የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” ክፍል -5

1,098 Views

በኡስታዝ አቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

4. መስፈርቶቹ፡-

ከትላንት በፊት ከ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” መስፈርቶች ሁለቱን ማለትም፡- ‹‹ትርጓሜውን ማወቅ›› እና ባወቅነውም ነገር ‹‹እርግጠኛ መሆን›› የሚሉትን አንስተን መጠነኛ ዳሰሳ አድርገን ነበር፡፡ ኢንሻአላህ ዛሬም በአላህ ፈቃድ ቀጣዮቹ ነጥቦች ይቀርባሉ፡-

ሐ. ‹‹ከልብ መቀበል››፡-

ይህም ሌላ መስፈርት ነው፡፡ የ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ”ን ትክክለኛ መልእክት ያወቀና የተረዳ፡ ባወቀውም ነገር እውነተኝነት፡ እርግጠኛ የሆነ ሰው፡ የሚጠበቅበት ነገር ቢኖር፡ ያን ያወቀውንና እርግጠኛ የሆነውን ነገር ከልብ አምኖ መቀበል ነው፡፡ አንዳንድ ጉደኞች አሉ፡፡ የኢስላም መልእክት ገብቷቸው ተረድተውት፡ እውነት እንደሆነም እርግጠኞች ሆነው፡ ለመቀበል ግን ትእቢትና የኩራት ስሜት የከለከላቸው፡፡ የነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ቀንደኛ ተቃዋሚ የነበሩት እነ አቡ-ጀህል፣አቡ ለሀብ… ኢስላምን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑት የ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ”ን መልእክት ለመረዳት ስላስቸገራቸው ወይም በጉዳዩ ጥርጣሬ ገብቷቸው ሳይሆን ትእቢትና የበላይነት ስሜት ነው፡፡ ይህን በተመለከተ ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡-

” ﺇِﻧَّﻬُﻢْ ﻛَﺎﻧُﻮﺍ ﺇِﺫَﺍ ﻗِﻴﻞَ ﻟَﻬُﻢْ ﻟَﺎ ﺇِﻟَﻪَ ﺇِﻟَّﺎ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻳَﺴْﺘَﻜْﺒِﺮُﻭﻥَ * ﻭَﻳَﻘُﻮﻟُﻮﻥَ ﺃَﺋِﻨَّﺎ ﻟَﺘَﺎﺭِﻛُﻮ ﺁﻟِﻬَﺘِﻨَﺎ ﻟِﺸَﺎﻋِﺮٍ ﻣَﺠْﻨُﻮﻥٍ * ﺑَﻞْ ﺟَﺎﺀَ ﺑِﺎﻟْﺤَﻖِّ ﻭَﺻَﺪَّﻕَ ﺍﻟْﻤُﺮْﺳَﻠِﻴﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺼﺎﻓﺎﺕ 35-37
“እነርሱ ከአላህ ሌላ አምላክ የለም በተባሉ ጊዜ ይኮሩ ነበሩ። እኛ ለዕብድ ባለቅኔ ብለን አማልክቶቻችንን የምንተዉ ነን? ይሉም ነበር። አይደለም እዉነቱን (ሃይማኖት) አመጣ። መልክተኞቹንም እዉነተኛነታቸዉን አረጋገጠ።” (ሱረቱ-ሷፍፋት 35-37)፡፡

” ﻭَﻛَﺬَﻟِﻚَ ﻣَﺎ ﺃَﺭْﺳَﻠْﻨَﺎ ﻣِﻦْ ﻗَﺒْﻠِﻚَ ﻓِﻲ ﻗَﺮْﻳَﺔٍ ﻣِﻦْ ﻧَﺬِﻳﺮٍ ﺇِﻟَّﺎ ﻗَﺎﻝَ ﻣُﺘْﺮَﻓُﻮﻫَﺎ ﺇِﻧَّﺎ ﻭَﺟَﺪْﻧَﺎ ﺁﺑَﺎﺀَﻧَﺎ ﻋَﻠَﻰ ﺃُﻣَّﺔٍ ﻭَﺇِﻧَّﺎ ﻋَﻠَﻰ ﺁﺛَﺎﺭِﻫِﻢْ ﻣُﻘْﺘَﺪُﻭﻥَ * ﻗَﺎﻝَ ﺃَﻭَﻟَﻮْ ﺟِﺌْﺘُﻜُﻢْ ﺑِﺄَﻫْﺪَﻯ ﻣِﻤَّﺎ ﻭَﺟَﺪْﺗُﻢْ ﻋَﻠَﻴْﻪِ ﺁﺑَﺎﺀَﻛُﻢْ ﻗَﺎﻟُﻮﺍ ﺇِﻧَّﺎ ﺑِﻤَﺎ ﺃُﺭْﺳِﻠْﺘُﻢْ ﺑِﻪِ ﻛَﺎﻓِﺮُﻭﻥَ * ﻓَﺎﻧْﺘَﻘَﻤْﻨَﺎ ﻣِﻨْﻬُﻢْ ﻓَﺎﻧْﻈُﺮْ ﻛَﻴْﻒَ ﻛَﺎﻥَ ﻋَﺎﻗِﺒَﺔُ ﺍﻟْﻤُﻜَﺬِّﺑِﻴﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺰﺧﺮﻑ 23-25
“(ነገሩ) እንደዚሁም ነው፤ ከበፊትህ በማንኛይቱም ከተማ ውስጥ አስፈራሪን አልላክንም፣ ቅምጥሎችዋ፣ እኛ አባቶቻችንን በሃይማኖት አገኘን፤ እኛም በፈለጎቻቸው ላይ ተከታዮች ነን ያሉ ቢሆኑ እንጅ። (አስፈራሪውም)፡- አባቶቻችሁን በርሱ ላይ ከአገኛችሁበት ይበልጥ ቀጥተኛን (ሃይማኖት) ባመጣላችሁም? አላቸው፤ እኛ በርሱ በተላካችሁበት ነገር ከሐዲዎች ነን አሉ።  ከነሱም ተበቀልን፤ ያስተባባዮቹም መጨረሻ እንዴት እንደነበረ ተመልከት።” (ሱረቱ-ዙኽሩፍ 23-25)፡፡

