የቅድመ ውሳኔን (ቀዷ ወል-ቀደር) ጽንሰ ሃሳብ በተመለከተ ክፍል -7

1,247 Views

አቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡

2ኛ. ከሁሉን ዐዋቂነቱ አንጻር፡-

ባለፈው በክፍል ስድስት ላይ ‹‹አላህ የፈለገውን ይመራል፣ የፈለገውን ደግሞ ያጠማል›› የሚለውን አምላካዊ ቃል አንስተን፡ በዚህ ሀሳብ ዙሪያ የሚነሳውን የፍትሕ ጥያቄ ከነመልሱ ለማየት ሞክረናል፡፡ ይህ ሀሳብ ጥቅላዊ እንደመሆኑ መጠን፡ ሀሳቡን የሚያብራሩና የሚገልጹ ሌሎች የቁርኣን ክፍሎችን በማንሳት፡ ለጥመት የሚዳረጉ ሰዎችንና ለምሪት የሚዳረጉትን አይተናል፡፡ ከጥቅል ሀሳብ ብቻ ተነስተን ‹‹አላህ የፈለገውን ይመራል፣ የፈለገውን ደግሞ ያጠማል›› የሚለውን መተንተን ስህተት ላይ እንደሚጥለንና፡ የግድ በሌላ ቦታ ከተነገሩ ዝርዝር ሀሳቦች ጋር ማስማማትና ማገናኘት እንዳለብን ተመልክተናል፡፡ በዝርዝር ሀሳቦቹም ላይ ሰዎችን ለጥመት ወይም ለምሪት የሚዳርጋቸው ምን ምን እንደሆነ የተወሰኑ ማስረጃዎችን ተመልክተናል፡፡ ዛሬ ደግሞ ከጥያቄው ሳንወጣ ሌላኛውን የመልስ አይነት በአላህ ፈቃድ እንመለከተዋለን ኢንሻአላህ፡፡

ፈጣሪ አምላካችን አላህ ከባሮቹ ውስጥ ‹‹የሚሻውን ይመራል፣ የሚሻውን ደግሞ ያጠማል›› መባሉ ምንም አዲስና እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በቀላሉ የሚሰጥጠው ምላሽ፡- አላህ ከባሮቹ መካከል የሚሻውን መምራቱና፡ እሱ የሚሻውን ማጥመሙ የሚያሳየን፡ ማን ለምሪት የተገባ እንደሆነ፡ ማን ደግሞ ጥመት የሚገባው እንደሆነ ልባቸውን በመመርመር የሚያውቅ አምላክ ስለሆነ ነው የሚል ነው፡፡ ቀጣዩ የአላህ ቃል ይህን እውነት ያጎላዋል፡-

” إِنَّكَ لَا تَهْدِي مَنْ أَحْبَبْتَ وَلَكِنَّ اللَّهَ يَهْدِي مَنْ يَشَاءُ وَهُوَ أَعْلَمُ بِالْمُهْتَدِينَ ” سورة القصص 56
“አንተ የወደድከውን ሰው ፈጽሞ #አታቀናም፡፡ ግን አላህ የሚሻውን ሰው ያቀናል እርሱም ቅኖቹን ዐዋቂ ነው፡፡” (ሱረቱል ቀሶስ 28፡56)፡፡

የቁርኣን ተንታኞች (ሙፈሲሪን) ቡኻሪና ሙስሊም ላይ የተቀመጠውን ዘገባ መሰረት በማድረግ፡ ይህ አንቀጽ የወረደው በአቡ ጧሊብ ሰበብ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ነቢያችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) አጎታቸውን አባ-ጧሊብ መጨረሻ ህይወቱ ላይ ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› በማለት ፍጻሜው እንዲስተካከል ጥረት አደረጉ፡፡ እሱ ግን ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› የሚለውን የምስክርነት ቃል መስጠት አልፈለገም፡፡ በአባቱ ዐብዱል-ሙጦሊብ መንገድ መሆኑን ገለጸና ሳይሰለም ሞተ፡፡ እሳቸውም ሳይሰልም በመሞቱ እጅግ አዘኑ፡፡ የአላህ ቃልም እንዲህ ሲል በመውረድ አጽናናቸው፡-
“አንተ የወደድከውን ሰው ፈጽሞ አታቀናም!” በዚህ ቃል መሰረት፡ ሰዎችን ማቅናትና ማስተካከል፡ እውነትንና እምነትን በልቦናቸው ማኖር የአላህ እንጂ የአንተ ድርሻ አይደለም አላቸው፡፡ አንተ ድርሻህ የእውነትን መንገድ ከሀሰት አበጥረህ ለሰዎች ማሳየት፡ መምራትና ማመላከት እንጂ፡ ያንኑ ያብራራኸውንና የገለጽከውን እውነት፡ ልባቸው ያምንና ይቀበለው ዘንድ እነሱን ማቅናትና ማስተካከል አይደለም አለ፡፡ ይህ ችሎታ የማን እንደሆነ ሲገልጽ ደግሞ ቀጠለና፡-

