የቅድመ ውሳኔን (ቀዷ ወል-ቀደር) ጽንሰ ሃሳብ በተመለከተ ክፍል -8

1,294 Views

አቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡

3ኛ. ከሁሉን ቻይነቱ አንጻር፡-

ሰሞኑን የቀዷ ወል-ቀደር ክፍል የሆነውን ‹‹መሺኣህ›› (የአላህ ፈቃድ)ን በተመለከተ የተወሰኑ ነጥቦችን ዳስሰናል፡፡ በተለይ ‹‹አላህ የፈለገውን ይመራል፣ የፈለገውን ደግሞ ያጠማል›› በሚለው ዙሪያ፡ የቃሉን መልእክት ለመግለጽ ሁለት አይነት መልሶችን ተመልክተናል፡፡ እነሱም፡-

1/ ‹‹አላህ የፈለገውን ይመራል፣ የፈለገውን ደግሞ ያጠማል›› የሚለው ሀሳብ ጥቅላዊ ሀሳብ በመሆኑ፡ መልእክቱን በአግባቡ ለመረዳት በሌላ ቦታ ላይ በጉዳዩ ዙሪያ የተነገረ ዝርዝር ሃሳብ መፈለግና፡ ያን ዝርዝር ሀሳብ በጥቅል ከተነገረው ጋር በማስማማትና በማገናዘብ ቃሉን መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ይህ ሀሳብ ጥቅላዊ እንደመሆኑ መጠን፡ ሀሳቡን የሚያብራሩና የሚገልጹ ሌሎች የቁርኣን ክፍሎችን በማንሳት፡ ለጥመት የሚዳረጉ ሰዎችንና ለምሪት የሚዳረጉትን በመጥቀስ አይተናል፡፡ በውስጡም አላህ የሚያጠማቸው፡- እራሳቸውን ከሐቅ መስመር ያሸሹ፣ በኃጢአት ባህር ላይ የዋኙ፣ ከእምነት በኋላ የካዱ፣ ሐቅን ለመቀበል ኩራት የያዛቸውና መሰሎቻቸው ላይ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል፡፡

በተቃራኒው ደግሞ፡- የነቢያትና የዳዒዎችን ምክር የሚሰሙ፣ በተውበት ወደ ጌታቸው የሚመለሱ፣ በተውሒድ ላይ ጽናትን ያሳዩትን ደግሞ አላህ በራሕመቱ ሂዳያን እንደሚለግሳቸውና ወደ እውነት መንገድም እንደሚመራቸው ተመልክተናል፡፡ ከዚህ ተነስተን ‹‹አላህ የፈለገውን ያጠማል፣ የፈለገውን ደግሞ ይመራል›› የሚለው፡ ውሳኔው ከአላህ ዘንድ ሁኖ ሰው ግን ለዚህ ምሪትም ሆነ ጥመት ሰበብ እንደሚሆን ተረድተናል ማለት ነው፡፡

2/ ‹‹አላህ የፈለገውን ይመራል፣ የፈለገውን ደግሞ ያጠማል›› የሚለውን ሀሳብ የምንረዳበት ሌላኛው መንገድ ከአላህ ሁሉን ዐዋቂነት አንጻር ነው፡፡ እሱም፡- ማን የአላህን መንገድ ፈላጊ እንደሆነና ማን ለስሜቱ ተገዢ እንደሆነ ልብን በመመርመር የሚያውቀው አላህ ብቻ ነው፡፡ በዚህም ሰበብ ሂዳያ ለሚገባው ሂዳያን በመለገስ፣ ጥመት ለሚገባው ጥመትን በመወሰን አላህ የሻውን ይሰራል፡፡ እሱ የጥበብ ባለቤት ነውና የሚለውን ተመልክተናል፡፡ ምሣሌም ይሆነን ዘንድ፡ የአቡ ጧሊብ፣ አቡ ለሀብና አቡ ጀህልን አንስተን የነሱን ጉዳይ ተመልክተናል፡፡ ለዛሬ ደግሞ አላህ ፈቃዱ ከሆነ ቀጣዩን ሶስተኛ ምላሽ እናያለን ኢንሻአላህ፡፡

