ግብረ-ሰዶም

ሼር ያድርጉ
585 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

ጌታ አላህ እሱ በብቸኝነት ይመለክ ዘንድ ሰዎችንና ጂንኒዎችን ፈጥሯል (አዝ-ዛሪያት 51፡56)፡፡ ትክክለኛ አምልኮ ምን እንደሆነና እንዴት እንደሚፈጸም፡ በንግግርም ሆነ በተግባር አርአያ በመሆን ያሳዩ ዘንድ፡ ከሰዎች መካከል ሰዎችን መርጦ፡ የመረጣቸውን ሰዎች የነቢይነት እና የመልክተኝነት ማዕረግ በመስጠት ወደ ህዝቦቻቸው ልኳቸዋል (አን-ነሕል 16፡36)፡፡ ለከፊሎቹም መለኮታዊ መጽሐፍን ሰጥቷቸዋል (አል-ሐዲድ 57፡25)፡፡

ከነዚህ ቀደምት ነቢያትና ሩሱሎች ውስጥ አንዱ ሉጥ (ዐለይሂ-ሰላም) ነው (አስ-ሷፍፋት 37፡133)፡፡ ሉጥ (ዐለይሂ-ሰላም) የነቢዩላህ ኢብራሂም (ዐለይሂ-ሰላም) የወንድሙ ልጅ ነው፡፡ መልክተኛ ሆኖ የተላከውም፡ ሰዱም (ሰዶም) ተብላ ወደምትጠራው መንደር እና በአካባቢዋ ለሚገኙት ነው፡፡ የዚህ መንደር ነዋሪዎች ሶዶማውያን በመባል ይታወቃሉ፡፡ ከክህደታቸው በተጨማሪ (ካፊር ከመሆናቸውም ሌላ) ሌላ የሚታወቁበት አስቀያሚ የኃጢአት ተግባር አልለ፡፡ እሱም፡- የተመሳሳይ ፆታ ግብረ-ስጋ ግኑኝነት (HOMO sexual) ነው፡፡
አላህ ፈቃዱ ከሆነ ለዛሬ የምንነጋገረው በዚህ አስቀያሚ ተግባር ላይ ኢስላም ያለውን አቋም በመጠኑ ዳሰሳ በማድረግ ይሆናል ኢንሻአላህ፡፡ መልካም ንባብ፡-

