ጨረቃ በኢስላም – ክፍል አንድ


ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣


ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
በዚህ ምድር ላይ ፍጹም አንድ አምላክ ብቻ መኖሩን የሚያውጅ ሃይማኖት ቢኖር ኢስላም ብቻ ነው!!፡፡

ፍጹም አንድ አምላክ ማለት፡- በህላዌው ሳይከፋፈል፣ በስራው አጋዥና አማካሪ ሳይኖረው፣ በባሕሪያቱ ሞክሼና ቢጤ ሳይገኝለት፣ በአምልኮም ተጋሪ ሳይበጅለት ብቻውን በአንድነቱ የሚመለክ፡ በእሱነቱ የሚሰበክ፡ በአንተነቱ የሚለመን፡ በእኔነቱ እራሱን የሚገልጥ፡ በእኛነቱ ታላቅነቱን የሚያሳይ አምላክ ማለት ነው፡፡ ታዲያ ይህን እውነተኛ አምላክ በዚህ መልክ የሚያመልክ ከሙስሊሞች ውጭ የት ይገኝ ይሆን? አልሐምዱ ሊላህ አለዚ-ሀዳና ሊል-ኢስላም፡፡

ናቸው! ተብሎ የሚነገርለት አምላክ የለም፡፡ እነሱ ተብሎ አይሰበክምና፡፡ በአንድነቱ ውስጥ ልይዩ ሶስትነት የሚል የ21ኛ ክፍለ ዘመን ፍልስፍናም የለም፡፡ ሶስት ነኝ ብሎ እራሱን አላስተዋወቀምና፡፡ ምስል ተሰርቶለት ነጭ ሽበት ያለው ጢም ፊቱ ላይ በቅሎ፡ ከቀኝና ከግራው እሱን የሚመስሉ ሁለት ቢጤዎች ተደርድረውለት፡ ይህ ነው አምላካችን አይባልም፡፡ እሱ አምሳያና ብጤ የለውምና፡፡

ይህ እውነተኛ አምላክ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነው፡፡ በቅዱስ ቃሉም ሲናገር እንዲህ ነው ያለው፡-
“ይህ ጌታችሁ አላህ ነው፡፡ ከእርሱ በቀር አምላክ የለም፡፡ ነገርን ሁሉ ፈጣሪ ነው፡፡ ስለዚህ ተገዙት፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ተጠባባቂ ነው፡፡” (ሱረቱል አንዓም 102)፡፡

“የሰማያትና የምድር ጌታ ማን ነው? በላቸው፤ አላህ ነው በል፤ ለነፍሶቻቸው ጥቅምንም ጉዳትንም የማይችሉን ረዳቶች ከርሱ ሌላ ያዛችሁን? በላቸው፤ ዕውርና የሚያይ ይተካከላሉን? ወይስ ጨለማዎችና ብርሃን ይተካከላሉን? ወይስ ለአላህ እንደርሱ አፈጣጠር የፈጠሩን ተጋሪዎች አደረጉለትና ፍጥረቱ በነሱ ላይ ተመሳሰለባቸውን? በል፤ አላህ ሁለመናውን ፈጣሪ ነው፤ እርሱም አንዱ አሸናፊው ነው በል።” (ሱረቱ-ረዕድ 16)፡፡

“አላህ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው። እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ አስተናባሪ ነው።” (ሱረቱ-ዙመር 62)፡፡
“ይሃችሁ፣ ጌታችሁ አላህ ነው፤ የነገር ሁሉ ፈጣሪ ነው፤ ከርሱ ሌላ አምላክ የለም፤ ታዲያ (ከእምነት) ወዴት ትመለሳላችሁ።” (ሱረቱ ጋፊር 62)፡፡

በአራቱም አምላካዊ ጥቅሶች መሰረት ጌታ አላህ የ‹ሁሉ ነገር› ፈጣሪ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ እንግዲያውስ ዛሬ የምንነጋገርበት አጀንዳ፡ ከነዚህ ‹ሁሉ› ተብለው በጌታችን ከተጠሩ ፍጥረቶቹ ውስጥ አንዱ የሆነውን ጨረቃን በማስመልከት ይሆናል፡፡

