የወንጌሉ ኢየሱስና ስህተቶቹ

ሼር ያድርጉ
726 Views

የወንጌሉ ኢየሱስ የገበሬ ስራዎችን አስመልክቶ አስተያየት ሲሰጥም ሆነ ተግባራትን ሲያከናውን በተደጋጋሚ ስህተት ውስጥ ይወድቃል። የበለስ ወር መሆኑን ባለማወቁ ምክንያት ወደ በለሷ ሒዶ እንዳሰበው ሳይሆን በለስ ባለማግኘቱ ምክንያት ያችን ሚስኪን በለስ ረግሟታል።

“ቅጠልም ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ምናልባት አንዳች ይገኝባት እንደ ሆነ ብሎ መጣ፥ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና መጥቶ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። መልሶም፦ ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ አላት። ደቀ መዛሙርቱም ሰሙ።” (ማርቆስ 11፥13-14)

“በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና፦ ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት። በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች።”
ማቴዎስ 21፥19

የበለሷ ጥፋት ምን እንደሆነ ባይገለፅም ለሱ ስህተት ግን ሌላውን ተወቃሽ ያደረገ አሳዛኝ ውሳኔ ሲያስተላልፍ እናያለን። ክርስቲያኖች “አምላክ” የሚሉት አካል መሳሳቱ ሳይሆን ለስህተቱ ሌላውን ሲቀጣ ማየትም ፍትሐዊነቱ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።

ከላይ ካነሳነው ሀሳብ በተጨማሪ ኢየሱስ ሲናገር እንዲህ ይላል፦

“እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፥ እርስዋም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ ታንሳለች፤ በተዘራችም ጊዜ ትወጣለች ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፥”
— ማርቆስ 4፥31

ኢየሱስ በዚህ አንቀጽ እንደሚነግረን በምድር ካለ ዘር ሁሉ የሚያንሰው ሰናፍጭ እንደሆነ ነው። ይህ ደግሞ ፈጽሞ ስህተት ነው። ዛሬ ሳይንስ እንደሚነግረን ከሰናፍጭም በታች በአይናችን እንኳን ልናያቸው የማንችላቸው 85 ማይክሮ ሜትር ወይንም 0.81 ማይክሮግራም ድረስ የሚመዝኑ ጥቃቅን ዘሮች ይገኛሉ። ይህንን ሳያውቁ በደፈናው “በምድር ካለ ዘር ሁሉ ያንሳል” ማለት የእውቀት ክፍተት ነው። አይደለም አምላክ የሚባል አካል ይቅርና በአምላክ የተላከ እውነተኛ ነብይ እንኳን ይፈጽመዋል ተብሎ የማይጠበቅ ስህተት ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች እንደመከራከሪያ “ይህንን የተናገረው በወቅቱ ለነበሩ የፍልስጤም ሰዎች እንዲገባቸው ነው” ሲሉ ያቀርባሉ።

ይህም ግን ሌላ ስህተት ነው። የመጀመሪያ ነገር ሰዎቹ የሚያውቁት ትንሹ ዘር ብሎ መግለጽና የምድራችን ትንሹ ዘር ብሎ መግለጽ ሁለቱ የተለያዩ ሀሳቦች ናቸው። ሲቀጥል እንደ ፕሮፌሰር ኦልሰን ገለፃ በወቅቱ እንኳን በፍልስጤም ምድር ከዚህ ያነሱ ሌሎች ለምሳሌ መቅረብ የሚችሉ ዘሮች ነበሩ። ያም ሁኖ ግን እነዛንም ዘሮች “የምድር ትንሹ ዘር” ካላቸው የስህተቱ ችግር እሱ ጋር ነው ያለው ማለት ነው።

በዚህም አለ በዚያ ይህንን ንግግሩን አስመልክቶ ሊያብራራ የሚችል አመኔታዊ ሙግት ማቅረብ አዳጋች ነው። ምክንያቱም ኢየሱስ ሀሳቡን “ከምድር ዘር ሁሉ” በሚል ጥቅል የስህተት ድምዳሜ አስሮታል። መሠል ስህተቶችን ጌታ ከተባለ አካል ይቅርና ጎበዝ ከሚባል ሳይንቲስት እንኳን ቢገኝ ያሳፍራል።

(የሕያ አብኑ ኑህ)

____

ተጨማሪ ንጽጽራዊ ትምህርቶችን ለመከታተል

❐ በቴሌግራም t.me/yahya5

❐ በፌስቡክ facebook.com/yahyanuhe/

❐ በድህረ ገጽ www.ethio-islamic.org