ጥፋት ሰርቶ በ”ቀደር” ማሳበብ?

ሼር ያድርጉ
472 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት የአላህ ባሮች ይሁን፡፡

ሰሞኑን በተደጋጋሚ ከሙስሊም ወንድሞቼ በኩል በኢንቦክስ አንድ ጥያቄ መጥቶልኝ ነበር፡፡ ጥያቄውም የአደምና የሙሳን (ዐለይሂማ-ሰላም) የቃል ምልልስ መሰረት ያደረገውን ሐዲሥ በመጠቅሰ ነበር፡፡ እናም ይህን ሐዲሥ በመጥቀስ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ በማለት ጥያቄ ያቀርባሉ፡- ሰው የሚሰራው ነገር ሁሉ (ኸይርም ሆነ ሸር) ቀድሞ የተጻፈ ከሆነ፡ ምኑን ነጻ ፈቃድ አለው ማለት ይቻላል? አደምስ (ዐለይሂ-ሰላም) ሙሳን (ዐለይሂ-ሰላም) የረታው በቀደር አሳብቦ አይደል? እኛስ ለጥፋታችን ቀዳ ወል-ቀደርን ማሳበብ አንችልም? የሚል ነው፡፡
እንደ-ምክንያት የተጠቀሰውን ሐዲሥ አቅርቤ ምላሽ ከመስጠቴ በፊት የተወሰኑ ነጥቦችን መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ ከዚያም ወደ ሐዲሡ እመለሳለሁ ኢንሻአላህ፡-

1ኛ. ፈጣሪ አምላካችን አላሁ ሱብሐነሁ ወተዓላ፡ ምድራዊ ሲሳያችንን (ሪዝቃችንን) ቀድሞ በማኅጸን ሳለን ወስኖታል፡፡ እሱ በወሰነውና ባወቀው ልክም የተገደበ ነው፡፡ ከዚህ ዕውቀቱ ውጪ ሊጨምርም ሆነ ሊቀንስ አይችልም፡፡ ይህም ከመሆኑ ጋር እኛን ደግሞ እንድንሰራ፡ ሪዝቃችንን ለማግኘት ሰበብ በመሆን መንቀሳቀስ እንዳለብን አዝዞናል፡፡
ይኸው አምላካችን አላህ ዕድሜያችንንም (ምድራዊ ቆይታችን) ገና በእናታችን ማኅጸን ፅንስ እያለን፡ ሩሕ (የህይወት መንፈስ) በሚነፋብን ጊዜ ወስኖታል፡፡ የተላከው መልአክም የዕድሜውን ገደብ እንዲጽፍ ታዝዟል፡፡ እንደዛም ሆኖ በህመም ጊዜ መድኃኒት እንድንፈልግ ታዝዘናል፡፡ እራሳችንን ለጉዳትና ለአደጋ ከሚዳርጉ ነገራትም እንድንርቅ ተመክረናል፡፡
በተጨማሪም ኻቲማችንም (ፍጻሜያችን) ቀድሞውኑ አላህ ዘንድ የታወቀና የተወሰነ ነው፡፡ ያም ሆኖ ጌታችን እኛን፡ ከመጥፎ ተግባራት እንድንርቅና በመልካም ስራዎች ላይ እንድንጠናከር አዝዞናል፡፡
አሁን ኃጢአትን እየሰራ ዛሬ በሰው ዘንድ፡ ነጌም በአኼራ አላህ ዘንድ ተወቃሽ ላለመሆን በቀደር ለሚያሳብበው ሰው ይህን ጥያቄ ማቅረብ ይኖርብናል፡- ቀዳ ወል-ቀደርን ለኃጢአትህ ምክንያት የምታደርግ ከሆነ፡ ለምን በሪዝቅህና በዕድሜህ ላይም ምክንያት አታደርገውም? የኑሮን ውጣ ውረድ ለማሸነፍ፡ ድኅነትን በሐብት ለመለወጥ ደፋ ቀና ማለቱ ለምን አስፈለገ? ያንተ ደኃ መሆን ቀደር አልነበረም እንዴ? እንዲሁም ስትታመም ወደ ፋርማሲ እና ክሊኒክ መድኃኒት ፍለጋ መሄዱ ለምን አስፈለግ? የታመምከውስ በቀደር አይደለምን? ስለዚህ ለመጣብህ ድኅነት እና ለያዘህ በሽታ እጅ ሰጥተህ ለምን አትቀመጥም? አይ! ምንም ቀዳ ወል-ቀደር ቢሆንም ሰበቡን አድርሼ ድኅነቱን በሐብት፡ በሽታውን በጤና ለመለወጥ እታገላለሁ የምትል ከሆነ፡ ለምን ኃጢአት በሰራህ ጊዜስ ነጌ በአኼራ እንዳትዋረድ ተውበት በማድረግ እና በምትኩ መልካም ስራን በመስራት እራስህን ለመቀየር ለምን አትነሳም? ቀደር ከሆነ ሁሉም ቀደር ነው፡፡ አንዱን ከሌላው ምን ለየው?

