✔ልፋት ለምኔ? ክፍል አሥራ ስድስት በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
490 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡

በቀዷ ወል-ቀደር የማመን ጥቅሞች!

በቀዷ ወል-ቀደር (ቅድመ ውሳኔ) ማመን ከስድስቱ የእምነት ማእዘናት አንዱ ነው፡፡ አንድ ሙስሊም በሱ እስካላመነ ድረስ ሙስሊም ተብሎ ሊጠራ አይችልም፡፡ በቀዷ ወል-ቀደር ማመን በአላህ ከማመን ጋር አብሮ የሚያያዝ ነው፡፡ ምክንያቱም ‹‹ቀደር›› የአላህ ዕውቀት፣ ጥበብ፣ ፈቃድና የመፍጠር ሁኔታ ውጤት ነውና፡፡

ለዛሬ ግን ትንሽ የማስታውሳችሁ በቀደር የማመንን ጥቅሞች ነው፡፡ በቀደር ማመን በአንድ ሙስሊም ህይወት ውስጥ ምን ፍሬ ያፈራል? የሚለውን ነው፡፡ ምክንያቱም፡- የቀደርን ፅንሰ ሀሳብ በደንብ ያልተረዱ ሰዎች፡- በቀደር ማመን፡ ለስንፍናና እጅ መስጠት ይዳርጋል፡፡ ለፍቶና ጥሮ እራስን ለመለወጥ ከመጣር ይልቅ፡ ‹እሱ ያለው አይቀርም!› በሚል ብሂል ወደ ኋላ መቅረትን ያስከትላል፡ የሚል ተቃውሞ በማንሳታቸው ነው፡፡ በርግጥ የቀደርን ፅንሰ ሀሳብ በአግባቡ አለመረዳት ለዚህ ስህተት ሊዳርግ ይችላል፡፡

በጥንት ጊዜ ‹‹ጀብሪያ›› የተሰኙ ጥቂት ቡድኖች ተነስተው ነበር፡፡ እነዚህም ሰዎች ስለ ቀደር የነበራቸው ግንዛቤ ትክክል ባለመሆኑ ለጌታቸው ትእዛዝ ክብር አልነበራቸውም፡፡ የተከለከሉትን የአላህን ድንበር ከጣሱ በኋላ እንዳይወቀሱ በቀደር ያሳብባሉ፡፡ የታዘዙትን የጌታቸውን ህግ ለመፈጸም ነፍሲያቸው ሲከብዳት ‹አላህ አልሻልንም› በማለት ያመካኛሉ፡፡ የሚገርመው ግን፡ ሰው በነሱ ላይ ወሰን ቢያልፍባቸው አሁንም ቀደር ነው ብለው እጅ ከመስጠት ይልቅ እራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል የቻሉትን ያህል መስዋእትነት መክፈላቸው ነው፡፡ የኑሮን ውጣ ውረድ ለማሸነፍ ላይ ታች በማለት ደፋ ቀና ሲሉ እንጂ፡ ‹አላህ የከፈተውን ጉሮሮ ማንም አይዘጋውም!› በማለት አርፈው ሲቀመጡ አይስተዋሉም፡፡ ታዲያ ይህን ሁሉ ልፋትና ጥረት የጌታቸው ህግ ላይ ሲሆን ለምን ረሱት? ይህ ከራስ ሀሳብ ጋር መጋጨት አይደለምን? ለማንኛውም በቀዷ ወል-ቀደር ማመን አንድን ሙስሊም ወደፊት እንጂ ወደኋላ እንደማይጎትተው፡ ጉብዝናን እንጂ ስንፍናን እንደማያላብሰው ለማሳየት የተወሰኑ የቀደርን ጥቅሞች እንመለከታለን፡፡ አላህ ይወፍቀን አሚን፡፡

1. ትግስትና ውዴታን፡-

በቀደር ማመን ለአንድ ሙስሊም ትግስተኝነትን (ሶብርን) ያጎናጽፈዋል፡፡ የጌታውንም ውሳኔ ወዶ እንዲቀበል ይዳርገዋል፡፡ ታጋሾች ደግሞ ጌታቸው አላህ ዘንድ የሚኖራቸው ምንዳ (የክብር ሽልማት) ያለ ገደብ ነው (ሱረቱ-ዙመር 39፡10)፡፡