ይህንን ለመጻፍ ያነሳሳኝ ከካፊሮች በኩል የተነሳን ጥያቄ አንብቤ ነው፡፡ ሙስሊሞች የምታመልኩት የጨረቃ አምላክን ነው፡፡ በመስጂዳችሁም የሰቀላችሁት ለዚህ ነው፡፡ የጨረቃ አምላክ የሚባለው ደግሞ ከፀሀይ አምላክ ጋር በመጋባት ሴት ከዋክብቶችን ወልዷል የሚል እንቶ ፈንቶ በማየቴ ነው፡፡


ከሁሉም የሚገርመኝ፡- እራሱን ከክህደት ያላጠራ፡ ሰውና አምላክ ተደባልቆበት ሰውን ከአምላክ መለየት ተስኖት፡ በተዋህዶ ሰው አምላክ ሆነ፣ አምላክም ሰው ሆነ የሚል የህልም ቅዠት ውስጥ የገባ ካፊር፣ አንድን ከሶስት መለየት አቅቶት፡ አንድም ሶስትም ናቸው የሚል ሙሽሪክ፡ እኛን ጨረቃ አምላኪዎች ናችሁ! ማለቱ ነው፡፡
እንደው ምላሹን ከመስጠቴ በፊት አንድ ነገር ልናገር፡-

እውነት ሙስሊሞች የጨረቃ አምላክን የምናመልክ ከሆነ፡ በርግጥም ባለቤቱ የሆነችውን የፀሀይ አምላክንም ማክበር ነበረብን! የተወለዱ ሴት ልጆችዋንም (ከዋክብትን) ልናከብራቸው ይገባ ነበር! ታዲያ የታሉ በመስጂድ ሚናራ ላይ? ለምንስ አብረው አልተሰቀሉም?

This image has an empty alt attribute; its file name is 58f9fe2c0ed2bdaf7c12832e.png

ደግሞስ ምነው ጨረቃና ፀሀይ ሴት ልጆችን ብቻ ወለዱ? ምነው ወንድ ልጅ አንድ እንኳ የላቸውም! ችግሩ ከባልየው ከጨረቃ ነው ወይስ ከሴቲቷ ፀሀይ? (ወደው አይስቁ አሉ)፡፡ ምነው ተረት ተረት ቢቀር!፡፡
ወደ ቁም-ነገሩ ስንገባ ጨረቃ በኢስላም ያለውን ምልከታ በመጠኑ እንዲህ አቀርበዋለሁ፡-

1. የአላህ ፍጡር ነው፡-
ጨረቃ ጌታ አላህ ከፈጠራቸው ፍጡራን መካከል አንዱ ነው፡፡ ከዚህ ፍጥረታዊ ማንነት የዘለለ ሚና የለውም፡-
“እርሱም ሌሊትና ቀንን ፀሐይንና ጨረቃንም፣ የፈጠረ ነው፤ ሁሉም በፈለካቸው ውስጥ ይዋኛሉ።” (ሱረቱል አንቢያእ 33)፡፡
“ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ ፀሐይንና ጨረቃንም የገራ ማን እንደሆነ ብትጠይቃቸው በእርግጥ አላህ ነው ይሉሃል፤ ታዲያ እንዴት ይመለሳሉ!።” (ሱረቱል ዐንከቡት 61)፡፡

