✔ልፋት ለምኔ? ክፍል አሥራ አራት በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
355 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56)፡ ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181)፡ የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
የሂዳያና የጥመት ምክንያቶች፡-
ባለፉት ተከታታይ ጽሑፎች ‹‹መምራት›› እና ‹‹ማጥመም›› በጌታ አላህ መለኮታዊ ውሳኔ ብቻ ሊፈጸሙ የሚችሉ መሆናቸውን አይተናል፡፡ ማንም ቢሆን የሰውን ልብ የመቀየርና፡ የፈለገውን የማጥመም የፈለገውን ደግሞ የማቅናት ስልጣን እንዳልተሰጠው ተመልክተናል፡፡ ባይሆን ነቢያትና ተከታዮቻቸው (የኢስላም ሰባኪያን) ሰበብ በመሆን የብርሐንን መንገድ ከጨለማው አበጥረው ማሳየት እንደሚችሉና፡ ግን እነዛኑ ሰዎች ማቅናትና ማስተካከል ግን ስልጣኑ እንዳልተሰጣቸው ተምረናል፡፡ የሰዎችን ልብ በመመርመር የሚገባቸውን መስጠት የአላህ ሥራ ብቻ ነውና፡፡
ዛሬ ደግሞ በአላህ ፈቃድ የምንመለከተው፡- ሰዎችን ለአላህ ምሪት የሚዳርጋቸው ምን ምን ነገራት እንደሆኑና በተቃራኒው ለጥመት አሳልፎ የሚሰጣቸው ነገራት ምን እንደሆኑ በመጠኑ በመዘርዘር ይሆናል ኢንሻአላህ፡፡ አላህ በራሕመቱ ወደ ቅን ጎዳና ከመራቸው መልካም ባሮቹ ያድርገን፡፡

1. የሂዳያህ (ምሪት) ሰበቦች፡-
ሀ/ ተውበት ማድረግ፡-
ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን (አል-ፋጢር 35፡45)፡፡ ከአባታችን የወረስነው ኃጢአት ባይኖርብንም፡ በግብር የምንፈጽመው ኃጢአት ግን የትየለሌ ነው፡፡ የአንዱ ስህተት ከሌላው በአይነቱም ሆነ በመጠኑ ቢለያይም ሁሉም ሰው ተሳሳች ነው፡፡ ከነዚህ ሰዎች በላጩ ደግሞ፡ ኃጢአተኛ መሆኑን አምኖ በተውበት ወደ አላህ የሚመለስ ነው፡፡ አላህ ተውበት አድራጊዎችን ቅኑን ጎዳና እንደሚመራቸው ተናግሯልና፡፡ ቃሉ እንዲህ ይነበባል፡-
” وَيَقُولُ الَّذِينَ كَفَرُوا لَوْلَا أُنْزِلَ عَلَيْهِ آيَةٌ مِنْ رَبِّهِ قُلْ إِنَّ اللَّهَ يُضِلُّ مَنْ يَشَاءُ وَيَهْدِي إِلَيْهِ مَنْ أَنَابَ ” سورة الرعد:27
“እነዚያም የካዱት፥ በርሱ ላይ ከጌታው ታምር ለምን አልተወረደም ይላሉ፤ አላህ የሚሻውን ያጠማል፤ *የተመለሰውንም ሰው ወደርሱ ይመራል*፥ በላቸው።” (ሱረቱ-ረዕድ 13፡27)፡፡
” شَرَعَ لَكُمْ مِنَ الدِّينِ مَا وَصَّى بِهِ نُوحًا وَالَّذِي أَوْحَيْنَا إِلَيْكَ وَمَا وَصَّيْنَا بِهِ إِبْرَاهِيمَ وَمُوسَى وَعِيسَى أَنْ أَقِيمُوا الدِّينَ وَلَا تَتَفَرَّقُوا فِيهِ كَبُرَ عَلَى الْمُشْرِكِينَ مَا تَدْعُوهُمْ إِلَيْهِ اللَّهُ يَجْتَبِي إِلَيْهِ مَنْ يَشَاءُ وَيَهْدِي إِلَيْهِ مَنْ يُنِيبُ ” سورة الشورى 13
“ለናንተ ከሃይማኖት ያንን በርሱ ኑሕን ያዘዘበትን ደነገገላችሁ፤ ያንንም በርሱ ኢብራሂምን፣ ሙሳንና ዒሳንም ያዘዘበትን፣ ሃይማኖትን በትክክል አቋቋሙ፣ በርሱም አትለያዩ ማለትን (ደነገግን) በአጋሪዎቹ ላይ ያ ወደርሱ የምትጠራቸው ነገር ከበዳቸው፤ አላህ የሚሻውን ሰው ወደርሱ (እምነት) ይመርጣል፤*የሚመለስንም ሰው ወደርሱ ይመራል*።” (ሱረቱ-ሹራ 42፡13)፡፡
” وَالَّذِينَ اجْتَنَبُوا الطَّاغُوتَ أَنْ يَعْبُدُوهَا وَأَنَابُوا إِلَى اللَّهِ لَهُمُ الْبُشْرَى فَبَشِّرْ عِبَادِ * الَّذِينَ يَسْتَمِعُونَ الْقَوْلَ فَيَتَّبِعُونَ أَحْسَنَهُ أُولَئِكَ الَّذِينَ هَدَاهُمُ اللَّهُ وَأُولَئِكَ هُمْ أُولُو الْأَلْبَابِ ” سورة الزمر 18-17
“እነዚያም ጣዖታትን የሚግገዟት ከመሆን የራቁ *ወደ አላህም የዞሩ* ለነርሱ ብስራት አላቸው፤ ስለዚህ ባሮቼን አብስር። እነዚያን ንግግርን የሚያዳምጡትንና መልካሙን የሚከተሉትን፣ (አብስር)፤ እነዚያ፣ *እነርሱ አላህ የመራቸው ናቸው*። እነዚያም እነሱ ባለ አእምሮዎች ናቸው።” (ሱረቱ-ዙመር 39፡17-18)፡፡

