“ይህ የመርየም ልጅ ዒሳ ነው፡፡ ያ በርሱ የሚጠራጠሩበት እውነተኛ ቃል ነው”

ሼር ያድርጉ
612 Views

ኢሊያህ ማህሙድ

ذَٰلِكَ عِيسَى ابْنُ مَرْيَمَ ۚ قَوْلَ الْحَقِّ الَّذِي فِيهِ يَمْتَرُونَ

በኣላህ ስም እጅግ ኣዛኝ እጅግ ሩህሩህ በኾነው እንጀምራለን፡፡ ለጥቀንም በቀምቀሚያው(በመጨረሻው) ዘመን በተላኩ ነብይ ሙሓመድ (ሰ.ዐ.ወ) ላይ የኣላህ ሰላምና ሰሏት ይኹን ብለን እንቀጥላለን፡፡ ወዳጄ እንደምን ከረሙ… ዜናዎቻችን ኹሉ ልብ ሚሰብሩ እየኾኑ በምን ዙሪያ እንኳ መናገር እንዳለብን “ዓይን ኣዋጅ” እየኾነብን አለን፡፡ ኣንዳንዶች በትክክል ሰብዓዊ ማንነት እንደሌላቸው በሚጽፉት ያደፉ ቃላት እየነገሩን፣ በቃላት ያልገለጹትና በውስጣቸው ያመቁት የጥላቻ ክምር ምን ያህል የገዘፈ እንደኾነ በቀላሉ እንድንገምት አድርጎናል፡፡ ኣላህ በቃሉ አስቀድሞ እንዲህ ነግሮናል፡-

“ጥላቻይቱ ከአፎቻቸው በእርግጥ ተገለጸች፡፡ ልቦቻቸውም የሚደብቁት ይበልጥ ትልቅ ነው” ኣልዒምራን/118

ወዳጄ የዛሬው ወጋችን ርዕስ ባደረግነው ሐሳብ ይኹን፡፡ በሱረቱል መርየም ከቁጥር 16 ጀምሮ ስለ መርየም፣ከዚያም መልኣኩ ጂብሪል (ዐ.ሰ) እንዴት እንደመጣት፣ እንዴት እንደጸነሰችና ልጇንም አዝላ ወደ ሕዝቦቿ ከተሰወረችበት ሥፍራ እንደዘለቀች ያወጋል፡፡ ከሕዝቦቿ እንግዳ ስለኾነው ልጇ ምን ዓይነት ክስና ወቀሳ እንደቀረበባት፣መልሷም ምን ይመስል እንደነበር….ወዘተ ይተርካል፡፡ የሕጻኑን ዒሳ (ዐ.ሰ) አስደማሚ መልስ ካስቀደመ በኋላ፡-

“ይህ የመርየም ልጅ ዒሳ ነው፡፡ ≠ ያ በርሱ ≠ የሚጠራጠሩበት እውነተኛ ቃል ነው፡፡…”

“That is Jesus, the son of Mary – the word of truth ≠about which≠ they are in dispute…”

በማለት በሰዎች ዘንድ ለነበረው ጥርጣሬና ሙግት በቂ መልስ መስጠቱን በመጠቆም ረዥሙን ትረካ ያሳርፍና ይቀጥላል፡-

(ዒሳ አለ) «አላህም ጌታዬ ጌታችሁም ነውና ተገዙት፡፡ ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው፡፡ከመካከላቸውም አሕዛቦቹ ≠በእርሱ ነገር ተለያዩ≠፡፡ ለእነዚያም ለካዱት ሰዎች ከታላቁ ቀን መጋፈጥ ወዮላቸው፡፡ »

በዚህ ረዘም ባለው የዒሳና የእናቱ መርየም (ዐ.ሰ.) ትረካ ላይ “… ያ በርሱ የሚጠራጠሩበት እውነተኛ ቃል ነው…” የሚለውን ሐረግ በቀጥታ ለዒሳ (ዐ.ሰ.) ለራሱ በመስጠት ዒሳ ብቸኛ “ቃል” የተባለ ነብይ (ኣካል) ነው የሚል ሙግት ይነሳል፡፡ ሙግቱን በመጀመሪያ ከሰዋስው (ኢዕራብ) አኳያ ማየት ሐሳቡን ለመረዳት ቀላል ያደርገዋል፡፡
[ሰዋስው]

