ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እና ራስን የማጥፋት ትርክቶች

በተለያዩ የእምነት ክፍል ውስጥ የሚገኙ እስልምናን የሚተቹ አካላት ይህንን አርዕስት በሰፊው ሲያራግቡት እናስተውላለን። ለጥያቄያቸው መሠረት የሆኑት በሰሒሕ አል ቡኻሪ ጥራዝ ውስጥ የሚገኙት የሀዲስ ዘገባዎች ሲሆኑ እነዚህን ዘገባዎች በማቅረብ ነብዩ (ሰዐወ) ራሳቸውን ሊያጠፉ ሙከራ ያደርጉ እንደነበር አድርገው ድምዳሜ ሊያስቀምጡ ይሞክራሉ።

ሀዲሱን ከታች አስቀምጠን ሀሳቡን በዝርዝር እንፈትሸዋለን።

⬛️ ሀዲሱ

በቡኻሪ ውስጥ የሚገኘው ሀዲስ በጣም ረጅም ሲሆን ለጥያቄው መሠረት የሆነውና ከውስጡ የሚገኘው ክፍል ይህንን ይመስላል፦

ثُمَّ لَمْ يَنْشَبْ وَرَقَةُ أَنْ تُوُفِّيَ وَفَتَرَ الْوَحْيُ فَتْرَةً حَتَّى حَزِنَ النَّبِيُّ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ فِيمَا بَلَغَنَا حُزْنًا غَدَا مِنْهُ مِرَارًا كَيْ يَتَرَدَّى مِنْ رُءُوسِ شَوَاهِقِ الْجِبَالِ فَكُلَّمَا أَوْفَى بِذِرْوَةِ جَبَلٍ لِكَيْ يُلْقِيَ مِنْهُ نَفْسَهُ تَبَدَّى لَهُ جِبْرِيلُ فَقَالَ يَا مُحَمَّدُ إِنَّكَ رَسُولُ اللَّهِ حَقًّا فَيَسْكُنُ لِذَلِكَ جَأْشُهُ وَتَقِرُّ نَفْسُهُ فَيَرْجِعُ

‘…ወረቃህ ከሞተ ከጥቂት ቀናት በኃላ መለኮታዊ ራዕዩ ለሆነ ጊዜ ያህል ተቋርጦ ነበር። በዚህም ምክንያት ነብዩ እጅግ አዝነው ነበር፤ እንደሰማነውም ብዙ ጊዜ ራሳቸውን ከትልቅ ተራራ ላይ ለመጣል ያስቡ ነበር… “

then after a few days Waraqa died and the Divine Inspiration was also paused for a while and the Prophet became so sad as we have heard that he intended several times to throw himself from the tops of high mountains and every time he went up the top of a mountain in order to throw himself down, Gabriel would appear before him and say, “O Muhammad! You are indeed Allah’s Messenger in truth” whereupon his heart would become quiet and he would calm down and would return home …“ (Sahih Bukhari, Kitabul Ta’beer, Hadith 6467)

⬛️ ራስን ማጥፋት/Suicide/ በሚለው ቃል ዙሪያ

ከላይ የጠቀስነው ሀዲስ ውስጥ የሚገኘው ጥቂቱ ክፍል ሰሒሕ/አስተማማኝ/ ሲሆን ሀዲሱ ያልተቆረጠ አስተላላፊ/ዘጋቢ/ እና ተዓማኒ አስተላላፊዎችን የያዘ ነው። ነገር ግን ስለ ራስ ማጥፋት የምታወራዋ ክፍል ግን በዘገባው ውስጥ ያልተላለፈች ነገር ግን በሀዲሱ አስተላላፊዎች በአንደኛው (ዙኽሪ) የተጨመረች ቃል ናት።

በግልፅ እንደምንመለከተው ቃላቶቹ እንዲህ ይላሉ፦

فِيمَا بَلَغَنَا
“ፊማ በለገና”
“እንደ ሰማነው”

ይህ የሚጠቁመን ስለ “ራስ ማጥፋት” አስከትለው የመጡት ቃላት ከዋናው ዘገባ የተያያዙ ሳይሆን እንዲሁ የተነገሩ “ስሚ ስሚ” ወይንም አሉባልታ ነበር።

ሀፊዝ ኢብን ሐጀር (ረሒሙሁላህ) እንዲህ ፅፈዋል፦

إِنَّ الْقَائِل فِيمَا بَلَغَنَا هُوَ الزُّهْرِيّ ، وَمَعْنَى الْكَلَام أَنَّ فِي جُمْلَة مَا وَصَلَ إِلَيْنَا مِنْ خَبَر رَسُول اللَّه صَلَّى اللَّه عَلَيْهِ وَسَلَّمَ فِي هَذِهِ الْقِصَّة وَهُوَ مِنْ بَلَاغَات الزُّهْرِيّ وَلَيْسَ مَوْصُولًا

“(በሐዲሱ ውስጥ) “እንደሰማነው” (ፊማ በለገና) ብሎ የገለፀው አል-ዙኽሪ ነው። ይህም ማለት ስለረሱል (ሰዐወ) ከሚያወራው ጥቅል ታሪክ ውስጥ ይህች የዙህሪ ንግግር ብቻ እንጅ ከዘገባው ጋር የተያያዘ አይደለም ማለት ነው” (1)