ስለ አላህ ማንነት መጠነኛ ግንዛቤ ያለው ሙስሊም ‹‹አላህ የፈለገውን ያጠማል፣ የፈለገውን ደግሞ ያቀናል›› የሚለው ሀሳብ ከእምነት አንጻር ምንም ችግርና ግራ የመጋባት ስሜት አይፈጥርበትም፡፡ ምክንያቱም ‹ፈቃድ› ሁሉ የአላህ እንደሆነ ስላወቀና ስላመነ!፡፡ ከሱ የሚጠበቀው፡ አቅሙ በቻለው መጠን የጌታውን ትእዛዝ በመፈጸምና ከከለከለው ነገር ለመራቅ እየታገለ የአላህን እገዛ መሻት፣ በኃጢአቱ ሰበብ ደግሞ የራሕመት በሩን ዘግቶበት እንዳያጠመው መፍራትና መጠንቀቅ፣ ኃጢአት ላይ ከወደቀም ቶሎ በተውበት መነሳት እንጂ፡ እንዴት እሱ የፈለገውን ያጠማል? ብሎ በመለኮታዊ አሰራሩ ጣልቃ በመግባት፡ የተቃውሞ ጥያቄ ማቅረብ አይደለምና፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-

” لَا يُسْأَلُ عَمَّا يَفْعَلُ وَهُمْ يُسْأَلُونَ ” سورة الأنبياء 23
“ከሚሠራው ሁሉ አይጠየቅም እነሱ (ፍጥረቶቹ) ግን ይጠየቃሉ።” (ሱረቱል አንቢያእ 21፡23)፡፡

አዎ! እሱ ጌታችን አላህ፡- በዕውቀቱ ምሉእ የሆነ የማይረሳ፣ በጥበቡ ከፍጡራኑ አምሳያ የሌለው ፍጹም ጥበበኛ፣ በችሎታው ምንም የማያቅተው ሁሉን ቻይ በመሆኑ፡ እሱ በወሰነውና በሚሰራው ነገር ማንም፡ ለምን እንዲህ አደረግህ? ብሎ ሊጠይቀው አይችልም!፡፡ እሱ ግን ባሮቹን በሰጣቸው ኃላፊነት ይጠይቃቸዋል፡፡ ይተሳሰባቸዋልም፡፡

ከተቃውሞ ጥያቄ ውጭ ግን፡ አላህ ይህን የማድረጉ ሚስጥር ምን ይሆን? አይነት ዕውቀትን የመሻት መጠይቅ በኢስላም አልተከለከለም፡፡ “የማታውቁ ከሆናችሁ የዕውቀት ባለቤቶችን ጠይቁ” የሚለው አምላካዊ ቃልና፡ ‹‹የመሃይም መድኃኒቱ መጠየቅ ነው›› ነው የሚለው ነቢያዊ ሐዲሥ ለጉዳዩ ህያው ምሥክር ናቸውና፡፡ ወደ ገደለው ስንገባ፡-

‹‹አላህ የፈለገውን ያጠማል›› በሚለው ሀሳብ ላይ፡ በተለይ ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች ጥሩ ስሜት አይሰማቸውም፡፡ ከአምላክ አዛኝነትና ፍጹም ፍትሐዊነት ጋር እንደሚጋጭ ይገምታሉ፡፡ እንዲህ ሲሉም ይደመጣሉ፡- ሰውን የሚያጠመው ሰይጣን ነው እንጂ፡ አምላክ አይደለም!፡፡ አምላክ ሰውን ወደ እውነት ይመራል እንጂ እንዴት ያጠማል? ማጥመም የሱ ስራ አይደለም! የሚል ነው፡፡

ሀሳቡ ከላይ ሲታይ ጥሩ መልእክት ይመስላል፡፡ አምላክን ከበደለኛነት የማራቅ ስሜት የወለደው ሀሳብ እንደሆነም ያስታውቃል፡፡ ነገር ግን ይህ አመለካከት ከኋላው እጅግ አደገኛ የሆነ ስህተትን አዝሏል፡፡ የአላህን አምላክነት የሚጋፋ ሌላ ኃይል እንዳለ በውስጠ-ታዋቂነት ይናገራል፡፡ እንዴት? የሚሉ ከሆነም፡ ረጋ ባለ መንፈስ ቀጥሎ የሚቀርቡትን ነጥቦች እንመልከታቸው፡-