ለ/ ተውሒድ ላይ የጸኑ፡-
በትክክለኛው የላ ኢላሀ ኢልለሏህ መስመር ላይ የሚጓዝ የአላህ ባሪያ፡ እምነቱን በሺርክ ካልቀላቀለ፡ አላህ እስከ መጨረሻው ዕለት ድረስ ይመራዋል፡፡ ቃሉም እንዲህ ይላል፡-
” الَّذِينَ آمَنُوا وَلَمْ يَلْبِسُوا إِيمَانَهُمْ بِظُلْمٍ أُولَئِكَ لَهُمُ الْأَمْنُ وَهُمْ مُهْتَدُونَ ” سورة الأنعام 82
“እነዚያ ያመኑና እምነታቸውን በበደል ያልቀላቀሉ እነዚያ ለእነርሱ ጸጥታ አላቸው፡፡ *እነሱም የተመሩ ናቸው*፤” (ሱረቱል አንዓም 6፡82)፡፡

ሐ/ በአላህ መንገድ መታገል፡-
የኢስላምን ዳር-ድምበር ለማስከበር፡ አላህን ዲን የበላይ ለማድረግ፡ በአላህ መንገድ የሚታገሉ ‹ሙጃሂዶች› አላህ ቅኑን ጎዳና ይመራቸዋል፡-
” وَالَّذِينَ جَاهَدُوا فِينَا لَنَهْدِيَنَّهُمْ سُبُلَنَا وَإِنَّ اللَّهَ لَمَعَ الْمُحْسِنِينَ ” سورة العنكبوت 29:69
“እነዚያም በኛ መንገድ የታገሉ መንገዳችንን በእርግጥ እንመራቸዋለን፤ አላህም በእርግጥ ክበጎ ሠሪዎች ጋር ነው።” (ሱረቱል ዐንከቡት 29፡69)፡፡

