የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” 27 በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
417 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
8. የሺርክ መከሰትና መስፋፋት ምክንያቶች፡-
ሐ. ብልሹ ዑለማኦች መኖር፡-
ዑለማእ (የሃይማኖት ሊቃውንት) የነቢያት ወራሽ ናቸው (አቡ ዳዉድ፣ ኢብኑ ማጀህ)፡፡ ከአማኞች መካከልም አላህን በእጅጉ ፈሪዎች ናቸው (ፋጢር 28)፡፡ አላህ ዘንድም በክብርና በደረጃ የላቁ ናቸው (አል-ሙጃዲላህ 11)፡፡ ይህ ሁሉ የትክክለኛ ሊቃውንት (ለሐቅ የቆሙት) ባሕሪ ነው፡፡
በዛው ጎን ደግሞ እውቀቱ ኖሯቸው፡ ነገር ግን ለሆዳቸው ያደሩ፡ ምድራዊ ጥቅምን በማስቀደም አኼራን የረሱ፡ እንደ በግ የሚነዳ ተከታይ ለማፍራትና ለማብዛት እንዲሁም ስምና ዝናን ለማግኘት ሲሉ ብቻ፡ ሐቅን ከመናገርና መጥፎን ከማስጠንቀቅ ምላሳቸውን የለጎሙ፡ የህዝብን ተቃውሞ ላለመስማት ከነጥመቱ እያዩ ለስራው እውቅና በመስጠት በዝምታ የሚያልፉ፡ የነቢያት ውርስ ከሆነው ‹‹ሸሪዐዊ ዕውቀት›› ድርሻቸውን የያዙም አሉ፡፡
የነዚህ አይነቱ መጥፎ ሊቃውንት በየዘመናቱና በየስፍራው መነሳት ለሺርክና ቢድዓ መስፋፋት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም የሐቅ ባለቤቶች ህዝቦቻቸውን ከዚህ አይነት የሺርክ ተግባር ሲያስጠነቅቁ፡ የነዚህ ሊቃውንት ዝም ማለት እና ብሎም አስጠንቃቂዎችን የመቃወም ስራ ለህዝቡ፡- ባላችሁበት ጥመት በጽናት ተጓዙ! የሚል መልእክት አለው፡፡ እነዚህ ሊቃውንት የአላህን ውዴታ ከመሻት ይልቅ የመሪዎቻቸው የባለስልጣናቱን ሙገሳና የሚሰጣቸውን ፍርፋሪ፡ እንዲሁም የህዝብን አድናቆትና የሚቸራቸውን ዝና የመረጡ ናቸው፡፡ ከሺህ አመታት በፊት ከእንዲህ አይነቶቹ ሊቃውንት እንድንጠነቀቅ እና እንድንርቅ ነቢያችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ በማለት ስጋታቸውን ገልጸውልናል፡-
ሠውባን (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “እኔ በኡመቶቼ ላይ የምፈራው አጥማሚ መሪዎችን ነው” (አሕመድ፣ አቡ ዳዉድ፣ ቲርሚዚይ፣ ዳሪሚይ)፡፡
ዑመር ኢብኑል ኸጣብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- “ኢስላምን ሶስት ነገራት ያፈርሱታል፡- የዐሊም መንሸራተት (መጥመም)፣ የሙናፊቅ በቁርኣን መከራከር እና የአጥማሚ መሪዎች መነሳት” (ዳሪሚይ 220)፡፡
ይህ በመሆኑም ዐሊሞችና ዳዒዎች ሰዎችን ወደ አላህ መንገድ መጣራት፡ በመልካም ማዘዝና ከመጥፎ መከልከል ይገባቸዋል ማለት ነው፡-
” ﻭَﻟْﺘَﻜُﻦْ ﻣِﻨْﻜُﻢْ ﺃُﻣَّﺔٌ ﻳَﺪْﻋُﻮﻥَ ﺇِﻟَﻰ ﺍﻟْﺨَﻴْﺮِ ﻭَﻳَﺄْﻣُﺮُﻭﻥَ ﺑِﺎﻟْﻤَﻌْﺮُﻭﻑِ ﻭَﻳَﻨْﻬَﻮْﻥَ ﻋَﻦِ ﺍﻟْﻤُﻨْﻜَﺮِ ﻭَﺃُﻭﻟَﺌِﻚَ ﻫُﻢُ ﺍﻟْﻤُﻔْﻠِﺤُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺁﻝ ﻋﻤﺮﺍﻥ 104