2. ለፈጠረው የሚሰግድ ነው፡-
ጨረቃም እንደሌሎች ፍጥረታት (ፀሀይ፣ ሰማይ፣ ምድር…) ለአምላኩ የሚሰግድ ነው፡-
“አላህ፣ በሰማያት ያለው ሁሉ፣ በምድርም ያለው ሁሉ ፀሐይና ጨረቃም፣ ክዋክብትም፣ ተራራዎችም፣ ዛፎችም፣ ተንቀሳቃሾችም፣ ከሰዎች ብዙዎችም ለርሱ የሚሰግዱለት መኾኑን አታውቁምን? ብዙውም በርሱ ላይ ቅጣት ተረጋገጠበት፤ አላህ የሚያዋርደው ሰው ለርሱ ምንም አክባሪ የለውም፤ አላህ የሻውን ይሠራልና።” (ሱረቱል ሐጅ 18)፡፡
“ሰባቱ ሰማያትና ምድርም በውስጣቸውም ያለው ሁሉ ለርሱ ያጠራሉ፣ ከነገርም ሁሉ ከማመስገን ጋር የሚያጠራው እንጂ አንድም የለም፤ ግን ማጥራታቸውን (እንዴት እንደሆነ) አታውቁትም፤ እርሱ ታጋሽ መሐሪ ነው።” (ሱረቱል ኢስራእ 44)፡፡
3. በአላህ ፈቃድ ስር የተገራ ነው፡-

ጨረቃ እንደሌሎቹ የአላህ ፍጥረታት በአላህ ፈቃድ ስር የተገራ ነው፡፡ ከቁጥጥሩ አይወጣም፡፡ ያለ ፈቃዱ አይንቀሳቀስም፡-
“ለናንተም ሌሊትንና ቀንን ፀሐይንና ጨረቃንም ገራላችሁ፤ ክዋክብትም በፈቃዱ የተገሩ ናቸው፤ በዚህ ውስጥ ለሚያውቁ ሕዝቦች በእርግጥ ታምራቶች አሉ።” (ሱረቱ-ነሕል 12)፡፡
“አላህ ሌሊትን በቀን ውስጥ የሚያስገባ ቀንንም በሌሊት ውስጥ የሚያስገባ፣ ፀሐይንና ጨረቃን የገራ፣ መኾኑን አታይምን? ሁሉም እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ይሮጣሉ፤ አላህም በምትሰሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው።”                   (ሱረቱ ሉቅማን 29)፡፡ በተጨማሪም፡- አል-አዕራፍ 54፣ አር-ረዕድ 2፣ ኢብራሂም 33፣ ፋጢር 13፣ አዝ-ዙመር 5 ይመልከቱ፡፡

4. የጊዜ ማወቂያ ምልክት ነው
አላህ ጨረቃን የጊዜ ማወቂያ፡ የወራትና የአመታት መቁጠሪያ ምልክት አድርጎታል፡-
“(ሙሐመድ ሆይ!) ከለጋ ጨረቃዎች (መለዋወጥ) ይጠየቁሃል፡፡ እነርሱ ለሰዎች ጥቅም ለሐጅም (ማወቂያ) ጊዜያቶች (ምልክቶች) ናቸው በላቸው…” (ሱረቱል በቀራህ 189)፡፡
“እርሱም ጎህን (ከሌሊት ጨለማ) ፈልቃቂ ሌሊትንም ማረፊያ ፀሐይንና ጨረቃንም (ለጊዜ) መቁጠሪያ አድራጊ ነው፡፡ ይህ የአሸናፊው የዐዋቂው (አላህ) ችሎታ ነው፡፡” (ሱረቱል አንዓም 96)፡፡

5. በፍጹም ሊመለክ አይገባውም፡-
ጨረቃ የአላህ ፍጥረት በመሆኑ፡ በፍጹም ስግደትም ሆነ ማንኛውም አይነት አምልኮ አይገባውም፡-
“ሌሊትና ቀንም፣ ጸሐይና ጨረቃም፣ ከምልክቶቹ ናቸው፤ ለፀሐይና ለጨረቃ አትስገዱ፤ ለዚያም ለፈጠራቸው አላህ ሰገዱ፤ እርሱን ብቻ የምትግገዙ እንደሆናችሁ፣ (ለሌላ አትስገዱ)” (ሱረቱ ፋሲለት 37)፡፡
እኛ ሙስሊሞች ስለ ጨረቃ ያለን አመለካከት ከሞላ ጎደል ይህን ይመስላል፡፡ ለጨረቃም ሆነ ለኢየሱስ አንሰግድም አንንበረከክም፡፡ ባይሆን ሁለቱን ለፈጠረው ጌታ አላህ እንጂ!!፡፡

