✔ልፋት ለምኔ? ክፍል ሁለት በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
54 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
በክፍል አንድ ትምህርታችን ላይ ‹‹ልፋት ለምኔ?›› በሚል ርእስ፡ በቀዷ ወል-ቀደር ዙሪያ የሚነሱ ብዥታዎችን ለማጥራት አሊፍ ብለን ጀምረናል፡፡ በውስጡም፡-
ሀ/ ስድስት የሰውነት ክፍለ አካላትን (አይን፣ ጆሮ፣ ምላስ፣ እጅ፣ እግር፣ ልብ እና ነጻ-ፈቃድን) እንደ አብነት በመጠቀም፡ በነዚህ ነገራት የፈቀድነውንና የፈለግነውን ነገር (ኸይርም ሆነ ሸር) እንደምንገለገልባቸው በተጨባጭ ምሣሌዎች አይተናል፡፡ በማያያዝም፡ እኛ ማለት ነጻ-ፈቃድ ያለን የአላህ ባሮች እንጂ፡ በተሞላው መልኩ ብቻ የሚንቀሳቀስ ሮቦት እንዳልሆንን በመግለጽ፡ ለምንፈጽመው የኃጢአት ተግባር ተውበት ከማድረግ ይልቅ ቀዷ ወል-ቀደርን ማሳበብ አግባብ እንዳልሆነና እፍረትም ሊይዘን እንደሚገባ ተመልክተናል፡፡ የሙስሊም አንደኛው ባሕሪ ‹‹ሐያእ›› ማድረግ ነው የሚለውን ነቢያዊ ሐዲሥ መሰረት በማድረግም፡ በሰው ሐቅ ላይ ጥፋት ስንፈጽም የመጸጸትን ባሕሪ እያሳዩ፡ በአላህ ህግ ላይ ግን ድንበር ሲጥሱ ‹አላህ ቀደረብኝ› ማለት ሼም እንደሆነ ተመልክተናል፡፡

ለ/ ከዚህ በመቀጠልም፡- ‹‹ሁሉ ነገር ቀድሞ የተጻፈና የተወሰነ ‹‹ቀዷ ወል-ቀደር›› ከሆነ፡ እኛ ታዲያ የምንለፋውና የምንሰራው ለምንድነው? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት፡ ሁለት ምላሾችን ተመልክተናል፡፡ እነሱም፡-
1/ የምንሰራውና የምንለፋው፡ ከጌታችን በኩል ስሩ የሚል ትእዛዝ ስለተላለፈልንና፡ ይህም አዛዣችን ጌታችን በመሆኑ፡ እኛም የርሱ ባሮች ስለሆንን ትእዛዙን አሚን ብሎ ተቀብሎ መፈጸም ትልቁ ነጻነታችን ስለሆነ ህጉን ማክበር አለብን የሚል ሲሆን፡
2/ ደግሞም እንደታዘዝነውና ጌታችን እንደፈለገው ህጉን ከፈጸምን፡ እሱም በራሕመቱ ስራችንን ከተቀበለው፡ በየውሙል ቂያም ጀነትን ይሰጠናል፡ የሱን መለኮታዊ ፊትም እናያለን፡ የነቢያችንንም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ጉርብትና እናገኛለን ብለን በአላህ ላይ ተስፋ ስለምናደርግና፡ እሱም ይህን ሊፈጽምልን ቃል ስለገባልን ነው የምንለፋውና የምንሰራው የሚል ነበር፡፡

ሐ/ በመጨረሻም፡- እንግዲያውስ እኛ ሰዎች ነጻ-ፈቃድ የሚባል ነገር ካለንና በፈቃዳችንም የፈለግነውን ነገር ከሆነ የምንሰራው፡ እንዲሁም ጌታችን ስራችንን መሰረት አድርጎ ከሆነ የቂያም እለት የሚተሳሰበን፡ ታዲያ ቀዷ ወል-ቀደር ምንድነው? ከኛስ ጋር ያለው ግኑኝነት ምንድነው? እኛስ በኛ ላይ ቀድሞ የተወሰነውን ነገር ጥሰን መውጣት እንችላለን ወይ? የሚል ጥያቄ አንስተን፡ መልሱን በክፍል ሁለት ላይ ስላሸጋገርነው፡ እነሆ በአላህ ፈቃድ ዛሬ ምላሹን ይዘን ቀርበናል አልሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡ አላህም ሐቁን እንድንገነዘብ የሁላችንንም ልብ ያስፋልን፡-
ቀዷ ወል-ቀደር ምንድነው?
