የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” 8 በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
409 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
7. አፍራሽ ተግባራት፡-
1. ሺርክ (ማጋራት) ባለፈው የሽርክን ጥቅላዊ ገጽታና ትርጉሙን በተወሰነ መልኩ ቃኝተናል፡፡ ዛሬ ደግሞ የሽርክን አስከፊ ገጽታ በተወሰነ መልኩ እንቃኘዋለን፡፡ ከዛም አላህ ፈቃዱ ከሆነ በቀጣዩ ክፍል ወደ አይነቶቹ እንመለሳለን፡፡
የሺርክ አስከፊነት፡-

ሀ. የበደሎች ሁሉ በደል መሆኑ፡- አላህን ምንም ሳያጋሩበት በብቸኝነት አምልኮ መገኘት (ተውሒድ) የፍትሕ ሁሉ ፍትሕ እንደሆነ ሁሉ፡ በአላህ ላይ ቅንጣት ታክል እንኳ ማጋራት የበደሎች ሁሉ በደል ነው፡፡ በደል ማለት ትርጉሙ፡- አንድን ነገር ተገቢው ስፍራ ላይ አለማስቀመጥ፡ የማይገባው ነገር ላይ ማኖር ማለት ነው፡፡ አምልኮ ለአላህ ብቻ የሚገባ ስራ ሆኖ ሳለ፡ ለማይገባው አካል አሳልፎ መስጠት (ፍጡርን ማምለክ) በደል ይሰኛል፡፡ ምክንያቱም ያለቦታው የተቀመጠ ድርጊት በመሆኑ!! ሺርክ እጅግ የከፋ በደል መሆኑን ከሚያመላክቱ ቅዱስ ቁርኣናዊ አንቀጾች መካከል ጥቂቱን እናንብብ፡-
” ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﺁﻣَﻨُﻮﺍ ﻭَﻟَﻢْ ﻳَﻠْﺒِﺴُﻮﺍ ﺇِﻳﻤَﺎﻧَﻬُﻢْ ﺑِﻈُﻠْﻢٍ ﺃُﻭﻟَﺌِﻚَ ﻟَﻬُﻢُ ﺍﻟْﺄَﻣْﻦُ ﻭَﻫُﻢْ ﻣُﻬْﺘَﺪُﻭﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻷﻧﻌﺎﻡ 82
“እነዚያ ያመኑና እምነታቸውን በበደል ያልቀላቀሉ እነዚያ ለእነርሱ ጸጥታ አላቸው፡፡ እነሱም የተመሩ ናቸው፤” (ሱረቱል አንዓም 82)፡፡
‹‹በበደል ያልቀላቀሉ›› የሚለው ፍቺው፡- በጌታቸው ላይ ያላጋሩ የሚል ነው፡፡ በተለይ ይህ አንቀጽ በወረደ ጊዜ ሶሓባዎች (ረዲየላሁ ዐንሁም) ቀጥታ ፍቺውን ብቻ ወስደው ስለተረዱ በድንጋጤ፡- ‹‹ከኛ ውስጥ ነፍሱን (በትናንሽ ኃጢአት) የማይበድል ማን አለ ታዲያ!›› በማለት ግራ ተጋቡ፡፡ በቃ ሁላችንም ጠፍተናል የሚል ሃሳብ ሲገባቸው፡ የአላህ መልክተኛ ደግሞ፡- ጉዳዩ እናንተ እንዳሰባችሁት አይደለም፡፡ እዚህ ጋር በደል የተባለው ሺርክ የሚለውን ለማሳየት ነው፡፡ የአላህ መልካም ባሪያ የሆነው ሉቅማን (ረዲየላሁ ዐንሁ) ለልጁ እንዲህ ማለቱን አልሰማችሁምን? በማለት የቁርኣኑን አንቀጽ ጠቅሰው የበደልን ትርጉም ነገሯቸው፡፡ የተጠቀሰው አንቀጽም ይህ ነበር፡-