2ኛ. አሁንም በድጋሚ ለሚሰራው የኃጢአት ተግባር ተውበት ከማድረግ ይልቅ ቀደርን የሚያሳብብ ሰው ከራሱ ሃሳብ ጋር የተጋጨ ሰው ነው፡፡ አንድ ወሰን አላፊ የሆነ ሰው፡ በሱ ላይ ድንበር በማለፍ ንብረቱን ቢነጥቀው፣ ደሙን ቢያፈሰው ወይም አደጋ ቢያደርስበትና ከዛም ይህ ወሰን አላፊ ሰው፡- እባክህ እኔን እንዳትወቅሰኝ! ይሄ ሁሉ ባንተ ላይ ወሰን ማለፌ አላህ በኔ ላይ ቀድሞ የወሰነው ቀደር ስለሆነ እንጂ እኔ ፈልጌ ያደረግሁት ነገር አይደለም ቢለው፡ ምክንያቱን ይቀበለዋል ወይስ የበለጠ ያስቆጣዋል? ምክንያቱን እንደማይቀበለው የታወቀ ነው፡፡ ታዲያ እኛም ለዚህ ኃጢአተኛ እንዲህ እንበለው፡- አንተስ ለምን በጌታህ ትእዛዝ ላይ አምጸህ፡ የከለከለህን ተዳፍረህ ወሰን በማለፍ ኃጢአት ላይ ስትዘፈቅ ቀደርን የምታሳብብ ከሆነ፡ እንዴት ሌላው ሰው ደግሞ ባንተና በንብረትህ ላይ ወሰን ሲያልፍብህ እሱም ቀደር ነው ብለህ አልተቀበልክም? ለራስህ ጊዜ የጌታህን ድንበር ስትጥስ የተጠቀምከውን ቀደር፡ ለሰዉ ጊዜ ባንተ ላይ ወሰን ሲያልፍብህ፡ እሱም ቀደር ነው ብለህ ካልተጠቀምከው ከራስህ ጋር መጋጨት አይሆንብህም? ሰውየው ንብረቴን የቀማኝ፡ እኔንም የጎዳኝ በፈቃዱ እንጂ ተገዶ አይደለም ካልክ፡ አንተም እኮ ኃጢአት የሰራኸው ፈልገህና ፈቅደህ እንጂ ተገደህ እኮ አይደለም፡፡ ስለዚህ ንብረትህን ከዘራፊ ለመጠበቅና ከተወሰደም ለማስመለስ ጥረት የምታደርገውን ያህል፡ ኃጢአት ላይ ስትወድቅም በተውበት ወደ መጀመሪያው ማንነትህ ለመመለስ ጥረት አድርግ፡፡

3ኛ. ሌላው ለሚሰራ ማንኛውም አይነት ኃጢአት በቀደር ማሳበብ ውጤቱ ለከፋ ግንዛቤ ይዳርጋል፡፡ እሱም የአላህ ወዳጆችና የሸይጧን ወዳጆችን በእኩል ማየት፡ የጀነት ሰዎችን ከጀሀነም ሰዎች አለማስበለጥ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም መልካም ሰሪዎቹም ሆነ መጥፎ ሰሪዎቹ፡ ስራቸው ቀድሞ በተጻፈው (በተቀደረው) መሰረት እንጂ እነሱ በፈለጉትና ባመነቡት መንገድ አይደለም የሚል መነሻ ስለተያዘ፡፡ ይህ አቋም ደግሞ ስህተት ነው፡፡ አማኞችን ወደ ‹‹ሰዒድ›› (ዘላለማዊ ዕድለኝነት) ያሸጋገራቸው ከጌታቸው ተውፊቅ ጋር በፈቃዳቸው የተገበሩት የእምነታቸውና የመልካም ስራቸው ፍሬ ነው፡፡ ከሀዲዎችን ደግሞ ወደ ‹‹ሸቂይ›› (ዘላለማዊ ክስረት) የዳረጋቸው፡ ከሸይጧን አሳሳችነት ጋር የክፉ ስራቸውና የመጥፎ እምነታቸው ውጤት ነው፡፡