ቀዷ ወል-ቀደር ማለት፡- በዚህ ዓለም ላይ የሚከሰት ማንኛውም ክስተት ጥሩም ሆነ መጥፎ፡ ከሰውም ይገኝ ከእንሰሳት፣ ከመላእክትም ይገኝ ከጂንኒዎች፣ ከበራሪዎችም ይሁን ከነፍሳት፣ በፈቃድና በምርጫም የተገኘ ይሁን በግዳጅ፡ ጉዳዩ አስቀድሞ አላህ ዘንድ የታወቀ፡ በለውሐል መሕፉዝ (ጥብቅ ሰሌዳ) ላይ ተወስኖ የተጻፈ፡ በአላህ ፈቃድና ይሁንታ የተከናወነ ነው ብሎ ማመን ማለት ነው፡፡
አንድ ሙስሊም ፈጣሪ አምላኩ አላህ፡- በፍጥረተ-ዓለሙ ላይ ያለውን ነገር በጠቅላላ አስቀድሞ በመለኮታዊ ዕውቀቱ ያወቀ መሆኑን፣ ደግሞም ይህን ነገር በለውሐል መሕፉዝ ላይ በጽሁፍ ያሰፈረው (ቀለምን እንዲጽፍ ያዘዘ) መሆኑን፡ እንደገናምም ያ የተጻፈለትና የተወሰነለት ጊዜው ደርሶ በተግባር መከናወን ሲጀምርም ያለሱ ፈቃድና ፍላጎት የማይከሰት መሆኑን፡ እንዲሁም እሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪና አስገኚ ብቸኛ ጌታ መሆኑን አምኖ ከተቀበለ በቀዷ ወል-ቀደር አምኗል፡ ሙስሊም ሆኗል ማለት ነው፡፡

ጥያቄ፡- አሁን በተሰጠው ገለጻ መሰረት፡ በዚህ ዓለም ላይ የሚከሰት ማንኛውም ክስተት በጠቅላላ አስቀድሞ በአላህ ዘነድ የታወቀና በመጽሐፍ የተመዘገበ፡ እንዲሁም በአላህ ፈቃድና ቁጥጥር ስር ሆኖ በሱ ይሁንታ የሚከናወን ከሆነ፡ እኛ የምንሰራውና የምንለፋው (ለኸይርም ሆነ ለሸር) እንዴት በራሳችን ፈቃድና ፍላጎት ነው ማለት እንችላለን? ምክንያቱም ቀድሞ ከታወቀው፣ ከተጻፈውና ከተወሰነው ነገር ሊወጣ የሚችል ነገር የለም ተብሏልና!! ታዲያ የኛ ፈቃድ ያለው የቱ ጋር ነው?

ምላሽ፡- ዋናውና ወሳኙ እንዲሁም መነሳት ያለበት የፍትሕ ጥያቄ ነው፡፡ የዚህን ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ለማግኘት ቀጥሎ ያሉትን ነጥቦች በደንብ እናስተውላቸው፡፡ ካልገቡንም ደጋግመን እናንብባቸው፡-
ሀ/ የኛ ነጻ ፈቃድ ያለው፡ እራሱ የተነሳነው ጥያቄ ላይ ነው፡፡ ማለትም፡- አንድ ሰው ስለ ቀዷ ወል-ቀድር ትምህርት ሲሰጠው፡ ሁሉም ነገር አስቀድሞ በአላህ ዘንድ ቀድሞ የታወቀ ነው የሚል ትምህርትን ሲሰማ፡ ቀድሞ መታወቅ ብቻም አይደለም በለውሐል መሕፉዝ ላይም በጽሁፍ የሰፈረ ነው ሲባል፡ ማወቅና በጽሑፍ ማስፈርም ብቻ አይደለም፡ እንደገናም በአላህ ፈቃድና ይሁንታ ነው የሚከናወነው ሲሉት፡ ታዲያ የኔ ምርጫ የቱ ጋር ነው ያለው? ነጻ ፈቃድ ማለቱስ ምንድነው ትርጉሙ? ማለቱ በራሱ ግለሰቡ ነጻ ፈቃድ ያለው ፍጡር መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