ሌሎች ደግሞ በምቀኝነትና በቅናት ስሜት ሐቅን እያወቁና እያረጋገጡ መቀበል የማይፈልጉ አሉ፡፡ ልክ እንደ አህሉል-ኪታቦች (አይሁድ እና ክርስቲያኖች) ያሉት፡፡ እነሱ የነቢዩን ነቢይነት እያወቁ፡ የመምጫ ምልክቱም በመጽሐቸው በትንቢት ተነግሮ፡ ለምን ነቢይነት ከምድረ ዐረብ ሆነ በሚል ምቀኝነት የካዱና እውነቱን የደበቁ ናቸው፡፡ ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-

” ﻭَﺩَّ ﻛَﺜِﻴﺮٌ ﻣِﻦْ ﺃَﻫْﻞِ ﺍﻟْﻜِﺘَﺎﺏِ ﻟَﻮْ ﻳَﺮُﺩُّﻭﻧَﻜُﻢْ ﻣِﻦْ ﺑَﻌْﺪِ ﺇِﻳﻤَﺎﻧِﻜُﻢْ ﻛُﻔَّﺎﺭًﺍ ﺣَﺴَﺪًﺍ ﻣِﻦْ ﻋِﻨْﺪِ ﺃَﻧْﻔُﺴِﻬِﻢْ ﻣِﻦْ ﺑَﻌْﺪِ ﻣَﺎ ﺗَﺒَﻴَّﻦَ ﻟَﻬُﻢُ ﺍﻟْﺤَﻖُّ ﻓَﺎﻋْﻔُﻮﺍ ﻭَﺍﺻْﻔَﺤُﻮﺍ ﺣَﺘَّﻰ ﻳَﺄْﺗِﻲَ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﺑِﺄَﻣْﺮِﻩِ ﺇِﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻋَﻠَﻰ ﻛُﻞِّ ﺷَﻲْﺀٍ ﻗَﺪِﻳﺮٌ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺒﻘﺮﺓ 109
“ከመጽሐፉ ባለቤቶች ብዙዎች እውነቱ ከተገለጸላቸው በኋላ ከነፍሶቻቸው በኾነው ምቀኝነት ከእምነታችሁ በኋላ ከሓዲዎች አድርገው ሊመልሱዋችሁ ተመኙ፡፡ አላህም ትዕዛዙን እስከሚያመጣ ድረስ ይቅርታ አድርጉ፤ እለፏቸውም፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ከሃሊ ነውና፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 109)፡፡

” ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﺁﺗَﻴْﻨَﺎﻫُﻢُ ﺍﻟْﻜِﺘَﺎﺏَ ﻳَﻌْﺮِﻓُﻮﻧَﻪُ ﻛَﻤَﺎ ﻳَﻌْﺮِﻓُﻮﻥَ ﺃَﺑْﻨَﺎﺀَﻫُﻢْ ﻭَﺇِﻥَّ ﻓَﺮِﻳﻘًﺎ ﻣِﻨْﻬُﻢْ ﻟَﻴَﻜْﺘُﻤُﻮﻥَ ﺍﻟْﺤَﻖَّ ﻭَﻫُﻢْ ﻳَﻌْﻠَﻤُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺒﻘﺮﺓ 146
“እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው ወንዶች ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ (ሙሐመድን) ያውቁታል፡፡ ከነሱም የተለዩ ክፍሎች እነርሱ የሚያወቁ ሲኾኑ እውነቱን በእርግጥ ይደብቃሉ፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 146)፡፡

