የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” 9 በኡስታዝ አቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
450 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
7. አፍራሽ ተግባራት፡-
1. ሺርክ (ማጋራት)
ባለፉት ቀናት ስለ ሺርክ ምንነት ጀምረን ሁለት ነጥቦችን ተመልክተናል፡፡ የሺርክን ምንነት፡ ትርጓሜውንና እንዲሁም የሺርክን አስከፊነት፡፡ ዛሬ አላህ ፈቃዱ ከሆነ ደግሞ የሺርክ ክፍሎችን እንመለከታለን፡-
– የሺርክ-አይነቶች፡-
ሺርክ በሁለት ይከፈላል፡፡ እነሱም፡- ትልቁ ሺርክ ‹‹ሺርኩን አክበር›› እና ትንሹ ሺርክ ‹‹ሺርኩን አስገር›› ይባላሉ፡፡
ሀ. ትልቁ ሺርክ፡- ይህ ማለት ስራን በጠቅላላ የሚያበላሽ፡ ባለቤቱን ከኢስላም አጥር የሚያስወጣ፡ ከሙሽሪኮች ጎራ የሚቀላቅል፡ ግለሰቡ ያለ-ተውበት ከሞተ ለዘላለም እሳት የሚዳርገው ማለት ነው፡፡
ለ. ትንሹ ሺርክ፡- ይህ ማለት ባለቤቱን ከኢስላም አጥር የማያስወጣ፡ ሙሉ ስራን የማያበላሽ፡ ግለሰቡ ያለ ተውበት ከሞተ ለዘላለም ቅጣት የማይዳርገው ነገር ግን ለቅጣት አሳልፎ የሚሰጠው ማለት ነው፡፡ በሁለቱ መሀከል ካለው ልዩነት ውስጥ፡-
1. ትልቁ ሺርክ ባለቤቱን የሚያከፍር (ክህደት ውስጥ የሚከት) ተግባር ሲሆን፡ ትንሹ ሺርክ ግን ሰውየውን ከኢስላም አጥር የማያስወጣ፡ ነገር ግን በሂደት ወደ ትልቁ ሺርክ የሚወስድ፡ የተውሒዱን እምነት የሚያጎድል ትልቅ ኃጢአት ነው፡፡
2. ትልቁ ሺርክ ውስጥ ከተመደቡት ኃጢአቶች ውስጥ አንዱን እንኳ የሚፈጽም ሰው ተውበት እስኪያደርግ ድረስ አጠቃላይ ሙሉ ስራው የሚበላሽና የሚጠፋበት ሲሆን፡ ትንሹን ሺርክ የፈጸመ ሰው ግን የሚበላሽበት ያ ሺርክ የተቀላቀለበትን ስራ ብቻ ነው፡-
” ﺫَﻟِﻚَ ﻫُﺪَﻯ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻳَﻬْﺪِﻱ ﺑِﻪِ ﻣَﻦْ ﻳَﺸَﺎﺀُ ﻣِﻦْ ﻋِﺒَﺎﺩِﻩِ ﻭَﻟَﻮْ ﺃَﺷْﺮَﻛُﻮﺍ ﻟَﺤَﺒِﻂَ ﻋَﻨْﻬُﻢْ ﻣَﺎ ﻛَﺎﻧُﻮﺍ ﻳَﻌْﻤَﻠُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻷﻧﻌﺎﻡ 88
“ይህ የአላህ መምሪያ ነው፡፡ በእርሱ ከባሮቹ የሚሻውን ሰው ይመራል፡፡ ባጋሩም ኖሮ ይሠሩት የነበሩት ከነሱ በታበሰ ነበር፡፡” (ሱረቱል አንዓም 88)፡፡
” ﻭَﻟَﻘَﺪْ ﺃُﻭﺣِﻲَ ﺇِﻟَﻴْﻚَ ﻭَﺇِﻟَﻰ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﻣِﻦْ ﻗَﺒْﻠِﻚَ ﻟَﺌِﻦْ ﺃَﺷْﺮَﻛْﺖَ ﻟَﻴَﺤْﺒَﻄَﻦَّ ﻋَﻤَﻠُﻚَ ﻭَﻟَﺘَﻜُﻮﻧَﻦَّ ﻣِﻦَ ﺍﻟْﺨَﺎﺳِﺮِﻳﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺰﻣﺮ 65
“ብታጋራ ሥራህ በእርግጥ ይታበሳል፤ በእርግጥም ከከሐዲዎቹ ትሆናለህ ማለት ወደ አንተም ወደነዚያም ካንተ በፊት ወደነበሩት በእርግጥ ተወርዷል።” (ሱረቱ-ዙመር 65)፡፡
3. በትልቁ ሺርክ ላይ እያለ ያለ ተውበት የሞተ ሰው ከእሳት መውጪያ የለውም፡፡ ሁሌም በውስጥዋ ይዘወትራል፡፡ የጌታው ምሕረት አይደርሰውም፡፡ በትንሹ ሺርክ ላይ ላይ እያለ ያለ-ተውበት የሞተ ሰው ግን አላህ ከፈለገ በሸፋዓ (በምልጃ) ወይንም በራሱ ምሕረት በእሳት ሳይቀጣው ወደ ጀነት ሊከተው ይችላል፡፡ ያ ካልሆነም የወንጀሉን ያህል ይቀጣውና ወደ ጀነቱ ይመልሰዋል፡፡
” ﺇِﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻟَﺎ ﻳَﻐْﻔِﺮُ ﺃَﻥْ ﻳُﺸْﺮَﻙَ ﺑِﻪِ ﻭَﻳَﻐْﻔِﺮُ ﻣَﺎ ﺩُﻭﻥَ ﺫَﻟِﻚَ ﻟِﻤَﻦْ ﻳَﺸَﺎﺀُ ﻭَﻣَﻦْ ﻳُﺸْﺮِﻙْ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻓَﻘَﺪِ ﺍﻓْﺘَﺮَﻯ ﺇِﺛْﻤًﺎ ﻋَﻈِﻴﻤًﺎ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻨﺴﺎﺀ 48
“አላህ በርሱ ማጋራትን በፍፁም አይምርም፤ ከዚህ ሌላ ያለውንም (ኀጢአት) ለሚሻው ሰው ይምራል። በአላህም የሚያጋራ ሰው ታላቅን ኀጢያት በእርግጥ ቀጠፈ።” (ሱረቱ-ኒሳእ 48)፡፡
” ﺇِﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻟَﺎ ﻳَﻐْﻔِﺮُ ﺃَﻥْ ﻳُﺸْﺮَﻙَ ﺑِﻪِ ﻭَﻳَﻐْﻔِﺮُ ﻣَﺎ ﺩُﻭﻥَ ﺫَﻟِﻚَ ﻟِﻤَﻦْ ﻳَﺸَﺎﺀُ ﻭَﻣَﻦْ ﻳُﺸْﺮِﻙْ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻓَﻘَﺪْ ﺿَﻞَّ ﺿَﻠَﺎﻟًﺎ ﺑَﻌِﻴﺪًﺍ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻨﺴﺎﺀ 116
“አላህ በርሱ የማጋራትን (ወንጀል) አይምርም ከዚህም ወዲያ ያለውን፣ ለሚሻ ሰው ይምራል። በአላህም የሚያጋራ ሰው (ከውነት) የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ።” (ሱረቱ-ኒሳእ 116)፡፡
” ﻟَﻘَﺪْ ﻛَﻔَﺮَ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﻗَﺎﻟُﻮﺍ ﺇِﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻫُﻮَ ﺍﻟْﻤَﺴِﻴﺢُ ﺍﺑْﻦُ ﻣَﺮْﻳَﻢَ ﻭَﻗَﺎﻝَ ﺍﻟْﻤَﺴِﻴﺢُ ﻳَﺎ ﺑَﻨِﻲ ﺇِﺳْﺮَﺍﺋِﻴﻞَ ﺍﻋْﺒُﺪُﻭﺍ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﺭَﺑِّﻲ ﻭَﺭَﺑَّﻜُﻢْ ﺇِﻧَّﻪُ ﻣَﻦْ ﻳُﺸْﺮِﻙْ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻓَﻘَﺪْ ﺣَﺮَّﻡَ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻋَﻠَﻴْﻪِ ﺍﻟْﺠَﻨَّﺔَ ﻭَﻣَﺄْﻭَﺍﻩُ ﺍﻟﻨَّﺎﺭُ ﻭَﻣَﺎ ﻟِﻠﻈَّﺎﻟِﻤِﻴﻦَ ﻣِﻦْ ﺃَﻧْﺼَﺎﺭٍ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻤﺎﺋﺪﺓ 72
“እነዚያ አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ፤ አልመሲሕም አለ፦ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ፤ እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፤ መኖሪያውም እሳት ናት፤ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም።” (ሱረቱል ማኢዳህ 72)፡፡
የሺርክን የክፍያ ሁኔታ በዚህ መልኩ ካየን፡ በቀጣዮቹ ተከታታይ ክፍሎች ደግሞ በአላህ ፈቃድ ከትልቁ ሺርክ በመጀመር አንዳንድ ነጥቦችን እየጠቀስን እንማራለን ኢንሻአላህ፡፡ ይቀጥላል፡፡