ስለዚህም ቀደርን እያሳበቡ አማኝን ከከሀዲ፡ መልካም ሰሪን ከመጥፎ ሰሪ ጋር ማወዳደር አይሰራም፡፡
” أَفَنَجْعَلُ الْمُسْلِمِينَ كَالْمُجْرِمِينَ * مَا لَكُمْ كَيْفَ تَحْكُمُونَ ” سورة القلم 35-36
“ሙስሊሞቹን እንደ ከሐዲዎች እናደርጋለን? ለናንተ ምን (አስረጅ) አላችሁ? እንዴት ትፈርዳላችሁ።” (ሱረቱል ቀለም 35-36)፡፡
” لَا يَسْتَوِي أَصْحَابُ النَّارِ وَأَصْحَابُ الْجَنَّةِ أَصْحَابُ الْجَنَّةِ هُمُ الْفَائِزُونَ ” سورة الحشر 20
“የእሳት ጓዶችና የገነት ጓዶች አይስተካከሉም፤ የገነት ጓዶች እነሱ ምኞታቸውን አግኚዎች ናቸው።” (ሱረቱል ሐሽር 20)፡፡

4ኛ. ለሚሰራ ኃጢአት ቀደርን እንደ ምክንያት ማቅረብ የሚቻል ቢሆን ኖሮ፡ ከዚህ በፊት አላህ በኃጢአታቸው ሰበብ በቅጣት ያጠፋቸው የነቢያት ህዝቦችም ቀደርን ምክንያት ማድረግ በቻሉ ነበር፡፡ በቅጣት በመጥፋታቸውም ተብደለዋል ማለት ነው፡፡ ጌታ አላህ ግን እንዲህ እያለ፡-
“እኛም አልበደልናቸውም፤ ግን ነፍሶቻቸውን በደሉ…” (ሱረቱ ሁድ 101)፡፡
በኃጢአት የተጨማለቀ ግለሰብ በቀደር ስር ለመሸሸግ መሞከሩ የማይጠቅመው መሃይምነት ነው፡፡ እንደውም ይጎዳዋል፡፡ ሌላ ተጨማሪ ኃጢአት ሆኖም ያስቀጣዋል፡፡

አንድ ሌባ አሚረል ሙእሚኒን ዑመር ኢብኑል-ኸጣብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ዘንድ ተይዞ ቀረበ፡፡ እሳቸውም፡- ለምን ሰረቅህ? ሲሉት፡ አላህ ቀደረው! ብሎ መለሰላቸው፡፡ እሳቸውም፡- 30 አለንጋን ግረፉት፡ ከዚያም እጁን ቁረጡት! በማለት ትእዛዝ ሰጡ፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ተብለው ሲጠየቁም፡- ስለሰረቀ እጁ ይቆረጣል! በአላህም ላይ ስለዋሸ ሰላሳ ይገረፋል! በማለት መለሱ፡፡