ሰው የአላህን የሂዳያ ተውፊቅ የሚጎናጸፈው፡ ራሱን ዝቅ በማድረግ ወዶ ለመቀበል ፈቃደኝነቱን ሲያሳይ ብቻ ነው፡፡ እኝም የሚጠበቅብን የ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ”ን መልእክት አውቆ መረዳት እንዲሁም በነገሩ እርግጠኛ መሆን ብቻ ሳይሆን ከልብ ወዶ መቀበልም ጭምር ነው፡፡ ይህ የአማኞች ባሕሪ ነውና፡፡

” ﺁﻣَﻦَ ﺍﻟﺮَّﺳُﻮﻝُ ﺑِﻤَﺎ ﺃُﻧْﺰِﻝَ ﺇِﻟَﻴْﻪِ ﻣِﻦْ ﺭَﺑِّﻪِ ﻭَﺍﻟْﻤُﺆْﻣِﻨُﻮﻥَ ﻛُﻞٌّ ﺁﻣَﻦَ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻭَﻣَﻠَﺎﺋِﻜَﺘِﻪِ ﻭَﻛُﺘُﺒِﻪِ ﻭَﺭُﺳُﻠِﻪِ ﻟَﺎ ﻧُﻔَﺮِّﻕُ ﺑَﻴْﻦَ ﺃَﺣَﺪٍ ﻣِﻦْ ﺭُﺳُﻠِﻪِ ﻭَﻗَﺎﻟُﻮﺍ ﺳَﻤِﻌْﻨَﺎ ﻭَﺃَﻃَﻌْﻨَﺎ ﻏُﻔْﺮَﺍﻧَﻚَ ﺭَﺑَّﻨَﺎ ﻭَﺇِﻟَﻴْﻚَ ﺍﻟْﻤَﺼِﻴﺮُ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺒﻘﺮﺓ 285
“መልክተኛው ከጌታው ወደርሱ በተወረደው አመነ፡፡ ምእምኖቹም (እንደዚሁ)፡፡ ሁሉም በአላህ፣ በመላዕክቱም፣ በመጻሕፍቱም፣ በመልክተኞቹም ከመልክተኞቹ «በአንድም መካከል አንለይም» (የሚሉ ሲኾኑ) አመኑ፡፡ «ሰማን፤ ታዘዝንም፡፡ ጌታችን ሆይ! ምሕረትህን (እንሻለን)፡፡ መመለሻም ወዳንተ ብቻ ነው» አሉም፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 285)፡፡

መ. ‹‹እውነተኛ መሆን››፡-

ይህ ማለት፡- ሰውየው በ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” እምነቱ እውነተኛ መሆን አለበት፡፡ በሃሰት ለማስመሰል ያላመነበትን ሆኖ ለመገኘት መጣር የለበትም፡፡ ይህ የመናፍቃን ባሕሪ ነው፡፡ እነሱ ከማኃበረሰቡ ላለመገለልና ባይተዋር ላለመሆን፡ ያላመኑበትን በሃሰት እንዳመኑ ሆነው ለመታየት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” ሊሉ ይችላሉ፡፡ እውነተኛ አማኝና ሃሰተኛው ግን የፈተና ወቅት ይበጠራል፡፡ ስለዚህም እኛ በ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” እምነታችን እውነተኛ ልንሆን ይገባናል፡፡ ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡-
” ﺍﻟﻢ * ﺃَﺣَﺴِﺐَ ﺍﻟﻨَّﺎﺱُ ﺃَﻥْ ﻳُﺘْﺮَﻛُﻮﺍ ﺃَﻥْ ﻳَﻘُﻮﻟُﻮﺍ ﺁﻣَﻨَّﺎ ﻭَﻫُﻢْ ﻟَﺎ ﻳُﻔْﺘَﻨُﻮﻥَ * ﻭَﻟَﻘَﺪْ ﻓَﺘَﻨَّﺎ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﻣِﻦْ ﻗَﺒْﻠِﻬِﻢْ ﻓَﻠَﻴَﻌْﻠَﻤَﻦَّ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﺻَﺪَﻗُﻮﺍ ﻭَﻟَﻴَﻌْﻠَﻤَﻦَّﺍﻟْﻜَﺎﺫِﺑِﻴﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻌﻨﻜﺒﻮﺕ 1-3
“አ.ለ.መ. (አሊፍ ላም ሚም) ሰዎቹ አምነናል በማለታቸው ብቻ እነሱ ሳይፈተኑ የሚትተዉ መሆናቸውን ጠረጠሩን? እነዚያንም ከነሱ በፊት የነበሩትን በእርግጥ ፈትነናል፤ እነዚያንም እውነት የተናገሩትን አላህ በእርግጥ ያውቃል፤ ውሸታሞችንም ያውቃል።” (ሱረቱል ዐንከቡት 1-3)፡፡