1/ የተወገዘ ኃጢአት መሆኑ፡-

ሀ/ ጌታ አላህ በባሪያዎቹ ላይ ከዋላቸው ከማይቆጠሩ ጸጋዎቹ የተወሰኑትን እያነሳ ሲያስታውሰን፡ አንደኛውን የገለጸው ‹‹ለኛ የትዳር አጋር የምትሆነን ሴትን›› ከኛው መፍጠሩን በመጠቆም ነው፡፡ ይህም ከአስደናቂ ምልክቶቹ መሆኑን አያይዞ ይነግረናል፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“وَمِنْ آيَاتِهِ أَنْ خَلَقَ لَكُم مِّنْ أَنفُسِكُمْ أَزْوَاجًا لِّتَسْكُنُوا إِلَيْهَا وَجَعَلَ بَيْنَكُم مَّوَدَّةً وَرَحْمَةً إِنَّ فِي ذَلِكَ لَآيَاتٍ لِّقَوْمٍ يَتَفَكَّرُونَ ” سورة الروم 21
“ለናንተም፣ ከነፍሶቻችሁ (ከጐሶቻችሁ) ሚስቶችን ወደነርሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ፤ በመካከላችሁም ፍቅርንና እዝነትን ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው፤ በዚህ ውስጥ ለሚያስውሉ ሕዝቦች ታምራቶች አሉ።” (ሱረቱ-ሩም 30፡21)፡፡
“وَاللّهُ جَعَلَ لَكُم مِّنْ أَنفُسِكُمْ أَزْوَاجًا وَجَعَلَ لَكُم مِّنْ أَزْوَاجِكُم بَنِينَ وَحَفَدَةً وَرَزَقَكُم مِّنَ الطَّيِّبَاتِ أَفَبِالْبَاطِلِ يُؤْمِنُونَ وَبِنِعْمَتِ اللّهِ هُمْ يَكْفُرُونَ ” سورة النحل 72
“አላህ ከነፍሶቻሁ (ከጐሶቻችሁ) ለናንተ ሚስቶችን አደረገ፤ ለናንተም ከሚስቶቻሁ ወንዶች ልጆችን የልጅ ልጆችንም አደረገላችሁ፤ ከመልካሞችም ጸጋዎች ሰጣችሁ፤ ታዲያ በውሸት (በጣዖት) ያምናሉን? በአላህም ጸጋ እነሱ ይክዳሉን?” (ሱረቱ-ነሕል 16፡72)፡፡
“فَاطِرُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ جَعَلَ لَكُم مِّنْ أَنفُسِكُمْ أَزْوَاجًا وَمِنَ الْأَنْعَامِ أَزْوَاجًا يَذْرَؤُكُمْ فِيهِ لَيْسَ كَمِثْلِهِ شَيْءٌ وَهُوَ السَّمِيعُ البَصِيرُ ” سورة الشورى 11
“ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ ነው፤ ከነፍሶቻችሁ (ከጎሶቻችሁ) ሴቶችን፣ ከቤት እንሰሳዎችም ዓይነቶችን (ወንዶችና ሴቶችን) ለእናንተ አደረገላችሁ፤ በርሱ (በማድረጉ) ያበዛችኋል፤ የሚመስለው ምንም ነገር የለም፤ እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው።” (ሱረቱ-ሹራ 42፡11)፡፡
ከነዚህ ሶስት አንቀጾች በግልጽ የምንረዳው ነገር፡- ጌታ አላህ ለኛ ተጣማሪን (የትዳር አጋር) ያደረገልን፡ ከሴቶች ጋር እንጂ፡ ከተመሳሳይ ፆታ ጋር አለመሆኑን ነው፡፡ ይህ የተቃራኒ ፆታ በጋብቻ መጣመር ከአላህ የሆነ ኒዕማ (ጸጋ) ከሆነ፡ ከዛ በተቃራኒው ሆኖ መገኘት (ወንድ ከወንድ ወይም ሴት ከሴት ጋር) ደግሞ እርግማንና ቁጣ እንጂ ሌላ አይሆንም፡፡ በዚህም ሰበብ ተግባሩ ኃጢአት መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ለ/ የሉጥ (ዐለይሂ-ሰላም) ህዝቦች ነቢያቸውን በማስተባበልና ባለመቀበላቸው ከሀዲ ሆነዋል፡፡ ከክህደት የሚበልጥ ኃጢአት የለም፡፡ ከዚህ ክህደታቸው ጋር ደግሞ በተጨማሪ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት በመፈጸማቸው አላህ አጥፍቷቸዋል፡፡ ይህም የሰዶምች ስራ (ግብረ-ሰዶም) የኃጢአት ተግባር ለመሆኑ ሌላ ማስረጃ ነው፡፡ ቀጣዮቹ ቅዱስ ቁርኣናዊ አንቀጾች ይህን ይገልጻሉ፡-
“وَلُوطًا إِذْ قَالَ لِقَوْمِهِ أَتَأْتُونَ الْفَاحِشَةَ مَا سَبَقَكُم بِهَا مِنْ أَحَدٍ مِّن الْعَالَمِينَ * إِنَّكُمْ لَتَأْتُونَ الرِّجَالَ شَهْوَةً مِّن دُونِ النِّسَاء بَلْ أَنتُمْ قَوْمٌ مُّسْرِفُونَ * وَمَا كَانَ جَوَابَ قَوْمِهِ إِلاَّ أَن قَالُواْ أَخْرِجُوهُم مِّن قَرْيَتِكُمْ إِنَّهُمْ أُنَاسٌ يَتَطَهَّرُونَ * فَأَنجَيْنَاهُ وَأَهْلَهُ إِلاَّ امْرَأَتَهُ كَانَتْ مِنَ الْغَابِرِينَ * وَأَمْطَرْنَا عَلَيْهِم مَّطَرًا فَانظُرْ كَيْفَ كَانَ عَاقِبَةُ الْمُجْرِمِينَ ” سورة الأعراف 84-80
“ሉጥንም ለሕዝቦቹ ባለ ጊዜ (አስታውስ)፤ አስቀያሚን ሥራ ትሰራላችሁን? በርሷ ከዓለማት አንድም አልቀደማችሁም። እናንተ ከሴቶች ሌላ ወንዶችን በመከጀል በእርግጥ ትመጡባቸዋላችሁ፤ በውነቱ እናንተ ወሰንን አላፊዎች ሕዝቦች ናችሁ። የሕዝቦቹም መልስ (ሎጥንና ተከታዮቹን) ከከተማችሁ አውጧቸው፣ እነሱ የሚጥራሩ ሰዎች ናቸውና ማለት እንጂ ሌላ አልነበረም። እርሱንና ቤተሰቦቹንም አዳንናቸው፣ ሚስቱ ብቻ ስትቀር፣ እርሷ (ለጥፋት) ከቀሩት ሆነች። በነርሱም ላይ (የእሳት) ዝናምን አዘነምንባቸው፤ የኃጢአተኞችም መጨረሻ እንዴት እንደ ነበረ ተመልከት።” (ሱረቱል አዕራፍ 7፡80-84)፡፡
“وَلُوطًا إِذْ قَالَ لِقَوْمِهِ إِنَّكُمْ لَتَأْتُونَ الْفَاحِشَةَ مَا سَبَقَكُم بِهَا مِنْ أَحَدٍ مِّنَ الْعَالَمِينَ* أَئِنَّكُمْ لَتَأْتُونَ الرِّجَالَ وَتَقْطَعُونَ السَّبِيلَ وَتَأْتُونَ فِي نَادِيكُمُ الْمُنكَرَ فَمَا كَانَ جَوَابَ قَوْمِهِ إِلَّا أَن قَالُوا ائْتِنَا بِعَذَابِ اللَّهِ إِن كُنتَ مِنَ الصَّادِقِينَ ” سورة العنكبوت 29-28
“እናንተ በእርግጥ ወንዶችን ትመጣላችሁን? መንገድን ትቆርጣላችሁን? በሸንጓችሁም የሚነወርን ነገር ትሠራላችሁን? (አላቸው)፤ የሕዝቦቹም መልስ ከውነተኞቹ እንደ ኾንክ የአላህን ቅጣት አምጣብን ማለት እንጂ ሌላ አልነበረም።” (ሱረቱል ዐንከቡት 29፡28-29)፡፡
“وَلُوطًا إِذْ قَالَ لِقَوْمِهِ أَتَأْتُونَ الْفَاحِشَةَ وَأَنتُمْ تُبْصِرُونَ * أَئِنَّكُمْ لَتَأْتُونَ الرِّجَالَ شَهْوَةً مِّن دُونِ النِّسَاء بَلْ أَنتُمْ قَوْمٌ تَجْهَلُونَ ” سورة النمل 55-54
“ሉጥንም ለሕዝቦቹ ባለ ጊዜ (አስታውስ)፤ «እናንተ የምታዩ ስትኾኑ ፀያፍን ነገር ትሠራላችሁን?፡፡ «እናንተ ከሴቶች አልፋችሁ ወንዶችን ለመከጀል ትመጣላችሁን በእውነቱ እናንተ የምትሳሳቱ ሕዝቦች ናቸሁ፡፡»” (ሱረቱ-ነምል 27፡54-55)፡፡

