የኢስላም መልእክት “ላ ኢላሀ ኢልለሏህ” ክፍል -1

ሼር ያድርጉ
595 Views

በኡስታዝ አቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

1. አስፈላጊነቱ፡-

ሰዎች ስለ “ላ ኢላሀ ኢልለሏህ” መማርና ማወቅ የሚያስፈልጋቸው ለምንድነው? የሚል ጥያቄ ቢነሳ መልስ መስጠት ያስችለን ዘንድ መጠነኛ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል፡፡ እኛ ስለ “ላ ኢላሀ ኢልለሏህ” መማርና ማወቅ ያስፈልጋል ከምንልበት ምክንያቶች መካከል፡-

ሀ. ነቢያት ሁሉ የተላኩበት ዋና ዓላማና ግብ መሆኑ፡-

አላህ ከሰዎች መካከል ሰዎችን መርጦ፡ የመረጣቸውን ሰዎች ነቢያትና መልክተኛ አድርጎ ወደ ህዝቦቻቸው ሲልካቸው በዋነኝነት እንዲያስተምሩ ያዘዛቸው “ላ ኢላሀ ኢልለሏህ” የሚለውን የእምነት ቃል ነው፡፡ ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡-

” ﻳُﻨَﺰِّﻝُ ﺍﻟْﻤَﻠَﺎﺋِﻜَﺔَ ﺑِﺎﻟﺮُّﻭﺡِ ﻣِﻦْ ﺃَﻣْﺮِﻩِ ﻋَﻠَﻰ ﻣَﻦْ ﻳَﺸَﺎﺀُ ﻣِﻦْ ﻋِﺒَﺎﺩِﻩِ ﺃَﻥْ ﺃَﻧْﺬِﺭُﻭﺍ ﺃَﻧَّﻪُ ﻟَﺎ ﺇِﻟَﻪَ ﺇِﻟَّﺎ ﺃَﻧَﺎ ﻓَﺎﺗَّﻘُﻮﻥِ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻨﺤﻞ 2
“ከባሮቹ በሚሻው ሰው ላይ መላእክትን ከራእይ ጋር በፈቃዱ ያወርዳል፤ (ከሐዲዎችን በቅጣት) አስጠንቅቁ፤ እነሆ ከኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም ፍሩኝም ማለትን (አስታውቁ በማለት ያወርዳል)።” (ሱረቱ-ነሕል 2)፡፡

” ﻭَﻟَﻘَﺪْ ﺑَﻌَﺜْﻨَﺎ ﻓِﻲ ﻛُﻞِّ ﺃُﻣَّﺔٍ ﺭَﺳُﻮﻟًﺎ ﺃَﻥِ ﺍﻋْﺒُﺪُﻭﺍ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻭَﺍﺟْﺘَﻨِﺒُﻮﺍ ﺍﻟﻄَّﺎﻏُﻮﺕَ ﻓَﻤِﻨْﻬُﻢْ ﻣَﻦْ ﻫَﺪَﻯ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻭَﻣِﻨْﻬُﻢْ ﻣَﻦْ ﺣَﻘَّﺖْ ﻋَﻠَﻴْﻪِ ﺍﻟﻀَّﻠَﺎﻟَﺔُ ﻓَﺴِﻴﺮُﻭﺍ ﻓِﻲ ﺍﻟْﺄَﺭْﺽِ ﻓَﺎﻧْﻈُﺮُﻭﺍ ﻛَﻴْﻒَ ﻛَﺎﻥَ ﻋَﺎﻗِﺒَﺔُ ﺍﻟْﻤُﻜَﺬِّﺑِﻴﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻨﺤﻞ 36
“በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ፤ በማለት መልክተኛን በእርግጥ ልከናል፤ ከነሱም ውስጥ አላህ ያቀናው ሰው አልለ፤ ከነሱም ውስጥ በርሱ ላይ ጥመት የተረጋገጠበት ሰው አለ፤ በምድርም ላይ ኺዱ፤ የአስተባባዮችም መጨረሻ እንዴት እንደ ነበረ ተመልከቱ።” (ሱረቱ-ነሕል 36)፡፡

