የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” ክፍል 7 በኡስታዝ አቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
410 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
7. አፍራሽ ተግባራት፡-
እስከዛሬ ባሳለፍናቸው ስድስት ክፍሎች በአላህ ፈቃድ የ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ”ን ምንነት በመጠኑ ተመልክተናል፡፡ በውስጡም፡- የ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ”ን አስፈላጊነት፣ ስሞቹን፣ ትርጓሜውንና መስፈርቱንም ጭምር ዳስሰናቸዋል፡፡ እነሆ ዛሬ ደግሞ የአላህ ፈቃዱ ከሆነ የ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ”ን እምነት አፍራሽ ተግባራት ምን ምን እንደሆኑ ለማየት እንሞክራለን፡፡
የ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ”ን እምነት የሚያሳድገውንና የሚገነባውን ማወቅ ብቻ ሳይሆን በተቃራኒውም የሚያፈርሰውንና የሚንደውንም ነገር ለጥንቃቄ ይረዳ ዘንድ ማወቁና መረዳቱ ግድ ነውና! መልካም ንባብ፡፡
1. ሺርክ (ማጋራት)፡-
የሰዎችን የ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” እምነት ከሚያፈርሱትና ከሚንዱት እንዲሁም ባለቤቱን ከኢስላም አጥር ከሚያስወጡ መጥፎ ተግባራት ውስጥ አንዱና ዋነኛው “ሺርክ” ነው፡፡ “ሺርክ” ማለት ቀጥታ ፍቺው ማጋራት ማለት ነው፡፡ በአንድ ነገር ላይ ሁለት እና ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎች መብት ካላቸው ‹‹ተጋሪዎች›› ተብለው ይጠራሉ፡፡ በልጅነት ዘመን መሬት ላይ ወድቆ የተገኘ እቃን ከጓደኛችን አንዱ ቀድሞ ቢያየውና ቢያነሳው እኛም በእቃው ላይ ድርሻ እንዲኖረን ‹‹ብጋራ!›› የሚል ቃል እንደምንጠቀም ታስታውሳላችሁ አይደል? እቃውን ተጋራን ማለት በዐረብኛው ልሳን ‹‹ተሻረክን›› ማለት ነው፡፡ ለኛ ያጋራንም ሰው ‹‹አሻረከን›› ማለት ነው፡፡
ይህን የሺርክን ቋንቋዊ ፍቺ በዚህ መልኩ ማስቀመጣችንን ሊያግዝ የሚችል ሁለት ቅዱስ ቁርኣናዊ አንቀጾችን እንመልከት፡-
” ﻭَﺍﺟْﻌَﻞْ ﻟِﻲ ﻭَﺯِﻳﺮًﺍ ﻣِﻦْ ﺃَﻫْﻠِﻲ * ﻫَﺎﺭُﻭﻥَ ﺃَﺧِﻲ * ﺍﺷْﺪُﺩْ ﺑِﻪِ ﺃَﺯْﺭِﻱ * ﻭَﺃَﺷْﺮِﻛْﻪُ ﻓِﻲ ﺃَﻣْﺮِﻱ ” ﺳﻮﺭﺓ ﻃﻪ 29-32
“ከቤተሰቦቼም ለኔ ረዳትን አድርግልኝ፤ ሃሩንን ወንድሜን። ኀይሌን በርሱ አበርታልኝ። በነገሬም አጋራው።” (ሱረቱ ጣሀ 29-32)፡፡
በአንቀጽ 32 ላይ ‹‹አጋራው›› ለሚለው የአማርኛ ትርጉም የተቀመጠው ዐረብኛ ቃል ‹‹አሽሪክሁ›› የሚለው ነው፡፡ ‹‹ማሻረክ›› ማለት ማጋራት ማለት ነውና፡፡
…” ﻓَﺈِﻥْ ﻛَﺎﻧُﻮﺍ ﺃَﻛْﺜَﺮَ ﻣِﻦْ ﺫَﻟِﻚَ ﻓَﻬُﻢْ ﺷُﺮَﻛَﺎﺀُ ﻓِﻲ ﺍﻟﺜُّﻠُﺚِ … ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻨﺴﺎﺀ 12
“…ከዚህም (ከአንድ) የበዙ ቢሆኑ እነርሱ በሲሶው ተጋሪዎች ናቸው…” (ሱረቱ-ኒሳእ 12)፡፡