ሐ/ በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ የስጋ ፍላጎትን ከሚስቶች ወይም በእጆቻችሁ ካሉ (ባሪያዎች) ጋር ብቻ ነው ይልና፡ ከዚህ ውጪ የሚፈልግ ግን እሱ ወሰን አላፊ ኃጢአተኛ ነው ይለናል፡፡ ‹‹ከዚህ ውጪ›› በሚለው አነጋገር ውስጥ የተመሳሳይ ጾታ ግኑኝነትም አብሮ ይካተታል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የተወገዘ ተግባር ነው፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“وَالَّذِينَ هُمْ لِفُرُوجِهِمْ حَافِظُونَ * إِلَّا عَلَى أَزْوَاجِهِمْ أوْ مَا مَلَكَتْ أَيْمَانُهُمْ فَإِنَّهُمْ غَيْرُ مَلُومِينَ * فَمَنِ ابْتَغَى وَرَاء ذَلِكَ فَأُوْلَئِكَ هُمُ الْعَادُونَ ” سورة المؤمنون 7-5
“እነዚያም እነርሱ ብልቶቻቸውን ጠባቂዎች የሆኑት (አገኙ)፡፡ በሚስቶቻቸው ወይም እጆቻቸው በያዟቸው (ባሪያዎች) ላይ ሲቀር፡፡ እነርሱ (በነዚህ) የማይወቀሱ ናቸውና፡፡ ከዚህም ወዲያ የፈለጉ ሰዎች እነዚያ እነርሱ ወሰን አላፊዎች ናቸው፡፡” (ሱረቱል ሙእሚኑን 23፡5-7)፡፡
“وَالَّذِينَ هُمْ لِفُرُوجِهِمْ حَافِظُونَ * إِلَّا عَلَى أَزْوَاجِهِمْ أَوْ مَا مَلَكَتْ أَيْمَانُهُمْ فَإِنَّهُمْ غَيْرُ مَلُومِينَ * فَمَنِ ابْتَغَى وَرَاء ذَلِكَ فَأُوْلَئِكَ هُمُ الْعَادُونَ ” سورة المعارج 31-29
“እነዚያም እነሱ ብልቶቻቸውን ጠባቂዎች የሆኑት። በሚስቶቻቸው ወይንም እጆቻቸው በያዙዋቸው (ባሮች)፣ ላይ ሲቀር። እነሱ (በነዚህ) የማይወቀሱ ናቸውና። ከዚያም ወዲያ የፈለገ ሰው፣ እነዚያ እነሱ ድንበር አላፊዎች ናቸው። ” (ሱረቱል መዓሪጅ 70፡29-31)፡፡