መ/ አላህን መፍራትና መጠንቀቅ፡-
ከህዋስ በራቁ ነገራት በማመን (መላእክት፣ ጀነት ጀሀነም…) በሶላቱም ላይ በመጽናት፡ ጌታውን የሚፈራና የሚጠነቀቅ የአላህ ባሪያ አላህ ይመራዋል፡-
” ذَلِكَ الْكِتَابُ لَا رَيْبَ فِيهِ هُدًى لِلْمُتَّقِينَ * الَّذِينَ يُؤْمِنُونَ بِالْغَيْبِ وَيُقِيمُونَ الصَّلَاةَ وَمِمَّا رَزَقْنَاهُمْ يُنْفِقُونَ * وَالَّذِينَ يُؤْمِنُونَ بِمَا أُنْزِلَ إِلَيْكَ وَمَا أُنْزِلَ مِنْ قَبْلِكَ وَبِالْآخِرَةِ هُمْ يُوقِنُونَ * أُولَئِكَ عَلَى هُدًى مِنْ رَبِّهِمْ وَأُولَئِكَ هُمُ الْمُفْلِحُونَ ” سورة البقرة 5-2
“ይህ መጽሐፍ (ከአላህ ለመኾኑ) ጥርጥር የለበትም፤ ለፈራህያን መሪ ነው፡፡ ለነዚያ በሩቁ ነገር የሚያምኑ ሶላትንም ደንቡን ጠብቀው የሚሰግዱ ከሰጠናቸውም ሲሳይ የሚቸሩ ለኾኑት፤ ለእነዚያም ወደ አንተ በተወረደውና ከአንተ በፊትም በተወረደው የሚያምኑ በመጨረሻይቱም (ዓለም) እነርሱ የሚያረጋግጡ ለኾኑት (መሪ ነው)፡፡ እነዚያ ከጌታቸው በመመራት ላይ ናቸው፤ እነዚያም እነሱ ፍላጎታቸውን ያገኙ ናቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡2-5)፡፡

ሠ/ ዱዓእ ማድረግ፡-
አላህ በራሕመቱ ቅኑን ጎዳና ይመራንና በዛውም ላይ ያጸናን ዘንድ፡ ከልብ የሆነ ዱዓእ ወሳኝ ነው፡፡ ዱዓእ ቀደርን እንኳ የመመለስ ኃይል አለውና!፡፡ ስለዚህ አላህ በሂዳያው ጎዳና ላይ ያጸናን ዘንድ ዱዓእ ላይ መበርታት ይጠበቅብናል፡-
” وَقَالَ رَبُّكُمُ ادْعُونِي أَسْتَجِبْ لَكُمْ إِنَّ الَّذِينَ يَسْتَكْبِرُونَ عَنْ عِبَادَتِي سَيَدْخُلُونَ جَهَنَّمَ دَاخِرِينَ ” سورة
غافر 60
“ጌታችሁም አለ፦ ለምኑኑኝ እቀበላችኋለሁና፤ እነዚያም እኔን ከመገዛት የሚኮሩት ተዋራጆች ሆነው ገሀነምን በእርግጥ ይገባሉ።” (ሱረቱ ጋፊር 40፡60)፡፡

2. ‹‹ደላል›› (ጥመት)ና ምክንያቶቹ፡-

ሰዎች በተፈጥሮ የተመሩ ናቸው፡፡ ማለትም አላህ በሰጣቸው አእምሮ ተጠቅመው የሚጠቅማቸውን ከሚጎዳቸው መለየት ይችላሉ (ሱረቱል አዕላ 1-3፣ ጣሀ 49፡50)፡፡ በነቢያትና በተከታዮቻቸው አማካይነት ደግሞ የሐቅን መንገድ ከጥሜት ጎዳናዎች ለይተው ያውቃሉ (ሱረቱ-ረዕድ 13፡7፣ አል-አዕራፍ 7፡181)፡፡ ታዲያ ሰዎችን ከዚህ የእውነት መንገድ ከሆነው ከአላህ ዲን ሊያወጣቸውና ወደ ጥሜት ሊከታቸው የሚችለው ነገር ምንድነው ቢባል ቀጥሎ ያለውን ለናሙና እንመለከታለን፡-

