የገና በዓል /Christmas/ እውነታ

619 Views

ዛሬ የምንመለከተው ከወቅቱ ሁኔታ ጋር ያገናዘበውን ገናን/Christmas/ አስመልክቶ ይሆናል፡፡ ይህን ነጥብ የምንመለከተው ከሁለት ጭብጦች አንጻር ነው፡-

፩- ክርስቲያን ወገኖቻችን በዓሉን በተመለከተ ትክክለኛውን ምንጭ በመጠኑም እንዲያውቁትና እንዲረዱት

፪- የተለያዩ ሙስሊም ወንድሞችም ይህንን በዓል በተመለከተ መጠነኛ መረጃ የሚፈልጉ ይኖራሉ የተወሰነ ሀሳብ ለመስጠት ነው።


በነጮቹ አቆጣጠር ዲሴምበር 25 የሮማ ጣኦታውያን “የጸሀይ አምላክ” ተብሎ የሚጠራው ‹‹ኩይሪኑስ›› የተወለደበት ቀን እንደሆነ በጣኦታውያኑ ዘንድ ይታመን ነበር፡፡ እነኝህ የሮማ ጣኦታውያን ደግሞ እየሱስ በነበረበት ጊዜ ጭምር አይሁዳውያንን ወረው በቅኝ ግዛት ሲያስዳድሩ ነበር፡፡ ወራሪ ሀይል ደግሞ ሀይማኖቱን ባህሉንና ወጉን በቅኝ ተገዢው ሀይል ላይ የማሳረፍ እድሉ በጣም ሰፊ ነው፡፡

በዚህ ብቻ አያበቃም ይህ ቀን የእየሱስ ልደት ነው ተብሎ እስከ 4ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ አይከበርም ነበር፡፡ ይህ ቀን የእየሱስ ልደት ነው ተብሎ መከበር የጀመረው ከእውቁ የኒቂያ ጉባኤ ማለትም 325 ዓ.ል በኋላ ነው፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ይህ በዓል ከሮማውያን ጣኦታውያን የወሰደው ቀኑን ብቻ አይደለም፡፡ ይልቅስ በበዓሉ ቀን የሚተገበሩ ጽድ እንደመቁረጥ ያሉ መጥፎ ልማዶችንም ጭምር ነው፡፡ እነኝህ ልማዶች በግልጽ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ሳይቀር የተተቹ ናቸው፡፡

“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአሕዛብን መንገድ አትማሩ ከሰማይ ምልክትም አትፍሩ፤ አሕዛብ ይፈሩታልና። የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፤ ዛፍ ከዱር ይቈረጣል፥ በሠራተኛም እጅ በመጥረቢያ ይሠራል። በብርና በወርቅ ያስጌጡታል፥ እንዳይናወጥም በችንካርና በመዶሻ ይቸነክሩታል። እንደ ተቀረጸ ዓምድ ናቸው እነርሱም አይናገሩም፤ መራመድም አይቻላቸውማን ይሸከሙአቸዋል። ክፉ መሥራትም አይቻላቸውምና፥ ደግምም መልካም ይሠሩ ዘንድ አይችሉምና አትፍሩአቸው።” ኤርምያስ 10፥2-5

ከዚህም በተጨማሪ የግለሰቦችን ልደት ክብረ በዓል አድርጎ መያዝም የጣኦታውያን ባህል ነው፡፡ በመጽሀፍ ቅዱስ ሳይቀር ልደታቸው እንደሚከበርቸው የተገለጹ ሰዎች ጣኦታውያን ናቸው፡፡

‹‹በሦስተኛውም ቀን ፈርዖን የተወለደበት ቀን ነበረ፥ ለሠራዊቱም ሁሉ ግብር አደረገ፤ የጠጅ አሳላፊዎቹን አለቃና የእንጀራ አበዛዎቹን አለቃ በአሽከሮቹ መካከል ከፍ አደረገ።›› ዘፍጥረት 40፡20
እንዲሁም
‹‹ነገር ግን ሄሮድስ የተወለደበት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ዘፈነች ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤›› ማቴወስ 14፡6

እነዚህ ሁለቱም ልደታቸውን ክብረ በዓል ያደርጉ እንደነበር መጽሀፍ ቅዱስ የገለጻቸው ሰዎች ጣኦታውያን ነበሩ፡፡ ዛሬ ሰዎቹ ባህሉን በመውረስ በራሳቸው አተረጓጎምና ለሚፈልጉት አካል መርጠው እያዋሉት ይገኛሉ፡፡ ጨውን ምንጊዜም እያሰማመርክ ብታስጊጠው ጨውነቱን አይለቅም፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የገና በዓል በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ምንም መሰረት የለውም፡፡ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥም በዓሉን አስመልክቶ የተጠቀሰ ምንም ነገር የለም፡፡ ሌላው ነገር እየሱስ በዲሴምበር 25 ለመወለዱ ምንም ዓይነት የታሪክ ማረጋገጫ ሰነድ የለንም፡፡

በዚህ ነጥብ ዙሪያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን ከዋናዎቹ /Mainstream Christianity/ ፕሮቴስታንትና የካቶሊክ ቤተክርስቲያናት ጋር የማይታረቅ ልዩነት አላት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ክርስቲያኑ ክስተቱን የሚያከብረው “አምላኩ የተወለደበትን ቀን” እንደሆነ በማሰብ ነው። አስቡት እስኪ አምላክ ልደቱ ሲከበር..?!

ክርስቲያኖች የገናን/christmas/በዓል ማክበር ይኖርባቸዋልን?