ሀ/ በዚህ ዓለም ላይ አንድ ፈቃድ እንጂ ሁለት ፈቃድ የለም፡፡ የሚሆነው ነገር በጠቅላላ ከዚሁ አንድ ፈቃድ ይሁንታ በኋላ የተገኘ እንጂ፡ የብዙ አካላት ፈቃዶች ውጤት አይደለም፡፡ ይህ አንድ ፈቃድም፡- ገደብ አልባ የሆነው የፈጣሪ አምላካችን አላህ ፈቃድ ነው፡፡ ዓለሙን በጠቅላላ የፈጠረና ደግሞም በዓለሙ ላይ የነገሠ ብቸኛ ንጉሥ እሱ ብቻ ነው፡፡ ከሱ ውጭ ፈጣሪ እንደሌለ ሁሉ፡ በዓለሙም ላይ የነገሠ ከሱ ውጭ ሌላ ንጉሥ የለም፡፡ ታዲያ ይህ ብቻውን ፈጣሪና ንጉሥ የሆነ አምላክ፡ በንግስናው ላይ ከፈቃዱ ውጭ የሆነ ነገር ይከሰታል ብሎ ማሰብ ይቻላልን? እሱ ሊመራቸው ያልፈለገውን ማን የመምራትና የማቅናት ስልጣን ይኖረዋል? እሱ ሊያጠማቸው ያልፈለገውን ባሮቹንስ ማን የማጥመምና ከሐቅ የማስወጣት አቅም ሊኖረው ይችላል? ዓለም የምትመራው በአንድ ፈቃድና ኃይል ወይስ በተለያዩ ፈቃዶች? ስለዚህ፡- ባሮቹን በፈቃዱ የሚመራውና የሚያቀናው እሱ ብቻ እንደሆነ ሁሉ፡ በፈቃዱ የፈለገውን የሚያጠመውም እሱ ብቻ ነው፡፡

“أَلَيْسَ اللَّهُ بِكَافٍ عَبْدَهُ وَيُخَوِّفُونَكَ بِالَّذِينَ مِنْ دُونِهِ وَمَنْ يُضْلِلِ اللَّهُ فَمَا لَهُ مِنْ هَادٍ * وَمَنْ يَهْدِ اللَّهُ فَمَا لَهُ مِنْ مُضِلٍّ أَلَيْسَ اللَّهُ بِعَزِيزٍ ذِي انْتِقَامٍ ” سورة الزمر 37-36
“አላህ ባሪያውን በቂ አይደለምን? በነዚያ ከርሱ ሌላ በሆኑትም፣ (ጣዖታት)፣ ያስፈራሩሃል፤ አላህ የሚያጠመውም እርሱ ምንም አቅኚ የለውም። አላህ የሚያቀናውም ሰው ለርሱ ምንም አጥማሚ የለውም፤ አላህ አሸናፊ፣ የመበቀል ባለቤት አይደለምን?” (ሱረቱ-ዙመር 39፡36–37)፡፡

ጌታ አላህ በዚህ አንቀጽ ውስጥ ለነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከለላቸውና ጠባቂያቸው እሱ መሆኑን እየተናገረ ነው፡፡ ሙሽሪኮች አማልክቶቻችንን በመጥፎ ካነሳሃቸው አንዳች ነገር ያደርጉሀል እያሉ በጣኦቶቻቸው ለማስፈራራት ሲሞክሩ፡ አላህ ደግሞ ለባሪያዬ ጥበቃ እኔ በቂ ነኝ እያለ ነው፡፡ በክህደታቸው ሰበብ ደግሞ አላህ ለጥመት የዳረጋቸውን ማንም ሊያቀናቸው እንደማይችል፡ እንዲሁም በአላህ ራሕመት ለምሪት ‹ለሂዳያ› የወፈቃቸውን ደግሞ ማንም ሊያጠማቸው እንደማይችል በግልጽ ተናገረ፡፡ አላህ ውሳኔው ተፈጻሚ፡ ቃሉ አሸናፊና ከሀዲያንንም ተበቃይ የሆነ አምላክ ነውና፡፡

ልባችንም ያለው በአላህ ቁጥጥር ስር ብቻ ነው፡፡ ማንም ሊያስተካክለውም ሆነ ሊያበላሸው አይችልም፡፡ ለዚህም ነው ሱጁድ ላይ ስንሆን ‹‹ያ ሙቀሊበል-ቁሉብ ሠቢት ቁሉበና ዓላ ዲኒክ›› የምንለው፡፡ (ልቦችን እንደፈለግህ የምትገለባብጥ ጌታችን አላህ ሆይ! ልባችንን አንተው በወደድከው ዲን ላይ ጽናትን ለግሰው) ማለት ነው፡፡