ሀ. የአላህን ትእዛዝ አለመፈጸም፡-
ጌታ አላህ ለባሪያዎቹ ከአቅም በላይ የሆነ ሊፈጽሙት የማችሉትን ነገር አላዘዛቸውም (አል-በቀራህ 2፡286)፡፡ ይህን አድርግ! እና ያንን አታድርግ! የሚሉት መለኮታዊ ህግጋቶች በጠቅላላ በሰው አቅም ልክ የተደነገጉ ናቸው፡፡ እሱ ከባሪያዎቹ የሚፈልገው የአቅማቸውን ያህል እንዲጠነቀቁትና እንዲፈሩት ነው (አት-ተጋቡን 64፡16)፡፡ ታዲያ ሰዎች ይህን የአምላካቸውን ትእዛዝ ሲጥሱና አላከብርም ሲሉ ብሎም ያለ ተውበት ከዘወተሩበት የስራቸው ዋጋ ይሆን ዘንድ ለጥሜት ሊዳረጉ ይችላሉ፡-
“وَمَا كَانَ اللَّهُ لِيُضِلَّ قَوْمًا بَعْدَ إِذْ هَدَاهُمْ حَتَّى يُبَيِّنَ لَهُمْ مَا يَتَّقُونَ إِنَّ اللَّهَ بِكُلِّ شَيْءٍ عَلِيمٌ ” سورة التوبة 115
“አላህም ሕዝቦችን ከአቀናቸው በኋላ፣ የሚጠነቀቁትን (ሥራ) ለርሱ እስከሚገልጽላቸዉ፣ (እስከሚተዉትም) ድረስ ጥፋተኛ የሚያደርግ አይደለም፤ አላህ በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነውና።” (ሱረቱ-ተውባህ 9፡115)፡፡

ለ. ኩራትና የበላይነት፡-
‹‹ኩራት›› ማለት፡- ጥሩ ለብሶ መታየትና መዋብ ሳይሆን፡ ሐቅን በሐቅነቱ አለመቀበልና ሰዎችን በንቀት አይን መመልከት ነው፡፡ የተነገረውን ሐቅ ለስሜቱ ወይም ለነገረው ሰው ጥላቻ ካልሆነም ለቡድናዊ አመለካከቱ ብሎ የሚመልስ ሰው እራሱን ለጥሜት ይዳርጋል፡-
“الَّذِينَ يُجَادِلُونَ فِي آيَاتِ اللَّهِ بِغَيْرِ سُلْطَانٍ أَتَاهُمْ كَبُرَ مَقْتًا عِنْدَ اللَّهِ وَعِنْدَ الَّذِينَ آمَنُوا كَذَلِكَ يَطْبَعُ اللَّهُ عَلَى كُلِّ قَلْبِ مُتَكَبِّرٍ جَبَّارٍ ” سورة غافر 35
“እነዚያ፤ የመጣላቸው አስረጅ ሳይኖር፣ በአላህ ታምራቶች የሚከራከሩ (ክርክራቸው) አላህ ዘንድና እነዚያም አመኑት ዘንድ መጠላቱ፣ በጣም ተለቀ፤ እንደዚሁ አላህ በኩሩ ጨካኝ (ሰው) ልብ ሁሉ ላይ ያትማል።” (ሱረቱ-ጋፊር 40፡35)፡፡

ሐ. መጥፎ ጓደኛ፡-
በምድራዊ ሕይወታችን የምንወዳጃቸው ሰዎች በእምነታችን ጉዳይ ላይ አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ተጽእኖ ይኖራቸዋል፡፡ አላህን ፈሪ የሆነ፣ መጥፎ ስትሰራ የሚገስጽህና ያላወከውን የሚያስተምርህ ሰው በሂዳያ መስመር እንድትጸና ሲያግዝህ፣ አላህ የማይፈራ፣ ሶላቱን የማይሰግድና ወደ ጥሩ ቦታ የማይጋብዝህ ሰው በጊዜ ካልራቅከው ወይም አንተ አሸንፈህ ካልመለስከው በሂደት ተሸንፈህ እጅ በመስጠት ጥመት ውስጥ ልትገባ ትችላለህ፡፡ ይህ በመሆኑም ማነው ባለንጀራዬ? የሚለውን ጥያቄ ለራስህ አንሳ፡-
“وَيَوْمَ يَعَضُّ الظَّالِمُ عَلَى يَدَيْهِ يَقُولُ يَا لَيْتَنِي اتَّخَذْتُ مَعَ الرَّسُولِ سَبِيلًا * يَا وَيْلَتَى لَيْتَنِي لَمْ أَتَّخِذْ فُلَانًا خَلِيلًا * لَقَدْ أَضَلَّنِي عَنِ الذِّكْرِ بَعْدَ إِذْ جَاءَنِي وَكَانَ الشَّيْطَانُ لِلْإِنْسَانِ خَذُولًا ” سورة الفرقان 29-27
“በዳይም፦ ከመልክተኛው ጋር ቀጥተኛን መንገድ ይዤ በሆነ ዋ ምኞቴ! እያለ (በጸጸት) ሁለት እጆቹን የሚነክስበትን ቀን (አስታውስ)።ዋ ጥፋቴ! እገሌን ወዳጅ ባልያዝኩ ኖሮ እመኛለሁ፤ (የእምነት ቃልን) ከመጣልኝ በኋላ ከማስታወስ በእርግጥ አሳሳተኝ፤ (ይላል)፤ ሰይጣንም ለሰው አጋላጭ ነው።” (ሱረቱል ፉርቃን 25፡27-29)፡፡

