِي إِلَيْهِ مَنْ يُنِيبُ ” سورة الشورى 13

“ለናንተ ከሃይማኖት ያንን በርሱ ኑሕን ያዘዘበትን ደነገገላችሁ፤ ያንንም በርሱ ኢብራሂምን፣ ሙሳንና ዒሳንም ያዘዘበትን፣ ሃይማኖትን በትክክል አቋቋሙ፣ በርሱም አትለያዩ ማለትን (ደነገግን) በአጋሪዎቹ ላይ ያ ወደርሱ የምትጠራቸው ነገር ከበዳቸው፤ አላህ የሚሻውን ሰው ወደርሱ (እምነት) ይመርጣል፤የሚመለስንም ሰው ወደርሱ ይመራል።” (ሱረቱ-ሹራ 42፡13)፡፡

” وَالَّذِينَ اجْتَنَبُوا الطَّاغُوتَ أَنْ يَعْبُدُوهَا وَأَنَابُوا إِلَى اللَّهِ لَهُمُ الْبُشْرَى فَبَشِّرْ عِبَادِ * الَّذِينَ يَسْتَمِعُونَ الْقَوْلَ فَيَتَّبِعُونَ أَحْسَنَهُ أُولَئِكَ الَّذِينَ هَدَاهُمُ اللَّهُ وَأُولَئِكَ هُمْ أُولُو الْأَلْبَابِ ” سورة الزمر 18-17

“እነዚያም ጣዖታትን የሚግገዟት ከመሆን የራቁ ወደ አላህም የዞሩ ለነርሱ ብስራት አላቸው፤ ስለዚህ ባሮቼን አብስር። እነዚያን ንግግርን የሚያዳምጡትንና መልካሙን የሚከተሉትን፣ (አብስር)፤ እነዚያ፣ እነርሱ አላህ የመራቸው ናቸው። እነዚያም እነሱ ባለ አእምሮዎች ናቸው።” (ሱረቱ-ዙመር 39፡17-18)፡፡

” الَّذِينَ آمَنُوا وَلَمْ يَلْبِسُوا إِيمَانَهُمْ بِظُلْمٍ أُولَئِكَ لَهُمُ الْأَمْنُ وَهُمْ مُهْتَدُونَ ” سورة الأنعام 82
“እነዚያ ያመኑና እምነታቸውን በበደል ያልቀላቀሉ እነዚያ ለእነርሱ ጸጥታ አላቸው፡፡ እነሱም የተመሩ ናቸው” (ሱረቱል አንዓም 6፡82)፡፡
” وَالَّذِينَ جَاهَدُوا فِينَا لَنَهْدِيَنَّهُمْ سُبُلَنَا وَإِنَّ اللَّهَ لَمَعَ الْمُحْسِنِينَ ” سورة العنكبوت 69

“እነዚያም በኛ መንገድ የታገሉ መንገዳችንን በእርግጥ እንመራቸዋለን፤ አላህም በእርግጥ ክበጎ ሠሪዎች ጋር ነው።” (ሱረቱል ዐንከቡት 29፡69)፡፡

በነዚህና መሰል አንቀጾች ስር፡ አላህ፡- ከጣኦታት ርቀው በተውበት የተመለሱትን፣ እምነታቸውን በበደል (በሽርክ) ያልቀላቀሉትን፣ በሱ መንገድም የታገሉትን ቅኑን ጎዳና በመምራት በሐቅ ላይ የሚያጸናቸው ከሆነ፡ እነዚህና መሰሎቻቸው ‹‹የፈለገውን ያጠማል›› የሚለው ውስጥ አይካተቱም ማለት ነው፡፡ እነሱ በአላህ ተውፊቅ ምሪቱን አግኝተዋልና፡፡

አጠቃላይ ሀሳቡ፡- ‹አላህ የፈለገውን ያጠማል፣ የፈለገውን ይመራል›› የሚለውን ጥቅላዊ ገለጻ፡ ከሌሎች የቁርኣን ዝርዝር ገለጻዎች ጋር በማዛመድ፡ አላህ ለጥመት የሻቸውንና፡ ሊመራቸው የፈለገው እነማንን እንደሆነ መረዳት ይቻላል ማለት ነው፡፡

ይህ ጥቅላዊ አንቀጾችን በዝርዝር ከተነገሩት ጋር በማዛመድና በማቆራኘት ‹‹አላህ የፈለገውን ይመራል፣ የፈለገውን ያጠማል›› ለሚለው መነሻ ሀሳብ የተሠጠ አንደኛው የመልስ መንገድ ነው፡፡ በቀጣዩ ክፍል ደግሞ፡ ሁለተኛና ሶስተኛ የመልስ መንገዶችን እንመለከታለን ኢንሻአላህ፡፡
ወአኺሩ ዳዕዋና ዐኒል-ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