እውን ይህ ግለሰብ ትምህርቱ ግራ ባይገባው ኖሮ እንዲህ አይነት ጥያቄን ያነሳ ነበርን? ደግሞስ ጥያቄውን ሲያነሳ ምን ብሎ መጠየቅ እንዳለበት በአእምሮው ካሰላሰለው ውጪ መረዳት ያልፈለገውን ጥያቄ ነው ያነሳውን? አይ! ግለሰቡ የጠየቀው እራሱ ነው፡፡ ያነሳውም ጥያቄ ግራ የገባውን ነገር ነው፡፡ ደግሞም ጠያቂውም በአእምሮው የመጣለትን እንጂ እንዲህ ብለህ ጠይቅ ተብሎ ተገዶ አይደለም የጠየቀው ብለን ከመለስን፡ ተስማማን ማለት ነው፡፡
ሰዎች ግራ የገባቸውን ነገር አልገባኝምና አስረዱኝ ብለው መምህራንን መጠየቃቸው፣ የጥያቄያቸውም ምንጩ በአእምሮአቸው የሚመላለሰውን ከሆነ፡ እነዚህ ሰዎች ፈቃድ ያላቸው ፍጡሮች ናቸው ማለት ነው፡፡ ፈቃድም ያላቸው በመሆናቸው ለመጠየቅ በቁ ማለት ነው፡፡ ይህ የመጀመሪያው ሎጂካዊ መልስ ነው፡፡ ስለዚህ ጥያቄው መሆን የነበረበት፡- የኛን ነጻ ፈቃድ ቀድሞ ከተወሰነው የቀደር ጉዳይ ጋር እንዴት እናስኪደው? ነው እንጂ፡ ሁሉ ነገር የተቀደረ ከሆነ እኛ ምን ነጻ ፈቃድ አለን? የሚል መሆን አልነበረበትም!!፡፡

ለ/ ጌታችን አላህ በዚህ ዓለም ላይ የሚከናወኑ ነገራትን አስቀድሞ ማወቁ፡ ሰው በነጻ ፈቃዱ እንዲፈጽም የተጣለበትን ኃላፊነት እንዳይፈጽመው የሚጋፋ ሳይሆን፡ ከሰዎች ስራ በፊት የሱ ዕውቀት የቀደመ መሆኑን ነው የሚገልጸው፡፡ አንተ ዛሬ ላይ የምትሰራውን ስራ (ኸይርም ሆነ ሸር) አላህ ዓለማትን ከመፍጠሩ በፊት በሁሉን አዋቂነቱ አስቀድሞ ያውቀው ነበር ብትባል፡ በጌታህ ዕውቀት ልትደነቅና ሱብሐነከ ያረቢ! ልትል ሲገባህ፡ ‹‹አንተ አስቀድመህ ካወቅኸውማ እኔ ምኑን ነጻ ፈቃድ ተሰጠኝ ታዲያ?›› ብለህ መስመር ትስታለህን?
የጌታህ ዕውቀት እኮ ያንተን የወደፊቱን ስራህን ቀድሞ ገለጸው፡ አየው፡ ተመለከተው እንጂ፡ ያ መለኮታዊ ዕውቀት ያለ ፈቃድህ አንድን ስራ እንድትሰራ አላስገደደህም፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-الَّذِينَ يَحْمِلُونَ الْعَرْشَ وَمَنْ حَوْلَهُ يُسَبِّحُونَ بِحَمْدِ رَبِّهِمْ وَيُؤْمِنُونَ بِهِ وَيَسْتَغْفِرُونَ لِلَّذِينَ آمَنُوا رَبَّنَا وَسِعْتَ كُلَّ شَيْءٍ رَحْمَةً وَعِلْمًا فَاغْفِرْ لِلَّذِينَ تَابُوا وَاتَّبَعُوا سَبِيلَكَ وَقِهِمْ عَذَابَ الْجَحِيمِ ” سورة غافر 7