” ﻭَﺇِﺫْ ﻗَﺎﻝَ ﻟُﻘْﻤَﺎﻥُ ﻟِﺎﺑْﻨِﻪِ ﻭَﻫُﻮَ ﻳَﻌِﻈُﻪُ ﻳَﺎ ﺑُﻨَﻲَّ ﻟَﺎ ﺗُﺸْﺮِﻙْ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﺇِﻥَّ ﺍﻟﺸِّﺮْﻙَ ﻟَﻈُﻠْﻢٌ ﻋَﻈِﻴﻢٌ ” ﺳﻮﺭﺓ ﻟﻘﻤﺎﻥ 13
“ሉቅማንም ለልጁ እርሱ የሚገስጸው ሲሆን፦ ልጄ ሆይ! በአላህ (ጣዖትን) አታጋራ፤ ማጋራት ታላቅ በደል ነውና ያለውን (አስታውስ)።” (ሱረቱ ሉቅማን 13)፡፡ (ቡኻሪይ 4776)፡፡
ያንተ ብቻ የሆነን ንብረት ካንተ ወስዶ ለማይገባውና ሐቁ ላልሆነ ሰው ቢሰጥ፡ ሰጪውን በደለኛ ነው ወይስ ፍትሐዊ ነው የምትለው? በደለኛ ነው የምለው ካልክ፡ ታዲያ የአላህን ሐቅ፣ ግላዊ መብቱ የሆነውን ለማይገባው ፍጡር አሳልፎ መስጠትስ እንዴት በደል አይሆንም?
ለ. ምሕረት አልባ መሆኑ፡- ከሽርክ ውጪ ያሉ ወንጀሎችን የሰራ ሰው ያለ ተውበት ቢሞት እንኳ የመዳን ተስፋ አለው፡፡ አላህ ከፈለገ በነቢያችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሸፋዐህ (ምልጃ) ሊታረቀው፣ ወይንም ከራሱ በመነጨ ምሕረት ይቅር ብሎት ያለምንም ቅጣት ወደ ጀነት ሊያስገባው ይችላል፡፡ ያ ካልሆነና በእሳት ልቅጣህ ብሎ ቢወስንበት እንኳ የወንጀሉን ያህል ቀጥቶት፡ በያዘው ተውሒድና በአላህ ላይ ባለማሻረኩ ደግሞ ወደ ጀነቱ ይመልሰዋል፡፡ በሽርክ ስራ ላይ እያለ ወደ አላህ በተውበት ሳይመለስ ከነ-ሽርኩ የሞተ ሰው ግን ምንም የመዳን ተስፋ የለውም፡፡ የኃጢአት ስርየት (ስረዛን) አያገኝም፡፡ የነቢያት ሸፋዐና የአላህ ራሕመት አይነካውም፡፡ ለዘላለሙ በእሳት እየተሰቃየ ይኖራል፡፡ ታዲያ ከዚህ የበለጠ አስከፊ ሁኔታ አለን?
” ﺇِﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻟَﺎ ﻳَﻐْﻔِﺮُ ﺃَﻥْ ﻳُﺸْﺮَﻙَ ﺑِﻪِ ﻭَﻳَﻐْﻔِﺮُ ﻣَﺎ ﺩُﻭﻥَ ﺫَﻟِﻚَ ﻟِﻤَﻦْ ﻳَﺸَﺎﺀُ ﻭَﻣَﻦْ ﻳُﺸْﺮِﻙْ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻓَﻘَﺪِ ﺍﻓْﺘَﺮَﻯ ﺇِﺛْﻤًﺎ ﻋَﻈِﻴﻤًﺎ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻨﺴﺎﺀ 48
“አላህ በርሱ ማጋራትን በፍፁም አይምርም፤ ከዚህ ሌላ ያለውንም (ኀጢአት) ለሚሻው ሰው ይምራል። በአላህም የሚያጋራ ሰው ታላቅን ኀጢያት በእርግጥ ቀጠፈ።” (ሱረቱ-ኒሳእ 48)፡፡
” ﺇِﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻟَﺎ ﻳَﻐْﻔِﺮُ ﺃَﻥْ ﻳُﺸْﺮَﻙَ ﺑِﻪِ ﻭَﻳَﻐْﻔِﺮُ ﻣَﺎ ﺩُﻭﻥَ ﺫَﻟِﻚَ ﻟِﻤَﻦْ ﻳَﺸَﺎﺀُ ﻭَﻣَﻦْ ﻳُﺸْﺮِﻙْ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻓَﻘَﺪْ ﺿَﻞَّ ﺿَﻠَﺎﻟًﺎ ﺑَﻌِﻴﺪًﺍ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻨﺴﺎﺀ 116
“አላህ በርሱ የማጋራትን (ወንጀል) አይምርም ከዚህም ወዲያ ያለውን፣ ለሚሻ ሰው ይምራል። በአላህም የሚያጋራ ሰው (ከውነት) የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ።” (ሱረቱ-ኒሳእ 116)፡፡
” ﻟَﻘَﺪْ ﻛَﻔَﺮَ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﻗَﺎﻟُﻮﺍ ﺇِﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻫُﻮَ ﺍﻟْﻤَﺴِﻴﺢُ ﺍﺑْﻦُ ﻣَﺮْﻳَﻢَ ﻭَﻗَﺎﻝَ ﺍﻟْﻤَﺴِﻴﺢُ ﻳَﺎ ﺑَﻨِﻲ ﺇِﺳْﺮَﺍﺋِﻴﻞَ ﺍﻋْﺒُﺪُﻭﺍ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﺭَﺑِّﻲ ﻭَﺭَﺑَّﻜُﻢْ ﺇِﻧَّﻪُ ﻣَﻦْ ﻳُﺸْﺮِﻙْ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻓَﻘَﺪْ ﺣَﺮَّﻡَ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻋَﻠَﻴْﻪِ ﺍﻟْﺠَﻨَّﺔَ ﻭَﻣَﺄْﻭَﺍﻩُ ﺍﻟﻨَّﺎﺭُ ﻭَﻣَﺎ ﻟِﻠﻈَّﺎﻟِﻤِﻴﻦَ ﻣِﻦْ ﺃَﻧْﺼَﺎﺭٍ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻤﺎﺋﺪﺓ 72
“እነዚያ አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ፤ አልመሲሕም አለ፦ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ፤ እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ላይ ጀነትን በእርግጥ እርም አደረገ፤ መኖሪያውም እሳት ናት፤ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም።” (ሱረቱል ማኢዳህ 72)፡፡
ሐ. ስራን በጠቅላላ ማበላሸቱ፡- ስራን አላህ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው መሟላት ያለባቸውን ሶስት መስፈርቶች (ኢማን፣ ኢኽላስ፣ ኢቲባዕ) አሟልቶ አላህን ሲያመልክ የነበረ ሰው፡ አንድ ቀን ትልቁ ሽርክ ላይ ቢወድቅ የነበረው ስራ ሁሉ ይበላሻል፡፡ በትክክለኛ ተውበት ስራውን ሁሉ ሳይመልስ ቢቀርና ሳይቶብት ቢሞት ከከሳሪዎች ይሆናል፡፡ ሌሎች ኃጢአቶች በራሳቸው ብቻ ባለቤቱን ያስጠይቁታል እንጂ ከነሱ ውጭ የሆነውን ስራ አያበላሹም፡፡ ሽርክ ግን የነበሩትን ስራዎች ሁሉ ነው የሚደመስሰው፡፡ አላህ ይጠብቀን፡፡
