የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” 26 በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
399 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
8. የሺርክ መከሰትና መስፋፋት ምክንያቶች፡-
ለ. በሷሊሖች ላይ ድንበር ማለፍ፡-
ባለፈው ለሺርክና ለኩፍር መስፋፋት ምክንያት ከሆኑት ውስጥ አንዱና ዋነኛው ‹‹የዕውቀት ማነስ››ን አንስተን ተነጋግረን ነበር፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ በሷሊሖች (ደጋግ የአላህ ባሮች) ላይ ወሰን ማለፍ ነው፡፡ አላህ ከፍጥረታቱ መሐል የሰውን ልጅ አክብሮታል (አል-ኢስራእ 70)፡፡ ከሰዎች ውስጥ ደግሞ ‹‹ሷሊሖች›› የተሻለ ደረጃ አላቸው (አል-ሙጃዲላህ 11)፡፡ ከሷሊሖች ደግሞ ‹‹ነቢያት›› የላቁና የበለጡ ናቸው፡፡ ከነቢያት መካከል ‹‹ሩሱሎችን›› በደረጃ ከፍ አደረጋቸው፡፡
ከሩሱሎቹ ውስጥ አምስቱን ‹‹ኡሉል-ዐዝም›› (የቆራጥ ባልተቤቶችን) መረጠ፡፡ ከአምስቱ ውስጥ ከሁሉም የበላይ የሆኑትን ‹‹ነቢያችንን›› (ዐለይሂ ሶላቱ ወስ-ሰላም) በደረጃና በማእረግ ከፍ አደረገ፡፡
ታዲያ እኛም ይህንኑ አላህ የሰጣቸውን ክብርና ደረጃ ከፍም ዝቅም ሳናደርግ ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ ልንሰጣቸው ሲገባ፡ አንዱን ከመጠን በላይ በመውደድና ከደረጃው በላይ በመስቀል፡ የተለየ ቦታ ከሰጠነው፡ ይህ ተግባር ቀስ በቀስ ያንን ሰው ወደ ማምለክ ይሸጋገራል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በሰዎች ውስጥ የተከሰተውን ሺርክን ራሱ ስንመለከተው፡ የዚሁ የድንበር ማለፍና የዕውቀት መጥፋት ውጤት ነው፡፡ በነቢዩላህ ኑሕ (ዐለይሂ ሰላም) ዘመን አምስት ሷሊሖች ነበሩ፡፡ በሞቱ ጊዜ፡ ሰይጣን በህይወት ወዳሉት በመምጣት በነዚህ ሰዎች መቃብር ላይ ሀውልትን በስማቸው እንዲገነቡና በስፍራውም እንዲቀመጡ መጎትጎት ጀመረ፡፡ እነሱም ሟቾቹን ሲያስታውሱ መልካምነታቸው ትዝ እያላቸው ለዒባዳ እንዲነሳሱ እንደሚረዳቸው ሹክ አላቸው፡፡ ሀውልቱም ተገነባ፡፡ ሰዎቹ ግን የሞቱትን ሰዎች መማጸን አልጀመሩም፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎችም ተራ ይደርሳቸውና ሲሞቱ፡ ሰይጣን ያንን የረጅም ጊዜ እቅዱን መተግበር ጀመረ፡፡ አሁን በህይወት ያሉ ሰዎች አባቶቻቸው ሀውልቱን ለምን እንደገነቡት ዕውቀቱ አልነበራቸውም፡፡ ሰይጣንም፡- አባቶቻችሁ በነዚህ ሙታኖች በመታገዝ ወደ አላህ ይቃረቡባቸው ነበር፡፡ እናንተም ይህንን ፈለግ ተከተሉ! ብሎ የጥመት ትምሕርቱን አሰራጨው፡፡ ሰዎቹም ከዕውቀት ማነስ የተነሳ የሞቱትን ሰዎች መማጸንና ወደ አላህ እንዲያቃርቧቸው እነሱን መገዛት ጀመሩ፡፡ ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-
” ﻭَﻗَﺎﻟُﻮﺍ ﻟَﺎ ﺗَﺬَﺭُﻥَّ ﺁﻟِﻬَﺘَﻜُﻢْ ﻭَﻟَﺎ ﺗَﺬَﺭُﻥَّ ﻭَﺩًّﺍ ﻭَﻟَﺎ ﺳُﻮَﺍﻋًﺎ ﻭَﻟَﺎ ﻳَﻐُﻮﺙَ ﻭَﻳَﻌُﻮﻕَ ﻭَﻧَﺴْﺮًﺍ ” ﺳﻮﺭﺓ ﻧﻮﺡ 23
“አሉም ፦ አምኮቻችሁን አትተዉ፤ ወድንም፤ ሱዋዕንም፣ የጉሥንም፣ የ ዑቅንም፣ ነስርንም አትተዉ።” (ሱረቱ ኑሕ 23)፡፡
ክርስቲያኖችንም ብንመለከታቸው፡ የመርየምን ልጅ ዒሳን ወደ ማምለክ የተሸጋገሩት ከዚሁ በውዴታ ድንበር ከማለፍ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለሆነም ነቢያችን (ዐለይሂ ሶላቱ ወስ-ሰላም) በሳቸው ላይ በፍቅርና በውዴታ ወሰን እንዳናልፍባቸው እንዲህ በማለት ይመክሩናል፡-