ብዙዎቻችን ይህንን ቃል “ሰዋሰው” ብለን እንጽፋለን እናነባለንም፡፡ ኾኖም ግን ትክክለኛ ቃሉ “ሰዋስው” ነው፡፡ ትርጉሙም መወጣጫ፣መሰላል ወይም መዳረሻ ማለት ሲኾን፣ ከቋንቋ አኳያ እያንዳንዱ ቃል በዓ/ነገር እንዴትና ለምን እንደገባ ለማወቅ የሚያዳርሰን መሰላል ነው፡፡ በዓረብኛ ቋንቋ “ኢዕራብ” የሚለው የእውቀት ዘርፍ የቃላትን የመጨረሻ ፊደል አለዋወጥ በማጥናት የቃላትን በዓ/ነገር አገባብ የምናውቅበት መንገድ ነው፡፡ኢዕራብ ከዓረብኛ ቋንቋ ውጭ ሌሎች ቋንቋዎች ላይ ለምሳሌ ኣማርኛና እንግሊዘኛ ላይ አይሰራም፡፡ ምክንያቱም በኣንድ ዓ/ነገር ውስጥ ባለቤት ኾኖ ያገለገለ ቃል፣በሌላ ዓ/ነገር ውስጥ ተሳቢ ሲኾን ቅርጹን አይለውጥም፡፡ “መሐመድ መጣ” በሚለው ዓ/ ነገርና “መሐመድን አየኹት” በሚለው ዓ/ነገር መካከል “መሐመድ” የሚለው ቃል ባለቤትም ኾኖ፣ ተሳቢም ኾኖ ያው መሐመድ ነው፡፡ የቅርጽ ለውጥ ኣላደረገም፡፡ በዓረብኛው ግን ይለያል፡፡ ኢዕራብ የሚባለውም በአጭሩ ይኸው ነው፡፡

ወደ ቁርኣ ጥቅስ ስንኼድ፡-

ذَٰلِكَ عِيسَى ابْنُ مَرْيَمَ ۚ قَوْلَ الْحَقِّ الَّذِي فِيهِ يَمْتَرُونَ

ذَٰلِكَ ≠ ይህ ቃል ኹለት ፊደላት ( ل ك) እና አመላካች ስምን ( ذا) የያዘ ሲኾን፣ “ላም” ፊደል ሩቅን ነገር ታመለክታለች፡፡ “ካፍ” ደግሞ እያናገርነው ያለ አካል መኖሩን የሚጠቁም ፊደል ነው፡፡ እዚህ ቦታ ላይ “ዛ” የሚለው ደግሞ አመላካች ስም ኾኖ በዚህ ዓ/ነገር ውስጥ “ሙብተዳእ” ይባላል፡፡ በቀላሉ የዓ/ነገር መጀመሪያ ብለን ልንረዳው እንችላለን፡፡ “ሙብተዳእ” ኹሌም መርፉዕ (ዷማና እሷን የሚተኳት- ኣሊፍ፣ ዋው፣ኑን ለመርፉዕ ምልክትነት ያገለግላሉ) ኾኖ ይመጣል፡፡ እዚህ ግር “ذا” የሚለው ቃል ምንም እንኳ የመጨረሻው ፊደል አሊፍ “ሳኪን” ኾኖ ቢመጣም፣ ቦታው የረፍዕ ስለኾነ፣ በረፍዕ ቦታ ስኩን የተደረገ” ብለን እንረዳዋለን፡፡

