የኢንጅልም ባለቤቶች በውስጡ አላህ ባወረደው ሕግ ይፍረዱ…”

ሼር ያድርጉ
115 Views

ኢሊያሕ ማሕሙድ

በአላህ ስም እጅግ አዛኝ እጅግ ሩህሩህ በሆነው እንጀምርና እንቀጥላን፡፡ ወዳጄ ዛሬ እንደወትሮው ሁሉ “ብላኤ ሰብ ዘክርስትያን” በሚል የጀመርነውን እንቀጥል ዘንድ አሰብኩና ግን ከሰሞኑን ባየሁት አንድ እንግሊዘኛ ውይይት ተበሳጭቼም ተደስቼም ስለነበር ያንኑ ርእስ ማድረግ መልካም መስሎ ታየኝ፡፡
አላህ በቃሉ እንዲህ ይላል፡-
“እኛ ተውራትን በውስጥዋ መምሪያና ብርሃን ያለባት ስትኾን አወረድን፡፡ እነዚያ ትዕዛዝን የተቀበሉት ነቢያት በእነዚያ አይሁዳውያን በኾኑት ላይ በርሷ ይፈርዳሉ፡፡ ሊቃውንቱና ዐዋቂዎቹም ከአላህ መጽሐፍ እንዲጠብቁ በተደረጉትና በርሱም ላይ መስካሪዎች በኾኑት (ይፈርዳሉ)፡፡ ሰዎችንም አትፍሩ፡፡ ፍሩኝም፡፡ በአንቀጾቼም አነስተኛን ዋጋ አትለውጡ፡፡ አላህም ባወረደው ነገር ያልፈረደ ሰው እነዚያ ከሓዲዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡ በእነርሱም ላይ በውስጧ «ነፍስ በነፍስ ዓይንም በዓይን አፍንጫም በአፍንጫ ጆሮም በጆሮ ጥርስም በጥርስ (ይያዛል)፡፡» ቁስሎችንም ማመሳሰል አለባቸው ማለትን ጻፍን፡፡ በእርሱም የመጸወተ (የማረ) ሰው እርሱ ለርሱ (ለሠራው ኃጢአት) ማስተሰሪያ ነው፡፡ አላህም ባወረደው ነገር የማይፈርድ ሰው፤ እነዚያ በደለኞቹ እነርሱ ናቸው፡፡
በፈለጎቻቸውም (በነቢያቶቹ ፈለግ) ላይ የመርየምን ልጅ ዒሳን ከተውራት በስተፊቱ ያለውን አረጋጋጭ ሲኾን አስከተልን፡፡ ኢንጂልንም በውስጡ ቀጥታና ብርሃን ያለበት በስተፊቱ ያለችውን ተውራትንም የሚያረጋግጥ ለጥንቁቆችም መሪና ገሳጭ ሲኾን ሰጠነው፡፡ የኢንጅልም ባለቤቶች በውስጡ አላህ ባወረደው ሕግ ይፍረዱ፡፡ አላህም ባወረደው የማይፈርድ ሰው እነዚያ አመጸኞች እነርሱ ናቸው፡፡ ‘’ አልማዒዳ 43-46
ዛሬ ዛሬ ክርስታን ወገኖች እነዚህን ጥቅሶች በመያዝ “እነሆ ቁርዓን በወንጌል ፍረዱ ማለቱ ወንጌል አለመበረዙን ያስረግጣል፤ከተበረዘ ለምንድነው በርሱ ፍርዱ የተባለው፤ በወንጌል ፍረዱ ሲል ወንጌል ትክክለኛና እስከአሁንም ድረስ ሊ’ሰራበት የሚገባ የፈጣሪ ቃል መሆኑን ያስረግጣል…” የሚሉ ወዘተረፈ ሙግቶችን አመክንዮአዊ ሆነው ሲሰነዝሩ ይታያል፡፡ አንዳንዶቹ እንድያውም አበክረው “ ወንጌል ተበርዟል የምትሉን ከሆነ፣ እንግድያውስ ቁርዓን በተሳሳተ መጽሃፍ ነው ፍረዱ የሚለን፤ ስለሆነም ቁርዓን መለኮታዊ አይደለም፡፡ ቁርዓን መለኮታዊ ከሆነ ደግሞ እንድንፈርድበት የተጠቆምነው ወንጌልም ትክክልና መለኮታዊም ነው” በማለት ሙግታቸውን ያጸናሉ፡፡
