ይድረስ -ለሜሮን አሰፋ

ሼር ያድርጉ
414 Views
ኢሊያህ ማሕሙድ በአላህ ስም እጅግ አዛኝ እጅግ ሩህሩህ በሆነው እንጀምርና በመቀምቀሚያው ነብይ ሙሐመድ ላይ (ሰ.ዐ.ወ) የአላህ ሰላምና እዝነት ይዝነብባቸው ብለን እንቀጥላለን፡፡ ወዳጃችን ሜሮን ስለ ክርስቶስ ጸሎተ-ጽዋ በጨዋነት የለጠፈችውን አነበብኩ፡፡ ቀጥዬም ጨዋነቷን አድንቄ የማውቀውንና እርግጠኛ የሆንኩበትን በጨዋነት ለመጻፍ መላክም መስሎ ታየኝ፡፡ “በወርቅ የሰፈረ እንደዚሁ ይሰፈራል” ነውና ተረቱ አሰፋፈሩን ለሚያሳምር እኛም ልናሳምር ከተቻለም “ልንመርቅለት” የግድ ነው፡፡ ወዳጃችን ሜሮን በማቴ 27:46 እና በማር 15:34 ላይ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሆኖ “ኤሎሔ ኤሎሔ እያለ ያለቅስ ነበር “አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውከኝ ” ማለት ነው፡፡ የሚለውን ጥቅስ ከሌሎች ጥቅሶች ጋር በማገናኘትና የቤተክርስትያን ብቻ አስተምህሮ የሆኑትንና ምንም መረጃ የሌላቸውንም መላ-ምቶች በማስደገፍ ለመተንተን ሞክራለች፡፡ ወደ ዝርዝር ሃሳቡ ከመዝለቃችን በፊት፡- አንድን ጥቅስ ከሌላ ጥቅስ ጋር ለማስማማት መጀመሪያ በታሪኮቹ መካከል ያለውን ዝምድና ጠልቆ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ በጥቅሶች መካከል ምንም የታሪክ ዝምድና ከሌላ የቃላት ወይም የአውድና ክስተት መመሳሰል ብቻውን ጥቅሶቹን አያዛምዳቸውም፡፡ በግድ ለማመሳሰል መሞከር ደግሞ ሸፍጥም በደልም ይሆናል፡፡ ሜሮን ዝርዘሯን ስትጀምር፡- ሜሮን # በማቴ 11/ 29 ; “ከእኔ ተማሩ” ብሎ ኢየሱስ ስላስተማረ በመከራ፣በሀዘን፣በጭንቀት ጊዜ ወደ እርሱ መጮህ እንዳለብን ሲያስተምረን ነው፡፡ብላ ለማስረዳት ትሞክራለች፡፡ እኛ# ኢየሱስ (ዐ.ሰ) እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ መሰረት ያንን ጩኹት ያሰማው ለማስተማር ከሆነ፣ ማንን ነበር የሚያስተምረው? ገና እሱ ከመሰቀሉ በፊት ሐዋርያት ሁሉ ጥለውት ሸሽተዋል- ማቴ 26/56(“በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ።” አንድም ደቀ-መዝሙር ከርሱ ጋር አልነበረም፡፡ ታዲያ ማንን ነበር የሚያስተምረው? ደቀ-መዛሙርቱ አይተው ያልተማሩትንስ ማን ቀድሟቸው ነው የሚማረው? ወዳጄ ምናልባት እዚህ ጋር አንድ ነገር ፍንትው ያለሎት መሰለኝ፡፡ “ደቀ- መዛሙርቱ ካላዩት ማነው ታዲያ ይኽንን ታሪክ የዘገበው?” የሚል፡፡ እውነት እውነት እሎታለሁ -እውነቶን ነው!!! ይኽንን ትረካ የዘገበው ማቴዎስ የሚባል ጸሐፊ ነው፡፡ ግን እሱም ቢሆን የአይን እማኝ አልነበረም፡፡ ሁሉም ሸሽተዋላ፡፡ ከዛም ባሻገር የማቴዎስ ወንጌል ጸሐፊና ደቀ-መዝሙሩ ማቴዎስ እየቅል ናቸው፡፡ “እንዴት” ካሉኝ ይኽንን ጥቅስ አንብበው ሲፈታቱት መልሱን ያገኙታል፡- ማቴ 9/9 “ኢየሱስም ከዚያ አልፎ በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረ ማቴዎስ ≠የሚባል≠ አንድ ሰው አየና፦ ተከተለኝ አለው። ተነሥቶም ተከተለው።” ወዳጄ ልብ ይበሉ፡፡ እርሶን መንገድ ላይ ከጓደኞቾ ጋር እኔ ኢሊያህ ማሕሙድ ባገኞና ምሳ አንድ ላይ ብንበላ፣ “ከኢሊያሕ ማሕሙድ ጋር ምሳ አንድ ላይ በላን” ነው የሚሉት ወይስ “ ኢሊያሕ ማሕሙድ ጓደኞቼን አግኝቶ፣ ምሳ አብሯቸው በላ?” እርሶ ምሳው ላይ ስለተሳተፉ “በላን” እንጂ “በሉ” እንደማይሉ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህም ተራ አምክንዬ አኳያ ማቴዎስ የሚባል አንድ ጻሐፊ ስለ ሌላ ማቴዎስ ስለሚባል የኢየሱስ ደቀ-መዝሙር የሰማውን እንደጻፈ እንረዳለን፡፡ ስለዚህ ጥያቄአችን ሲጠቀለል “የኢየሱስ ጩኸትና ልመና ማንን ለማስተማር ነበር? ደቀ-መዛሙርቱ ሁሉ ከሸሹ ማን ይህንን ታሪክ ዘገበው? በመቀጠልም በትክክል ከጥቅሱ የምንማረው እንኮ በመከራና ችግር ወደ አምላክ እንድንጮህ እንጂ ወደ ኢየሱስ እንድንጮህ አይደለም፡፡ ነው ከተባላ ደግሞ ኢየሱስ አምላክ ሆኖ ሳላ ወደ ሌላ አምላክ ጮኸ የሚል ግንዛቤ ያደርሰናል፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ ሲሰቀል አብ አብሮት አልተሰቀለም፤ ይልቁንም ኢየሱስ ወደ አልተሰቀለው አብ ነው የጸለየው፡፡ ሜሮን #2, የአዳምን ጩከት ነው የጮኸው
መፅሐፍ ቅዱስ ክርስቶስን እንዲህ ይለዋል 1ኛ , ቆሮ15/45 “ዳግማዊ አዳም” ይለዋል ይሔ ማለት በአዳም ቦታ ገብቶ የአዳምን እዳ በደል ከፍሎ የአዳምን ፅዋ (ሞት) ተቀብሎ አዳምን ነፃ ሊያወጣ የመጣ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ የአዳምን ጩኸት ጮኸ አዳም በአመተ ፍዳ በአመተ ኩነኔ በአመተ አለም በሲኦል ሆኖ በመከራ ብዛት እያለቀሰ ነበርና ክርስቶስ ደግሞ የአዳምን ስጋ ለብሷልና የአዳምን ጩኸት ጮኸ፡፡ እኛ# ከንዑስ ርዕሱ ጀምሮ ትንተናው በጣም የተፋለሰ ነው፡፡ “የአዳምን ጩኸት ጮኸ” ለማለት እማሬአዊ(ግልጽ) በሆነ መልኩ አዳም የጮኸው ጩኸት (ጸሎት) መኖር አለበት፡፡ ለወገናችን ሜሮን የምንጠይቀው ጥያቄ የኢየሱስ ን ጸሎት ከአዳም ጋር ከማመሳሰልሽ በፊት በመጀመሪያ የአዳም ጸሎት ምን እንደነበር ንገሪን፡፡ በርግጥ አዳም በመጽሃፍ-ቅዱስ አስተምህሮ መሰረት ወደ አምላኩ ጸልይዋልን? “አዎን” ከሆነ መልሱ፣ ጸሎቱ ይነገረን!!! ወዳጄ በመጽሃፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ጸሎት የሚባለው የቃይል ጸሎት ነው፡፡ (ዘፍ 4/10-16)
“አዳም በአመተ-ፍዳ በሲዖል እያለቀሰ ነበር” ለሚለውም ኦርቶዶክሳዊ ሙግት መጽሐፍ-ቅዱሳዊ ማስረጃ እንፈልጋልን፡፡ ወዳጄ ከዚህ ክርስቲያናዊ ሙገታ በጣም ተጻራሪ በሆነ መልኩ በሉቃስ ወንጌል 16/19-31 የሰፈረው ታሪክ ሰዎች በቀጥታ ከስራቸው አኳያ ብቻ ገነትንና ሲዖል እንደሚወርሱ እንማራለን፡፡ ትረካው በአጭሩ በጣም ድሃ የነበረ አልዓዛር የሚባል በሽተኛና በጣም ሃብታም ሰው ነበሩ፡፡ ድሃው ከሃብታሙ ትራፊ ቢበላ ይመኝ ነበር፡፡ ያ ሳይሆን ቀረና ሁለቱም የምድር ህይወታቸውን ጨርሰው ሲያልፉ ድሃው በመንግስተ ሰማያት በአብራሃም እቅፍ መላእክት አኖሩት፤ ሃብታሙ ደግሞ ሲዖል ገባ…፡፡ ይህንን ታሪክ ሲነግራቸው ኢየሱስ (ዐ.ሰ) ገና አልተሰቀለም፡፡ ገና እሱ ሳይሰቀልና እንደ ክርስትናም አስተምህሮ ቤዛ ሳይሆን አብራሃምና አልዓዛር ከመንግስተ ሰማይት ገብተዋል፡፡ታዲያ አዳም በሲዖል ሲያለቅስ ነበር ማለት ምን ማለት ነው? ወይስ የኢየሱስ (ዐ.ሰ) ቤዛነት ለአብራሃምና ለአልአዛር አይሰራም? ትውልድ ሁሉ ከስቅለት በፊት ሲዖል ነበሩ የሚለውስ ክርስትያናዊ (ሜሮን ባትጠቅሰውም) ሙግት ከሉቃስ ታሪክ ጋር እንዴት ይስማማል? ሜሮን#3, ሕማም የሚሰማውን የሰዎችን ስጋ ገንዘቡ ማድረጉን ለመግለፅ ነው