ከዚህ አስተሳብ ውጪ በሆነ መልኩ፡ ሰይጣንም የፈለገውን ያጠማል! የምንል ከሆነ፡ ለዓለማችን ሁለት ጌታን አበጅተናል ማለት ነው፡፡ አንደኛው የፈለገውን የሚመራና የሚያቀና ሲሆን፡ ሌላኛው ደግሞ የፈለገውን የሚያበላሽና የሚያጠም ማለት ነው፡፡ አንደኛው የመራውን ሌላኛው ካጠመመበት፡ ወይንም ሌላኛው ያጠመመውን ይኸኛው ካስተካከለውና ካቀናበት፡ ‹‹የፈለገውን› የሚለው ለሁለቱም አይሰራም ማለት ነው፡፡ ምክነያቱም በአንዱ ፍላጎት ላይ ሌላው ጣልቃ እየገባ ነውና፡፡ ታዲያ ዓለማችን የምትመራው በአንድ ፈቃድ ወይስ ምን?

ለ/ የሚያጠመው ‹ሰይጣን› እንጂ አምላክ አይደለም የምትሉ ሰዎች ሆይ!፡- ይህ እምነታችሁና አቋማችሁ ከሆነ፡ ቀጣዩን ጥያቄ ለመመለስ ሞክሩ፡፡ እሱም፡- አምላክ ሊመራው የፈለገውን ሰው ነው ሰይጣን የሚያጠመው፡ ወይስ አምላክ መጥመሙ የሻለትን ሰው ነው ሰይጣን የሚያጠመው?
የናንተ መልስ፡- አምላክ ሊመራው የፈለገውን ባሪያውን ሰይጣን ግን አጠመመው! የሚል ከሆነ፡ የሰይጣን ፈቃድ ከአምላክ ፈቃድ በላይ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህን ባሪያ አምላክ ሊመራው ፈለገ፡፡ ሰይጣን ደግሞ ሊያጠመው ፈለገ፡፡ በውጤቱም በሰውየው ላይ የታየው ሰይጣን የፈለገው ነገር ከሆነ፡ የሰይጣን ፈቃድ አሸናፊ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ታዲያ አምላክ የሚባለው ሰይጣን ወይስ ማን?

አይ! አምላክ ሊመራው ያልፈለገውን ነው ሰይጣን ያጠመመው! ካላችሁ ደግሞ፡ ከንግግራችሁ ተመልሳችኋል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም አምላክ ሊመራው ያልፈለገውን ሰው ነው ማለት፡ በተቃራኒው ሊያጠመው ፈልጓል ማለት ነው፡፡ በመምራትና በማጥመም መሀል ሶስተኛ አማራጭ የለምና፡፡ሰይጣንም ይህን የአምላክ ባሪያ ያጠመመው ቀድሞውኑ አምላክ መጥመሙን በመፈለጉ፡ ለሰይጣን አሳልፎ ሰጠው ማለት ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ ሰይጣንም ከአምላክ ፈቃድ መውጣት እንደማይችልና አላህ ሊመራው በፈለገው ባሪው ላይ ድርሻ እንደሌለው ነው፡፡ ከሁለት አንዱን ምረጡና አቋም ያዙ፡፡ አላህ ቃል ግን እንዲህ ያስተምራል፡-

” فَإِذَا قَرَأْتَ الْقُرْآنَ فَاسْتَعِذْ بِاللَّهِ مِنَ الشَّيْطَانِ الرَّجِيمِ * إِنَّهُ لَيْسَ لَهُ سُلْطَانٌ عَلَى الَّذِينَ آمَنُوا وَعَلَى رَبِّهِمْ يَتَوَكَّلُونَ * إِنَّمَا سُلْطَانُهُ عَلَى الَّذِينَ يَتَوَلَّوْنَهُ وَالَّذِينَ هُمْ بِهِ مُشْرِكُونَ ” سورة النحل 100-98

“ቁርአንንም ባነበብህ ጊዜ፣ ርጉም ከሆነው ሰይጣን በአላህ ተጠበቅ። እርሱ በነዚያ ባመኑትና በጌታቸው ላይ በሚጠጉት ላይ ለርሱ ሥልጣን የለውምና። ሥልጣኑ በነዚያ በሚታዘዙት ላይና በነዚያም እነርሱ በርሱ (ምክንያት) አጋሪዎች በሆኑት ላይ ብቻ ነው።” (ሱረቱ-ነሕል 16፡98-100)፡፡

