የኢስላም መልእክት “ላ ኢላሀ ኢልለሏህ” ክፍል -3

ሼር ያድርጉ
495 Views

በኡስታዝ አቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

3. መጠሪያ ስሞቹ፡-

ዛሬ በክፍል ሶስት ላይ ደግሞ የምንመለከተው የ”ላ ኢላሀ ኢልለሏህ”ን መጠሪያ ስሞች ነው፡፡ “ላ ኢላሀ ኢልለሏህ” ሃሳቡን ሊገልጹና ሊያብራሩት የሚችሉ የተለያዩ አይነት መጠረያ ስሞች አሉት፡፡ ከነዚህም መሐከል፡-

ሀ. ከሊመቱል-ዐቂዳህ:- ‹‹ዐቂዳህ›› የሚለው ቃል ‹‹ዐቅድ›› ከሚለው ሀረግ የተመዘዘ ነው፡፡ ‹‹ዐቅድ›› ማለት አንድ ነገር በደንብ መቋጠር፣ እንዳይላላ ማጥበቅ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም የጋብቻ ቃል-ኪዳን ‹‹ዑቅደቱ-ኒካህ›› ተብሎ ይጠራል፡፡

የ”ላ-ኢላሀ ኢለሏህ” እምነትም በአንድ ሙስሊም ልብ ውስጥ በጠነከረ መልኩ መያዝ ስላለበት ‹‹ከሊመቱል-ዐቂዳህ›› ተብሎ ይጠራል፡፡ አንድ ሰው አንተን፡- ዐቂዳህ ምንድነው? ብሎ ቢጠይቅህ፡ ትርጉሙ፡- በልብህ አምነህ የያዝከውና የቋጠርከው ምንድነው? ማለቱ ነው፡፡ በዚህ ስያሜም ከተዘጋጁ ኪታቦች ውስጥ፡-

1. ‹‹አል-ዐቂዳህ›› ኢማሙ አሕመድ ኢብኑ-ሐንበል (241 ሒጅ.)
2. ‹‹አል-ዐቂደቱ ጠሀዊያህ›› አቡ ጀዕፈር አጥ-ጠሃዊይ (321 ሒጅ.)
3. ‹‹ኢዕቲቃዱ አኢመቱል-ሐዲሥ›› አቡ-በክር አል-ኢስማዒሊይ (371 ሒጅ.)
4. ‹‹አል-ኢዕቲቃድ›› አል-ኢማም አል-በይሀቂይ (458 ሒጅ.)
5. ‹‹አል-ዐቂደቱል ዋሲጢያህ›› ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያህ (728 ሒጅ.)

ለ. ከሊመቱ-ተውሒድ፡- ‹‹ተውሒድ›› ማለት፡- የአላህን ፍጹማዊ አንድነት (በህልውናውም፣ በስራውም፣ በባሕሪያቱም፣ በአምልኮትም) አምኖ መቀበል ማለት ነው፡፡ የቃሉ ስርወ ግንድ ‹‹ዋሒድ›› የሚለው ቃል ነውና፡፡ የ”ላ-ኢላሀ ኢለሏህ” እምነትም አላህን በብቸኝነት ማምለክን የሚጠይቅ በመሆኑ ‹‹ከሊመቱ-ተውሒድ›› ተብሎም ይጠራል፡፡ በዚህ ስያሜ ከተዘጋጁ ኪታቦች መሐከል፡-

1. ‹‹ኪታቡ-ተውሒድ›› ሙሐመድ ኢብኑ ኢስሐቅ ኢብኑ ኹዘይማህ (311 ሒጅ.)፡፡
2. ‹‹አት-ተውሒድ›› አቡ መንሱር አል-ማቱሪዲይ (333 ሒጅ.)
3. ‹‹ኪታቡ-ተውሒድ›› ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዱል-ወሃብ (1206 ሒጅ.)፡፡

ሐ. ኢማን፡- ‹‹ኢማን›› ማለት፡- ልብ አምኖ የተቀበለው፣ ምላስ ለእውነተኝነቱ የመሰከረለት፣ ሰውነት በስራ የገለጸው ማለት ነው፡፡ የ”ላ-ኢላሀ ኢለሏህ” መልእክትም ሰው በልቡ የሚያምነው፣ በአንደበቱ በሸሀዳህ የሚመሰክረው፣ በሰውነቱም በስራ የሚገልጸው ስለሆነ ኢማን ይባላል፡፡ ደግሞም ከኢማን ክፍሎች ትልቁ ላ ኢላሀ ኢልለሏህ እንደሆነም በሐዲሥ ተነግሯል፡፡ በዚህ ስያሜ ከተዘጋጁ መጻህፍት መካከል፡