” ﻭَﻣَﺎ ﺃَﺭْﺳَﻠْﻨَﺎ ﻣِﻦْ ﻗَﺒْﻠِﻚَ ﻣِﻦْ ﺭَﺳُﻮﻝٍ ﺇِﻟَّﺎ ﻧُﻮﺣِﻲ ﺇِﻟَﻴْﻪِ ﺃَﻧَّﻪُ ﻟَﺎ ﺇِﻟَﻪَ ﺇِﻟَّﺎ ﺃَﻧَﺎ ﻓَﺎﻋْﺒُﺪُﻭﻥِ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻷﻧﺒﻴﺎﺀ 25
“ከአንተ በፊትም፣ እነሆ ከኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ፣ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢሆን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም።” (ሱረቱል አንቢያእ 25)፡፡

” ﻭَﺍﺳْﺄَﻝْ ﻣَﻦْ ﺃَﺭْﺳَﻠْﻨَﺎ ﻣِﻦْ ﻗَﺒْﻠِﻚَ ﻣِﻦْ ﺭُﺳُﻠِﻨَﺎ ﺃَﺟَﻌَﻠْﻨَﺎ ﻣِﻦْ ﺩُﻭﻥِ ﺍﻟﺮَّﺣْﻤَﻦِ ﺁﻟِﻬَﺔً ﻳُﻌْﺒَﺪُﻭﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺰﺧﺮﻑ 45
“ከመልክተኞቻችንም ካንተ በፊት የላክናቸውን (ተከታዮቻቸውን) ከአልረሕማን ሌላ የሚገዙዋቸው የሆኑን አማልክት አድርገን እንደሆነ ጠይቃቸው።” (ሱረቱ-ዙኽሩፍ 45)፡፡

2. ወደ ኢስላም መግቢያ በር በመሆኑ፡-

የአንድ ሰው እስልምና የሚረጋገጠው በሸሀደተይን ነው፡፡ ይህን የምስክርነት ቃል በአንደበቱ በመግለጽ ያልመሰከረ ሰው (ከዲዳዎች በስተቀር) ሙስሊም ሊባል አይችልም፡፡ ላ ኢላሀ ኢልለሏህ ከኩፍር ወደ ኢስላም መሸጋገሪያ ድልድይ ናትና፡-
የአላህ መልክተኛ(ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሙዐዝ ኢብኑ ጀበልን ወደ የመን በላኩት ጊዜ እንዲህ ነበር ያሉት፡- “አንተ የመጽሐፉ ሰዎች (አይሁድና ክርስቲያን) ወደሆኑት ትመጣለህና የመጀመሪያ ጥሪህ፡- አላህን በብቸኝነት እንዲያመልኩት ይሁን…” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡

3. ከዕውቀት ሁሉ በላጭ መሆኑ፡-

የሰው ልጅ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን ከማወቅ የበለጠ ዕውቀት አልተሰጠውም፡፡ የዕውቀት ደረጃ የሚለካው በሚታወቀው ነገር ልክ ከሆነ፡ ከአላህ የሚበልጥ ክብር ያለው ነገር የለምና፡ ስለ አላህም ማወቅ ከዕውቀቶች ሁሉ በላጭና ተቀዳሚ ተግባር ይሆናል ማለት ነው፡-

” ﻓَﺎﻋْﻠَﻢْ ﺃَﻧَّﻪُ ﻟَﺎ ﺇِﻟَﻪَ ﺇِﻟَّﺎ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻭَﺍﺳْﺘَﻐْﻔِﺮْ ﻟِﺬَﻧْﺒِﻚَ ﻭَﻟِﻠْﻤُﺆْﻣِﻨِﻲﻥَ ﻭَﺍﻟْﻤُﺆْﻣِﻨَﺎﺕِ ﻭَﺍﻟﻠَّﻪُ ﻳَﻌْﻠَﻢُ ﻣُﺘَﻘَﻠَّﺒَﻜُﻢْ ﻭَﻣَﺜْﻮَﺍﻛُﻢْ ” ﺳﻮﺭﺓ ﻣﺤﻤﺪ 19
“እነሆ ከአላህ ሌላ አምላክ አለመኖሩን ዕወቅ፤ ስለ ስሕተትም ለምእመናንም ምሕረትን ለምን፤ አላህም መዘዋወሪያችሁን መርጊያችሁንም ያውቃል።” (ሱረቱ ሙሐመድ 19)፡፡

4. ጀነት የመግቢያ ሰበብ መሆኑ፡-

የመጨረሻ ህይወቱ ተስተካክሎ ፍጻሜው በ ላ ኢላሀ ኢልለሏህ የተጠናቀቀለት ሙስሊም የጀነት ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡-
ሙዐዝ ኢብኑ ጀበል(ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ(ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “የመጨረሻ ንግግሩ ላ ኢላሀ ኢልለሏህ የሆነ ሰው ጀነት ገባ” (አቡ ዳዉድ 3118፣ አሕመድ 22087)፡፡

5. በሚዛን ላይ ታላቅ መሆኑ፡-

የ ላኢላሀ ኢለሏህ ደረጃን ሊስተካከልና ሊመዝን የሚችል አንድም ኸይር ስራ የለም ሊኖርም አይችልም፡፡ ከስራዎች ሁሉ በላጭ በሚዛንም ታላቅ ነውና፡-
አቢ-ሰዒድ አል-ኹድሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ(ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ሙሳ(ዐለይሂ ሰላም) እንዲህ አለ፡- ‹‹ጌታዬ ሆይ! አንተን የማወድስበትና የምማጸንበት የሆነ የዚክር ቃልን አሳውቀኝ›› ጌታችንም፡- ‹‹ሙሳ ሆይ! ላ ኢላሀ ኢልለሏህ በል›› አለው፡፡ ሙሳም፡- ‹‹ጌታዬ ሆይ! ይህንማ ሁሉም ባሮችህ ይሉታል›› አለ፡፡ አላህም፡- ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› በል አለው፡፡ ሙሳም፡- ‹‹ላ ኢላሀ ኢልላ አንተ (ከአንተ በስተቀር በእውነት የሚመለክ ሌላ አምላክ የለም) አና፡- ‹‹እኔ የምፈልገው ግን ለየት ያለ ነገር እንድትሰጠኝ ነው›› አለ፡፡ ጌታችንም፡- ‹‹ሙሳ ሆይ! ሰባት ሰማያትና ነዋሪዎቻቸው፣ ሰባት ምድርና ነዋሪዎቻቸው በአንድ የሚዛን ክንፍ ላይ ቢቀመጡ ላ ኢላሀ ኢልለሏህ በሌላ የሚዛን ክንፍ ላይ ቢሆን ላ ኢላሀ ኢልለሏህ ያመዝን ነበር›› አለው” (ኢብኑ ሒባን 14/102፣ ሐኪም አል-ሙስተድረክ 1/710፣ ነሳኢይ ሱነኑል ኩብራ 6/208)፡፡

ዐብደላህ ኢብኑ ዐምሩ ኢብኑል-ዐስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “አላህ የቂያም ቀን ከኡመቶቼ መካከል አንድን ሰው በፍጥረታት መሐል ይለየውና ያወጣዋል፡፡ ከዛም ኃጢአቱ የተመዘገበበት ዘጠና ዘጠኝ መዛግብት ይዘረጉበታል፡፡ እያንዳንዱ መዝገብ ትልቀቱ አይን ማየት በሚችለው ርቀት ያህል ነው፡፡ ከዛም ጌታችን ሰውየውን፡- ‹‹ከዚህ ውስጥ የምትቃወመው ነገር አለን? ተጠባባቂ ጸሀፊዎቼ (መላእክት) በድለውሀልን?›› ሲለው፡ እሱም፡- ‹‹በፍጹም!›› ብሎ ይመልሳል፡፡ አላህም፡- ‹‹የምታቀርበው ምክንያት አለህን?›› ሲለው፡ ሰውየም፡- ‹‹ጌታዬ ሆይ! ምንም የለኝም›› ይላል፡፡ አላህም፡- ‹‹እንግዲውስ እኛ ዘንድ የተቀመጠልህ አንድ መልካም ስራ አለህ፡፡ ዛሬ በአንተ ላይ በደል የለም›› ይለውና፡ አሽሀዱ አን-ላ ኢላሀ ኢልለሏህ፡ ወአሽሀዱ አን-ነ ሙሐመደን ረሱሉላህ ብሎ የመሰከረባት አንዲት ብጣሽ ወረቀት ትወጣለታለች፡፡ ከዛም ጌታችን፡- ‹‹የሚዛንህን ውጤት ቀርበህ ተመልከት›› ይለዋል፡፡ እሱም፡- ‹‹ጌታዬ ሆይ! ይህች ብጣሽ ወረቀት ከነዛ መዛግብት አንጻር ምንድነች?›› ሲል፡ አላህም፡- ‹‹አንተ በፍጹም አትበደልም›› ይለዋል፡፡ ከዛም ዘጠና ዘጠኙ መዛግብት በአንድ የሚዛን ክንፍ ብጣሽዋ ወረቀት ደግሞ በሌላ ክንፍ ትቀመጣለች፡፡ ብጣሽዋ ወረቀት ግን ሚዛን ትደፋለች፡ ከአላህ ስም ጋር ሊመዝን የሚችል ነገር የለምና” (ቲርሚዚይ 2639)፡፡