መ/ ተመሳሳይ የፆታ ግኑኝነት በመፈጸም የሉጥ ህዝቦችን አይነት ስራ በመስራት የተሰማሩ ሰዎች በነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) አንደበት ለእርግማን ተዳርገዋል፡፡ እርግማኑ የሚያመላክተው ደግሞ፡ ኃጢአቱ እጅግ የከፋ ተግባር መሆኑን ነው፡፡ ሐዲሡ እንዲህ ይነበባል፡-
وروى أحمد (2915) عَنِ ابْنِ عَبَّاسٍ رضي الله عنهما أَنَّ نَبِيَّ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ قَالَ : ( لَعَنَ اللَّهُ مَنْ عَمِلَ عَمَلَ قَوْمِ لُوطٍ ، لَعَنَ اللَّهُ مَنْ عَمِلَ عَمَلَ قَوْمِ لُوطٍ ، ثَلاثًا ) وحسنه شعيب الأرنؤوط في تحقيق المسند .
ዐብደላህ ኢብኑ ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም)፡- “የሉጥ ህዝቦችን አይነት ስራ የሚሰራን ሰው አላህ ከራሕመቱ ያርቀው፣ የሉጥ ህዝቦችን አይነት ስራ የሚሰራን ሰው አላህ ከራሕመቱ ያርቀው በማለት ሶስት ጊዜ ደጋግመው ተናግረዋል፡፡” (ሙስነድ ኢማሙ አሕመድ 2915)፡፡
ሹዐይቡል-አርነኡጥ ሰነዱ ሐሰን መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
عن عبدالله بن عباس رضي الله عنهما : أن النبي صلى الله عليه وسلم قال:- “لا ينظرُ اللهُ عزَّ وجلَّ إلى رجلٍ أتَى رجلًا أو امرأةً في دبرِها”. الترغيب والترهيب -: 3/273
ከዐብደላህ ኢብኑ ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) በድጋሚ እንደተላለፈልን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ:– “አንድ ወንድ መሰል ብጤውን ወንድን ወይም ሴትን ከቆሻሻ መውጪያ ከተገናኘ አላህ (በራሕመት እይታው) አይመለከተውም” (አት–ተርጊብ ወት–ተርሂብ 3/273)።
የትንሳኤ ቀን (የውሙል ቂያም) የጌታውን ራሕመት (እዝነት) ማግኘት ያልቻለ ሰው: የሚጠብቀው ቅጣት ነው ማለት ነው።