“ከናንተም ወደ በጐ ነገር የሚጠሩ፣ በመልካም ሥራም የሚያዙ፣ ከክፉ ነገርም የሚከለክሉ፣ ህዝቦች ይኑሩ። እነዚያም እነሱ የሚድኑ ናቸዉ።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 104)፡፡
” ﻛُﻨْﺘُﻢْ ﺧَﻴْﺮَ ﺃُﻣَّﺔٍ ﺃُﺧْﺮِﺟَﺖْ ﻟِﻠﻨَّﺎﺱِ ﺗَﺄْﻣُﺮُﻭﻥَ ﺑِﺎﻟْﻤَﻌْﺮُﻭﻑِ ﻭَﺗَﻨْﻬَﻮْﻥَ ﻋَﻦِ ﺍﻟْﻤُﻨْﻜَﺮِ ﻭَﺗُﺆْﻣِﻨُﻮﻥَ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ …” ﺳﻮﺭﺓ ﺁﻝ ﻋﻤﺮﺍﻥ 110
“ለሰዎች ከተገለጸች ሕዝብ ሁሉ በላጭ ሆናችሁ፤ በጽድቅ ነገር ታዛላችሁ ከመጥፎም ነገር ትከለክላላችሁ በአላህም (አንድነት) ታምናላችሁ…” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 110)፡፡
” ﻭَﺍﻟْﻤُﺆْﻣِﻨُﻮﻥَ ﻭَﺍﻟْﻤُﺆْﻣِﻨَﺎﺕُ ﺑَﻌْﻀُﻬُﻢْ ﺃَﻭْﻟِﻴَﺎﺀُ ﺑَﻌْﺾٍ ﻳَﺄْﻣُﺮُﻭﻥَ ﺑِﺎﻟْﻤَﻌْﺮُﻭﻑِ ﻭَﻳَﻨْﻬَﻮْﻥَ ﻋَﻦِ ﺍﻟْﻤُﻨْﻜَﺮِ ﻭَﻳُﻘِﻴﻤُﻮﻥَ ﺍﻟﺼَّﻠَﺎﺓَ ﻭَﻳُﺆْﺗُﻮﻥَ ﺍﻟﺰَّﻛَﺎﺓَ ﻭَﻳُﻄِﻴﻌُﻮﻥَ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻭَﺭَﺳُﻮﻟَﻪُ ﺃُﻭﻟَﺌِﻚَ ﺳَﻴَﺮْﺣَﻤُﻬُﻢُ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﺇِﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻋَﺰِﻳﺰٌ ﺣَﻜِﻴﻢٌ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺘﻮﺑﺔ 71
“ምእምናንና ምእምናትም ከፊሎቻቸዉ ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው በደግ ነገር ያዛሉ፤ ከክፉም ይከለክላሉ፤ ሶላትንም ይሰግዳሉ፤ ዘካንም ይሰጣሉ፤ አላህንና መልክተኛዉንም ይታዘዛሉ፤ እነዚያን አላህ በእርግጥ ያዝንላቸዋል፤ አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና።” (ሱረቱ-ተውባህ 71)፡፡
” ﻳَﺎ ﺑُﻨَﻲَّ ﺃَﻗِﻢِ ﺍﻟﺼَّﻠَﺎﺓَ ﻭَﺃْﻣُﺮْ ﺑِﺎﻟْﻤَﻌْﺮُﻭﻑِ ﻭَﺍﻧْﻪَ ﻋَﻦِ ﺍﻟْﻤُﻨْﻜَﺮِ ﻭَﺍﺻْﺒِﺮْ ﻋَﻠَﻰ ﻣَﺎ ﺃَﺻَﺎﺑَﻚَ ﺇِﻥَّ ﺫَﻟِﻚَ ﻣِﻦْ ﻋَﺰْﻡِ ﺍﻟْﺄُﻣُﻮﺭِ ” ﺳﻮﺭﺓ ﻟﻘﻤﺎﻥ 17
“ልጄ ሆይ! ሰላትን አስተካክለህ ስገድ፤ በበጎ ነገርም እዘዝ፤ ከሚጠላም ሁሉ ከልክል፤ በሚያገኝህም መከራ ላይ ታገሥ፤ ይህ በምር ከሚይያዙ ነገሮች ነው።” (ሱረቱ ሉቅማን 17)፡፡
አምላካችን አላህ ሆይ! ዐሊሞቻችንና ዳዒዎቻችን የአንተን ፊት ብቻ ፈልገው የሚሰሩ፡ ለሐቅ የቆሙ ሀሰትን የሚያረክሱና እውነትን የሚያነግሱ አድርጋቸው፡፡ እኛንም ለሐቅ ተገዢዎች ለባጢል ጠዪዎች አድርገን አሚን፡፡