መ. ስሜትን መከተል፡-
ያለምንም መለኮታዊ መመሪያ ስሜቱን የሚከተል ሰው፡ የነፍሲያውን ፍላጎት የሚያሟላ፡ ያለ ምንም ጥርጥር ጥመት ውስጥ ይወድቃል፡-
“يَا دَاوُودُ إِنَّا جَعَلْنَاكَ خَلِيفَةً فِي الْأَرْضِ فَاحْكُمْ بَيْنَ النَّاسِ بِالْحَقِّ وَلَا تَتَّبِعِ الْهَوَى فَيُضِلَّكَ عَنْ سَبِيلِ اللَّهِ إِنَّ الَّذِينَ يَضِلُّونَ عَنْ سَبِيلِ اللَّهِ لَهُمْ عَذَابٌ شَدِيدٌ بِمَا نَسُوا يَوْمَ الْحِسَابِ ” سورة ص 26
“ዳውድ ሆይ! እኛ በምድር ላይ ምትክ አድርገንሃልና በሰዎች መካከል በእውነት ፍረድ፡፡ ዝንባሌሀንም አትከተል፤ከአላህ መንገድ ያሳሳትሃልና፡፡ እነዚያ ከአላህ መንገድ የሚሳሳቱ የምርመራውን ቀን በመርሳታቸው ለእነርሱ ብርቱ ቅጣት አላቸው፡፡” (ሱረቱ 38፡ሷድ 26)፡፡

ሠ. ሸይጧን፡-
ከመጀመሪያው ሰው አባታችን አደም (ዐለይሂ ሰላም) ጀምሮ የሰው ዘር ሁሉ ጠላት የሆነው ሸይጧን ሰዎችን ከአላህ መንገድ ለማውጣትና ለማጥመም የቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ በሰራዊቱ አማካኝነት ቀን ከሌሊት ይተጋል፡-
“أَلَمْ تَرَ إِلَى الَّذِينَ يَزْعُمُونَ أَنَّهُمْ آمَنُوا بِمَا أُنْزِلَ إِلَيْكَ وَمَا أُنْزِلَ مِنْ قَبْلِكَ يُرِيدُونَ أَنْ يَتَحَاكَمُوا إِلَى الطَّاغُوتِ وَقَدْ أُمِرُوا أَنْ يَكْفُرُوا بِهِ وَيُرِيدُ الشَّيْطَانُ أَنْ يُضِلَّهُمْ ضَلَالًا بَعِيدًا ” سورة النساء 60
“ወደ እነዚያ፣ እርሱ ባንተ ላይ በተዋረደውና ከአንተ በፊትም በተወረደው አምነናል ወደሚሉት አላየህምን? በርሱ እንዲክዱ በእርግጥ የታዘዙ ሲሆኑ ወደ ጣዖት መፋረድን ይፈልጋሉ፤ ሰይጣንም (ከውነት) የራቀን መሳሳት ሊያሳስታቸው ይፈልጋል።” (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡60)፡፡
ይቀጥላል
ወአኺሩ ዳዕዋና ዐኒል-ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡
Click and Like ➤➤ https://www.facebook.com/Ustaz.Abuhyder