የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” ክፍል -4

ሼር ያድርጉ
423 Views

በኡስታዝ አቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

4. መስፈርቶቹ፡-

በክፍል ሶስት ትምሕርት መሰረት የ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ”ን ሃሳብና መልእክት ሊገልጹ የሚችሉ መጠሪያ ስሞችን በመጥቀስ ከተረዳን፡ አሁን ደግሞ በ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” ውስጥ መካተት ስለሚገባቸው መስፈርቶች የተወሰነ እንማራለን ኢንሻአላህ፡፡

ሀ. ‹‹መልእክቱንና ትርጉሙን ማወቅ››፡-

ይህ የመጀመሪያው መስፈርት ነው፡፡ የ”ላ-ኢላሀ ኢለልሏህ”ን የምስክርነት ቃል በልባቸው አምነው በአንደበታቸው የሚናገሩ ሰዎች፡ መልእክቱንና ትርጉሙንም ጭምር ያወቁ መሆን አለባቸው፡፡ የ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ”ን ትክክለኛ ትርጓሜ ማወቅ የጎላ ጠቀሜታ አለው፡፡ ከጥቅሞቹም ውስጥ፡- ሽርክ ውስጥ እንዳንዘፈቅ ጋሻ ይሆነናል፡፡ ሰዎች በአንደበታቸው “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” እያሉ በተግባር ግን ሽርክ ላይ የሚገኙበት ዋናው ምክንያት የተውሒድ ጠላት ወይም ሌላ ተልእኮ ያላቸው ስለሆኑ ሳይሆን፡ የ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ”ን መልእክት በአግባቡ አለመረዳታቸው ነው፡፡ ስለሆነም ይህ የምትሰሩት ስራ ሽርክ ነውና አቁሙ! ተብለው ሲመከሩ፡- እኛ እኮ ሙስሊሞች ነን! “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” እያልን እኮ ነው! ብለው ይከራከራሉ፡፡ የሚሰሩት የሽርክ ተግባር ከ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” ጋር የሚጋጭ መሆኑን አለመገንዘብ ያመጣው ችግር ነው፡፡ አላሁመ-ነጂና፡፡

“ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” ማለት፡- አላህን በብቸኝነት አምልኮ መገኘትና፡ ለአላህ የሚገባውን ማንኛውንም አይነት የአምልኮ ዘርፍ ከአላህ ውጪ ላለ አካል አሳልፎ አለመስጠት መሆኑን የተረዳ ሰው፡ እንዴት ሽርክን ይተግብራል? በጥቅም መታወርና ትእቢት ካልሆነ በስተቀር፡፡ ሶላት ለአላህ ብቻ የሚገባ የዒባዳ አይነት መሆኑን የተረዳ ሰው እንዴት ለፍጡር ይሰግዳል? በሩቁ መማጸን (ዱዓእ) ዒባዳ መሆኑን ያወቀ ሰው፡ እንዴት የሞተ አካልን ይማጸናል? አላህን በገይብ (በሩቁ) መፍራት አምልኮ መሆኑን የተረዳ ሰው፡ እንዴት ፍጡርን በሩቅ ይፈራል? የዚህ ሁሉ መንስኤው የ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ”ን ትርጓሜና መልእክት በአግባቡ አለመረዳት ነው፡፡ ስለዚህም ትርጓሜውን ማወቅ የመጀመሪያው መስፈርት ነው፡፡ ትርጉሙን በተመለከተ በክፍል ሁለት ላይ በሰፊው ተዳስሶአል፡፡

ሌላው ጥቅሙ ደግሞ የሞራል የበላይነት ‹‹ዒዝዘቱ-ነፍስ››ን ያጎናጽፋል፡፡ ህይወቱና ሞቱ በጠቅላላ፡ ለአንድ አላህ ብቻ መሆኑን የተረዳ አንድ ሙስሊም፡ የሚያመልከውና የሚሰግድለት ጌታ እሱ ብቻ መሆኑን ያወቀ ሙስሊም፡ በችግር ሰዓትም አላህን ብቻ ድረስልኝ፡ በደስታውም ጊዜ አላህን ብቻ ተመስገን ጌታዬ! ያለ ሙስሊም፡ በህይወቱ ላይ ሌላ ኃይልና ስልጣን ያለው አካል እንደሌለ ይረዳል፡፡ እሱም የአንድ ጌታ ባሪያና ታዛዥ ብቻ መሆኑን ሲያውቅ ነፍሱ በደስታ ትፈነድቃለች፡፡ የሞራል የበላይነትም ይሰማዋል፡፡ በመሆኑም የ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ”ን መልእክት ሁላችንም በአግባቡ ማወቅና መረዳት ይኖርብናል፡፡ ዕውቀት መስፈርት መሆኑን ከሚያመላክቱ መረጃዎች ውስጥ ከፊሎቹን ቀጥለን እንመልከታቸው፡-

” ﻓَﺎﻋْﻠَﻢْ ﺃَﻧَّﻪُ ﻟَﺎ ﺇِﻟَﻪَ ﺇِﻟَّﺎ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻭَﺍﺳْﺘَﻐْﻔِﺮْ ﻟِﺬَﻧْﺒِﻚَ ﻭَﻟِﻠْﻤُﺆْﻣِﻨِﻲﻥَ ﻭَﺍﻟْﻤُﺆْﻣِﻨَﺎﺕِ ﻭَﺍﻟﻠَّﻪُ ﻳَﻌْﻠَﻢُ ﻣُﺘَﻘَﻠَّﺒَﻜُﻢْ ﻭَﻣَﺜْﻮَﺍﻛُﻢْ ” ﺳﻮﺭﺓ ﻣﺤﻤﺪ 19
“እነሆ ከአላህ ሌላ አምላክ አለመኖሩን ዕወቅ፤ ስለ ስሕተትም ለምእመናንም ምሕረትን ለምን፤ አላህም መዘዋወሪያችሁን መርጊያችሁንም ያውቃል።” (ሱረቱ ሙሐመድ 19)፡፡

በዚህ አንቀጽ ላይ ጌታ አላህ ከርሱ በቀር ሌላ የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን ‹‹እመን›› ወይም ‹‹ተናገር›› ሳይሆን ያለው ‹‹ዕወቅ›› በማለት ነው የገለጸው፡፡ ለትክክለኛ እምነትና ንግግር መሰረቱ የተስተካከለ ዕውቀት ነውና!!

ኢማሙል ቡኻሪይም (ረሒመሁላህ) በኪታባቸው ላይ ይህን የቅዱስ ቁርኣን አንቀጽ ዋቢ በማድረግ እንዲህ ይላሉ፡- ‹‹አል-ዒልሙ ቀብለል-ቀውሊ ወል-ዐመል›› “ዕውቀት ከንግግና ከስራ በፊት ቀዳሚ ነው”፡፡ (ቡኻሪይ፡ ኪታቡል-ዒልም 10ኛው ባብ)፡፡

” ﻭَﻟَﺎ ﻳَﻤْﻠِﻚُ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﻳَﺪْﻋُﻮﻥَ ﻣِﻦْ ﺩُﻭﻧِﻪِ ﺍﻟﺸَّﻔَﺎﻋَﺔَ ﺇِﻟَّﺎ ﻣَﻦْ ﺷَﻬِﺪَ ﺑِﺎﻟْﺤَﻖِّ ﻭَﻫُﻢْ ﻳَﻌْﻠَﻤُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺰﺧﺮﻑ 86
“እነዚያም ከአላህ ሌላ የሚግገዟቸው እነሱ የሚያውቁ ሆነው በውነት ከመሰከሩት በስተቀር ምልጃን አይችሉም።” (ሱረቱ-ዙኽሩፍ 86)፡፡

በዚህ የቁርኣን አንቀጽ ላይ ‹‹የእውነት ምስክርነት የተባለው›› የ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” ምስክርነት እንደሆነ ታላቁ የቁርኣን ሙፈሲር ኢማሙል-በገዊይ ረሒመሁላህ (433-516 ሒጅ.) በተፍሲር ኪታባቸው ላይ ገልጸውታል፡፡ አያይዘውም ‹‹የሚያውቁ ሆነው›› የሚለውንም ሲያብራሩት፡- አንደበታቸው የመሰከረውን በልባቸውም የተረዱት ሆነው በማለት ገልጸውታል፡፡ (መዓሊሙ-ተንዚል፡ ሱረቱ-ዙኽሩፍ 86)፡፡ በመሆኑም ስለ “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” የሚመሰክር ሰው ትርጉሙን ማወቅ እና መረዳት አለበት ማለት ነው፡፡

ዑሥማን ኢብኑ-ዐፋን (ረዲየላሁ ዐንሁ) ባስተላለፈው ሐዲሥ ላይ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን አውቆ (አምኖ) የሞተ ሰው ጀነት ገባ” (ሙስሊም 145)፡፡ ከዚህ ሐዲሥም የምንወስደው ትምህርት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ”ን በአግባቡ ማወቅ እንዳለብን ነው፡፡

ለ. ‹‹እርግጠኛ መሆን››፡-

ሌላው መስፈርት ደግሞ፡- ባወቅነውና ባመንነው ነገር ላይ ያለ-ምንም መወላወል ፍጹም እርግጠኞች ልንሆን ይገባናል፡፡ በጥርጣሬ ላይ የተገነባ እምነት ዋጋ የለውም፡፡ አላህ ከአማኝ ባሪያዎቹ የሚፈልገው ፍጹም እርግጠኝነትን ነው፡፡ አዎ! ከጌታችን አላህ ውጪ አምላክና ፈጣሪ እንደሌለ፡ ከርሱም በስተቀር እውነተኛ አምልኮ የሚገባው ማንም እንደሌለ በፍጹም እርግጠኝነት ያለ-ምንም ማመንታት እናምናለን እንመሰክራለንም!!! አላህ የአማኞች ባሕሪ ምን አይነት እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡-