⬛️ ቃላቱ ጥርጣሬን ያዘሉ ነበሩ

ዘገባው ከሙሉ ሀዲሱ ጋር የተያያዘ ካለመሆኑ በተጨማሪ አዙህሪ የተናገራት ክፍል ተዓማኒ እንዳልሆነችም በሀዲስ መስክ ሊቃውንቱ (ሙሀዲሲን) ተጠቅሷል።

የእስልናውን አለምን የሀዲስ ጥናት መስክና የአረብኛ ሰዋሰውን ጠንቅቆ ለማያውቅ ሙስሊም ያልሆነ አካል ከላይ ያሉት ማብራሪያዎች እንዲሁ ለመልስ ብቻ ተብለው የቀረቡ መስለውት ላያሳምነው ይችላል። ሙስሊም ካልሆኑ ኦሬንታሊስቶች ልጥቀስ፦

አልፈርድ ጉልዌም ታዋቂ እንግሊዛዊ የአረብኛ ሰዋሰው ሊቅ ነው። እንዲህ ይላል፦

“”ዛማ” ወይንም “ዛሙ” የሚለውን ቃል አስከትለው የመጡ ንግግሮች የሚጠቁሙን ነገር ንግግሩ ትክክል ላይሆን እንደሚችል ነው…. በተመሳሳይ መልኩ “ፊማ ዙኪረኒ” አልያም “ፊማ በለገኒ” ብሎ ከመጣም ተመሳሳይ ጥቆማ ይሰጠናል” (2)

ከላይ ባለው ገለፃ እንደምንረዳው አንድ ክርስቲያን የሆነ ግለሰብ ሳይቀር “ፊማ በለገና” የሚለው ቃል አጠራጣሪ ነገሮችን ለመጥቀስ አገልግሎት ላይ እንደሚውል ይነግረናል።

ከዚህም በተጨማሪ ሀሳቡ በሌሎች ተመሳሳይ ሀዲሶች ሳይቀር ይደገፋል። ከነዚህም ውስጥ

– ቡኻሪ 3
– ሙስሊም 231
– ሙስተድረክ አል ሐኪም 4830
– በይሀቂ ደላኢሉ ኑቡዋ 445
– ሙስነድ አህመድ 24681
እንዲሁም ኢብን ሀጀር እንደሚናገሩት በአቡ ነዒም፣ ኢስማኤልና ኢብን መርዳዊያህ ስራዎች ውስጥ አንዳቸውም ስለራስ ማጥፋት የሚያወራውን ዘገባ አላካተቱም።

በአጭሩ እውነታው፦ ይህ ታሪክ የደረሰን ረሱልን በአካል አይቶ ከማያውቅና ሌሎች ሰነዶች ያልጠቀሱት ብቸኛ ከሆነ ግለሰብ ነው። በዚህም የተነሳ ራስን ማጥፋትን አስመልክቶ አንድም አስተማማኝ የሆነ የሀዲስ ዘገባ አይገኝም። በዚህ ዙሪያ ያሉ የሚሽነሪ ክሶችም እንዲሁ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚፈረካከሱ ናቸው፤ ምስጋና ለአለማቱ ጌታ ለአላህ ይገባው።

⬛️ ማጠቃለያ

1- በሰሒሕ ቡኻሪ ውስጥ የሚገኘው ሀዲስ ልክ እንደሌሎች ሀዲሶች አስተማማኝ/ሰሒሕ/ ሲሆን በመጨረሻዋ ክፍል ስለራስን ማጥፋት የምታወራዋ ክፍል ግን በሌሎች አስተማማኝ ጥራዝ ውስጥ የማይገኝና አስተላላፊው በጥርጣሬ የተናገራት ቃል ናት።

2- ሙስሊም ምሁራን ብቻ ሳይሆን ምዕራባውያን ኦሬንታሊስቶችም ሳይቀር “ፊማ በለገና” የሚለው ቃል አጠራጣሪ ቃላትን ለማስተላለፍ የሚጠቀሙበት ቃል እንደሆነ የገለፁት ነው።

3- ተመሳሳይ አገላለፆች በተለያዩ ዘገባዎች ውስጥ የተጠቀሱ ሲሆን ከላይ ለቀረበው ማስረጃ አቃፊ ድጋፍ ያላቸው ናቸው።

⬛️ መደምደሚያ

ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ራሳቸውን ለማጥፋት ሙከራ አድርገዋል የሚለው ቃል መሠረቱ ተአማኒ ምንጭ አይደለም። አባባሉም በግለሰቦች የተነገረ አጠራጣሪ ቃል እነጅ ከሀዲሱ ጋር የተያያዘ አስተማማኝ ንግግር አይደለም።

ወሏሁ አዕለም..!

⬛️ ማጣቀሻ/Reference/

(1) (ፈትሑል ባሪ 19/449 ኪታቡ ተዕቢር)

(2) (The Life of Muhammad: A translation of Ishaq’s Sirat Rasul Allah with introduction and notes by A. Guilluame Oxford University Press, Karachi, Seventeenth impression, 2004, p. xix)
______________

(የሕያ ኢብኑ ኑህ)

ሼር ያድርጉ