በዚህ ዱንያ ላይ የተፈጠርነው ለዘልዓለም ልንኖር አይደለም፡፡ ልንፈተን ነው፡፡ (ሱረቱል ሙልክ 67፡2)፡፡ በጌታችን አላህ፡ ነጻ ፈቃድ ያለን ፍጡር ሆነን የተሰራነው፡ ይህን አድርግ! ያን ደግሞ አታድርግ! በሚለው መለኮታዊ ትእዛዙ ሊፈትነን ነው፡፡ ማን በፈቃደኝነት እሱን እሺ ብሎ ጌታውን ይግገዛል?፡ ማን ደግሞ እምቢ ብሎ ስሜቱን በመከተል የክህደትን መስመር ይከተላል? የሚለውን በተግባር ለመለየት ነው፡፡ ምንም እንኳ እሱ በቀዳማይ ዕውቀቱ ታዛዦችን ከአመጸኞች ለይቶ ያወቀ ቢሆንም፡ እኛን ግን እራሳችንን እንድናውቅ፡ እንደ ስራችን መጠን ደግሞ ዋጋችንን እንቀበል ዘንድ ወደ ተግባሩ ዓለም አምጥቶ ፈጠረን፡፡ ደግሞም ታዛዥነታችን በፈተናዎች ውስጥ እንዲያልፉ ፈቀደ፡፡ መንገዱን ሁሉ ሶፍትና ጨርቅ አላደረገውም፡፡ እሾህና የጠርሙስ ስባሪም አለው፡፡ የአላህን እገዛ በመሻት ተጠንቅቆ መጓዝ ግን የኛ ኃላፊነት ነው፡፡ ችግር ሲገጥመን ትእግስት እናደርግም ዘንድ አዘዘን፡፡ ከችግር ጋር ምቾት አለና፡፡ ጌታ አላህም በቃሉ እንዲህ ይላል፡-

“وَلَنَبْلُوَنَّكُمْ بِشَيْءٍ مِنَ الْخَوْفِ وَالْجُوعِ وَنَقْصٍ مِنَ الْأَمْوَالِ وَالْأَنْفُسِ وَالثَّمَرَاتِ وَبَشِّرِ الصَّابِرِينَ * الَّذِينَ إِذَا أَصَابَتْهُمْ مُصِيبَةٌ قَالُوا إِنَّا لِلَّهِ وَإِنَّا إِلَيْهِ رَاجِعُونَ * أُولَئِكَ عَلَيْهِمْ صَلَوَاتٌ مِنْ رَبِّهِمْ وَرَحْمَةٌ وَأُولَئِكَ هُمُ الْمُهْتَدُونَ ” سورة البقرة 157-155
“ከፍርሃትና ከረኃብም በጥቂት ነገር፣ ከገንዘቦችና ከነፍሶችም፣ ከፍራፍሬዎችም በመቀነስ በእርግጥ እንሞክራችኋለን፡፡ ታጋሾችንም (በገጀነት) አብስር፡፡ እነዚያን መከራ፤ በነካቻቸው ጊዜ «እኛ ለአላህ፤ ነን እኛም ወደርሱ ተመላሾች» ነን የሚሉትን (አብስር)፡፡እነዚያ በእነርሱ ላይ ከጌታቸው የኾኑ ምሕረቶች ችሮታም አልሉ፡፡ እነርሱም (ወደ እውነት) ተመሪዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡155-157)፡፡

አንድ ሙስሊም ሰጋጅ ሶላቱን ካጠናቀቀ በኋላ ከሚለው የዚክር ቃላት ውስጡ አንዱ፡- “አልላሁመ ላ-ማኒዐ ሊማ-አዕጠይት፣ ወላ-ሙዕጢየ ሊማ-መነዕት፣ ወላ-ራድደ ሊማ-ቀዶይት፣ ወላ-የንፈዑ ዘል-ጀድዲ ሚንከል-ጀድ” የሚለው ነው፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም የዘገቡት)፡፡
ትርጉሙም፡- “አምላኬ አላህ ሆይ! አንተ ለሰጠኸው ከልካይ (ነሺ) የለውም፣ አንተ ለከለከልከው (ለነሳኸው) ሰጪ የለውም፣ አንተ ለወሰንከው መላሽ (እንዳይሆን የሚያግድ) የለውም፣ የሀብት ባለቤትም፡ ሀብቱ ካንተ ዘንድ (ጥገኛ ከመሆንና ቅጣት) ሊያብቃቃው አይችልም” ማለት ነው፡፡