ሐ/ ጥያቄው ፊቱን ወደኛ በማዞር እንዲህ ተብለን ልንጠየቅ እንችላለን፡- በናንተስ እምነት ሰይጣን እንደሚያጠም አልተገለጸም ወይ? የሚል፡፡
ምላሹም፡- በሚገባ እንጂ! የሚል ነው፡፡ በብዙ የቁርኣን ክፍሎች ላይ ሸይጧን ወደ ጥመት ጎዳና እንደሚጣራና የተከተሉትንም እንደሚያጠማቸው ተገልጾአል፡፡ ልዩነቱ ግን፡ በነዚህ ክፍሎች ላይ የሸይጧን አጥማሚነት የተገለጸው፡ ሰበብ ‹ምክንያት› ከመሆን አንጻር እንጂ ከመወሰንና የልብን በር ከመዝጋት አንጻር አይደለም፡፡ ማለትም፡-

ሸይጧን ሰዎችን ከሐቅ መንገድ ለማውጣት፡ በኃጢአት ባህር ውስጥ እንዲዋኙ ለማድረግ፡ አላህን ከማምለክ ሰዎችን ለማዘናጋት የሚያደርገው ጥረት በጠቅላላ ‹‹ጉትጎታ›› ላይ ብቻ የተገደበ ነው፡፡ ይህንን የሸይጧንን ጉትጎታ በእምቢተኝነት አለመቀበል እንችላለን፡፡ እንቢተኝነታችንን ቀይሮ እሺ እንድንለው ለማድረግ ግን ልባችን ላይ ስልጣን ስላልተሰጠው አይችልም፡፡

በዚህም ሰበብ ጥመትን ወደ ሸይጧን በማስጠጋት ‹‹ሸይጧን አጠመመ›› ስንል፡ ወደ ክህደት መስመር መጣራቱን፣ ሀሰትን እውነት አድርጎ ለማቅረብ ማስመሰሉን፣ ሰዎችን ከአምልኮ ለማዘናጋት መንገዶችን መጠቀሙን እንጂ፡ በልባችን ላይ ተሹሞ የፈለገውን ሊያጠም ኃይል ተሰጠው ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሸይጧንን ጥርሪ መቃወም እና በተቃራኒው የአላህን ጥርሪ በመቀበል መልካሙን መንገድ መከተል እንችላለንና፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-

” الَّذِينَ آمَنُوا يُقَاتِلُونَ فِي سَبِيلِ اللَّهِ وَالَّذِينَ كَفَرُوا يُقَاتِلُونَ فِي سَبِيلِ الطَّاغُوتِ فَقَاتِلُوا أَوْلِيَاءَ الشَّيْطَانِ إِنَّ كَيْدَ الشَّيْطَانِ كَانَ ضَعِيفًا ” سورة النساء 76
“እነዚያ ያመኑት ሰዎች፣ በአላህ መንገድ ይጋደላሉ፤ እነዛ የካዱትም በጣዖት መንገድ ይጋደላሉ፤ የሰይጣንንም ጭፍሮች ተጋደሉ። የሰይጣን ተንኮል ደካማ ነውና።” (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡76)፡፡

ነገር ግን በኃጢአቱ ሰበብ አላህ ሊያጠመው የፈለገውን ሰው፡ ማን ሊከላከልለት ይችላል? ከፍጡራንስ ይህ አቅም ያለው ሰው አልለ? ማንም የለም!!፡፡ በመሆኑም ‹‹አላህ የፈለገውን ያጠማል›› ብለን ስንናገር አላህ በባሪያዎቹ ላይ ሙሉ ስልጣን ያለው አምላክ መሆኑን፣ ልባቸውም በሱ ቁጥጥር ስር ስለሆነ ለፈለገው በራሕመቱ ሂዳያውን በመለገስ ቅኑን ጎዳና እንደሚመራውና፡ ማንም ሰው ይህን የተመራ የአላህ ባሪያን፡ ከአላህ መንገድ በገዛ ኃይሉ ሊያስወጣው እንደማይችል፣ በተቃራኒው በኃጢአቱ ሰበብ አላህ ለጥመት የፈለገውን ሰው፡ ሊያጠመውና ልቡን ሊዘጋበት እንደሚችል፣ ማንም ሰው ይህን የጠመመ ባሪያን፡ ወደ እውነት መመለስ እንደማይችል እንረዳለን ማለት ነው፡፡