ሠ/ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ለኡመታቸው እጅግ በጣም አሳቢ ናቸው፡፡

አንድም ነፍስ እንዲጠፋ አይፈልጉም፡፡ ስለሆነም፡- መልካም ሆኖ እኛን የሚጠቅመንን ነገር ሳይጠቁሙንና ሳያነሳሱን፡ መጥፎ ሆኖ እኛን የሚጎዳንን ነገር ሳያስጠነቅቁንና ሳይገስጹን በፍጹም አያልፉም፡፡
ወደፊት ለኡመቶቼ ይከሰታል ብዬ ከምፈራላቸው አስፈሪ ነገር አንዱ፡ የተመሳሳይ ፆታ ግኑኝነት መሆኑን ጠቁመውናል፡፡ ይህም ተግባሩ በኢስላም የተወገዘ መሆኑን ያመላክታል፡፡ እንዲህ ብለው ነበር፡-
عَنْ جَابِرِ بْنِ عَبْدِ اللَّهِ قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ -صلى الله عليه وسلم- « إِنَّ أَخْوَفَ مَا أَخَافُ عَلَى أُمَّتِى عَمَلُ قَوْمِ لُوطٍ ». ابن ماجه 2563 , الترمذي 1457 وحسنه , الحاكم 4/357 وصححه ووافقه الذهبي , حسنه الألباني في الترغيب.
ጃቢር ኢብኑ ዐብዲላህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “እኔ በህዝቦቼ (ኡመቶቼ) ላይ ከምፈራላቸው ነገራት የበለጠ እጅጉኑ አስፈሪው ነገር የሉጥ ህዝቦች ስራ ነው” (ኢብኑ ማጀህ 2563፣ ቲርሚዚይ 1457፣ ሓኪም አል-ሙስተድረክ 4/357)፡፡
ሸይኽ አልባኒይ (ረሒመሁላህ) በተርጊብ ወት-ተርሒብ ላይ የዚህን ሐዲሥ ሰንሰለት መልካም እንደሆነ ሐሰን በማለት ገልጸውታል፡፡

2/ ሸሪዐዊ ቅጣቱ፡-

ከነቢያችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በተገኘው ሐዲሥ መሰረት፡ በዚህ ተግባር ላይ ሆኖ ንሰሀ (ተውበት) ከማድረጉ በፊት በአይን ምስክሮች የተገኘ፣ ለአካለ መጠን የደረሰ ሰው ቅጣቱ ‹‹መገደል›› ነው፡፡ ይህም የድርጊቱን አስቀያሚነት፡ ማኃበረሰብ የሚበክል ትውልድ እንዳይቀጥል የሚያደርግ እንቅፋት በመሆኑ ነው፡፡ ሐዲሡ እንዲህ ይነበባል፡-
وروى الترمذي (1456) وأبو داود (4462) وابن ماجه (2561) عَنْ ابْنِ عَبَّاسٍ رضي الله عنهما قَالَ : قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ : ( مَنْ وَجَدْتُمُوهُ يَعْمَلُ عَمَلَ قَوْمِ لُوطٍ فَاقْتُلُوا الْفَاعِلَ وَالْمَفْعُولَ بِهِ ) وصححه الألباني في صحيح الترمذي .
ዐብደላህ ኢብኑ ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም)፡- “የሉጥ ህዝቦችን አይነት ስራ የሚሰራን ሰው ካገኛችሁት የሚፈጽመውንም፣ የሚፈጸምበትንም ሰው ግደሉ” (ቲርሚዚይ 1456፣ አቡ ዳዉድ 4462፣ ኢብኑ ማጀህ 2561)፡፡