عِيسَى ≠ ይህ ቃል ለሙብተዳው “ኸበር” ወይም ዓ/ነገር ማጠቃለያ (ማሟያ) ነው፡፡
ابْنُ مَرْيَمَ  ≠ ይህ ቃል “ነዕት ወይም ሲፋ” (ቅጽል) ነው፡፡ ስለኾነም “ዒሳ ማነው…ወይም የቱ ዒሳ” ለሚለው ጥያቄ ግልጽ የኾነ መልስ የሚሰጥ ሐረግ ነው፡፡
قَوْلَ الْحَقِ ≠ “ቀውለ” የሚለው ቃል “መፍዑሉል ሙጥለቅ” ةفعول المطلق ይባላል፡፡ አገባቡም ዓ/ነገሩን ለማጠንከር ነው፡፡ ከፊት ለፊቱ ያልተነገረ ግን በውስጠ ተዋቂነት አለ፡፡ أقول የሚል ሌላ ቃል አለ፡፡ ትርጉሙም “እውነተኛውን ቃል እናገራለኹ أقول قول الحق የሚል ትርጉም አለው፡፡ ወዳጄ በዚህ “ኣያት” ዙሪያ ሌሎችም ኢዕራቦች ስላሉ “አቲብያን ፊ ኢዕራቢል ቁርኣን” የሚለውን ኪታብ ቅጽ 2 ገጽ 182 ይመለከቷል፡፡
ይህንን ጥቅስ ኢማሙ አጠበሪ በተፍሲራቸው ላይ እንዲህ ያተነትኑታል፡-
وَلَيْسَ الأَمْرُ فِي إِعْرَابِهِ عِنْدِي عَلَى مَا قَالَهُ الَّذِينَ زَعَمُوا أَنَّهُ رُفِعَ عَلَى النَّعْتِ لِعِيسَى ، إِلاَّ أَنْ يَكُونَ مَعْنَى الْقَوْلِ الْكَلِمَةَ …فَيَصِحُّ حِينَئِذٍ أَنْ يَكُونَ نَعْتًا لِعِيسَى ، وَإِلاَّ فَرَفْعُهُ عِنْدِي بِمُضْمَرٍ، —، وَذَلِكَ أَنَّ الْخَبَرَ قَدْ تَنَاهَى عَنْ قِصَّةِ عِيسَى وَأُمِّهِ عِنْدَ قَوْلِهِ {ذَلِكَ عِيسَى ابْنُ مَرْيَمَ} ثُمَّ ابْتَدَىء الْخَبَرَ بِأَنَّ الْحَقَّ فِيمَا فِيهِ تَمْتَرِي الأُمَمُ مِنْ أَمْرِ عِيسَى ، هُوَ هَذَا الْقَوْلُ ، الَّذِي أَخْبَرَ اللَّهُ بِهِ عَنْهُ عِبَادَهُ ، دُونَ غَيْرِهِ.
ለመረዳት እንዲመች ስንገረድፈው፡-
“ ከኢዕራብ አኳያ ሌሎች እንደሞገቱት “ቀውል” የሚለውን “ከሊመት” በሚለው ካልተረጎምነው በስተቀር “እውነተኛ ቃል”
የሚለው ለዒሳ ቅጽል ኾኖ የገባ አይደለም፡፡ “ከሊመት” በሚለው ከተረዳነው “እውነተኛ ቃል” የሚለው፣ ቅጽል መኾኑ ይመቻል፡፡ካልኾነ ግን “ቅጽል” ማድረጉ እኔ ዘንድ ግልጽ ትረጉም አይኖረውም፡፡ ትረካው ስለ ዒሳና እናቱ አውርቶ ተጠናቋል፤ እንዲህ በማለት “ይህ የመርየም ልጅ ዒሳ ነው…”፡፡ ከዚያም ሰዎች ከዒሳ አኳያ የሚጠራጠሩበትን ጉዳይ ጀመረና፣ትክክለኛው እዚህ ቦታ ላይ ኣላህ ለባሪያዎቹ የተናገረው እንደኾነ ይጠቁማል፡፡”

እዚህ ቦታ ላይ ኢማም አሸዕራዊ በተፍሲር አሸዕራዊ ለየት ያለ እይታ አላቸው፡፡ “አልሐቅ” የሚለው የኣላህ ስም ነው፡፡ “ቀውለል ሐቅ” ማለት “የኣላህ ቃል” የሚል ትርጉም ኣለው፡፡ ጥቅል ትርጉሙም፡-
“ሐቅ ኣላህ ነው፤ይህንን ታሪክ የተረከልህ ኣላህ ነው፤ንግግሩም እውነት ነው” የሚል ይኾናል፡፡

እንግዲህ ወዳጄ “እውነተኛ ቃል” የሚለው ከሰዋስው አኳያ ያለውን አገባብ በስርዓቱ ከተረዱ፣ ዒሳን የሚያመላክት ሳይኾን ኣላህ ስለዒሳ ያወራው ጉዳይ እውነተኛ መኾኑን የሚያሳይ ሐረግ ነው፡፡ ዒሳን ያመላክታል ካልንም፣ ትርጉሙ “ከሊመት” ከሚለው ጋር ስምሙ ነው፡፡ አስገንዝቦውም ዒሳም ኾነ ከኣላህ ውጪ ያሉ ነገሮች ኹሉ “ኹን” በሚል ቃል የተፈጠሩ እንጂ በራሳቸው የኣላህ ቃል አለመኾናቸውን ነው፡፡ የኣላህ ቃል ባሕሪው እንጂ ፍጡር አይደለምና፡፡ በቃሉ ኹሉን እንዳስገኘ፣ ዒሳንም እንደዚሁ አስገኝቷል የሚል ምልከታ አለው፡፡

في آمان الله

 

Shortlink http://q.gs/Eye4v