” ﻭَﻣِﻦَ ﺍﻟﻨَّﺎﺱِ ﻣَﻦْ ﻳَﻘُﻮﻝُ ﺁﻣَﻨَّﺎ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻭَﺑِﺎﻟْﻴَﻮْﻡِ ﺍﻟْﺂﺧِﺮِ ﻭَﻣَﺎ ﻫُﻢْ ﺑِﻤُﺆْﻣِﻨِﻴﻦَ * ﻳُﺨَﺎﺩِﻋُﻮﻥَ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻭَﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﺁﻣَﻨُﻮﺍ ﻭَﻣَﺎ ﻳَﺨْﺪَﻋُﻮﻥَ ﺇِﻟَّﺎ ﺃَﻧْﻔُﺴَﻬُﻢْ ﻭَﻣَﺎ ﻳَﺸْﻌُﺮُﻭﻥَ * ﻓِﻲ ﻗُﻠُﻮﺑِﻬِﻢْ ﻣَﺮَﺽٌ ﻓَﺰَﺍﺩَﻫُﻢُ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻣَﺮَﺿًﺎ ﻭَﻟَﻬُﻢْ ﻋَﺬَﺍﺏٌ ﺃَﻟِﻴﻢٌ ﺑِﻤَﺎ ﻛَﺎﻧُﻮﺍ ﻳَﻜْﺬِﺑُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺒﻘﺮﺓ 8-10
“ከሰዎችም «በአላህና በመጨረሻው ቀን አምነናል» የሚሉ አልሉ፤ እነርሱም አማኞች አይደሉም፡፡አላህንና እነዚያን ያመኑትን (ሰዎች) ያታልላሉ፤ የማያውቁ ሲኾኑ ነፍሶቻቸውን እንጅ ሌላን አያታልሉም፡፡በልቦቻቸው ውስጥ (የንፍቅና) በሽታ አለባቸው፡፡ አላህም በሽታን ጨመረባቸው፡፡ ለነርሱም ይዋሹ በነበሩት ምክንያት አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 8-10)፡፡

” ﻣِﻦَ ﺍﻟْﻤُﺆْﻣِﻨِﻴﻦَ ﺭِﺟَﺎﻝٌ ﺻَﺪَﻗُﻮﺍ ﻣَﺎ ﻋَﺎﻫَﺪُﻭﺍ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻋَﻠَﻴْﻪِ ﻓَﻤِﻨْﻬُﻢْ ﻣَﻦْ ﻗَﻀَﻰ ﻧَﺤْﺒَﻪُ ﻭَﻣِﻨْﻬُﻢْ ﻣَﻦْ ﻳَﻨْﺘَﻈِﺮُ ﻭَﻣَﺎ ﺑَﺪَّﻟُﻮﺍ ﺗَﺒْﺪِﻳﻠًﺎ * ﻟِﻴَﺠْﺰِﻱَ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﺍﻟﺼَّﺎﺩِﻗِﻴﻦَ ﺑِﺼِﺪْﻗِﻬِﻢْ ﻭَﻳُﻌَﺬِّﺏَ ﺍﻟْﻤُﻨَﺎﻓِﻘِﻴﻦَ ﺇِﻥْ ﺷَﺎﺀَ ﺃَﻭْ ﻳَﺘُﻮﺏَ ﻋَﻠَﻴْﻬِﻢْ ﺇِﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻛَﺎﻥَ ﻏَﻔُﻮﺭًﺍ ﺭَﺣِﻴﻤًﺎ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻷﺣﺰﺍﺏ 23-24
“አማኞቹ፥ በርሱ ላይ ለአላህ ቃል ኪዳን የገቡበትን በውነት የፈጸሙ ወንዶች አልሉ፤ ከነሱም ስለቱን የፈጸመ (ለሃይማኖቱ የተገደለ) አልለ፤ ከነሱም ገና የሚጠባበቀው አልለ፤ (የገቡበት ቃል) መለወጥንም አልለወጡም። አላህም እውነተኞችን በውነተኛነታቸው ሊመነዳ፣ መናፍቃንንም ቢሻ ሊቀጣ፣ ወይም (ቢመለሱ) በነሱ ላይ ጸጸታቸውን ሊቀበል፥ (ይህን አደረገ)፤ አላህ መሐሪ አዛኝ ነውና።” (ሱረቱል አሕዛብ 23-24)፡፡

ጌታችን አላህ ሆይ! በአንተ አምላክነት እና ብቸኛ ተመላኪነት ላይ፡ ወዶ የሚቀበል ልብና ከኒፋቅ የጠራ እውነተኝነትን ለግሰን አሚን፡፡ ይቀጥላል