ሀይማኖታዊ ውይይቶችን አስመልክቶ

1,874 Views

ብዙ ሰዎች ሀይማኖታዊ ውይይትን አስመልክቶ ያላቸው አመለካከት የተሳሳተ ነው። ማህበረሰባችን በሚያምንበት አጀንዳ ዙሪያ ፊትለፊት መወያየት ላይ የጠነከረ ባህል የለውም። ያልጣመንን ነገር ቀጥታ ማውገዝ እንጅ በሰለጠነ መልኩ የማናምንበትን ነገር እያስቀመጥን መሞገት አለመደብንም። በዚህ ምክንያት ውይይት ሲባል ጦርነት የተባለ እስኪመስለን እንጨነቃለን። ይህ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። ውይይት የሰለጠነ ማህበረሰብ መገለጫ እንጅ የሚያናጭ አውድማ አይደለም።

በታሪክ ከጥንት ፈላስፋዎች ጀምሮ የሚያምኑበትን ነገር ይዘው ህዝብ ፊት ተሟግተዋል። በጥንታዊ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ አባቶች ከተለያዩ የእምነት አባቶች ጋር በነገስታት ፊት ሳይቀር እንደተሟገቱ እናነባለን። ከአይሁድ እምነት አባቶች ጀምሮ እስከ ካቶሊኮች ከጥንት የእርቶዶክስ አባቶች ጋር ተወያይተዋል፣ተከራክረዋል።

በእስልምናውም ያለው እሳቤ ተመሳሳይ ነው። ከነብዩ መሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ ሊቃውንት ማስረጃዎችን እየነቀሱ ተሟግተዋል። በነብዩ ጊዜ የነበሩ የነጅራን ክርስቲያኖች መስጅድ ድረስ በመምጣት ከነብዩ ጋር ተወያይተዋል። በወቅቱ የነበሩ አይሁዶችም መሠል አጀንዳዎችን እየያዙ ከነብዩ ጋር ይመጡና ይከራከሩ ነበር። ከቀደምት ሰለፎች መካከል እንደ ኢብን ሀዝም፣ ሸይኹል ኢስላም ኢብን ተይሚያህ፣ ኢማም አል-ገዛሊ በዚህ ዘርፍ የተካኑ ነበሩ።

በቅርብ ጊዜያትም ይህ አካሄድ የተለመደ ነበር። የዘመናዊው አለም የንፅፅር አዋቂ የሚባሉት ከ200 አመት በፊት የነበሩት ራሀመቱላሂ አል ሂንዲ (የኢዝሀሩል ሀቅ ማራኪ ጥራዝ ደራሲ) ሌላው የቅርብ ጊዜ ፋና ወጊ ተሟጋች ናቸው። ባለንበት ዘመን አሻራቸውን ያሳረፉት ሸይኽ አህመድ ዲዳት፣ ዶ/ር ዛኪር ናይክ፣ ዶ/ር ሻቢር አሊ ወዘተ .. ሌላው የዘርፉ ተጠቃሽ ሰዎች ናቸው።

እናም ወገኖቼ ሀይማኖታዊ ውይይት የሚያስበረግግ ጉዳይ ሳይሆን የሚበረታታ የሰለጠነ ሰው መለያ ነውና ሊደገፍ የሚገባው ተግባር ነው። ከዚህ በዘለለ ምናልባት ውይይቱን ወደ ብሽሽቅ ሊያመሩ የሚችሉ ዘለፋና ስድቦችን አስመልክቶ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። በሰለጠነ መንገድ ተነጋግሮ መግባባት ካልተቻለ በመልካም ቃላት መለያየት ተገቢና እስልምናው የሚያስተምረን ተግባር ነው።

© (የሕያ ኢብኑ ኑህ)