1. ‹‹አል-ኢማን ወመዓሊሙሁ›› አቢ-ዑበይድ ቃሲም ኢብኑ-ሰላም (223 ሒጅ.)
2. ‹‹አል-ኢማን›› ሙሐመድ ኢብኑ-የሕያ አል-ዑደኒይ (243 ሒጅ.)
3. ‹‹አል-ኢማን›› ሙሐመድ ኢብኑ ኢስሐቅ ኢብኑ-መንደህ (395 ሒጅ.)
4. ‹‹አል-ኢማን ወኡሱሊሂ›› አቡ መንሱር አብዱል-ቃሂር አል-ባግዳዲይ (429 ሒጅ.)
5. ‹‹አል-ኢማን›› ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያህ (728 ሒጅ.)

መ. አል-ዑርወቱል ውሥቃ፡- ‹‹አል-ዑርወቱል ውሥቃ›› ማለት፡- የማይበጠስ የሆነ ጠንካራ ዘለበት ማለት ነው፡፡ በላ ኢላሀ ኢልለሏህ እምነት የተሳሰረን ሰው፡ አስተማማኝ በሆነ መልኩ ወደ ጀነት የሚያደርሰው ድልድይ በመሆኑ፡ ‹‹አል-ዑርወቱል ውሥቃ›› ተብሎ ይጠራል፡፡ አላህ በቅዱስ ቃሉ እንዲህ ይላል፡-

” ﻟَﺎ ﺇِﻛْﺮَﺍﻩَ ﻓِﻲ ﺍﻟﺪِّﻳﻦِ ﻗَﺪْ ﺗَﺒَﻴَّﻦَ ﺍﻟﺮُّﺷْﺪُ ﻣِﻦَ ﺍﻟْﻐَﻲِّ ﻓَﻤَﻦْ ﻳَﻜْﻔُﺮْ ﺑِﺎﻟﻄَّﺎﻏُﻮﺕِ ﻭَﻳُﺆْﻣِﻦْ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻓَﻘَﺪِ ﺍﺳْﺘَﻤْﺴَﻚَ ﺑِﺎﻟْﻌُﺮْﻭَﺓِ ﺍﻟْﻮُﺛْﻘَﻰ ﻟَﺎ ﺍﻧْﻔِﺼَﺎﻡَ ﻟَﻬَﺎ ﻭَﺍﻟﻠَّﻪُ ﺳَﻤِﻴﻊٌ ﻋَﻠِﻴﻢٌ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺒﻘﺮﺓ 256
“በሃይማኖት ማስገደድ የለም፡፡ ቅኑ መንገድ ከጠማማው በእርግጥ ተገለጠ፡፡ በጣዖትም የሚክድና በአላህ የሚያምን ሰው ለርሷ መበጠስ የሌላትን ጠንካራ ዘለበት በእርግጥ ጨበጠ፡፡ አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 256)፡፡

ኢብኑ ከሢር (ረሒመሁላህ) በተፍሲራቸው ላይ ፡- ‹‹አል-ዑርወቱል ውሥቃ (ጠንካራ ዘለበት)›› የተባለው ምን እንደሆነ ለማብራራት፡ ሰዒድ ኢብኑ ጁበይርንና ደሓክን (አላህ ይዘንላቸው) ዋቢ በማድረግ የሰጡት ትርጉም፡- ‹‹ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ›› የሚለው ነው ብለዋል፡፡

ሠ. ‹‹አል-ቀውሉ-ሣቢት››፡- ‹‹አል-ቀውሉ-ሣቢት›› ማለት፡- የጸናች ቃል ማለት ነው፡፡ በምድራዊ ህይወታቸው በእምነታቸው ጸንተው የሞቱ ሙስሊሞች፡ ቀብር ውስጥም በመልአኮቹ ጌታህ ማነው? ነቢይህስ? ሃይማኖትህስ? የሚል ጥያቄ በሚቀርብላቸው ጊዜ፡ አላህ የዛኔም እነሱን በማጽናት በላኢላሀ ኢልለሏህ እና ሙሐመዱን ረሱሉሏህ እንዲመልሱ ያጸናቸዋል፡፡ ቅዱስ ቁርአን እንዲህ ይላል፡-