“እነዚያ ዐርሹን የሚሸከሙት፣ እነዚያም በዙሪያው ያሉት፣ በጌታቸው ምስጋና ያወድሳሉ፤በርሱም ያምናሉ፤ ጌታችን ሆይ! ነገሩን ሁሉ በእዝነትና በዕውቀት ከበሃል፤ ስለዚህ ለነዚያ ለተጸጸቱት፣ መንገድህንም ለተከተሉት ምሕረት አድርግላቸው፤ የእሳትንም ቅጣት ጠብቃቸው፣ እያሉ ለነዚያ ላመኑት ምሕረትን ይለምናሉ።” (ሱረቱ ጋፊር 40፡7)፡፡
በዚህ አንቀጽ ስር ‹‹ጌታችን ሆይ! ነገሩን ሁሉ በእዝነትና በዕውቀት ከበሃል›› የሚለው ቃል ትልቅ መልእክት አለው፡፡ ጌታ አላህ በዕውቀቱ ሁሉንም ነገር ያካበበ ነው፡፡ ከሱ ዕውቀት የሚወጣ ምንም ነገር የለም፡፡ በቀላል መንገድ ነገሩን ቀረብ አድርጎ ለመረዳት፡-
የአላህ ዕውቀት በኛ ላይ ማለት፡ ልክ እንደ ጣሪያ እንዳጠለለን ሰማይና እንደ ተሸከመችን ምድር ማለት ነው፡፡ እኛ የቱንም ያህል ብንዘል፣ ብንሮጥ፣ ብንበር ከሰማይና ምድር ክልል ጥሰን መውጣት እንደማንችለው ሁሉ፡ ከአላህ ዕውቀትም መሸሽና መደበቅ አንችልም፡፡ በሰማይና ምድር ሰፊ ክልል ስር መኖራችን፡ በምንሰራው ስራ ላይ ሰማይና ምድር ያለ ፈቃዳችን ያስገድዱናል ማለት እንዳልሆነው ሁሉ፡ በአላህ መለኮታዊ ዕውቀት ስር መሆናችንም የአላህ ዕውቀት እኛን ያለ-ፈቃዳችን አንድን ነገር እንድንሰራ ያስገድደናል ማለት አይደለም፡፡ ‹ዒልሙላሂ ካሺፉን ላ ሙጁቢር›

ሐ/ ጌታችን አላህ በዚህ ዓለም ላይ የሚከናወኑ ነገራትን በጠቅላላ አስቀድሞ መጻፉና በለውሐል መሕፉዝ ላይ ማስፈሩ፡- የሱን ሁሉን ዐዋቂነት ለመጠቆም፣ መልካም ባሮቹን ከትእቢትና ከተስፋ መቁረጥ ስሜት ለመጠበቅ መፈለጉን፣ የሱ ፈቃድ የባሮቹን ፈቃድ ሁሉ የሚያሸንፍና የሚፈጸም መሆኑን ለመግለጽ እንጂ፡ የባሮቹን ነጻ ፈቃድ የሚጋፋና ያለ ፈቃዳቸው ያልፈለጉትን ነገር እንዲሰሩ የሚያስገድድ አይደለም፡፡ ለእያንዳንዱ ምሣሌዎችን እንመልከትለት፡-
” قَالَ فَمَنْ رَبُّكُمَا يَا مُوسَى * قَالَ رَبُّنَا الَّذِي أَعْطَى كُلَّ شَيْءٍ خَلْقَهُ ثُمَّ هَدَى * قَالَ فَمَا بَالُ الْقُرُونِ الْأُولَى * قَالَ عِلْمُهَا عِنْدَ رَبِّي فِي كِتَابٍ لَا يَضِلُّ رَبِّي وَلَا يَنْسَى ” سورة طه 52-49
“(ፈርዖንም)፦ ሙሳ ሆይ ጌታችሁ ማነው? አለ። ጌታችን ያ ለፍጥረቱ፣ ነገርን ሁሉ (የሚያስፈልገውን) የሰጠ ከዚያም የመራው ነው አለው። (ፈርዖንም) የመጀመሪያይቱ ዘመናት ሕዝቦች ሁኔታ ምንድን ነው? አለ። (ሙሳም) ዕውቀትዋ እጌታዬ ዘንድ በመጽሃፍ የተመዘገበ ነው፤ ጌታዬ አይሳሳትም አይረሳምም አለው።” (ሱረቱ ጣሀ 20፡49-52)፡፡