በዚህ የውርስ አንቀጽ ላይ ‹‹ተጋሪዎች›› ለሚለው የአማርኛ ትርጉም በዐረብኛው ‹‹ሹረካእ›› ተብሎ ነው የተጠቀሰው፡፡ በጥቅሉ አንድን ነገር ከአንድ በላይ ለሆነ አካል በእኩልም ይሁን በመጠኑ መስጠትና ማከፋፈል ‹‹ማሻረክ›› (ማጋራት) የሚል ስያሜ እንደሚኖረው ለመረዳት ቀላል ነው፡፡
ወደ ሃይማኖታዊ ፍቺው ስንገባ ደግሞ ሺርክ ማለት፡- ጌታ አላህ የግል ንብረቱና መብቱ በሆነ ነገር ላይ ሌላን ተጋሪ (በእምነትም ይሁን በንግግር ወይም በስራ) ማበጀት ማለት ነው፡፡ ጌታ አላህ በህላዌ ማንነቱ (በዛቱ) ከፍጡራን የተለየ፣ በጌትነት ስራው (ሩቡቢያ) አጋዥና አማካሪ እንዲሁም ተወዳዳሪ የሌለው፣ በስሞቹና በባሕሪያቱ (አስማእ-ወስ-ሲፋት) ፈጽሞ አምሳያና ሞክሼ የሌለው፣ በመመለኩም (ኡሉሂያ) አጋርን የማይሻ ብቻውን የሚመለክ እውነተኛ አምላክ ነው፡፡ ከነዚህ የጌታችን መብቶች ውስጥ አንዱን እንኳ በሙሉም ይሁን በከፊል ለፍጡር አሳልፎ መስጠት፡ በአላህ ላይ ማጋራት ‹‹ማሻረክ›› ይባላል፡፡ ግለሰቡም ሙሽሪክ ተብሎ ይሰየማል አላህ ይጠብቀን፡፡
ሀ. በህላዌው (በዛቱ) ማጋራት፡- ይህ ማለት፡ አንድ ሰው የፍጡርን ዛት (አካል) እንደ አላህ ማንነት (ዛት) ነው ብሎ ከተናገረ ወይም ካመነ ፍጡርን ከጌታው ማንነት (ዛት) ጋር በማመሳሰሉና በማቀራረቡ በአላህ ላይ አጋራ ይባላል፡፡
ለ. በስሞቹና በባሕሪያቱ (አል-አስማኡ ወስ-ሲፋት) ማጋራት፡- ይህ ማለት ደግሞ፡ ከፍጡራን መካከል አንዱን በመጥቀስ ከአላህ ስሞችና ባሕሪያት ውስጥ አንዱን ወይም የተወሰኑትን ለዛ ሰው ማጋራት ማለት ነው፡፡ ምሣሌ፡- የሩቅን ማወቅ፣ ሁሉን ተመልካችነት፣ በሩቅ መስማት፣ ሁሉን ቻይነትና የመሳሰሉት የአላህ ብቸኛ ባሕሪያትና መገለጫዎች የነበሩትን ለፍጡር አሳልፎ መስጠት ማለት ነው፡፡
ሐ. በአላህ ስራ (ሩቡቢያህ) ማጋራት፡- ይህ ደግሞ፡ አላህ በስራው ከፍጡራን ሁሉ በተለየ መልኩ እሱ ብቻ የሚከውናቸውን ነገራት ሌሎች አካላትም ያንኑ በሙሉም ይሁን በከፊል ይሰራሉ ብሎ ማመን ወይም መናገር በጌትነት መገለጫው ላይ ማጋራት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- መፍጠር፣ ሲሳይን መለገስ፣ ሕይወትን መስጠትና መግደል፣ ዓለሙን ማስተዳደር እና የመሳሰሉት የአላህ የጌትነት (የሩቡቢያህ) መገለጫዎቹ ላይ እነዚህንም የሚሰራ ሌላ አካል አልለ ብሎ ማመንና መናገር ማጋራት ይባላል፡፡
መ. በአምልኮት (ኡሉሂያ) ማጋራት፡- ይህ ማለት ደግሞ፡ ለአላህ ብቻ የሚገቡ የሆኑ፣ በልብ፣ በምላስና በስራ የሚገለጹ የሆኑ የአምልኮ ዘርፎችን ለፍጡር አሳልፎ መስጠት ማለት ነው፡፡ ለምሣሌ፡- ተማጽኖ (ዱዓእ)፣ በሩቁ መፍራት (ኸውፍ)፣ መመካት (ተወኩል)፣ ከጭንቅ መውጫ የእርዳታ ጥሪ (ኢስቲጋሳ)፣ ስግደት (ሱጁድ)፣ ስለት (ነዝር)፣ እርድ (ዘብሕ) እና የመሳሰሉትን ለአላህ እንጂ ለማንም የማይገቡ ሆነው ሳለ፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱን እንኳ ቢሆን ለፍጡር አሳልፎ መስጠት በአላህ ላይ ማጋራት (ማሻረክ) ይባላል፡፡ በተለይ የብዙ ሰዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሽርክ ላይ የመውደቅ ሁኔታ በዚህኛው ክፍል ላይ ያለው የሽርክ አይነት ጎልቶ ይታያል፡፡ ኢስላም ከሁሉም አይነት የሽርክ ተግባራት አስጠንቅቆአል፡፡ ፍጹም የሆነ መከልከልንም ከልክሏል፡፡
ለዛሬ የሽርክን ትርጉም ከተመለከትንና ከተረዳን፡ በቀጣዩ ደግሞ ቀሪ ሀሳቦችን እንመለከታለን ኢንሻአላህ፡፡ይቀጥላል