” ﻳُﺜَﺒِّﺖُ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﺁﻣَﻨُﻮﺍ ﺑِﺎﻟْﻘَﻮْﻝِ ﺍﻟﺜَّﺎﺑِﺖِ ﻓِﻲ ﺍﻟْﺤَﻴَﺎﺓِ ﺍﻟﺪُّﻧْﻴَﺎ ﻭَﻓِﻲ ﺍﻟْﺂﺧِﺮَﺓِ ﻭَﻳُﻀِﻞُّ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﺍﻟﻈَّﺎﻟِﻤِﻴﻦَ ﻭَﻳَﻔْﻌَﻞُ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻣَﺎ ﻳَﺸَﺎﺀُ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺇﺑﺮﺍﻫﻴﻢ 27
“አላህ እነዚያን ያመኑትን በቅርቢቱም ሕይወት በመጨረሻይቱም (በመቃብር) በተረጋገጠው ቃል ላይ ያረጋቸዋል፤ ከሐዲዎችንም፣ አላህ ያሳስታቸዋል፤ አላህም የሚሻውን ይሠራል።” (ሱረቱ ኢብራሂም 27)፡፡

ይህንን የቁርኣን አንቀጽ አስመልክቶ በራእ ኢብኑ ዐዚብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ከአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የሰማውን እንዲህ ይገልጸዋል፡- “ሙስሊም በቀብር ውስጥ በተጠየቀ ጊዜ፡- ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ እንደሌለና ሙሐመድም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ መልክተኛ መሆናቸውን ይመሰክራል፡፡ ይህም እንዲህ የሚለው የቁርኣን ቃል ነው፡- ‹‹አላህ እነዚያን ያመኑትን በቅርቢቱም ሕይወት በመጨረሻይቱም (በመቃብር) በተረጋገጠው ቃል ላይ ያረጋቸዋል፤››” (ቡኻሪይ 4699)፡፡

ረ. ከሊመቱ-ጦይዪባህ፡- ‹‹ከሊመቱ-ጦይዪባህ›› ማለት መልካም ንግግር ማለት ነው፡፡ ከ ላ ኢላሀ ኢልለሏህ የሚበልጥ መልካም ንግግር ደግሞ በዓለማችን ላይ የለም፡፡ ይህን አስመልከቶ ታላቁ ነቢይ እንዲህ ይላሉ፡- “ከዱዓዎች ሁሉ በላጩ የዐረፋ ቀን ዱዓእ ነው፡፡ እኔና ከበፊቴ የነበሩት ነቢያት ከተናገርነው ቃላት ሁሉ በላጩ፡- ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏሁ፡ ወሕደሁ፡ ላ-ሸሪከ ለህ፣ ለሁል-ሙልኩ፡ ወለሁል-ሐምድ፣ ወሁወ ዐላ-ኩሊ ሸይኢን ቀዲር›› የሚለው ነው” (ቲርሚዚይ 3585፣ ሶሒሑል-ጃሚዕ 3274)፡፡ በቅዱስ ቁርኣን ውስጥም ይህን ሃሳብ የሚደግፍ አንቀጽ አለ፡-

” ﺃَﻟَﻢْ ﺗَﺮَ ﻛَﻴْﻒَ ﺿَﺮَﺏَ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻣَﺜَﻠًﺎ ﻛَﻠِﻤَﺔً ﻃَﻴِّﺒَﺔً ﻛَﺸَﺠَﺮَﺓٍ ﻃَﻴِّﺒَﺔٍ ﺃَﺻْﻠُﻬَﺎ ﺛَﺎﺑِﺖٌ ﻭَﻓَﺮْﻋُﻬَﺎ ﻓِﻲ ﺍﻟﺴَّﻤَﺎﺀِ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺇﺑﺮﺍﻫﻴﻢ 24
“አላህ መልካምን ቃል ሥርዋ (በምድር ውስጥ) የተደላደለች ቅርንጫፍዋም ወደ ሰማይ (የረዘመች) እንደሆነች መልካም ዛፍ አድርጎ ምሳሌን እንዴት እንደገለጸ አላየኽምን?” (ሱረቱ ኢብራሂም 24)፡፡

ኢብኑ ከሢር (ረሒመሁላህ) በተፍሲር ኪታባቸው ላይ ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስን (ረዲየላሁ ዐንሁማ) ዋቢ በማድረግ ‹‹ከሊመተን-ጠይዪባህ (መልካም ቃል)›› የተባለችዋ፡- ላ ኢላሀ ኢልለሏህ እንደሆነች ይገልጻሉ፡፡

ሰ. ከሊመቱ-ሰዋእ፡- ‹‹ከሊመቱ-ሰዋእ›› ማለት፡- የእኩልነት ቃል ማለት ነው፡፡ ሰዎችን ሁሉ በዘር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በስልጣን..ያለ ምንም ማበላለጥ እኩል ሊያደርጋቸው የሚችለው ቃል፡ ይኸው ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› የሚለው የእምነት ቃል ነው፡፡ ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-