2. የቀልብ እርጋታን፡-

በቀደር ማመን ለአንድ ሙስሊም የቀልብ እርጋታን፡ የኅሊና እረፍትን ያጎናጽፈዋል፡፡ ተስፋ የመቁረጥና የመቆጨት ስሜትን ከውስጡ ያስወግድለታል፡፡ ምክንያቱም ይህ ሙስሊም፡ የአላህ ዕውቀት እጅጉኑ ሰፊና ሁሉን ያካበበ እንደሆነ ያውቃል (ሱረቱ ጋፊር (ሙእሚን) 40፡7)፡፡ መልካም ማለት ደግሞ አላህ ለሱ የመረጠለት እንጂ እሱ ለግዜው የታየው ብቻ እንዳልሆነ ይረዳል፡፡ መልካም ነገራት ሁሉ በጌታው እጅ ብቻ ነውና፡፡ ስለዚህም እንዲህ በሚለው የአላህ ቃል ይጽናናል፡-

“كُتِبَ عَلَيْكُمُ الْقِتَالُ وَهُوَ كُرْهٌ لَكُمْ وَعَسَى أَنْ تَكْرَهُوا شَيْئًا وَهُوَ خَيْرٌ لَكُمْ وَعَسَى أَنْ تُحِبُّوا شَيْئًا وَهُوَ شَرٌّ لَكُمْ وَاللَّهُ يَعْلَمُ وَأَنْتُمْ لَا تَعْلَمُونَ ” سورة البقرة 216

“መጋደል እርሱ ለእናንተ የተጠላ ሲሆን በእናንተ ላይ ተጻፈ፡፡ አንዳች ነገርን እርሱ ለናንተ የበለጠ ሲሆን የምትጠሉት መኾናችሁ ተረጋገጠ፡፡ አንዳችንም ነገር እርሱ ለናንተ መጥፎ ሲሆን የምትወዱት መሆናችሁ ተረጋገጠ፡፡ አላህም (የሚሻላችሁን) ያውቃል ግን እናንተ አታውቁም፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡216)፡፡

ሙስሊሞች ለሃይማኖታቸው ክብርና ለዲናቸው የበላይነት፡ ጠላትን መታገል ተደነገገባቸው፡፡ ግን ይህ ድንጋጌ ለነፍስ የተጠላች እንደሆነችም ተነገረ፡፡ ምክንያቱም ትግል፡ ከሚወዱት ቤተሰብ፣ ጎረቤትና ማኅበረሰብ ተነጥሎ፡ የማይፈልጉትን የጠላት ፍልሚያ መጋፈጥ ስለሆነ!፡፡ ደግሞም እስከ ሞት ድረስ ህይወትን ሊያስከፍል ይችላል፡፡ ቢሆንምለናንተ የተሻለ ነው ይለናል ጌታችን፡፡ በዚህ ምድር ላይ ከአላህ ባሮች ላይ የጠላትን እርምጃ በመመከት ህዝቦችን መታደግ፣ ሃይማኖታቸውና ክብራቸው ተጠብቆ ጌታቸውን በነጻነት እንዲያመልኩ፡ መስዋእትነትን መክፈል እጅግ ታላቅና በላጭ ነው፡፡ በአኼራም የአላህን ጀነት መጎናጸፍ ነው ውጤቱ፡፡ እኛም የሚሻለንን ‹እኔ አውቅላችኋለሁ› በማለቱ በጌታችን ረካን!!

ሰዎች የነገራትን ፍጻሜ ከወዲሁ መገመት እንጂ በትክክል ማወቅ አይችሉም፡፡ የሚጠቅመንን ነገራት ለማምጣት እና የሚጎዱንን ደግሞ ከራስ ላይ ለመከላከል ደካሞች ነን፡፡ ፍጻሜው ምን እንደሆነ ለማናውቀው ነገር ውሳኔ መስጠት እንቸገራለን፡፡ ስለሆነም ብዙ ጊዜ በስራችን እንጸጸታለን፡፡ ያም ስለሆነ ነው በኢስላም ውስጥ “ሶላቱል ኢስቲኻራ” የሚባል ነገር የተደነገገው፡፡ (ቡኻሪይ፣ አቡ ዳዉድና ቲርሚዚይ)፡፡

“ኢስቲኻራ” ማለት፡- ሁለት ነገራት አጣብቂኝ ውስጥ ከተውን፡ ወደየት ማዘንበልና ውሳኔ መስጠት አቅቶን በሚቸግረን ወቅት፡ ጌታችን አላህ በሁሉን ዐዋቂነቱ ለኛ የተሻለውን ይመርጥልንና ያመላክተን ዘንድ፡ እንዲሁም ያመላከተንን ነገር እንድንፈጽመውና እናገኘው ዘንድ እርዳታውን በመሻት የሚከወን የሶላት አይነት ነው፡፡ ይህ ሰጋጅ ሙስሊም፡ ውጤቱን በህልሙ ሊያየው ይችላል፡፡ ወይንም በሀሳቡ ወደተሻለው ነገር እንዲያጋድል አላህ ልቡን ይመራዋል፡፡ መንገዶቹ እጅግ ብዙ ነውና፡፡