” ﺫَﻟِﻚَ ﻫُﺪَﻯ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻳَﻬْﺪِﻱ ﺑِﻪِ ﻣَﻦْ ﻳَﺸَﺎﺀُ ﻣِﻦْ ﻋِﺒَﺎﺩِﻩِ ﻭَﻟَﻮْ ﺃَﺷْﺮَﻛُﻮﺍ ﻟَﺤَﺒِﻂَ ﻋَﻨْﻬُﻢْ ﻣَﺎ ﻛَﺎﻧُﻮﺍ ﻳَﻌْﻤَﻠُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻷﻧﻌﺎﻡ 88
“ይህ የአላህ መምሪያ ነው፡፡ በእርሱ ከባሮቹ የሚሻውን ሰው ይመራል፡፡ ባጋሩም ኖሮ ይሠሩት የነበሩት ከነሱ በታበሰ ነበር፡፡” (ሱረቱል አንዓም 88)፡፡
” ﻭَﻟَﻘَﺪْ ﺃُﻭﺣِﻲَ ﺇِﻟَﻴْﻚَ ﻭَﺇِﻟَﻰ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﻣِﻦْ ﻗَﺒْﻠِﻚَ ﻟَﺌِﻦْ ﺃَﺷْﺮَﻛْﺖَ ﻟَﻴَﺤْﺒَﻄَﻦَّ ﻋَﻤَﻠُﻚَ ﻭَﻟَﺘَﻜُﻮﻧَﻦَّ ﻣِﻦَ ﺍﻟْﺨَﺎﺳِﺮِﻳﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺰﻣﺮ 65
“ብታጋራ ሥራህ በእርግጥ ይታበሳል፤ በእርግጥም ከከሐዲዎቹ ትሆናለህማለት ወደ አንተም ወደነዚያም ካንተ በፊት ወደነበሩት በእርግጥ ተወርዷል።” (ሱረቱ-ዙመር 65)፡፡
መ. ምድራዊ ዋስትና ማሳጣቱ፡- በአላህ የሚያጋሩ ሰዎች በአንድ የችግር ወቅት ከአላህም ሆነ ከአማኞች ዘንድ ንብረታቸው ተጠብቆ በህይወት ሰላም ሆነው የመቆየት ዋስትና የላቸውም፡፡ እንዴት ከፈጣሪቸው ተጣልተው በሱም አምልኮ ላይ ሌላን አጋርተው በሰላም ይኖራሉ? እንኳን የአላህን መብት የጣሰ ይቅርና የሰውን መብት የጣሰ ሰው ያለ ቅጣት መች በሰላም የመኖር ዋስትና ተሰጠውና? ሙሽሪኮችም በአካልም ሆነ በልቦናቸው ሰላም አይኖራቸውም፡፡ አላህ በልቦናቸው ላይ ፍርሐትን ይጥላል፡፡ በነፍሳቸውም ላይ የመገደል አደጋ ይደርስባቸዋል፡፡
” ﺳَﻨُﻠْﻘِﻲ ﻓِﻲ ﻗُﻠُﻮﺏِ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﻛَﻔَﺮُﻭﺍ ﺍﻟﺮُّﻋْﺐَ ﺑِﻤَﺎ ﺃَﺷْﺮَﻛُﻮﺍ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻣَﺎ ﻟَﻢْ ﻳُﻨَﺰِّﻝْ ﺑِﻪِ ﺳُﻠْﻄَﺎﻧًﺎ ﻭَﻣَﺄْﻭَﺍﻫُﻢُ ﺍﻟﻨَّﺎﺭُ ﻭَﺑِﺌْﺲَ ﻣَﺜْﻮَﻯ ﺍﻟﻈَّﺎﻟِﻤِﻴﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺁﻝ ﻋﻤﺮﺍﻥ 151