ከዛ ውጭ የሸይጧንና የከሀዲያን ሰውን ከሐቅ መንገድ የማስወጣት ጥረት ከጉትጎታ የዘለለ ሚና የለውም፡፡ የሁለቱ ወላጆቻችንን የአደምና የሐዋእን (ዐለይሂማ-ሰላም) ታሪክ ማየቱ በራሱ ትልቅ አስረጂ ነው፡፡ ከነበሩበት የድሎት ዓለም (ጀነት) የወጡት በሸይጧን ሰበብ ነው፡፡ በወቅቱ ግን የሸይጧን ሚና ከጉትጎታ የዘለለ አልነበረም፡፡ አላህ እንዳይቀርቡት የከለከላቸውን ዛፍ፡ በግድ ከፍሬው ወይም ከቅጠሉ ወስዶ አላጎረሳቸውም፡፡ ባይሆን የተከለከሉት፡- ከዛፉ ወስደው ከበሉ ዘላለም መኖር እንደሚችሉና የማይቋረጥ የሆነን ንግስና እንደሚያገኙ በመጠቆም አታለላቸው እንጂ፡፡ እነሱም የሸይጧንን የሀሰት ምክር በመቃወም ከፊታቸው ማባረር ይችሉ ነበር፡፡ ለሱ የመጎትጎት ነጻ ፈቃድ እንደተሰጠው ሁሉ፡ አደምና ሐዋእም (ዐለይሂማ-ሰላም) መቃወምና ማባረር ይችሉ ነበር፡፡ ምኞት አታለላቸውና እጅ በመስጠት ተሸነፉ እንጂ፡፡ ሆኖም ኋላ ላይ ወደ አላህ ተውበት በማድረግ ተመልሰው ከወደቁበት በመነሳት ድል የነሳቸውን ሸይጧን አሁን ደግሞ በተራቸው ድል ነሱት፡፡ ማንኛውም ነገር ፍፃሜው ሲያምር ደስ ይላል፡፡ አላህ መጨረሻችንን ያሳምርልን፡፡

ማጠቃለያ፡-

‹‹አላህ የፈለገውን ያጠማል›› መባሉ ከተሳሳተ ትርጓሜ በመነሳት መጥፎ ስሜት ሊፈጥርብን በፍጹም አይገባም!፡፡ እኛ የአላህ ንብረቶች ነን፡፡ አላህ በንብረቱ ላይ የፈለገውን የማድረግ ሙሉ ስልጣን አለው፡፡ የፈለገውን ማድረጉም ‹‹መብት›› እንጂ ‹‹በደል›› አይሰኝም፡፡ በደል ማለት፡- አንድን ነገር ተገቢው ስፍራ ላይ አለማስቀመጥ ወይንም በሌሎች ንብረት ያለ ፈቃዳቸው መጠቀም ማለት ነው፡፡
ታዲያ አላህ በገዛ ንብረቱ እንደፈለገ ቢጠቀምብን መብቱ አይደለምን? ወደ ሐቅ ጎዳና ቢመራንና ከቅጣቱ ቢያዝንልን፡ ይህ የ‹ራሕመቱ› ውጤት እንጂ የኛ ስራ ተገቢነት አይደለም፡፡ ሂዳያን ቢከለክለንና ቢቀጣን ደግሞ፡ የፍትሀዊነቱ ውጤት እንጂ ‹በደል‹ አይደለም፡፡ ስራችን ለቅጣት እንጂ ለራሕመት የሚያደርስ አይደለምና፡፡ ኃጢአታችን እጅጉኑ በዝቷልና፡፡ እስካሁንም ያለነው በራሕመቱ ሰበብ እንጂ መች በስራችን ሆነና፡፡ ስለዚም፡-
ጌታችን ሆይ! በእዝነትህና በቸርነትህ እውነቱን ጎዳና ከመራኻቸው ባሮችህ አድርገን፣ በወንጀላቸውና በኃጢአታቸው ሰበብ ለቅጣትና ለጥመት አሳልፈህ ከሰጠሀቸው ባሮችህ አታድርገን እንበል፡፡

ወአኺሩ ዳዕዋና ዐኒል-ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