ወዳጄ ምናልባት እርሶም የለጠፍኩትን አማርኛ ትርጉም አንብበው “ልክ ነው” ወይም “ሙግቱ የሚያስኬድ ይመስላል” ሊሉ ይችል ይሆናል፡፡ ግና ሁላችንም ልብ ልንል የሚገባው አማርኛውም ሆነ ሌሎች ትርጉሞች ተመጣጣኝ ቃል ለማስቀመጥ የሞከሩ እንጂ አውዳዊ ትርጉሙንም ሆነ ሰዋሰዋዊ አገባቡን በመተንተን ዝርዝርና ጥልቅ ሃሳቡን ለማስጨበጥ የተተረጎሙ አይደሉም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ምናልባት ሰዋሰዋዊና አውዳዊ አገባቡን በጥልቀት ለመዘርዘር ቢሞክር ጭብጡ ለአብዛኛው ሰው የሚርቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምንም ግን ቀጥታ የቃል በቃል ትርጉሞች በምንም መልኩ ምሉዕ ትርጉሙን ሊያስጨብጡን አይችሉም፡፡ በምልዐት(በጥቅል) ግን እንድንረዳ ሚናቸው የጎላ ነው፡፡
ወደ ጥቅሶቹ ስንመለስ፡-
إِنَّا أَنزَلْنَا التَّوْرَاةَ فِيهَا هُدًى وَنُورٌ ۚ يَحْكُمُ بِهَا النَّبِيُّونَ الَّذِينَ أَسْلَمُوا لِلَّذِينَ هَادُوا وَالرَّبَّانِيُّونَ وَالْأَحْبَارُ بِمَا اسْتُحْفِظُوا مِن كِتَابِ اللَّهِ وَكَانُوا عَلَيْهِ شُهَدَاءَ ۚ فَلَا تَخْشَوُا النَّاسَ وَاخْشَوْنِ وَلَا تَشْتَرُوا بِآيَاتِي ثَمَنًا قَلِيلًا ۚ وَمَن لَّمْ يَحْكُم بِمَا أَنزَلَ اللَّهُ فَأُولَٰئِكَ هُمُ الْكَافِرُونَ*وَكَتَبْنَا عَلَيْهِمْ فِيهَا أَنَّ النَّفْسَ بِالنَّفْسِ وَالْعَيْنَ بِالْعَيْنِ وَالْأَنفَ بِالْأَنفِ وَالْأُذُنَ بِالْأُذُنِ وَالسِّنَّ بِالسِّنِّ وَالْجُرُوحَ قِصَاصٌ ۚ فَمَن تَصَدَّقَ بِهِ فَهُوَ كَفَّارَةٌ لَّهُ ۚ وَمَن لَّمْ يَحْكُم بِمَا أَنزَلَ اللَّهُ فَأُولَٰئِكَ هُمُ الظَّالِمُونَ وَقَفَّيْنَا عَلَىٰ آثَارِهِم بِعِيسَى ابْنِ مَرْيَمَ مُصَدِّقًا لِّمَا بَيْنَ يَدَيْهِ مِنَ التَّوْرَاةِ ۖ وَآتَيْنَاهُ الْإِنجِيلَ فِيهِ هُدًى وَنُورٌ وَمُصَدِّقًا لِّمَا بَيْنَ يَدَيْهِ مِنَ التَّوْرَاةِ وَهُدًى وَمَوْعِظَةً لِّلْمُتَّقِينَ وَلْيَحْكُمْ أَهْلُ الْإِنجِيلِ بِمَا أَنزَلَ اللَّهُ فِيهِ ۚ وَمَن لَّمْ يَحْكُم بِمَا أَنزَلَ اللَّهُ فَأُولَٰئِكَ هُمُ الْفَاسِقُونَ*ወዳጄ እስኪ እነዚህን ግሶች ልብ ብለው ያንብቧቸውእና “أَنزَلْنَا” “وَكَتَبْنَا” “وَقَفَّيْنَا” እና “وَآتَيْنَاهُ” በአማርኛ “አወረድን“ “ጻፍን” “አስከተልን” እና “ሰጠነው” የሚል ትርጉም ሲኖራቸው በሶስቱ ግሶች ላይ “ወው” ፊደል አያያዥ መስተጻምር (ሃርፉል ዓጥፍ ዓለል መካን ወልሃል) ሆኖ ገብቷል፡፡ በሚቀጥለው ጥቅስ ላይ “ወልየህኩም” ከሚለው ግስ ጋር ተያይዞ አሁንም “ ወው” አያያዥ መሰተጻምር ሆኖ ዳግም የገባ ሲሆን ካለፉት ግሶች ጋር የተያያዘው ግስ ግን የተደበቀ (ሙስተቲር) ሆኖ ነው ያለው፡፡
“ወልየህኩም” በሚለው ግስ ውስጥ ያለው “ላም” ፊደል እዚህ ቦታ ላይ በሁለት መልኩ ተቀርቷል፡፡ አንደኛው ቂርዓት “ላምን” መጅዙም (ሳኪና) በማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ቂርዓት ደግሞ “ላምን” ከስራ በማድረግ የሚነበብ ነው፡፡ በነዚህ በሁለቱ ቂርዓት መካከል የሰዋሰው ስያሜአዊ ልዩነት ቢኖርም ከትርጉም አኳያ ተመሳሳይ መልዕክት አላቸው፡፡
የመጀመሪያው ሳኪና የሆነው “ላም” “ላሙል አምር” የሚባለው ሲሆን ከዚህ “ላም” ጋር ተያይዞ የሚመጣው ግስ ትዕዛዛዊ ይሆናል፡፡ ከዚህ አኳያ “ወልየህኩም” የሚለው ግስ ትርጉሙ “ይፍረዱ” የሚል ትዕዛዛዊ ስሜት አለው፡፡ አስቀድመን እንዳወራነው “ወው” ፊደል አያያዥ ሆኖ መጥቷል፡፡ ከዚህ አኳያ ከቀደሙት ግሶች ጋር “ወው” ፊደልን አያይዥ መስተጻምር አድርገን ስንተረጉመው ፡- “እኛ ተውራትን በውስጥዋ መምሪያና ብርሃን ያለባት ስትኾን አወረድን…የመርየምን ልጅ ዒሳን ከተውራት በስተፊቱ ያለውን አረጋጋጭ ሲኾን አስከተልን…የኢንጅልም ባለቤቶች በውስጡ አላህ ባወረደው ሕግ ይፍረዱ (ብለን አዘዝናቸው)፡፡ የሚል አውዱን የጠበቀ ትርጉም ይሰጠናል፡፡ የተወረደላቸውን መጽኃፍ -ኢንጂልን- ይፈርዱበት ዘንድ የታዘዙት ያኔ በዒሳ (ዐ.ሰ) ዘመን እንደሆነ ከአውዱ በቀጥታ መረዳት ይቻላል፡፡ እዚህ ጋር በቅንፍ ውስጥ “ብለን አዘዝናቸው” የሚለው ሃረግ እላይ ሙስተቲር ብለን ያልነው ለመሆኑ ልብ ይሏል!!!