በዚህ አንቀጽ መሰረት ነቢዩላህ ሙሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ከጠማማው ፊርዐውን በኩል ለቀረበለት ጥያቄ በቂ ምላሽን ሲሰጥ እናያለን፡፡ ፊርዐውን፡- የቀደምት ህዝቦች ታሪክ ሁኔታ እንዴት እንደነበረና ፍጻሜያቸው ጀሀነም እሳት ወይስ ምን? እንደነበረ ሲጠይቅ፡ የአላህ መልክተኛ የሆነው ሙሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ደግሞ፡- የነዚህ ህዝቦች ታሪክ ዕውቀቱ ያለው አላህ ዘንድ እንደሆነና፡ ደግሞም በመጽሐፍ (ለውሐል መሕፉዝ) ላይ ሰፍሮ የተቀመጠ ነገር መሆኑን ገለጸለትና፡ ይህ ጌታዬ አላህ ደግሞ በዕውቀቱ መርሳትም ሆነ መሳሳት የማይገጥመው ነው በማለት አብራራለት፡፡
ስለዚህ ነገራት በጠቅላላ ቀድመው መጻፋቸውና በዛው መልኩም በተግባር መከናወናቸው፡ የአላህን ሁሉን ዐዋቂነት የሚያጎሉ ናቸው እንጂ፡ የተጻፈባቸውን ሰዎች ያለ-ፈቃዳቸው ስራን የሚያሰሩ ናቸው ማለት አይደለም፡፡
የተማሪዎቹን ሁኔታ በአግባቡ የሚያውቅ መምህር፡ ከሳምንት በኋላ በሚያቀርበው ፈተና ላይ፡ ከክፍሉ ተማሪዎች ማን እንደሚወድቅና ማን እንደሚልፍ፡ ከፈተናው በፊት በማርክ መስጫ ሊስቱ ላይ ስማቸውን ቢዘግብና፡ ከፈተናውም በኋላ የተማሪዎቹ ውጤት ሲታይ መምህሩ አስቀድሞ በመዝገቡ ላይ ካሰፈረው ጋር አንድ አይነት ሆኖ ቢገኝ፡ ተማሪዎች በመምህሩ ብስለትና የተማሪዎቹን ጉብዝናና ስንፍና ለይቶ በማወቁ ይደነቁበታል እንጂ፡ የወደቁት ተማሪዎች፡- መምህራችን አስቀድሞ በመዝገቡ ላይ ትወድቃላችሁ ብሎ ባይጽፍብን ኖሮ አንወድቅም ነበር! ብለው ስሞታ አያቀርቡበትም፡፡ እነሱ የወደቁት በስንፍናቸው ነው፡፡ ደግሞም መምህሩ ማን ማን እንደሚወድቅ መች ነገራቸውና!!
እንግዲህ የመምህሩ ግምት ሰው ነውና ሊሳሳት ከመቻሉ ጋር ተማሪዎቹን ከመፈተኑ በፊት ሰነፉና ጎበዙን ቀድሞ መለየቱ የሚያስደንቀው ከሆነ፡ ፈጽሞ ስህተትና መርሳት የማይጠጋው ሁሉን ዐዋቂ የሆነው አላህ ዓለማትን ከመፍጠሩ በፊት፡ ወደፊት የሚመጡት የሱ ባሮች በተሰጣቸው ነጻ ፈቃድ ምን ሊሰሩ እንደሚችሉና ውጤቱም ምን እንደሆነ አስቀድሞ ቢወስንና፡ ዛሬ ላይም የኛ ሁኔታ እሱ ቀድሞ ከወሰነውና ከጻፈው ነገር የትንኝ ክንፍ ያህል እንኳ ልዩነት ባይኖረው፡ ጌታችን ሆይ! ጥራት ይገባህ! አንተ ሁሉን ዐዋቂ አምላክ ነህ! ብለን በዕውቀቱ መደነቅ ሲገባን፡ ጥፋት እንሰራና ነገ እንዳንጠየቅ፡- ቀድመህ ባትጽፍብን ኖሮ ይህን ጥፋት እኛ አንሰራውም ነበር! ማለት አግባብ ነውን? ይህን ኃጢአት ከመስራትህ በፊት እንደተጻፈብህ ተነግሮህ ነበርን? ለምን ይዋሻል?