” ﺇِﻧَّﻤَﺎ ﺍﻟْﻤُﺆْﻣِﻨُﻮﻥَ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﺁﻣَﻨُﻮﺍ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻭَﺭَﺳُﻮﻟِﻪِ ﺛُﻢَّ ﻟَﻢْ ﻳَﺮْﺗَﺎﺑُﻮﺍ ﻭَﺟَﺎﻫَﺪُﻭﺍ ﺑِﺄَﻣْﻮَﺍﻟِﻬِﻢْ ﻭَﺃَﻧْﻔُﺴِﻬِﻢْ ﻓِﻲ ﺳَﺒِﻴﻞِ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﺃُﻭﻟَﺌِﻚَ ﻫُﻢُ ﺍﻟﺼَّﺎﺩِﻗُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺤﺠﺮﺍﺕ 14
“(እውነተኛዎቹ) ምእመናን እነዚያ በአላህና በመልክተኛው ያመኑት ከዚያም ያልተጠራጠሩት፣ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸውም በአላህ መንገድ የታገሉት ብቻ ናቸው፤ እነዚያ እነሱ ውነተኞቹ ናቸው።” (ሱረቱል ሑጁራት 14)፡፡

በዚህ አንቀጽ ውስጥ በአላህና በመልክተኛው ያመኑ ሰዎች የማይጠራጠሩ መሆን እንደሚገባቸው እንማራለን፡፡
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ባስተላለፈው ሐዲሥ ላይም የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- “በልቡ እርግጠኛ ሆኖ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን ሲመሰክር ያገኘኸውን ሰው በጀነት አበስረው” (ሙስሊም 156)፡፡

አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) በድጋሚ ባስተላለፈው ሌላሐዲሥ ላይ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- “ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩና እኔም የሱ መልክተኛ መሆኔን እመሰክራለሁ፡፡ በነዚህ ቃላቶች ያልተጠራጠረ ሆኖ አንድ ባሪያ አላህን አይገናኝም ጀነት የገባ ቢሆን እንጂ” (ሙስሊም 147)፡፡

መጠራጠር የመናፍቃን ባሕሪ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉም ጨርሰው አይክዱ፡ ወይም የተረጋጋ አማኝ አይሆኑም፡፡ ሁሌም በዋለለ ጥርጣሬ ውስጥ ናቸው፡፡ የነሱ መንገድ፡- ‹‹ጀነትና እሳት ቢኖርም ባይኖርም፡ ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም›› የምትለዋ ብሂል ነች፡፡ ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡-

” ﻟَﺎ ﻳَﺴْﺘَﺄْﺫِﻧُﻚَ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﻳُﺆْﻣِﻨُﻮﻥَ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻭَﺍﻟْﻴَﻮْﻡِ ﺍﻟْﺂﺧِﺮِ ﺃَﻥْ ﻳُﺠَﺎﻫِﺪُﻭﺍ ﺑِﺄَﻣْﻮَﺍﻟِﻬِﻢْ ﻭَﺃَﻧْﻔُﺴِﻬِﻢْ ﻭَﺍﻟﻠَّﻪُ ﻋَﻠِﻴﻢٌ ﺑِﺎﻟْﻤُﺘَّﻘِﻴﻦَ * ﺇِﻧَّﻤَﺎ ﻳَﺴْﺘَﺄْﺫِﻧُﻚَ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﻟَﺎ ﻳُﺆْﻣِﻨُﻮﻥَ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻭَﺍﻟْﻴَﻮْﻡِ ﺍﻟْﺂﺧِﺮِ ﻭَﺍﺭْﺗَﺎﺑَﺖْ ﻗُﻠُﻮﺑُﻬُﻢْ ﻓَﻬُﻢْ ﻓِﻲ ﺭَﻳْﺒِﻬِﻢْ ﻳَﺘَﺮَﺩَّﺩُﻭﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺘﻮﺑﺔ 45
“እነዚያ በአላህና በመጨረሻዉ ቀን የሚያምኑት በገንዘቦቻቸዉና በነፍሶቻቸው ከመታገላቸው (ለመቅረት) ፈቃድን አይጠይቁህም፤ አላህም የሚፈሩትን ዐዋቂ ነው። ፈቃድን የሚጠይቁህ እነዚያ በአላህና በመጨረሻዉ ቀን የማያምኑት ልቦቻቸዉም የተጠራጠሩት ብቻ ናቸው፤ እነሱም በጥረጣሬያቸው ዉስጥ ይዋልላሉ።” (ሱረቱ-ተውባህ 45)፡፡

ጌታችን አላህ ሆይ! ስላንተ ትክክለኛ ዕውቀትን፡ ባንተና በመጨረሻውም ቀን እርግጠኛ የሆነ እምነትን በራሕመትህ ለግሰን አሚን፡፡
ይቀጥላል ቢኢዝኒላህ ኢንሻአላህ

Shortlink http://q.gs/Ey5yH