“ግን አላህ የሚሻውን ሰው ያቀናል” አለ፡፡ ማቅናትና ማስተካከል የኔ ብቻ ነው እያለ ነው፡፡ ምክንያቱም፡-
“እርሱም ቅኖቹን ዐዋቂ ነው” ይለናል፡፡ የነቢያትንም ሆነ የአማኞችን ዳዕዋ (ሃይማኖታዊ ስብከት) በመስማት ሐቅ ፈላጊ የሆነና ያልሆነ ልብን አበጥሮ የሚያውቀው እሱ ብቻ ነውና፡፡ ለሁሉም እንደ ልፋቱ ተገቢውን ካሳ ይከፍለዋል ማለት ነው፡፡ እኛ የምናውቀው ውጪያዊ ገጽታን (ንግግርና ተግባርን) ብቻ ነውና፡፡ እንደው ይህ ልጅ እኮ ላ ኢላሀ ኢልለሏህ ማለት ብቻ ነው የቀረው እንጂ፡ ሁሉ ነገሩ እኮ የሙስሊም ጸባይ ነው፡ ምናለ አላህ ሂዳያ በሰጠው! የምንልለት ስንት ሰው አልለ፡፡ አላህ ደግሞ ከኛ በላይ ዐዋቂና፡ ለባሮቹም እናት ለልጇ ከምታዝነው የበለጠ የሚራራ ጌታ ስለሆነ ሂዳያ ለሚገባው እሱ ይሰጠዋል፡፡

አዎ! ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ወደ እውነት ጎዳና ይጣራሉ፣ ያስተምራሉ፣ ያመላክታሉ፣ ይመራሉ፡፡ ነገር ግን ማቅናት እና ማስተካከል ፈጽሞ አይችሉም፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-

” وَكَذَلِكَ أَوْحَيْنَا إِلَيْكَ رُوحًا مِنْ أَمْرِنَا مَا كُنْتَ تَدْرِي مَا الْكِتَابُ وَلَا الْإِيمَانُ وَلَكِنْ جَعَلْنَاهُ نُورًا نَهْدِي بِهِ مَنْ نَشَاءُ مِنْ عِبَادِنَا وَإِنَّكَ لَتَهْدِي إِلَى صِرَاطٍ مُسْتَقِيمٍ * صِرَاطِ اللَّهِ الَّذِي لَهُ مَا فِي السَّمَاوَاتِ وَمَا فِي الْأَرْضِ أَلَا إِلَى اللَّهِ تَصِيرُ الْأُمُورُ ” سورة الشورى 53-52
“እንደዚሁም ወደ አንተ ከትእዛዛችን ሲሆን መንፈስን፣ (ቁርአንን) አወረድን፤ መጽሐፉም እምነቱም ምን እንደሆነ የምታውቅ አልነበርክም። ግን (መንፈሱን) ከባሮቻችን የምንሻውን ሰው በርሱ የምንመራበት ብርሃን አደረግነው። አንተም ወደ ቀጥተኛው መንገድ በእርግጥ #ትመራለህ። ወደዚያ በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የርሱ ወደ ሆነው አላህ መንገድ፣ (ትመራለህ)፤ ንቁ ነገሮቹ ሁሉ ወደ አላህ ይመለሳሉ።” (ሱረቱ-ሹራ 42፡52-53)፡፡

ከዚህ በመነሳት ‹‹አላህ የፈለገውን ያጠማል፣ የፈለገውን ደግሞ ይመራል›› የሚለውን በጤናማ መልኩ መረዳት ይቻላል ማለት ነው፡፡ እሱም፡- ማን እውነትን ፈላጊ እንደሆነ፡ ማን ደግሞ ስሜቱን ተከታይ እንደሆነ አላህ የልብን ዐዋቂ ጌታ በመሆኑ፡ ለሁሉም ተገቢውን በመለገስ፡ ምሪት ለሚገባው ምሪትን፣ ጥመት ለሚገባው ደግሞ ጥመትን ይወስንበታል ማለት ነው፡፡

ተጨባጭ ማስረጃዎችን እንኳ እንመልከት ከተባለ፡ ብዙ ማየት እንችላለን፡፡ ገና በሕይወት ዘመናቸው እያሉ ሳይሞቱ፡ የጀሀነም ወይም የጀነት መሆናቸው የተነገራቸው ብዙ ነበሩ፡፡ ይህ የሚያሳየው አላህ የነዚህ ሰዎች ልብ ምን እንደሚመስል እስከ ዕለተ-ሞታቸው ያለውን ሂደት ጠንቅቆ የሚያውቅ ጌታ መሆኑን ነው፡፡ ለምሣሌ ሁለቱን እንመልከት፡-