ሰለፉ-ሷሊሕ፡ ለሚሰራው አመጽ ቀደርን የሚያሳብብን ሰው በጣም ያወግዙት ነበር፡፡ ብርቱ የሆነ ወቀሳንም ይወቅሱት ነበር፡፡ ይኸው አንዱን ምሳሌ፡-
ሰዎች ወደ ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር (ረዲየላሁ ዐንሁማ) ዘንድ በመምጣት፡- አባ አብዲ-ራሕማን ሆይ! ሰዎች ዝሙት እየፈጸሙ፣ ኸምር እየጠጡ፣ እየሰረቁና ነፍስ እያጠፉ፡ ይህ ተግባራችን ቀድሞ አላህ ዘንድ የታወቀና የተወሰነ ስለሆነ ከሱ መዳን አልቻልንም በማለት በቀደር ያሳብባሉ አሏቸው፡፡ እሳቸውም በጣም ተቆጡ፡፡ ከዚያም እንዲህ አሉ፡- ‹‹ሱብሐነላሂል ዐዚም፡ እነሱ ዛሬ ላይ በምርጫቸው እንደሚሰሩት በርግጥም አላህ ቀድሞ ያውቀው ነበር፡፡ የአላህ ቀድሞ ማወቅ ግን ወደ ኃጢአቱ አልወሰዳቸውም፡፡ የአላህ ዕውቀት በናንተ ውስጥ ማለት እኮ፡ እንዳጠለላችሁ ሰማይ እና እንደተሸከማችሁ ምድር ማለት ነው፡፡ የቱንም ያህል ብትንቀሳቀሱ ከስፋታቸው አንጻር ከሰማይና ምድር ክልሎች መውጣት እንደማትችሉ ሁሉ፡ የትም ተሸሽጋችሁ ምንም ብታደርጉ ከአላህ ዕውቀት ማምለጥ አትችሉም፡፡ ሰማይና ምድር ከስፋታቸው አንጻር እናንተን ከበቧችሁ ማለት በፈቃዳችሁ በምትሰሩት ስራ ላይ ተጽእኖ ፈጠሩባችሁ ማለት እንዳልሆነ ሁሉ የአላህ ዕውቀትም ስራዎቻችሁን ሁሉ ያካበበ ነው ማለት እንድትሰሩት ገፋፋችሁ ማለት አይደለም›› አሉና ከዚያም አስከትለው እንዲህ አሉ፡- ‹‹ኃጢአትን ሰርቶ የገዛ ነፍሱን የሚወቅስ የአላህ ባሪያ፡ ቀኑን እየጾመ ለሊቱን እየቆመ ከዚያም በኃጢአት ጊዜ በቀደር ከሚያሳብበው የአላህ ባሪያ የበለጠ እኔ ዘንድ ተወዳጅ ነው፡፡›› (ሪሳለቱል ሙስተርሺዲን 96)፡፡
በመሆኑም የአንድ ሙእሚን ባሕሪ ኃጢአት ላይ በወደቀ ጊዜ በቀደር ከማሳበብ ይልቅ ወደ ተውበትና ኢስቲግፋር ነው መቻኮል ያለበት፡፡ አደምና ሐዋእ (ዐለይሂማ-ሰላም) እንዳሉትም ይበል፡-
” قَالَا رَبَّنَا ظَلَمْنَا أَنْفُسَنَا وَإِنْ لَمْ تَغْفِرْ لَنَا وَتَرْحَمْنَا لَنَكُونَنَّ مِنَ الْخَاسِرِينَ ” سورة الأعراف 23
“ጌታችን ሆይ! ነፍሶቻችንን በደልን፤ ለኛ ባትምር ባታዝንልም በእርግጥ ከከሳሪዎቹ እንሆናለን አሉ።” (ሱረቱል አዕራፍ 23)፡፡

5ኛ. ኃጢአት ከሰራ በኋላ ተውበት ከማድረቅ ይልቅ ቀደርን ለማሰበብ ለሚቸኩለው ሰው እንዲህ ብለን እንጠይቀው፡- አንተ ወደ ኃጢአት ስፍራ ስትሄድ ይህ ተግባርህ ቀድሞ የተጻፈብህ መሆኑን ማን ነገረህ? ወይንስ ከሰራሁት በኋላ በቀደር አሳብባለሁ ብለህ ነው? የመጀመሪያውን በማለት አይመልስም፡፡ ቀድሞ የተጻፈውን ሊያውቅ አይችልምና፡፡ ሁለተኛውን ካለ ደግሞ፡- ለምን እራስህን ታታልላለህ? አላህ የልብህን የሚያውቅ መሆኑን አልተረዳህምን? ከዛ ይልቅ ለምን ወደ መልካም ነገር ቦታ ሄደህ ጥሩ ስራና ይህን ስራ በአላህ ተውፊቅ (ዕገዛ) የሰራሁት ነው ለምን አትልም? ይባላል፡፡
ከላይ ባየነው 5 መንገዶች መሰረት ሰው ለሚሰራው ክፉ ተግባር ቀደርን ማሳበቡ ተገቢ እንዳልሆነ በመጠኑም ቢሆን ለማየት ሞክረናል፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ሐዲሡ እንመለስ፡፡ ሐዲሡ ይህንን ይመስላል፡-
عن أبي هريرة قال قال رسول الله صلى الله عليه وسلم: “احتج آدم وموسى فقال موسى يا آدم أنت أبونا خيبتنا وأخرجتنا من الجنة فقال له آدمأنت موسى اصطفاك الله بكلامه وخط لك التوراة بيده أتلومني على أمر قدره الله علي قبل أن يخلقني بأربعين سنة فقال النبي صلى الله عليه وسلم فحج آدم موسى فحج آدم موسى فحج آدم موسى” رواه أبو داود.
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ባስተላለፈው ሐዲሥ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “አደምና ሙሳ (ዐለይሂማ-ሰላም) ተከራከሩ፡፡ ሙሳም፡- አደም ሆይ! አንተ አባታችን ነህ፡፡ አዋረድከን ከጀነትም አስወጣኸን አለው፡፡ አደምም፡- ሙሳ ሆይ! አላህ አንተን በቀጥታ በማናገሩ መርጦሀል፡፡ ተውራትንም በመለኮታዊ እጁ ጽፎ ሰጥቶሀል፡፡ ታዲያ አላህ እኔን ከመፍጠሩ ከአርባ ዓመት በፊት ቀድሞ በወሰነብኝ ነገር ትወቅሰኛለህን? አለው፡፡ ነቢያችንም (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) አደም ሙሳን ረታው (አሸነፈው)፣ አደም ሙሳን ረታው፣ አደም ሙሳን ረታው አሉ” (አቡ ዳዉድ)፡፡