ትንቢተ ኢሳ 53:4-5 ; “በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ህማማችንንም ተሸክሟል” ይላል በለበሰው ስጋ መከራ ፣ ሀዘን፣ ጭንቀት፣ ሕማሙ ሁሉ ስለሚሰማው መከራ እየደረሰበት መሆኑን ለመግለፅ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ አለ፡፡ እኛ# ማቴ 8/16-17 “በመሸም ጊዜ አጋንንት ያደረባቸውን ብዙዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ በነቢዩ በኢሳይያስ፦ እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ የተባለው ≠ይፈጸም≠ ዘንድ፥ መናፍስትን በቃሉ አወጣ፥ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ።” ወዳጄ ልብ ይበሉ! በትንቢተ ኢሳያስ የተተነበየው ትንቢት ለኢየሱስ (ዐ.ሰ) ነው ከተባለ፣ ድውዮችን እንደሚፈውስ ከህመማቸውም እንደሚያጸዳቸው የተነገረና ትንቢቱም በዚያ እንደሚፈጸም እንጂ ቤዛ እንደሚሆን አይደለም፡፡ ማቴዎስ ራሱ ትንቢቱ ≠ይፈጸም ዘንድ≠ አጋንንት የያዛቸውን ሰዎች ወደርሱ አመጡ ፈወሳቸውም ብሎ ነው ያስነበበን፡፡ ወይ የናንተ ክርስቲያኖች ትርጉም ተዛብቷል ወይም ማቴዎስ ትንቢቱን በቅጡ አልተረዳውም- የትኛው ይሻላል? ሜሮን #4, ለአቅርቦተ ሰይጣን እኛ# ወዳጄ ይች ሙግት ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በብዛት እንደምትጠቀምበት ሳይታዘቡ አይቀርም፡፡ ሰይጣን ነፍስን ወደ ሲዖል ይወስድ ነበር፡፡ ኢየሱስ ም ይህን ያውቅ ስለነበር ልክ እንደ ተራ የሰው ልጅ “አምላኬ” አምላኬ” ብሎ ለመነ፡፡ ሰይጣንም ተጠጋውና ነፍሱን ሊወስዳት ሲል ቀጨም አድርጎ በንፋስ አውታር አሰረው….፡፡ ይህ ማለት በሌላ አባባል ኢየሱስ ሰይጣንን ሸውዶ አሰረው እንደማለት ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ይህ ሁሉ ትረካ መጽሐፍ-ቅዱስ ውስጥ አለመኖሩ ነው፡፡ ለዛም ነው ወዳጃችን ሜሮን ተመሳሳይ ጥቅስ እንኳ ሳታስቀምጥ የዘለለችው፡፡ መጽሐፋቸው የሚለን ይህንን ነው፡-“እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤” (ዕብራ 5/7)
ኢየሱስ ያሰማው ጩኸት ከሞት ለመዳን ከመፈለገ እንጂ ሰይጣንን ለመሸወድ አይደለም፡፡ ይልቁንም የሰይጣን ስም እዚህ ጋር አልተወሳም፡፡ ከኦርቶዶክስ እምነት ውጪ ያሉ ክርስትያኖችም ሰይጣንን ለማሳሳት የሚል አምክንዮ ሳይሆን “በስጋው ወራት” ስለሚል ሰብዓቢነቱንም ለማሳየት ነበር የሚል ሙግት ያቀርባሉ፡፡ ይህም ቢሆን ግን የሚያዋጣ አይደለም፡፡ “እንዴት?” ካሉ እነዚህን ትርጉሞች ይውረዷቸው፡- {New Living Translation} While Jesus was here on earth, he offered prayers and pleadings, with a loud cry and tears, to the one who could rescue him from death. And God heard his prayers because of his deep reverence for God. “ኢየሱስ ም ≠በምድር ሳለ≠ ጸሎትና ምልጃን አቀረበ…” {International Standard Version} As a mortal man, he offered up prayers and appeals with loud cries and tears to the one who was able to save him from death, and he was heard because of his devotion to God. “≠እንደ ሚሞትም ሰው≠ ጸሎትና ምልጃን አቀረበ…” በነዚህ ትርጉሞች ውስጥ “በስጋው ወራት” የሚል ሃረግ አይገኝም፡፡ ስለሆነም ሰብዓዊነቱን ለማሳየት ነበር የሚለው ሙግት ጠንካራ እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡ ቸር እንሰንብት