6. እሳት ላይ ላለመዘውተር ዋስትና መሆኑ፡-

ሰዎች ወንጀላቸው በዝቶ ጌታ አላህ ልቅጣችሁ ብሎ ቢወስንና በእሳት ቢቀጣቸው እንኳ፡ በዱንያ ሳሉ ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› ሲሉ የነበሩ ሰዎች በውስጥዋ አይዘወትሩም፡፡ በሷ ሰበብ ከእሳት እንዲወጡ ይደረጋሉ፡-
አነስ ኢብኑ ማሊክ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ላ ኢላሀ ኢልለሏህ ያለ ሰው በልቡ ላይ የገብስ ፍሬ ያህል እንኳ የሚመዝን ጥሩ ስራ ካለው ከእሳት ይወጣል…” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡

7. ሰዎችን እኩል የሚያደርግ መሆኑ፡-

ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች ሙስሊም ከሆኑት ሰዎች ጋር አላህ ዘንድ እኩል እንዲሆኑ ከተፈለገ፡ እኩል የሚያደርጋቸው ቃል ይኸው ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› የሚለው የምስክርነት ቃል ነው፡-

” ﻗُﻞْ ﻳَﺎ ﺃَﻫْﻞَ ﺍﻟْﻜِﺘَﺎﺏِ ﺗَﻌَﺎﻟَﻮْﺍ ﺇِﻟَﻰ ﻛَﻠِﻤَﺔٍ ﺳَﻮَﺍﺀٍ ﺑَﻴْﻨَﻨَﺎ ﻭَﺑَﻴْﻨَﻜُﻢْ ﺃَﻟَّﺎ ﻧَﻌْﺒُﺪَ ﺇِﻟَّﺎ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻭَﻟَﺎ ﻧُﺸْﺮِﻙَ ﺑِﻪِ ﺷَﻴْﺌًﺎ ﻭَﻟَﺎ ﻳَﺘَّﺨِﺬَ ﺑَﻌْﻀُﻨَﺎ ﺑَﻌْﻀًﺎ ﺃَﺭْﺑَﺎﺑًﺎ ﻣِﻦْ ﺩُﻭﻥِ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻓَﺈِﻥْ ﺗَﻮَﻟَّﻮْﺍ ﻓَﻘُﻮﻟُﻮﺍ ﺍﺷْﻬَﺪُﻭﺍ ﺑِﺄَﻧَّﺎ ﻣُﺴْﻠِﻤُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺁﻝ ﻋﻤﺮﺍﻥ 64
“የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! በኛና በናንተ መካከል ትክክል ወደሆነች ቃል ኑ፤ (እርሷም) አላህን እንጅ ሌላን ላንገዛ በርሱም ምንንም ላናጋራ፣ ከፊላችንም ከፊሉን ከአላህ ሌላ አማልክት አድርጐ ላይይዝ ነዉ፤ በላቸዉ። እምቢ ቢሉም ፡- እኛ ሙስሊሞች መሆናችንን መስክሩ በሏቸው” (ሱረቱ አለ-ዒምራን 64)፡፡

Shortlink http://q.gs/Ey5Oh