ጽዮን ጽላት ዘ አክሱም
የኣጼዎች ተረት- ሬትና ገተት

ሼር ያድርጉ
539 Views
ክፍል አንድ ኢሊያስ ማሕሙድ በኣላህ ስም እጅግ አዛኝ እጅግ ሩህሩህ በኾነው እንጀምርና በመቀምቀሚያው ዘመን በተላኩ ነቢይ ሙሓመድ (ሠ) ላይ የኣላህ ሰላምና እዝነት ይውረድ ብለን እንቀጥላለን፡፡ ወዳጄ እኔ “ተረት ተረት…” ብዬ ጀምርኹ፡፡ እርሶ ከተመቾ “የላም -በረት” ወይም “ኩበት” ብለው ይቀጥሉ፡፡ ከኛ የዘመን ጫፍ ቁልቁል ተወርውረን ወደ አጼዎቻችን ድፍርስ የታሪክ-ጅረት ገብተን ስንቦራጨቅ፤ የዛሬዎቹ የፓስተሮቻችን ነጠላ ዜማዎች በሌላ ቨርዥን ሲቀኙ እንሰማለን-“ጽዮን ጽላት-ወ-ቅድስት ምድር” በሚል!!! የፓስተሮቻችንን በመንፈስ ስም የሚረገጥ ዳንኪራ፤ አጋንንት እንደሚያቀባዥሩት እብድ ትርጉም አልባ ጓጎራና ልፍፍ፤ የመድረክ ላይ ሩጫና “አስረሽ-ምችውን”ለጊዜው እናቆየውና የኣጼዎቹን ተረት እስኪ አብረን እንውረደው፡- ድሮ ነው አሉ አንዲት የሳባውያን ንግስት (የኣቢሲኒያ አለመኾኗን ልብ ይሏል!) ስለ “ጠቢቡ” ሰለሞን ምትሃታዊ የአስተዳደር ብቃት፤ አንደበት-ርቱእነትና እንቆቅልሽ ኣዋቂነት ሰማች፡፡ ከአንደበቱ የደጋ-ማር እንደሚቆረጥ፤ ገድሉን የሰሙ መበለታትም ኾኑ ልጃገረዶች፤ ባልትዳሮችም ባሎቻቸውን ከቤት አኑረው ከሩቁ በምናብ በአፉ መሳም ይሳመኝ…ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ መልካም ነውና እያሉ እንደ አዜሙለት፤ ስለ መልከጸዴቅነቱ እንስታት እንደተቀኙ፤ ስለወንድነቱ አንሶላ የተጋፈፉ ሳይኾን ባሻጋሪ የሰሙ ኮረዳዎችም፤ሳዱላዎችም መብለታትም ጭምር በምናብ ከርሱ ጋር ጎጆ እንደወጡ፤በውበቱ መላእክትም ጭምር እንደተንበረከኩ፤እስራኤላዊ እንስቶች ሁሉ ከሱ ውጪ ላሳር በሚል ከባል እንደተከለከሉ….ሌላም ሌላም ሰማች፡፡ ሰማችናም በልቧ ያንን ድንቅ የወንዶች ፈርጥ በኣይኗ ለማየት፤አፏን ከፍታ ለማውራት ቆረጠች፡፡ ግመሎቿንም በእጅ መንሻዎች አጭቃ ከአሽከሯ ጋር ፊቷን ወደ ፍልስጤም ምድር አዞረች፡፡ ከረዥም ጉዞ በኋላ ከዚያ ስሙ ከአድማስ ባሻገር ከተሰማው፤ተራራዎች ከሰበኩለት፤ በጉዞዋ እያሰላሰለችው ከነበረው ንጉሰ-ነገስት ዘ-ዓለም ፊት ደረሰች፡፡ እጅ መንሻዎቿን ከፊት ለፊቱ ዘርግፋ ማንነቷን አስተዋወቀች፡፡ ጠቢቡም ለርሷና ለአሽከሮቿ “ታላቅ” ግብዣን አደረገ-ጨው የበዛበት ምግብ!!! ንግስቲቱ ጉዞ ያዳከመው ወገቧን ከተዘጋጀላት መኝታ ቤት ከማሳረፏ በፊት “ጎረምሳው” ንጉሱ ሰለሞን የ“አንሶላ እንጋፈፍ” ጥያቄ አቀረበ፡፡ እሷም በሀገሯ ልጀገረድ እንጂ እንደማይነግስ አስረድታው የሞቀ ስጋው ላይ ውኃ ከለሰችበት፡፡ የንግስቲቱ አሻፈረኝ ማለት ምን ሊረባ!!! ያ ከእግዚኣብሄር “በተገለጠለት” ጥበብ አማካኝነት የወጠወጠውና ያበሰለው ጨው