“በነዚያ በካዱት ሰዎች ልቦች ዉስጥ፤ አላህ በርሱ አስረጅ ያላወረደበትን ነገር በአላህ በማጋራታቸዉ ምክንያት ፍርሃትን እንጥላለን መኖሪያቸዉም እሳት ናት፤ የበዳዮችም መኖርያ ምን ትከፋ!” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 151)፡፡
” ﻓَﺈِﺫَﺍ ﺍﻧْﺴَﻠَﺦَ ﺍﻟْﺄَﺷْﻬُﺮُ ﺍﻟْﺤُﺮُﻡُ ﻓَﺎﻗْﺘُﻠُﻮﺍ ﺍﻟْﻤُﺸْﺮِﻛِﻴﻦَ ﺣَﻴْﺚُ ﻭَﺟَﺪْﺗُﻤُﻮﻫُﻢْ ﻭَﺧُﺬُﻭﻫُﻢْ ﻭَﺍﺣْﺼُﺮُﻭﻫُﻢْ ﻭَﺍﻗْﻌُﺪُﻭﺍ ﻟَﻬُﻢْ ﻛُﻞَّ ﻣَﺮْﺻَﺪٍ ﻓَﺈِﻥْ ﺗَﺎﺑُﻮﺍ ﻭَﺃَﻗَﺎﻣُﻮﺍ ﺍﻟﺼَّﻠَﺎﺓَ ﻭَﺁﺗَﻮُﺍ ﺍﻟﺰَّﻛَﺎﺓَ ﻓَﺨَﻠُّﻮﺍ ﺳَﺒِﻴﻠَﻬُﻢْ ﺇِﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻏَﻔُﻮﺭٌ ﺭَﺣِﻴﻢٌ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺘﻮﺑﺔ 5
“የተከበሩትም ወሮች ባለቁ ጊዜ አጋሪዎቹን በአገኛችኋቸው ስፍራ ግደሉዋቸዉ፤ ያዙዋቸዉም፤ ክበቡዋቸውም፤ ለነሱም (መጠባበቅ) በየመንገዱ ተቀመጡ፤ ቢጸጸቱም፤ ሶላትንም በደንቡ ቢሰግዱ፣ ግዴታ ምጽዋትንም ቢሰጡ፣ መንገዳቸውን ልቀቁላቸዉ አላህ መሐሪ አዛኝ ነውና።” (ሱረቱ-ተውባህ 5)፡፡
ሠ. ክብርን ያጎድፋል፡- ሰው ከሌሎች ፍጡሮች በላጭ ሁኖ ነው የተፈጠረው (ሱረቱል-ኢስራእ 70)፡፡ በምድር ላይ ያሉ ነገራት ሁሉ ለሱ ጥቅምና ግልጋሎት ሲፈጠሩ (አል-በቀራህ 29) እሱ ደግሞ ፈጣሪ አምላኩን አላህን እንዲገዛና በብቸኝነት እንዲያመልክ ተፈጠረ (አዝ-ዛሪያት 56)፡፡ በመሆኑም አላህን ብቻ አምልኮ መገኘትና የአንድ አላህ ብቻ ባሪያ መሆን ትልቅ ነጻነትና ዕድል ሲሆን፡ ከአላህ ውጭ ያለን መገዛት ደግሞ ትልቅ ውርደትና ክብረ-ቢስነት ነው፡፡ እንዴት ሰው ለመሰል ፍጡሩ ያጎበድዳል? ከአላህ ውጭ ምንም ሊያብቃቃው ለማይችል ፍጡር እንዴት ይሰግዳል? ታዲያ ከዚህ የከፋ ውርደትና ዝቅተኝነት ይኖራልን?
” ﺣُﻨَﻔَﺎﺀَ ﻟِﻠَّﻪِ ﻏَﻴْﺮَ ﻣُﺸْﺮِﻛِﻴﻦَ ﺑِﻪِ ﻭَﻣَﻦْ ﻳُﺸْﺮِﻙْ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻓَﻜَﺄَﻧَّﻤَﺎ ﺧَﺮَّ ﻣِﻦَ ﺍﻟﺴَّﻤَﺎﺀِ ﻓَﺘَﺨْﻄَﻔُﻪُ ﺍﻟﻄَّﻴْﺮُ ﺃَﻭْ ﺗَﻬْﻮِﻱ ﺑِﻪِ ﺍﻟﺮِّﻳﺢُ ﻓِﻲ ﻣَﻜَﺎﻥٍ ﺳَﺤِﻴﻖٍ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺤﺞ 31
