የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” 28 በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
493 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
9. ትሩፋቱ (ጥቅሙ)፡-
እስከዛሬ በቆየንባቸው 27 ተከታታይ ክፍል ስር ስለ ‹‹ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ›› ምንነት ስምንት ነጥቦችን አንስተን በተወሰነ መልኩ ቃኝነተን ነበር፡፡ እነሱም፡-
1. አስፈላጊነቱ
2. ትርጉሙ
3. የላኢላሀ ኢልለሏህ መጠሪያ ስሞች
4. የላኢላሀ ኢልለላህ መስፈርቶች
5. የሺርክ ምንነት
6. የኩፍር ምንነት
7. የኒፋቅ ምንነት
8. የሽርክ መከሰት ምክንያቶች
ዛሬ ደግሞ ‹‹ላ-ኢላሀ ኢለሏህ›› ማለት፡ ለባለቤቱ ምን አይነት ጥቅም ያስገኝለታል የሚለውን መጠነኛ ዳሰሳ እናደርግበታለን፡፡ መልካም ንባብ!
ሀ. ለጀነት ይዳርጋል፡-
ከ‹‹ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ›› አንዱና ዋነኛ ጥቅሞች ውስጥ ባለቤቱን ለጀነት ማብቃቱ ነው፡፡ የዚህ እምነት ባለቤቶች በዚሁ ‹‹ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ›› ጸንተው ከሞቱና በተለይ የመጨረሻ ቃላቸው በ‹‹ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ›› ከተዘጋ የጀነት ይሆናሉ፡፡ አላህ ይወፍቀን፡-
ሙዐዝ ኢብኑ ጀበል (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “የመጨረሻ ንግግሩ ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ የሆነ ሰው ጀነት ገባ” (አቡ ዳዉድ 3118፣ አሕመድ 22087)፡፡
አቡ ዘር (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ ብሎ ከዛም በዚህ እምነት የሚሞት አንድም የአላህ ባሪያ የለም ጀነት የገባ ቢሆን እንጂ!” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
ዑሥማን ኢብኑ-ዐፋን (ረዲየላሁ ዐንሁ) ባስተላለፈው ሐዲሥ ላይ ደግሞ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን አውቆ (አምኖ) በዚሁ እምነቱ የሞተ ሰው ጀነት ገባ” (ሙስሊም 145)፡፡
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ባስተላለፈው ሐዲሥ ላይም የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- “በልቡ እርግጠኛ ሆኖ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን ሲመሰክር ያገኘኸውን ሰው በጀነት አበስረው” (ሙስሊም 156)፡፡
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) በድጋሚ ባስተላለፈው ሐዲሥ ላይ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- “ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩና እኔም የሱ መልክተኛ መሆኔን እመሰክራለሁ፡፡ በነዚህ ቃላቶች ያልተጠራጠረ ሆኖ አንድ ባሪያ አላህን አይገናኝም ጀነት የገባ ቢሆን እንጂ” (ሙስሊም 147)፡፡
ዒትባን ኢብኑ-ማሊክ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ(ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “የአላህ ፊት(ለማየት) ፈልጎ ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ ባለ ሰው ላይ አላህ እሳትን እርም አድርጎባታል” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
ለ. የነቢዩን ሸፋዐህ ያስገኛል፡-
ነጌ በጭንቁ ቀን ጸሀይ በአናትችን ትይዩ ስንዝር በምትቀርብበት ወቅት፣ እያንዳንዱ ሰው እንደ ወንጀሉ መጠን የገዛ ላቡ ከእግሩ እስከ አፍንጫው እንደ በርሜል ውሃ በሚያጠምቀው ጊዜ፣ ሁሉም ወዴት ልሽሽ እያለ ነፍሴ ነፍሴ ብሎ በሚጮህበት ወቅት፣ ሁሉም የጌታችንን ቁጣ በመፍራት ወደ አላህ የሚያስታርቀን አማላጅ በጠፋ ጊዜ ፣ ኡመቴ! ኡመቴ! በማለት ነቢያችን (ዐለይሂ ሶላቱ ወስ-ሰላም) ለዚች ቀን እኔ አለሁ! ይላሉ፡፡ ታዲያ እኛም በሳቸው ሸፋዐህ አላህ ተጠቃሚ እንዲያደርገን በ ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ እምነት ጥላ ስር በኢኽላስ መኖር ይጠበቅብናል፡-