ሁለተኛው ቂርዓት ደግሞ “ላም” መክሱር ሆኖ የሚመጣበት ሲሆን ይህንን ደግሞ የሰዋሰው ልሂቃን “ላሙ ከይ” ብለው ይጠሩታል፡፡ ምክንያት አመላካች እንደማለት ነው፡፡ እንግዲህ ከዚህ ምክንያት አመልካች ከሆነው “ላም” አኳያ አውዱን ጠብቀን ስንተረጉመው ፡-“እኛ ተውራትን በውስጥዋ መምሪያና ብርሃን ያለባት ስትኾን አወረድን…የመርየምን ልጅ ዒሳን ከተውራት በስተፊቱ ያለውን አረጋጋጭ ሲኾን አስከተልን…የኢንጅልም ባለቤቶች በውስጡ አላህ ባወረደው ሕግ ይፍረዱ (ዘንድ ኢንጂልን አወረድነው)፡፡ የሚል ትርጉም ይኖረዋል፡፡
ወዳጄ በሁለቱም ቂርዓቶች የኢንጂል ባለቤቶች “ፍረዱ” የተባሉት በቀደመው ዘመናቸው እንደነበር አሁን ግልጽ የሆነሎ መሰለኝ፡፡ በተጨማሪም ኢንጂል እስከአሁንም ድረስ በአላህ (ሰ.ወ) ተጠብቋል የሚለው ሙግት ውድቅ መሆኑንም አክለው ይረዱ፡፡ ለዚህ መደምደሚያችን ከጀመርናቸው የቁርዓን ጥቅሶች ሳንወጣ አንድ አስደናቂ ቃል ደግሞ ጠጋ ብለን እንመርምር፡፡
በመጀመሪያው ጥቅስ ላይ اسْتُحْفِظُو (ኢስቱህፊዙ) የሚል ቃል እናነባለን፡፡ ይህ ቃል ተመጣጣኝ አማርኛዊ ትርጓሜው “እንዲጠብቁ ተደረጉ፣ ተጠየቁ” የሚል ሲሆኑ ከግልብ ትርጉሙ ተነስተን ብቻ ለኢንጂል ጥበቃ አላህ ዋስትና እንዳልወሰደ ይልቁንም ጥበቃው ለራሳቸው ለአማኞቹና ለልሂቃኑ እንደተተወ በቀላሉ መረዳት እንችላለን፡፡ በግልጽ እንደምናየው በአረብኛው ቃል ውስጥ “ሲን” እና “ታ” የሚባሉ ፊደላት አሉ፡፡ እነዚህ ፊደላት ግስ ላይ ተቀጥላ ሆነው ሲገቡ ግሱ ጥያቄንና ፍላጎትን (ጠለብን) ያመላክታል፡፡ ይህ ማለት አሁንም ከአውዱ አኳያ ስንረዳው “ኢንጅልን እራሳችሁ መጠበቅ የግድ ይላችኋል” የሚል የመጠበቅ ጥያቄ እንደቀረበላቸው ይጠቁማል፡፡ በአጠቃላይ በዚህ መልኩ ባለቤታቸው ሳይጠቀስ የሚነገሩ ግሶች (ናኢቡ ፋዒል) አድራጊ ባለቤቶቹ የተለያዩ አካላት እንደሆኑ ሊያመላክቱ ይችላል፡፡ ለምሳሌ እዚህ ጋር “ኢስቱህፊዙ” ወይም “እንዲጠብቁ ታዘዙ” በሚለው ቃል ውስጥ ማን ጠብቁ አላቸው የሚለው አልተጠቀሰም፡፡ ስለሆነም እንዲጠብቁ ያዘዛቸው በመጀመሪያ ደረጃ አላህ (ሰ.ወ) ከዚያም መልዕክተኞቹ ሙሳና ዒሳ (ዐ.ሰ) ከዚያም በነሱ ስር የነበሩት ልሂቃኑ በተመሳሳይ መልኩ ለተራው ተከታይ ጥበቃውን አሳስበዋል ማለት ነው፡፡
ወዳጄ በውይይቱ መበሳጨቴ ተወያዮቹ አጥጋቢ መልስ ማጣታቸውን ሳይ፤ መደሰቴ ደግሞ ጉዳዩ ወገኖቻችን እንደሚረዱት ስላልሆነ ነበር፡፡ ቸር እንሰንብት!!!