3. ለስራ መበርታትን፡-

በቀደር ማመን፡ አንድን ሙስሊም ወደ ስራና ትግል ያነሳሳዋል እንጂ አያሳንፈውም፡፡ ምክንያቱም ሙስሊም ሁሌም የሚያስበው የወደፊቱን እንጂ ያለፈውንና ያመለጠውን አይደለም፡፡ አንዴ ያለፈ ነገር (ቀደር የሆነ ነገር) ተመልሶ ሊመጣ አይችልምና፡፡ የሆነውንም ነገር እንዳልሆነ ለማድረግ መቀየር አይቻልምና፡፡ ባለፈው ጊዜ በመጸጸትና በመቆጨት እራሱን ለአደጋ አያጋልጥም፡፡ ባይሆን ለወደፊቱ ትምህርት ሊያገኝበት በሚችለው መልኩ ብቻ ካለፈው ስህተት ይማራል እንጂ፡፡ ብሂሉም የሚለው ‹‹ባሳለፍከው ነገር ከምትጸጸት፡ የምትጸጸትበትን ደቂቃ ተጠቀምበት›› አይደል!፡፡

ወይኔ እንዲህ ባደርግ ኖሮ! የሚባል ባእድ ቋንቋ ሙስሊሙ ዘንድ ዋጋ የለውም፡፡ ‹‹ኖሮ›› የሚለው ቃል ለቁጭትና ለጸጸት በር ከመክፈት ውጪ ጥቅምን አያመጣምና፡፡ ‹‹በነበር በነበር፡ እንትን የኛ ነበር›› እንዳሉ ሰዎች መሆን ስንፍና ነው፡፡ የአላህ መልክተኛም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ይህን ጉዳይ አስመልክተው እንዲህ ይመክሩናል፡-

عَنْ أَبِى هُرَيْرَةَ قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ -صلى الله عليه وسلم- « الْمُؤْمِنُ الْقَوِىُّ خَيْرٌ وَأَحَبُّ إِلَى اللَّهِ مِنَ الْمُؤْمِنِ الضَّعِيفِ وَفِى كُلٍّ خَيْرٌ احْرِصْ عَلَى مَا يَنْفَعُكَ وَاسْتَعِنْ بِاللَّهِ وَلاَ تَعْجِزْ وَإِنْ أَصَابَكَ شَىْءٌ فَلاَ تَقُلْ لَوْ أَنِّى فَعَلْتُ كَانَ كَذَا وَكَذَا. وَلَكِنْ قُلْ قَدَرُ اللَّهِ وَمَا شَاءَ فَعَلَ فَإِنَّ لَوْ تَفْتَحُ عَمَلَ الشَّيْطَانِ ». رواه مسلم 2664.

አቢ ሁረይራ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ጠንካራ ሙእሚን ከደካማው ሙእሚን የበለጠ አላህ ዘንድ የተሻለና ተወዳጅ ነው፡፡ በሁለቱም ውስጥ መልካምነት አልለ፡፡ የሚጠቅምህን ነገር ለማግኘት ጣር እንጂ አትስነፍ፡፡ ደግሞም በአላህ ታገዝ (እገዛን ጠይቀው)፡፡ አንዳች ነገር ቢያገኝህ፡- እንዲህ ሰርቼው ቢሆን ኖሮ እንዲህ ይሆን ነበር! አትበል፡፡ ነገር ግን፡- አላህ ወሰነ፡ እሱ የሻውንም ሰራ በል፡፡ ‹‹ቢሆን ኖሮ›› (የምትለዋ ቃል) የሸይጣንን ስራ ትከፍታለችና” (ሙስሊም 2664)፡፡

ቁጣ ከሸይጧን ነው፡፡ ባሳለፈው ድርጊት ምነው እንዲህ ባደረግሁ ኖሮ! እያለ የሚቆጭ ሰው ደግሞ ለሰይጣን የስራ በር ከፈተለት ማለት ነው፡፡ ደግሞም የአላህን ውሳኔ ወዶ አለመቀበልን ያስከትላልና፡፡ ይህ ደግሞ የባሰ አደጋ ነው፡፡
ይቀጥላል
ወአኺሩ ዳዕዋና ዐኒል-ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