3/ የሰውየው ማንነት፡-

በሸሀደተይን ሙስሊምነቱ የተረጋገጠ፣ ለጌታው አላህ በቀን አምስት ጊዜ የሚሰግድ የአላህ ባሪያ፡ ይህን ሸሀደተይን ሊያፈርስ የሚችል የሺርክ/ኩፍር ተግባር እስካልፈጸመና እስካልተናገረ ድረስ፡ በከባኢረ-ዙኑብ (በታላላቅ ኃጢአት) ኃጢአት ላይ መዘፈቁ፡ ከኢስላም አጥር አያስወጣውም፡፡
ኃጢአቱ በውስጡ ያለውን ኢማን ያዳክመዋል እንጂ፡ ኩፍር ውስጥ አይከተውም፡፡ በዚህ ተግባር ላይ ሁኖ ያለ ተውበት ቢሞትም እንኳ፡ ጉዳዩ ወደ አላህ የሚመለስ (አላህ ከፈለገ ሊምረው፣ ካልሆነም የኃጢአቱን ያህል ሊቀጣው) እንጂ እኛ የምንፈርድበት አይደለም፡፡
ግብረ-ሰዶም ከታላላቅ ኃጢአት ተርታ የሚመደብ እንጂ በራሱ ኩፍር የሆነ ተግባር አይደለም፡፡ ይህ አስቀያሚ ስራ ከአንድ ሙስሊም ላይ ቢገኝ እና ያ ሙስሊም ያለ ተውበት ቢሞት፡ የሰውየው ጉዳይ ወደ አላህ ይመለሳል እንጂ፡ ማንም ሰው እሱ የጀሀነም ነው ማለት አይችልም፡፡
ሰውየውን ሊያከፍረው የሚችለው ይህ አስቀያሚ ተግባር ሐላል ነው ብሎ ካመነ ወይም ከተናገረ ብቻ ነው፡፡ የዛኔ ስራው ላይ ባይገኝም በዚህ እምነቱ ብቻ ይከፍራል፡፡ ከዛ ውጪ ተግባሩ ኃጢአት መሆኑን ልቡ ያመነ ሙስሊም፡ በነፍሲያው ፍላጎት ኃጢአቱ ላይ ቢወድቅ ከፈረ አይባልም፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡

4/ ማጠቃለያ፡-

የሰዶማውያን ተመሳሳይ የፆታ ግንኙነት በቀላሉ ቀጥሎ ያሉትን ግላዊና ማኃበራዊ ችግሮች ያስከትላል፡-
ሀ/ ከተፈጥሮአዊ ማንነት መጣረስን፡- ይህን ተግባር ንጹህ ህሊና ያወግዘዋል፡፡ ስሜታችንም አይቀበለውም፡፡ በዚህ ስራ ላይ መገኘት ከተፈጥሮ ስርአት መውጣት ነው፡፡
ለ/ ወጣቱን አካል ማኮላሸትን፡- ወጣቶች ከወዲሁ እራሳቸውን ተጣማጃቸውን በመፈለግ በትዳር ካልታቀፉ፡ ለዚህ ተግባር በቀላሉ ተጠቂ ይሆናሉ፡፡ ስሜታቸውም ያለ አግባብ ይባክናል፡፡
ሐ/ የዘር መቋረጥን፡- ዘር ሊገኝ የሚችለው በወንድና ሴት ጋብቻ እንጂ፡ በተመሳሳይ ፆታ አይደለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ሰው ከተመሳሳይ ፆታ ጋር ግንኙነትን ከቀጠለ፡ ትውልዱ ቀጣይነት አይኖረውም፡፡ ዘር ይቋረጣል፡፡
መ/ የሴቶች ብሉሹነት፡- ባለቤቶቻቸው ፊታቸውን ወደ መሰል ፆታቸው ካዞሩ፡ ሴቶችም ስሜታቸውን ለማብረድ በመፈለግ ወደ ሐራም ተግባር የመዘፈቅ እድሉ የሰፋ ይሆናል፡፡
ሠ/ ያልተፈቀደ ግንኙነት፡- ከወንዶች ጋር ያንን አስቀያሚ ተግባር የለመደ ሰው፡ ወደ ሴቶችም ሲመጣ ስሜቱን ማርካት የሚፈልገው ዘር ከሚገኝበት ቦታ ሳይሆን፡ ከተወገዘው ሌላኛው ስፍራ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ ብሉሹነት ነው፡፡
ረ/ የቤተሰብ መበታተንን፡- ተግባሩ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ፡ የቤተሰብ ህይወት ይናጋል፡፡ በመሀከላቸውም ጸብና ጥላቻ ይሰፍናል፡፡ ህይወት ይበላሻል፡፡ ሌሎችም…

አላህ ወንድሞችንና እህቶቻችንን ከዚህ አስቀያሚ ተግባር ይጠብቅልን፡፡

Shortlink http://q.gs/EwiqZ