የገና በዓል በውጭው ዓለም በሰፊው የሚከበር አመታዊ ክብረ በዓል ሲሆን አብዛኛው ክርስቲያን ይህ ክብረ በዓል ሀይማኖታዊ መሰረት እንዳለውና በማክበሩም በረከት እንደሚያገኝ ያምናል፡፡ ነገር ግን ታሪካዊና ሀይማኖታዊ ዳራውን ነጻ ሆነን በጥልቀት ከፈተሸነው ይህ በዓል መከበር የሌለበት መጤ ልማድ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ከዚህ በታች ለክርስቲያን ወገኖቼ በዓሉ መከበር የሌለበት ስለመሆኑ ሶስት ምክንያቶችን በማስቀመጥ ለማሳየት እሞክራለሁ!!!

፩- የጥንት ክርስቲያኖች በዓሉን አላከበሩትም
ምናልባት ይህ ነጥብ ብዙዎችን ሊያስገርም ይችላል፡፡ ግን እውነት ነው የትኛውም የእየሱስ ደቀመዝሙር እንዲሁም ሀዋርያት በዓሉን አላከበሩትም፡፡ ጥንታዊ የቤተክርስቲያን አባቶች ኢራኒየስ እና ተርቱሊያን በወቅቱ በቤ/ክርስቲያን ውስጥ የነበሩ የደስታ ድግሶችን ሲጠቅሱ ይህን በዓል ግን አልጠቀሱም ነበር፡፡ ሌላው የቤ/ክርስቲያን አባት ኦሪገን ደግሞ ልደታቸውን ማክበር ያለባቸው ሀጥያተኞች ብቻ እንደሆኑ ሞግቷል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በእየሱስ የስብከት ጊዜያት ይህ ክስተት እንደነበር የሚጠቁም ምንም ዓይነት የወንጌል መረጃ የለም፡፡ በየትኛውም የፕሮቴስታንትም ሆነ የካቶሊክ ጥንታዊ የቤተክርስቲያን አስተምህሮቶች ውስጥ ይህ በዓል ከ3ኛው ክፍለ ዘመን በፊት ይተገበር እንደነበር የሚገልጽ ማስረጃ የለም፡፡

፪- ክርስቲያኖች በአንድ ወቅት ይህ በዓል እንዳይከበር እገዳ ጥለው ነበር፡፡
ይህንን በዓል አስመልክቶ ከመጽሀፍ ቅዱስ መሰረት የሌለውና ከካቶሊክ የተቀዳ የፈጠራ በዓል ነው በሚል በ1644 የእንግሊዝ ፕሮቴስታንቶች በዓሉ እንዳይከበር እገዳ ጥለው ነበር፡፡ ይህንን የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን አባቶች እገዳም መሰረት በማድረግ በወቅቱ የእንግሊዝ ፓርላማ በፈረንጆቹ ሰኔ 1647 እገዳውን በሀገር ደረጃ አጽድቆት ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የገና በዓል ማክበር በቦስተን ከ1659 እስከ 1681 ክልክል ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በእንግሊዚ እስከ 1856 ድረስ ህጋዊ ክብረበዓል አልነበረም፡፡

3. ከላይ እንደተመለከትነው የገና በዓል ምንጩ የሮማ ጣኦታውያን ሰርጎ ገብ አመለካከት ነው፡፡

ታዲያ እነኝህ ሁሉ መሰረታዊ ነጥቦች ባልተሟሉበት ሁኔታ ነው እንግዲህ በዓሉ እንዲሁ በደመነፍስ የሚከበረው፡፡ አልፎ አልፎ እንደሚስተዋለውም ሙስሊሙ ማህበረሰብ ይህን ከጣኦታውያን የተወረሰ የተሳሳተ ባህል አብሮ በማሰተጋባት በየዋህነት ስህተት ውስጥ መውደቅ የለበትም፡፡

وَكَذَٰلِكَ زَيَّنَ لِكَثِيرٍ مِّنَ الْمُشْرِكِينَ قَتْلَ أَوْلَادِهِمْ شُرَكَاؤُهُمْ لِيُرْدُوهُمْ وَلِيَلْبِسُوا عَلَيْهِمْ دِينَهُمْ ۖ وَلَوْ شَاءَ اللَّهُ مَا فَعَلُوهُ ۖ فَذَرْهُمْ وَمَا يَفْتَرُونَ [٦:١٣٧]

‹‹እንደዚሁም ከአጋሪዎቹ ለብዙዎቹ፤ ተጋሪዎቻቸው ሊያጠፉዋቸው ሃይማኖ ታቸውንም በእነሱ ላይ ሊያቀላቅሉባቸው (ሊያመሳስሉባቸው) ልጆቻቸውን መግደልን አሳመሩላቸው፡፡ አላህም በሻ ኖሮ ባልሠሩት ነበር፡፡ ከቅጥፈታቸውም ጋር ተዋቸው፡፡›› 6፡137

وَدَّت طَّائِفَةٌ مِّنْ أَهْلِ الْكِتَابِ لَوْ يُضِلُّونَكُمْ وَمَا يُضِلُّونَ إِلَّا أَنفُسَهُمْ وَمَا يَشْعُرُونَ [٣:٦٩]

‹‹ከመጽሐፉ ባለቤቶች የኾኑ ጭፍሮች ነፍሶቻቸውን እንጂ የማያሳስቱ ሲኾኑ ሊያሳስቱዋችሁ ተመኙ ግን አያውቁም፡፡›› አል-ኢምራን 69

ወሏሁ አእለም!!!!

___________

ተጨማሪ ለማንበብ፦

– Martindale, Cyril Charles. “Christmas”. The catholic Encyclopedia vol 3: Robert Appleton company,1998
– Melina remy. “The Surprising truth: Christians once banned Christmas.” Live science. Tech media Network

© የሕያ ኢብኑ ኑህ

Shortlink