ሀ/ አቡ ለሐብና እና ሚስቱ፡-

” تَبَّتْ يَدَا أَبِي لَهَبٍ وَتَبَّ * مَا أَغْنَى عَنْهُ مَالُهُ وَمَا كَسَبَ * سَيَصْلَى نَارًا ذَاتَ لَهَبٍ * وَامْرَأَتُهُ حَمَّالَةَ الْحَطَبِ * فِي جِيدِهَا حَبْلٌ مِنْ مَسَدٍ ” سورة المسد 5-1
“የአቡ ለሀብ ሁለት እጆች ከሰሩ (ጠፉ፤እርሱ) ከሰረም። ከርሱ ገንዘቡና ያም ያፈራው ሁሉ ምንም አልጠቀመውም። የመንቀልቀል ባለቤት የኾነችን እሳት በእርግጥ ይገባል። ሚስቱም (ትገባለች)፤ እንጨት ተሸካሚ ስትኾን፤ በአንገትዋ ላይ ከጭረት የኾነ ገመድ ያለባት ስትኾን።” (ሱረቱል መሰድ 110፡1-5)፡፡

ይህ የቁርኣን ሱራ በወረደበት ጊዜ አቡ ለሐብና ሚስቱ በሕይወት ነበሩ፡፡ ሁለቱም የዚህን ሱራ መልእክት ሰምተዋል፡፡ ነገር ግን አንድም ቀን ቢሆን ለይስሙላ እንኳ እኛ ከነበርንበት የሺርክ ተግባርተውበት አድርገን ወደ ኢስላም ተመልሰናል ለማለት አልቻሉም፡፡ ካፊር ሆኖው ኖሩ፡ ካፊር ሆነው ሞቱ፡፡

የሳቸው ዳዕዋ ሰው ዘንድ ተሰሚነት እንዳያገኝ ደፋ ቀና ሲል የነበረው አቡ ለሐብ፡ እንዴት ይህቺን አጋጣሚ አልተጠቀመባትም? እንዲህ በማለት ፡- ‹‹እናንተ ሰዎች ሆይ! እኔ ከዛሬ ጀምሮ ሙስሊም መሆኔን አውጄአለሁ!! እሳቸው ግን ካፊር ሆነህ ትሞታለህ፡ የመንቀልቀል ባለቤት የሆነችን እሳት ከነ ባለቤትህ ትገባለህ የሚል ወሕይ ወረደልኝ እያሉ ነው፣ እኔ ግን ይኸው ሰልሜአለሁ፣ ታዲያ ማነው ትክክል?›› ብሎ የሳቸውን ነቢይነት ጥርጣሬ ውስጥ መክተት አይችልም ነበር? ስንት ሳያምኑ አምነናል የሚሉ ሙናፊቆች በዘመኑ አልነበሩምን? እንዴት ይህ ሀሳብ ከሱ አእምሮ ተሸሸገ? እኮ እንዴት?

ግን ሁሉን ዐዋቂ የሆነው አላህ፡ በአቡ ለሐብና በባለቤቱ አእምሮ ይህ ሀሳብ ፈጽሞ እንደማይመጣ ከጥንቱኑ ቀድሞ የሚያውቅ አምላክ ነውና፡ ገና በህይወት እያለ ‹ካፊር› ሆኖ እንደሚሞት፣ ለጀሀነም እሳት ቅጣትም እንደሚዳረግ ተነገረው ማለት ነው፡፡ ይህ ነው ሁሉን ዐዋቂነት!!
ለዚህም ነው አላህ ‹‹የሚሻውን›› በማለት ማቅናትና ማስተካከልን ወደራሱ ያደረገው!!፡፡ አለበዚያ ‹‹የሚሻውን›› የሚለውን ቃል በዘፈቀደ ለማለት ነው ብሎ መተርጎም ስህተት ላይ ይጥላል፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡

ለ/ አቡ ጀህል፡-

” أَرَأَيْتَ الَّذِي يَنْهَى * عَبْدًا إِذَا صَلَّى * أَرَأَيْتَ إِنْ كَانَ عَلَى الْهُدَى * أَوْ أَمَرَ بِالتَّقْوَى * أَرَأَيْتَ إِنْ كَذَّبَ وَتَوَلَّى * أَلَمْ يَعْلَمْ بِأَنَّ اللَّهَ يَرَى * كَلَّا لَئِنْ لَمْ يَنْتَهِ لَنَسْفَعًا بِالنَّاصِيَةِ * نَاصِيَةٍ كَاذِبَةٍ خَاطِئَةٍ * فَلْيَدْعُ نَادِيَهُ * سَنَدْعُ الزَّبَانِيَةَ * كَلَّا لَا تُطِعْهُ وَاسْجُدْ وَاقْتَرِبْ ” سورة العلق 19-9
“አየህን? ያንን የሚከለክለውን፣ ባሪያን በሰገደ ጊዜ፤ አየህን ንገረኝ (ተከልካዩ) በትክክለኛ መንገድ ላይ ቢሆን፣ ወይም (ፈጣሪውን) በመፍራት ቢያዝ፤ አየህን? ንገረኝ (ከልካዩ) ቢያስተባብልና (ከእምነት) ቢሸሽ፤ አላህ የሚያይ መሆኑን አያውቅምን? ይተው ባከለከል አናቱን ይዘን እንጎትተዋለን። ውሸታም ስሕተተኛ የሆነችውን አናቱን። ሸንጎውንም ይጥራ፤ (እኛም) ዘበኞቻችንን እንጠራለን። ይከልከል፤ አትታዘዘው፤ ስገድም፤ (ወደ አላህ) ተቃረብም።” (ሱረቱል ዐለቅ 96፡9-19)፡፡

እነዚህ አንቀጾች የወረዱት በአቡ ጀህል ሰበብ ነው፡፡ ሰበቡም፡- በኢማሙ ሙስሊም ሶሒሕ ዘገባ መሰረት፡ አቡ ጀህል፡- በላትና በዑዝዛህ ይሁንብኝ! እሳቸው በከዕባ ዘንድ ሲሰግዱ ካየኋቸው ጫንቃቸውን ረግጣቸዋለሁ፡ ወይንም ፊታቸውን ከአሸዋው ጋር አደባልቀዋለሁ! በማለት ለራሱ ቃል ገባ፡፡ አንድ ቀን በከዕባ ዘንድ ሲሰግዱ ያገኛቸውና ቃል የገባውን ሊፈጽም ወደሳቸው ይሄዳል፡፡ ልክ አጠገባቸው እንደተቃረበ፡፡ በእጁ እየተከላከለ ወደኋላ መመለስ ጀመረ፡፡ ሰዎችም ‹‹ምን ሆነሀል?›› ሲሉት፡- በእኔና በሳቸው መሀል የእሳት ጉድጓድ እንዲሁም የሚያስፈራ ክንፍ ይታየኛል! በማለት መለሰ፡፡ የአላህ መልክተኛም ከሶላታቸው በኋላ፡- ትንሽ ወደኔ ቀረብ ቢል ኖሮ፡ መላእክት ሰውነቱን በብልት በብልት በቆራረጡት ነበር! አሉ፡፡ (ሙስሊም 2797)፡፡

እንግዲህ ይህ ከሀዲ ሰው ገና በህይወት ዘመኑ እያለ ‹‹አናቱን ይዘን እንጎትተዋለን›› በማለት፡ አላህ መላእክቱን በማዘዝ የውሙል ቂያም ወደ እሳት እንደሚወረውሩት አስቀድሞ ተናገረ፡፡ የባሮቹን ልብ የሚያውቅ፡ እንደ ዕውቀቱና ፍትሐዊነቱ፡ ለሁሉም ተገቢ በሆነ መልኩ ለሚገባው ‹‹ምሪትን›› በመለገስ፡ ወይንም ለማይገባው ‹‹ጥመትን›› የሚወስን እሱ ብቻ ነው፡፡ ሙያ የሚያምረው በባለቤቱ ነውና፡፡

በዛው ተቃራኒ የጀነት መሆናቸው የተመሰከረላቸው የትየለሌ ናቸው፡፤ ሁሉም የሚያውቃቸው ‹‹ዐሸረቱል ሙበሸሪነ ቢል-ጀንና›› (የጀነት መሆናቸው የተነገራቸው አስሩ ሶሓባዎች) እንኳ ለዚህ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡ ሌሎችም አልሉ፡፡ እንደዛም ሆኖ እነዚህ ሰዎች እስከ ዕለተ-ሞታቸው ድረስ የጀነት መሆንን የሚቃረን ተግባር አልፈጸሙም!!

ወንድምና እህቶች! ይህ ‹‹አላህ የሻውን ይመራል፣ የሻውን ደግሞ ያጠማል›› ለሚለው ጥቅላዊ ሐሳብ የተሰጠ ሁለተኛው አይነት ምላሽ ነው፡፡ አላህ ከፈቀደ ደግሞ በቀጣዩ ሶስተኛውን አይነት ምላሽ እንመለከታለን ኢንሻአላህ፡፡
ወአኺሩ ዳዕዋና ዐኒል-ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