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- “የአላህ መልክተኛን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከሰዎች ሁሉ በርሶ ሸፋዐህ እድለኛው ማነው? ብዬ ጠየቅኋቸው፡፡ እሳቸውም፡- …‹‹በኔ ምልጃ ከሰዎች ሁሉ እድለኛ የሚሆነው ከልቡ በኢኽላስ ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ ያለ ሰው ነው›› በማለት መለሱልኝ” (ቡኻሪይ 6570)፡፡
ሐ. ደሙና ንብረቱ ዋስትና ያገኛል፡-
አህሉል ኪታቦች (አይሁድና ክርስቲያን) እንዲሁም መጁሳዎች (ዞረስቲያንስ) በሚኖሩበት ሀገር ለኢስላማዊው መንግስት ግብርን ከፍለው ሃይማኖታቸው፣ ደማቸውና ንብረታቸው ተጠብቆ የመኖር መብት አላቸው፡፡ ከዛ ውጭ ያሉት ሙሽሪኮች (በተለይ ዲኑን የሚዋጉ) ግን ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ የምትለውን የምስክርነት ቃል እስኪሰጡ ድረስ የአላህ ነቢይ እንዲጋደሏቸው ታዘዋል፡፡ “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” የሚለውን የምስክርነት ቃል ከሰጡ ግን ደማቸውም ንብረታቸውም የተጠበቀ ይሆናል፡-
ኢብኑ ዑመር (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደተናገረው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ሰዎችን (ሙሽሪኮችን) ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩንና እኔም የሱ መልክተኛ መሆኔን እስኪመሰክሩ፣ ሶላትንም በደንቡ እስኪሰግዱ፣ ዘካንም ባግባቡ እስኪሰጡ ድረስ እንድጋደላቸው ታዝዣለሁ፡፡ ይህንን ከሰሩ ግን ኢስላም በሚፈልገው ሐቅ ካልሆነ በቀር ደማቸውም ሆነ ንብረታቸው የተጠበቀ ይሆናል፡፡ (ልባቸውን) መመርመሩ በአላህ ላይ ነው” (ቡኻሪይ 392)፡፡
በሌላም ሐዲሥ ላይ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ ብሎ ከአላህ ውጪ በሚመለኩ ነገራት የካደ ሰው ደሙን ማፍሰስም ሆነ ንብረቱን መውረስ አይበቃም፡፡ ምርመራውም አላህ ዘንድ ብቻ ነው” (ሙስሊም 139)፡፡
መ. ለደከመ ኢማን ማደሻ ነች፡-
ኢማን በአማኞች ልቦና ውስጥ አንዴ ከገባ፡ ተረጋግቶ ሳይጨምር ሳይቀንስ ባለበት የሚቀጥል ነገር አይደለም፡፡ በስነ ምግባርና በመልካም ተግባራት እያደገና እየጨመረ፣ በኃጢአትና በክፉ ተግባራት እየቀነሰና እየተዳከመ የሚቀያየር ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ኢማናችንን ማደስና ማጠናከር ከፈለግን ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ ማለትን እናብዛ፡-
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ባስተላለፈው ሐዲሥ ላይ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- “ኢማናችሁን አድሱ! ሶሐቦቹም፡- ‹‹እንዴት ነው ኢማናችንን የምናድሰው?›› ሲሉ፡ እሳቸውም፡- ‹‹ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ ማለትን አብዙ›› አሉ” (አሕመድ 8944፣ ሐኪም አል-ሙስተድረክ 7657)፡፡
ሠ. ትልቁ የኢማን ክፍል ነው፡-
ኢማን ከሰባ በላይ ቅርንጫፎች አሉት፡፡ ከነዚህ ሁሉ በላጩ ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ የሚለው ነው፡-
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- “ኢማን ሰባ ከምናምን ክፍሎች አሉት፡፡ ከሁሉም በላጩ ‹‹ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ›› የሚለው ነው፡፡ ዝቅተኛው ደግሞ የሚያስቸግርን ነገር ከመንገድ ላይ ማንሳት ነው” (ሙስሊም 162፣ ቲርሚዚይ 2614)፡፡