የጠፉ የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍሎች

ሼር ያድርጉ
312 Views

“የጠፉ የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍሎች” የሚለውን አርዕስት ስትመለከቱ ምናልባት ፀሀፊዎቻቸው ስለማይታወቁ የመፅሀፍ ቅዱስ ክፍሎች አስመልክቶ የቀረበ ፁሁፍ መስሎ ሊታያችሁ ይችላል። በርግጥ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ፀሀፊያቸው የማይታወቅ በርካታ መፅሀፍቶች አሉ። ከሙሴ ኦሪት ጀምሮ አብዛኛው የይዘቱ ክፍል በማን እንደተፃፈ በትክክል አይታወቅም። ነገር ግን ዛሬ የምናወራው ከዛም ስለከፋ ነገር ነው። ይኸውም የመጽሀፉ ህልውና በስያሜ ደረጃ ተነግሮ ነገር ግን ያ የተነገረው መፅሀፍ ከነ አካቴው የት እንዳለ ስለማይታወቅ መጽሀፍ ነው። መሠል ንግግሮች መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ተደጋግመው ተጠቅሰው እናገኛለን። ለአብነት ጥቂቶችን ከታች ለመጥቀስ እሞክራለሁ፦

1- የእግዚአብሔር የጦርነት መጽሀፍ

❝ስለዚህ በእግዚአብሔር የጦርነት መጽሐፍ እንዲህ ተባለ፦ ዋሄብ በሱፋ፥ የአርኖንም ሸለቆች፥❞ ዘኍልቁ 21: 14

❐ እግዚአብሔር የጦርነት መጽሀፍ እንደነበረው መስማት አስደናቂ ቢሆንም እንዳለመታደል ሁኖ ግን ይህ መጽሀፍ አሁን ላይ የውሃ ሽታ ሁኗል። መጽሀፉ እንደነበረ ተገለፀልን እንጅ መጽሀፉ የት እንደገባ አይታወቅም..!

2- የሰለሞን ታሪክ

❝የቀረውም የሰሎሞን ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጥበቡም፥ እነሆ፥ በሰሎሞን ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።❞ 1ኛ ነገሥት 11: 41

❐ ይህ የሰለሞን ታሪክ መፅሀፍ ከወዴት ይገኛል?

3- የያሻር መጽሀፍ

❝ሕዝቡም ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሐይ ቆመ፥ ጨረቃም ዘገየ። ይህስ በያሻር መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ፀሐይም በሰማይ መካከል ዘገየ፥ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል ለመግባት አልቸኰለም።❞
ኢያሱ 10: 13

በተጨማሪም

❝የይሁዳንም ልጆች ያስተምሩ ዘንድ አዘዘ። እነሆ፥ ይህ በያሻር መጽሐፍ ተጽፎአል።❞
2ኛ ሳሙኤል 1: 18

❐ የያሻር መጽሀፍ አሁን ታዲያ መገኛው ወዴት ነው?

4- የጠፉ የሰለሞን ምሳሌዎችና መኃልዬች

❝እርሱም ሦስት ሺህ ምሳሌዎች ተናገረ፤ መኃልዩም ሺህ አምስት ነበረ።❞
1ኛ ነገሥት 4: 32

❐ እነዚህ መፅሀፍት ወዴት ይሆን የሚገኙት?

5- የነብዩ ናታን ታሪክና የባለራእዩ የአዶ ራእይ

❝የቀረውም ፊተኛውና ኋለኛው የሰሎሞን ነገር በነቢዩ በናታን ታሪክ፥ በሴሎናዊውም በኦሒያ ትንቢት፥ ስለ ናባጥም ልጅ ስለ ኢዮርብዓም ባየው በባለ ራእዩ በአዶ ራእይ የተጻፈ አይደለምን?❞ 2 ዜና 9: 29

❐ የነብዩ ናታን ታሪክና የባለራእዩ የአዶ ራእይስ ከወዴት ይገኛል?

6- የነብዩ ሸማያና የአዶ የትውልድ ታሪክ መጽሀፍ

❝የሮብዓምም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር በነቢዩ ሸማያና በባለ ራእዩ በአዶ የትውልድ ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከልም በዘመናቸው ሁሉ ሰልፍ ነበረ።❞ 2 ዜና 12: 15

Mm የነብዩ ሸማያና የአዶ የትውልድ ታሪክ መጽሀፍ አሁን ከወዴት ይገኛል?

7- የነብዩ ኢሳያስ ድርሳን

❝የቀረውንም የፊተኛውንና የኋለኛውን የዖዝያንን ነገር ነቢዩ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ጽፎታል።❞ 2 ዜና 26: 22

❐ ነብዩ ኢሳያስ የቀረውን የዖዝያንን ነገር የጻፈበት ድርሳኑስ ከወዴት ይገኛል?

8- የሳሙኤል፣የናታንና የጋድ ታሪክ

❝የንጉሡም የዳዊት የፊተኛውና የኋለኛው ነገር፥ እነሆ፥ በባለ ራእዩ በሳሙኤል ታሪክ፥ በነቢዩም በናታን ታሪክ፥ በባለ ራእዩም በጋድ ታሪክ ተጽፎአል።❞
1 ዜና 29: 29

❐ የሳሙኤል፣የናታንና የጋድ ታሪክ አሁን ላይ ከወዴት ይገኛሉ?

◼ ሲጠቃለል

ይህ ብዙ ትንተና ሳያስፈልገው በግልጽ ቋንቋ የነኝህ ሰዎችና ነብያት ራዕይና ድርሳን ጠፍቷል፡፡ የነብያት ጹሁፍና ራእያቸው አይጠፋም እያሉ የሚከራከሩን ክርስቲያኖች እነዚህ ስያሜያቸው ብቻ ለታሪክ የቀሩ መጽሀፍቶች እንዴት ከምድረ ገፅ ሊጠፉ እንደቻሉ ሊነግሩን ይችላሉ?

(የሕያ ኢብኑ ኑህ)