የመስጂድ ምልክት፡-
ከከሀዲያን በኩል የሚነሳው ጥያቄ ይህ ነው፡፡ እናንተ ሙስሊሞች ጨረቃን የማታመልኩ ከሆነ ለምን በመስጂድ መናራህ ላይ ተከላችሁት ታዲያ? የሚል ነው፡፡ ይህ ጥያቄ በራሱ እነሱ በአምልኮ ቦታቸው ላይ የሰቀሉትን መስቀል እንደሚያመልኩ በግልፅ ያሳያል፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ከኛው ጋር ተመሳስሎባቸው መች ለጥያቄ ይጋበዙ ነበር!! ለነገሩ ‹መስቀል ኃይላችን ነው!› ሲሉ አይደል የሚደመጡት፡፡

ወደኛ ጉዳይ ስንመለስ ግን፡ የሙስሊሞች የአምልኮ ስፍራ ወይም መስጂድ ከጨረቃ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም፡፡ በመናራዎቹም ላይ ጨረቃን እንደ ምልክት ማንጠልጠሉ ሃይማኖታዊ መሰረት የለውም፡፡ ይህ ድርጊት ዘግይቶ የመጣ ነው፡፡ በነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ዘመን፣ በሶሓቦች ዘመን፣ በታቢዒዮች ዘመን አይታወቅም፡፡ ከብዙ መቶ አመት በኋላ ዘግይቶ የመጣ ነው፡፡ በዑሥማኒያዎች ስርወ መንግስት ዘመን፡ ኢስላም አድማሱን አስፍቶ የክህደት ኃይላትን አንበርክኮ በተቆጣጠራቸው ሀገራት ላይ የአምልኮ ቦታቸው አናት ላይ መስቀልን ሲያስቀምጡ በመመልከት፡ የነሱን እውነተኛ አምልኮ ስፍራ (መስጂድ) ከከሀዲያን ጋር እንዳይመሳሰል በሚል የጨረቃን ምልክት እንዳደረጉ ጸሀፍት ይገልጻሉ፡፡ እንዲሁም ይህን ምልክት ፋርሶች ናቸው የጀመሩት፡ አይደለም አፍሪካኖች ናቸው የሚል ሀሳብም አልለ (ዐብዱል-ሐይ አል-ከታኒ፡- አት-ተራቲቡል ኢዳሪየህ 1/320)፡፡

ያም ሆነ ይህ ጉዳዩ ከአምልኮ ጋር የተያያዘ ሳይሆን፡ የአላህን ቤቶች (መስጂድ) ከጣኦት አምልኮ ስፍራዎች ለመለየት እንደ-ምልክትነት የተገለገሉበት በመሆኑ፡ በኢስላም ሊቃውንት ዘንድም ውግዘት አልገጠመውም፡፡ ስለሆነም እኛ የምናመልከው የጨረቃ ፈጣሪና አስገኚ የሆነውን አላህ እንጂ፡ የተፈጠረውን ጨረቃ አይደለም፡፡ እናንተም የፈለጋችሁትን አምልኩ፡፡ ውጤቱም የቂም ቀን ይታያል፡-

“አላህን ሃይማኖቴን ለርሱ ያጠራሁ ሆኜ እግገዛዋለሁ በል። ከርሱ ሌላ የሻችሁትን ተገዙ፤ ከሳሪዎች ማለት እነዚያ በትንሣኤ ቀን ነፍሶቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ያከሰሩ ናቸው፤ ንቁ፤ ይህ እርሱ ግልጽ ከሳራ ናቸው በላቸው።” (ሱረቱ-ዙመር 14-15)፡፡

(ኡስታዝ አቡ ሀይደር)

ሼር ያድርጉ
  • 1
    Share