” ﻗُﻞْ ﻳَﺎ ﺃَﻫْﻞَ ﺍﻟْﻜِﺘَﺎﺏِ ﺗَﻌَﺎﻟَﻮْﺍ ﺇِﻟَﻰ ﻛَﻠِﻤَﺔٍ ﺳَﻮَﺍﺀٍ ﺑَﻴْﻨَﻨَﺎ ﻭَﺑَﻴْﻨَﻜُﻢْ ﺃَﻟَّﺎ ﻧَﻌْﺒُﺪَ ﺇِﻟَّﺎ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻭَﻟَﺎ ﻧُﺸْﺮِﻙَ ﺑِﻪِ ﺷَﻴْﺌًﺎ ﻭَﻟَﺎ ﻳَﺘَّﺨِﺬَ ﺑَﻌْﻀُﻨَﺎ ﺑَﻌْﻀًﺎ ﺃَﺭْﺑَﺎﺑًﺎ ﻣِﻦْ ﺩُﻭﻥِ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻓَﺈِﻥْ ﺗَﻮَﻟَّﻮْﺍ ﻓَﻘُﻮﻟُﻮﺍ ﺍﺷْﻬَﺪُﻭﺍ ﺑِﺄَﻧَّﺎ ﻣُﺴْﻠِﻤُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺁﻝ ﻋﻤﺮﺍﻥ 64
“የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! በኛና በናንተ መካከል ትክክል ወደሆነች ቃል ኑ፤ (እርሷም) አላህን እንጅ ሌላን ላንገዛ በርሱም ምንንም ላናጋራ፣ ከፊላችንም ከፊሉን ከአላህ ሌላ አማልክት አድርጐ ላይይዝ ነዉ፤ በላቸዉ። እምቢ ቢሉም ፡- እኛ ሙስሊሞች መሆናችንን መስክሩ በሏቸው” (ሱረቱ አለ-ዒምራን 64)፡፡

ሸ. ደዕወቱል-ሐቅ፡- ‹‹ደዕወቱል-ሐቅ›› ማለት፡- የእውነት ጥሪ ማለት ነው፡፡ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን በማስተማር ወደ ላ ኢላሀ ኢልለሏህ ከሚደረግ ጥርሪ የበለጠ እውነተኛ ግብዣ የለም፡፡ ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡-

” ﻟَﻪُ ﺩَﻋْﻮَﺓُ ﺍﻟْﺤَﻖِّ ﻭَﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﻳَﺪْﻋُﻮﻥَ ﻣِﻦْ ﺩُﻭﻧِﻪِ ﻟَﺎ ﻳَﺴْﺘَﺠِﻴﺒُﻮﻥَ ﻟَﻬُﻢْ ﺑِﺸَﻲْﺀٍ ﺇِﻟَّﺎ ﻛَﺒَﺎﺳِﻂِ ﻛَﻔَّﻴْﻪِ ﺇِﻟَﻰ ﺍﻟْﻤَﺎﺀِ ﻟِﻴَﺒْﻠُﻎَ ﻓَﺎﻩُ ﻭَﻣَﺎ ﻫُﻮَ ﺑِﺒَﺎﻟِﻐِﻪِ ﻭَﻣَﺎ ﺩُﻋَﺎﺀُ ﺍﻟْﻜَﺎﻓِﺮِﻳﻦَ ﺇِﻟَّﺎ ﻓِﻲ ﺿَﻠَﺎﻝٍ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺮﻋﺪ 14
“ለርሱ (ለአላህ) የውነት መጥሪያ አለው፤ እነዚያም ከርሱ ሌላ የሚግገዙዋቸው (ጣዖታት) ወደ አፉ ይደርስ ዘንድ ወደ ውሃ መዳፎቹን (በሩቅ ሆኖ) እንደሚዘረጋ (ሰው መልስ) እንጂ ለነርሱ በምንም አይመልሱላቸውም፤ እርሱም ወደ አፉ ደራሽ አይደለም፤ የከሐዲዎችም ጥሪ በከንቱ እንጂ አይደለም።” (ሱረቱ-ረዕድ 14)፡፡

ኢብኑ ከሢር (ረሒመሁላህ) በተፍሲር ኪታባቸው ላይ ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስንና ቀታዳህን (ረዲየላሁ ዐንሁም) ዋቢ በማድረግ ‹‹ደዕወቱል-ሐቅ (እውነተኛ ጥሪ)›› የተባለችዋ፡- ላ ኢላሀ ኢልለሏህ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ ስምንቱ ከብዙ በጥቂቱ የቀረቡ ናቸው፡፡ የላኢላሀ ኢለሏህን መልእክት በተለያየ ስያሜ የሚገልጹ የሆኑ ማለት ነው፡፡ አላህ ሰምተው ከሚጠቀሙ ባሮቹ ያድረገን አሚን፡፡

Shortlink http://q.gs/Ey5xu