” مَا أَصَابَ مِنْ مُصِيبَةٍ فِي الْأَرْضِ وَلَا فِي أَنْفُسِكُمْ إِلَّا فِي كِتَابٍ مِنْ قَبْلِ أَنْ نَبْرَأَهَا إِنَّ ذَلِكَ عَلَى اللَّهِ يَسِيرٌ * لِكَيْلَا تَأْسَوْا عَلَى مَا فَاتَكُمْ وَلَا تَفْرَحُوا بِمَا آتَاكُمْ وَاللَّهُ لَا يُحِبُّ كُلَّ مُخْتَالٍ فَخُورٍ ” سورة الحديد 23-22
“በምድርም በነፍሶቻችሁም መከራ (ማንንም) አትነካም ሳንፈጥራት በፊት በመጽሐፍ የተመዘገበች ብትሆን እንጅ፤ ይህ በአላህ ላይ ገር ነው። (ይህ ማሳወቃችን) ባመለጣችሁ ጸጋ ላይ እንዳታዝኑ አላህም በሰጣችሁ ነገር (በት ዕቢት) እንዳትደሰቱ ነው፤ አላህም ኩራተኛን ጉረኛን ሰው አይወድም።” (ሱረቱል ሐዲድ 57፡22-23)
በዚህ አንቀጽ መሰረት፡- ጌታ አላህ በኛ ላይ የሚደርሱብንም ሆነ የሚደርሱን ነገራት ሁሉ ቀድመው በመጽሐፍ ላይ ያሉና የነበሩ ቢሆኑ እንጂ፡ ሌላ እንዳልሆኑ የሚገልጽልን፡ ወሰን በማለፍ ድንበር እንዳንጥስ ነው፡፡ እሱም፡- መልካም ነገር ሲገጥመን የአላህ ራሕመት መሆኑን አውቀን እንድናመሰግን እንጂ፡ በዕውቀቴና በዘሬ ነው ያገኘሁት እያልን እንዳንንጠባረር፣ ያመለጠን ጸጋ ካለ ደግሞ፡ ለኸይርና ለፈተና ነው ብለን እራሳችንን ለትእግስት እንድናዘጋጅና፡ ዕድለ ቢስነቴ ነው እንዲህ የሚያረገኝ ብለን ተስፋ ወደ መቁረጥ ስሜት እንዳንጓዝ ለመርዳት ነው፡፡ (ተፍሲር በሕሩል-ሙሒጥ፡ አቡ-ሓይያን አል-አንደሉሲይ)፡፡
عن ابن عباس عن النبي صلى الله عليه وسلم قال : وَاعْلَمْ أَنَّ الأُمَّةَ لَوْ اجْتَمَعَتْ عَلَى أَنْ يَنْفَعُوكَ بِشَيْءٍ لَمْ

يَنْفَعُوكَ إِلاَّ بِشَيْءٍ قَدْ كَتَبَهُ اللَّهُ لَكَ ، وَلَوْ اجْتَمَعُوا عَلَى أَنْ يَضُرُّوكَ بِشَيْءٍ لَمْ يَضُرُّوكَ إِلاَّ بِشَيْءٍ قَدْ كَتَبَهُ اللَّهُ عَلَيْكَ ، رُفِعَتِ الأَقْلاَمُ وَجَفَّتْ الصُّحُفُ ) .رواه الترمذي 2516 ) وصححه الألباني في ” صحيح الترمذي ” .
ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “…ህዝቦች አንተን ለመጥቀም አስበው ቢሰባሰቡ፡ አላህ አስቀድሞ ተጠቀም በማለት ላንተ የጻፈልህን ካልሆነ በስተቀር በምንም ነገር ሊጠቅሙህ አይችሉም፡፡ ህዝቦች አንተን ለመጉዳት ቢሰባሰቡ፡ አላህ አስቀድሞ ባንተ ላይ የጻፈብህን ካልሆነ በስተቀር በምንም ነገር ሊጎዱህ አይችሉም…” (ቲርሚዚይ 2516)፡፡
በዚህ መልኩ በመግለጽ በዚህ ዓለም ላይ የሚከሰት ነገር በጠቅላላ ቀድሞ የተጻፈ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ሙስሊም የሆነ ሰውም የአላህ ፈቃድ ካልታከለበት፡ የሰው ሀሳብና ምኞት ብቻውን ምንም ሊያመጣ እንደማይችል ከተረዳ፡ ለጌታው ያለው ከበሬታ ይጨምራል፡፡ ከፍጡራን ላይ ያለው የፍርሀት ቀንበር ይነሳለታል፡፡
ታዲያ አስቀድሞ ተጽፏል መባሉ፡- የአላህን ሁሉን ዐዋቂነት፣ ባሮቹንም ከተስፋ ቢስነትና ከትእቢት ስሜት ጠባቂነት፣ እንዲሁም የሱን የበላይ ተቆታጣሪነት ከመግለጽ ውጪ፡ የሰው ልጅ ነጻ ፈቃድ የሌለው ፍጡር መሆኑን ይጠቁማል ብለን ማሰብ እንችላለንን?
4/ እንግዲውስ ነገሩ እንደዛ ከሆነ ሁሉም ነገር በኛ ምርጫ ብቻ ነው የሚሆነው ማለት ነውን? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ የዚህን ምላሽ በቀጣይ ክፍል ይቀርባል ኢንሻአላህ፡፡
ወአኺሩ ዳዕዋና ዐሊል-ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