የበዛበት ምግብ ስራውን ሰራ፤ንግስቲቱ ሌሊቱን ውኃ ጥም ያቃጥላት ጀመር፡፡ ከዚያም አሽከሯን ቀስቅሳ “ውኃ ጥም አቃጥሎኛልና ከኣንዳች ስፍራ ለመፈለግ ከመነሳቴ በፊት የንጉሱን መተኛት አስረግጭልኝ …” አለቻት፡፡ አሽከሪቱም ወጣ ብላ ሰለል… ሰለል… ስታደርግ ጎረምሳው “ጠቢቡ ሰለሞን” አገኛትና አወቃት( ደረሰባት)፡፡ አሸከሪቱ የምንተ እፍረቷን ምንም ሳትተነፍስ ከመኝታዋ ተመለሰች፡፡ ንግስቲቱም በራሷ ውኃ መፈለግ እንዳለባት ተረዳች፡፡ ተረዳችናም ውኃ ላገኝ እችላለኹ ብላ በምታስብባቸው አቅጣጫዎች ውርውር ስትል አድፍጦ ይጠባበቅ የነበረው “የነገስታት ንጉስ የልሂቃን ሁሉ ልሂቅ” ሰለሞን አፈፍ አረገና ….የኾነው ኾነ፡፡ ወዳጄ እዚህ ጋር ቆም ይበሉና “ ጨው የበዛበት ምግብ” የሚለውን ሃረግ ያስምሩበት፡፡ በዘመኑ የነበረውን ስልጣኔ ይመራ ከነበረ ከዘመናት የታሪክ ማማ ጫፍ ተሰቅሎ እስከ አሁንም ካልወረደ ከታላቁ ንጉስ ቤተ-መንግስት እንግዳ ኾና ለተጣደች ንግስት የዚህ ዓይነት አቀባበል ተደረገ ብሎ ይታሰባልን? እንደኔ ግምት ሰለሞን ፈጽሞት አይደለም ካሰበው እንኳ ያለምንም ቅድሚያ መንደርደሪያ ታላቅነቱን በዜሮ አባዝቶ ለዜሮ ያካፍለዋል፡፡ ሰለሞን ጨው የበዛበት ምግብ የማስበላቱ ምክንያት ሴቶቹን በውድቅት ለሊት ያለምንም ገላጋይ ለማግኘት እንደኾነ ልብ ይሏል፡፡ ግን ደግሞ ሰለሞንን በዘመኑ የነበሩ ሴቶች በስጋም በመንፈስም እንዳካበቡት ስንረዳ፤ ኹሉ በጁ ኹሉ በደጁ የነበረ ሰው ስጋው ስጋ አጥቶ የዚህ ዓይነት ቀመር አልባ ድመራና ቅነሳ ብሎም ፍጹም አለሌኣዊ ምግባር ውስጥ ይገባል ብሎ ማሰብ ክፉ ስህተት ነው፡፡ቀንድ ያወጣ ውሸት!!!ከኣንድ ሺህ ሴቶች ጋር የሚኖር ኣንድ ወንድ፤ ሴት ኣጣኹ ብሎ እንግዶች ላይ እንደ ኮርማ ከብት “ቄብ” ኣለ ማለት ለጆሮም ይከብዳል፡፡ ይቀፋልም፡፡!!! በስተመጨረሻ ንግስቲቱና አሸከሪቱ ከህልማቸው ወንድ “ወኔ” ቀድተው…ከወራት በኋላ የጉዟቸውን “ትሩፋት” ወንድ ልጆችን በመታቀፍ አከበሩ፡፡ ልጆቹም አደጉ…፤አባታችንን አሳዩን ብለው እናቶቻቸውንም ጠየቁ…፤ እናቶቻቸውም የኣባታቸውን ምስል አስይዘው ወደ እየሩሳሌም ሰደዷቸው፡፡ ሰለሞንም “አባታችንን ኣሳዩን” ሚሉ ብላቴኖች ወደ መንግስቱ እንደዘለቁ ሲሳማ የበለጠ ብልኹን ልጅ ለመለየት ከተራ ሰዎች መካከል ተቀላቀለ፡፡ አንደኛው ልጅ አንዱን ግለሰብ “ኣባቴ ይህ ነው” በማለት ሳመው፤ አባቱ ያልኾነውን -ነው በማለቱ “ዛጉዌ” ተባለ- ያዘገመ እንደማለት፡፡ ኹለተኛውም ልጅ በፊናው ኣባቱ ሰለሞንን ከሰዎች መካከል ለይቶ “ይህ አባቴ ነው” በማለት ሳመው፡፡ አባቱም “ምን-ትልክ” ኣለው… ወዳጄ አሁን ደግሞ የልጆቹ ስያሜ ላይ ቀይ መስመር ያስምሩና “ለመኾኑ አማርኛ እንደ ቋንቋ በሰለሞን ዘመን ነበርን? ሰለሞንስ ኣማርኛን ይናገር ነበርን? ብለው ይጠይቁ… ሕሊናዎ መልሱን በቅጽበት ይነግሮታል፡፡ ወደ ክርስትያኖቹ መጽሐፍ ዘገደው ብለን ስንገባ መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 10/1 መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 9/1መጽሐፈ ኢዮብ“ 1/15 ላይ ሴቲቱ የሳባውያን ንግስት እንደኾነችና (የኢትዮጵያ ንግስት እንዳልኾነችና ስሟም ሳባ እንዳልነበር ልብ ይሏል) ወደ ሰለሞንም እንቆቅልሽ ልትጠይቀው እንደኼደች፤ በኋላም በጥበቡ ተደንቃ እንደተመለሰች ብቻ ይጠቅሳል፡፡ ከርሱ ወልዳ በነበረ ኖሮ የኣባቱን የዳዊትን፤የነኖህን…የሌሎችንም “ምርጥ ምርጥ” የዝሙት ትርከቶችን ልክ እንደ ጋሽ ስብኃት “ትኩሳት” ልብ-ወለድ እንደወረደ የነገረን ክርስትያናዊው መጽሐፍ የ”ሰለሞንን” የሸፍጥ ስራ እንደማይዘለው እሙን ነው፡፡ ስለሚያስተምር -ስላቅiii
ከዚያስ?… ከዚያማ ልጆቹ በኣባታቸው ፊት አደጉ ወደ “አጋራቸው” ኢትዮጵያም ሊመለሱ ወደዱ፤…ሲመለሱም ለሙሴ ተሰጥቶ ከነበሩት የ”ማርያም”ና የ”ሚካኤል” ጽላት አንዱን -የ”ሚካኤልን”- ይዘው ከኣሽከሮች ጋር ቀይ ባህርን ይሻገሩ ዘንድ የሰለሞን በጎ ፈቃድ ኾነ፡፡ ኾኖም ግን ከተጓዦቹ አንዱ በ”ሚካኤል” ጽላት ፈንታ የ”ማርያምን” ቀይሮ በማርያም ጽላት ቦታ የሚካኤልን አኖረ፡፡ የ”ማርያምን” ጽላት ተሸክመው ቀይ ባህርን እንደተሻገሩ በእየሩሳሌም ታላቅ ነውጥ ኾነ፡፡ ሰለሞንና ባለሟሎቹ ምክንያቱን ሲመረምሩ የ”ማርያም” ጽላት እንደተሰረቀ በቦታውም የ”ሚካኤል” እንደተኖረ አወቁ ፡፡ ምን-ይልክና ዛጉዌ ከነአሽከሮቻቸው ቀይ ባህርን ተሻግረው ስለነበር ሰለሞን “አትመልሷቸው …ጽላቱም ከነሱ ጋር ይኹን” ብሎ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ የጽዮን ጽላትም በዚህ መልኩ ወደ “ተስፋይቷ” ምድር ኢትዮጵያ ገባ፡፡ ወዳጄ እስኪ ደግመን ክርስትያናዊውን መጽሐፍ ዋቢ እናድርግ-መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ ምዕራፍ 35ን ስናነብ የሙሴ ጽላት ከሰለሞን በኋላ አስራ ስምንተኛ የእስራኤል ንጉስ ኾኖ እስከ ነገሰው እዮስያስ ዘመነ ስልጣን ድረስ በእስራኤል ምድር እንደነበር እንረዳለን፡፡ ኦሪትንም ስናነብ በሚካኤልም ኾነ በማርያም ስም ለሙሴ የተሰጠ ጽላት እንደሌለ እንረዳለን፡፡ አጼዎቻችን በህልም ዘርተው፣ በህልም አጭደው፣ በህልም ፈጭተውና ጋግረው በህልም ያከፋፈሉት የ”ጽዮን ጽላት” የህልም እንጀራ-ታሪክ ይሕ ነው፡፡ ፈጽሞ ከክርስትያኑ መጽሐፍ ጋር እንደሚጋጭና ኹሉም አጼዎች የፈጠሩት ተራ ውሸት እንደኾነ ይረዷል፡፡ ክፍል ኹለትን እንቀጥላለን!!!
ቸር እንሰንብት