ይህን ሐዲሥ ቡኻሪና ሙስሊም እንዲሁም ሌሎች የሐዲሥ መዛግብት በውስጣቸው ያሰፈሩት የሆነ ታላቅ ሐዲሥ ነው፡፡ መልእክቱንም በደንብ ላስተዋለው ሰው በውስጡ፡- ለሚሰራ ጥፋት ቀደርን ማሳበብ ይበቃል የሚል ሽታም እንኳ አያገኝበትም፡፡ እንዴት የሚባልም ከሆነ ቀጥለን እንየው፡-

1ኛ. በሙሳና በአደም(ዐለይሂማ-ሰላም) መካከል የተካሄደው ክርክር ከጀነት መውጣትን የተመለከተ እንጂ፡ በጀነት ውስጥ ቅጠሉን ስለመብላት አልነበረም፡፡ ሙሳም አደምን፡- አንተንም እኛንም ለምን ከጀነት አስወጣኸን? በማለት ጠየቀው እንጂ፡ ከተከለከልከው ከዛፍ ፍሬ ወስደህ ለምን በላህ? አላለውም፡፡ አደም በጀነት እያለ ከተከለከለው የዛፍ ፍሬ ወስዶ መብላቱ ‹መዕሲያህ› (አመጽ) ሲሆን፡ ከጀነት መውጣቱ ደግሞ ‹ሙሲባህ› (መከራ፡ ፈተና) ነው፡፡ ውይይቱ የሚያተኩረው ሙሲባው ላይ ነው፡፡

2ኛ. አደም በጀነት እያለ ለፈጸመው አመጽ (መዕሲያህ) በቀደር ሳይሆን ያሳበበው፡ እራሱን በመውቀስ የጌታውንም ምሕረት በመሻት ከባለቤቱ ጋር ተውበት ገብቷል፡፡ አላህም ይቅር ብሏቸዋል፡፡ የኃጢአት ምሕረትንም አግኝተዋል፡፡ ‹አት-ታኢቡ ሚነ-ዘንቢ ከመን-ላ ዘንበ ለሁ› (ከኃጢአት በተውበት የሚመለስ ኃጢአት እንደሌለበት ነውና) አደምም ተውበት ባደረገበት ጥፋት ሊወቀስ አይገባም፡፡ ሙሳም (ዐለይሂ ሰላም) ይህን ነገር ጠንቅቆ ያውቃልና ‹ሊማዛ አከልተ ሚነ-ሸጀራህ?› (ከዛፊቷ ወስደህ ለምን በላህ?) በማለት ወቀሳን አላቀረበም፡፡ ያቀረበው ወቀሳ ‹ሊማዛ አኽረጅተና ወነፍሰከ ሚነል-ጀንናህ?› (ለምን እራስህንም እኛንም ከጀነት አስወጣኸን?) ነበር ያለው፡፡ የአደም ከጀነት መውጣት ደግሞ ሙሲባህ ነው፡፡ ሙሲባህ (መከራንና ፈተናን) ደግሞ ሰው በገዛ ፈቃዱ ፈልጎና አቅዶ የሚያመጣው ነገር ባለመሆኑ፡ አደምም፡- ሙሳ ሆይ! አላህ እኔን ከመፍጠሩ ከአርባ ዓመት በፊት ቀድሞ በወሰነብኝ ነገር ትወቅሰኛለህን? በማለት በቀደር በማሳበብ መለሰለት፡፡ ነቢያችንም (ዐለይሂ ሶላቱ ወስ-ሰላም) አደም ሙሳን ረታው በማለት የንግግሩን እውነተኝነት አጸደቁለት፡፡