“ለአላህ ታዛዦች በርሱ የማታጋሩ ሆናችሁ (ከሐሰት ራቁ)፤ በአላህም የሚያጋራ ሰው ከሰማይ እንደ ወደቀና በራሪ እንደምትነጥቀው፣ ወይም ነፋሰ እርሱን በሩቅ ስፍራ እንደምትጥለው ብጤ ነው።” (ሱረቱል ሐጅ 31)፡፡
ረ. የወንጀሎች ሁሉ ቁንጮ መሆኑ፡- ኃጢአት በጠቅላላ በባሕሪው የተወገዘ ቢሆንም፡ እንደ አይነቱና እንደ ፈጻሚው የክብደት ደረጃው ይለያያል፡፡ ሁሉም በእኩል መጠን አይታዩም፡፡ በምድር ላይ ከሚፈጸሙ ኃጢአቶች ሁሉ የከፋው ግን ሺርክ ነው፡፡ ከሱ የሚከፋ ሌላ የለም፡፡
ﻋﻦ ﺃﺑﻲ ﺑَﻜْﺮَﺓ ﻗﺎﻝ : ﻗﺎﻝ ﺭﺳﻮﻝ ﺍﻟﻠﻪ ﺻﻠﻰ ﺍﻟﻠﻪ ﻋﻠﻴﻪ ﻭﺳﻠﻢ : ” ﺃﻻ ﺃﻧﺒﺌﻜﻢ ﺑﺄﻛﺒﺮ ﺍﻟﻜﺒﺎﺋﺮ؟ ” ﻗﻠﻨﺎ : ﺑﻠﻰ، ﻳﺎ ﺭﺳﻮﻝ ﺍﻟﻠﻪ . ﻗﺎﻝ : ” ﺍﻹﺷﺮﺍﻙ ﺑﺎﻟﻠﻪ ﻭﻋﻘﻮﻕ ﺍﻟﻮﺍﻟﺪﻳﻦ – ﻭﻛﺎﻥ ﻣﺘﻜﺌﺎ ﻓﺠﻠﺲ، ﻓﻘﺎﻝ -: ﺃﻻ ﻭﻗﻮﻝ ﺍﻟﺰﻭﺭ، ﺃﻻ ﻭﺷﻬﺎﺩﺓ ﺍﻟﺰﻭﺭ ” ﺭﻭﺍﻩ ﺍﻟﺒﺨﺎﺭﻱ ﻭﻣﺴﻠﻢ .
አቢ በክረህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- “እጅግ በጣም የከበደ ኃጢአትን ልንገራችሁን? ሲሉ፡ ሶሐቦችም፡- ‹‹እንዴታ ይንገሩን እንጂ!›› አሉ፡፡ እሳቸውም፡- ‹‹በአላህ ማጋራት፣ ወላጆችን መጨቆን›› ተደግፈው ነበርና ቁጭ ብለው፡- ‹‹አዋጅ! የሐሰት ቃል፣ የውሸት ምስክርነትም፣ አዋጅ! የሐሰት ቃል፣ የውሸት ምስክርነትም›› አሉ፡፡” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
ﻋَﻦْ ﻋَﺒْﺪِ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﺍﺑﻦ ﻣﺴﻌﻮﺩ ﺭﺿﻲ ﺍﻟﻠﻪ ﻋﻨﻪ ﻗَﺎﻝَ : ﺳَﺄَﻟْﺖُ ﺍﻟﻨَّﺒِﻲَّ ﺻَﻠَّﻰ ﺍﻟﻠﻪُ ﻋَﻠَﻴْﻪِ ﻭَﺳَﻠَّﻢَ ” : ﺃَﻱُّ ﺍﻟﺬَّﻧْﺐِ ﺃَﻋْﻈَﻢُ ﻋِﻨْﺪَ ﺍﻟﻠَّﻪِ؟ ﻗَﺎﻝَ : ‏« ﺃَﻥْ ﺗَﺠْﻌَﻞَ ﻟِﻠَّﻪِ ﻧِﺪًّﺍ ﻭَﻫُﻮَ ﺧَﻠَﻘَﻚَ ‏» . ﺭﻭﺍﻩ ﺍﻟﺒﺨﺎﺭﻱ ﻭﻣﺴﻠﻢ .
ዐብዱላህ ኢብኒ-መስዑድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- “የአላህ መልክተኛን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከወንጀሎች ሁሉ ታላቁ የቱ ነው? አልኳቸው፡፡ እሳቸውም ‹‹አላህ እሱ ፈጥሮህ ሳለ ለሱ (በአምልኮ) ብጤ ማበጀትህ›› ነው አሉኝ” (ቡኻሪይ 4477፣ ሙስሊም 141)፡፡
አላህ ከሽርክ ጠብቆ በተውሒድ ላይ ጸንተው ከሚሞቱ መልካም ባሮቹ ያድርገን አሚን፡፡ ይቀጥላል