3ኛ. ሙሲባህ ከአላህ ዘንድ የሚመጣ ነው፡፡ ሰበቡ የሰዎች ኃጢአት መብዛት ሊሆን ይችላል (አን-ኒሳእ 79)፡፡ ወይንም አላህ ባሪያዎቹን ለመፈተን የሚያደርገው ሊሆን ይችላል (አል-በቀራህ 155-156)፡፡ በሁለቱም መንገድ ብናየው እንኳ ሰው በሚደርስበት ሙሲባህ ሳይሆን የሚወቀሰው፡ በሰራው ኃጢአት ነው የሚወቀሰው፡፡ ምክንያቱም ኃጢአቱ ላይ የገዛ ፈቃዱ ስለታከለበትና ፈልጎ ስለሰራው ሲሆን፡ ሙሲባውን ግን ፈልጎ ያመጣው ነገር ስላልሆነ ነው፡፡ አደምና ሐዋእም (ዐለይሂማ-ሰላም) ከዛፊቷ ወስደው ሲበሉ በሸይጧን አሳሳችነት ሁሌም ህያው የሚሆኑ መስሏቸው እንጂ ከጀነት ለመውጣት አቅደው አይደለም፡፡ ለፈጸሙት ጥፋት ተውበት አደረጉ፡፡ አላህም ማራቸው፡፡ ቀድሞ በተወሰነው መሰረት ደግሞ ከጀነት እንዲወጡና በምድር ላይ እንዲኖሩ ተደረጉ፡፡ አላህ አስቀድሞውኑ ሰውን ሳይፈጥር በፊት ለመላእክት፡- እኔ በምድር ላይ ምትክን አድራጊ ነኝ! ብሎ አሳወቃቸው እንጂ፡ በጀነት ላይ አደርጋለሁ አላለም (አል-በቀራህ 30)፡፡

4ኛ. ሁኔታውን ግልጽ ለማድረግ አንድ ምሳሌ እንመልከት፡-
ወደ ሌላ ከተማ ለመሄድ ጓዝህን ጠቅልለህ እየተሳፈርክ ሳለ፡ በጉዞህ ላይ የመኪና መገልበጥ አደጋ ቢደርስብህና በሰውነትህ ላይ ጉዳት ቢደርስብህ፡ ቤተሰቦችህ፡- ለምን ወደዚያ ከተማ አቀናህ? እቤት አርፈህ ብትቀመጥ ኖሮ ይህ ሁሉ ጉዳት ሊደርስብህ አይችልም ነበር! በማለት አንተን መውቀስ ይችላሉን? በፍጹም አይችሉም፡፡ ምክንያቱም፡- አንተ ወደ ከተማው ያቀናኸው ለጉዳይ እንጂ ሰውነትህን አደጋ ላይ ለመጣል አይደለም፡፡ እሱ በመንገድ እያለህ ካንተ ፈቃድ ውጪ ሆኖ የተከሰተ የአላህ ቀደር ነው፡፡ ስለዚህ አንተ ልትወቀስበት አይገባም፡፡ አደምና ሐዋእም ለምን ከጀነት ወጣችሁ? ተብለው እንዳይወቀሱ፡ መች ከጀነት እንውጣ ብለው ከዛፊቷ በሉ? የሚል ጥያቄ ይነሳልና፡፡

5ኛ. እኛም ከዚህ ሐዲሥ የምንወስደው ትምህርት፡- ኃጢአት በሰራን ጊዜ በቀደር ከማሳበብ ይልቅ እንደ ሁለቱ ወላጆቻችን በፍጥነት ተውበት መግባትንና፡ የሆነ ሙሲባ በሚደርስብን ጌዜ ደግሞ ‹‹ቀደረላሁ ወማ ሻአ ፈዐል›› (አላህ ወሰነ እሱ የሻውን ሰራ!) በማለት ቀደርን መጠቀም እንዳለብን ነው፡፡ አላህ የበለጠውን ዐዋቂ ነው፡፡

Shortlink http://q.gs/Ewij2