ዑመር ኢብኑል ኸጣብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) በሚንበር ላይ ሆኖ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ሲሉ ሰማሁ አለ፡- “ክርስቲያኖች የመርየምን ልጅ (ጌታና የጌታ ልጅ በማለት) እንደጠሩት እንዳትጠሩኝ፡፡ እኔ ባሪያው ነኝና፡ የአላህ ባሪያና መልክተኛው በሉኝ” (ቡኻሪይ 3445)፡፡
በዛው መልኩ አላህ በየዘመናቱና በየስፍራው መልካም የሆኑ ሷሊሕ ባሮች ይኖሩታል፡፡ እኛ እነዚህን መልካም የአላህ ባሮች ልናከብራቸውና ልንወዳቸው ይገባል፡፡ ውዴታችን ወሰን አልፎ እነሱን ወደ ማምለክ፡ በመቃብራቸው ላይ ቆሞ መማጸንና ለነሱ መሳል፡ ከቤት ሁነን ያዩናል ይሰሙናል የሚል አመለካከት ወደ መያዝ ከተቀየረ ግን፡ ፍቅርና ውዴታ መሆኑ ይቀርና አምልኮ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሷሊሖች ከሞቱ በኋላ ከዚህ ዓለም ጋር ያላቸው ግኑኝነት ተቋርጣል፡፡ ተመልሰው ወደ ዱንያ መምጣት አይችሉም፡፡ እኝ እነሱ ወደ ገቡበት መቃብር እንሄዳለን እንጂ፡፡ ከመቃብር በታች ሆነው፡ ከመቃብር በላይ በምድር ጀርባ ላይ ስለሚፈጸመው ነገር ምንም የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ እኛ ቀብራቸው ላይ የምንሄደው ለምንድነው? ተናግረን ሊሰሙን አይችሉም፡፡ ጠይቀን ሊሰጡንም አቅሙ የላቸውም፡፡ ያልሞተና የማይሞት ሕያው አምላክ አላህ እያለ እንዴት ከሞቱ ሰዎች እርዳታ ይፈለጋል? ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡-
…” ﺫَﻟِﻜُﻢُ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﺭَﺑُّﻜُﻢْ ﻟَﻪُ ﺍﻟْﻤُﻠْﻚُ ﻭَﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﺗَﺪْﻋُﻮﻥَ ﻣِﻦْ ﺩُﻭﻧِﻪِ ﻣَﺎ ﻳَﻤْﻠِﻜُﻮﻥَ ﻣِﻦْ ﻗِﻄْﻤِﻴﺮٍ * ﺇِﻥْ ﺗَﺪْﻋُﻮﻫُﻢْ ﻟَﺎ ﻳَﺴْﻤَﻌُﻮﺍ ﺩُﻋَﺎﺀَﻛُﻢْ ﻭَﻟَﻮْ ﺳَﻤِﻌُﻮﺍ ﻣَﺎ ﺍﺳْﺘَﺠَﺎﺑُﻮﺍ ﻟَﻜُﻢْ ﻭَﻳَﻮْﻡَ ﺍﻟْﻘِﻴَﺎﻣَﺔِ ﻳَﻜْﻔُﺮُﻭﻥَ ﺑِﺸِﺮْﻛِﻜُﻢْ ﻭَﻟَﺎ ﻳُﻨَﺒِّﺌُﻚَ ﻣِﺜْﻞُ ﺧَﺒِﻴﺮٍ ” ﺳﻮﺭﺓ ﻓﺎﻃﺮ 13-14
“…ይሃችሁ ጌታችሁ አላህ ነው፤ ንግሥናው የርሱ ብቻ ነው፤ እነዚያም ከርሱ ሌላ የምትግገዟቸው የተምር ፍሬ ሺፋን እንኳ አይኖራቸውም። ብትጠሩዋቸው ጥሪያችሁን አይሰሙም፤ ቢሰሙም ኖሮ ለናንተ አይመልሱላችሁም፤ በትንሣኤም ቀን (እነርሱን በአላህ ማጋራታችሁን ይክዳሉ፤ እንደ ውስጠ አዋቂው ማንም አይነግርህም።” (ሱረቱ ፋጢር 13-14)፡፡
” ﻭَﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﻳَﺪْﻋُﻮﻥَ ﻣِﻦْ ﺩُﻭﻥِ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻟَﺎ ﻳَﺨْﻠُﻘُﻮﻥَ ﺷَﻴْﺌًﺎ ﻭَﻫُﻢْ ﻳُﺨْﻠَﻘُﻮﻥَ * ﺃَﻣْﻮَﺍﺕٌ ﻏَﻴْﺮُ ﺃَﺣْﻴَﺎﺀٍ ﻭَﻣَﺎ ﻳَﺸْﻌُﺮُﻭﻥَ ﺃَﻳَّﺎﻥَ ﻳُﺒْﻌَﺜُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻨﺤﻞ 20-21
“እነዚያም ከአላህ ሌላ የምትግገዟቸው ምንንም አይፈጥሩም፤ እነርሱም ይፈጠራሉ፡፡ ሕያው ያልሆኑ ሙታን ናቸው፤ መቼ እንደሚቀሰቀሱም አያውቁም።” (ሱረቱ-ነሕል 20-21)፡፡
ከኛ የሚጠበቀው እነዚህን የሞቱትን ሷሊሖች መማጸን ሳይሆን፡ መልካም አርአያነታቸውን በመከተል ለነሱ ዱዓእ ማድረግ ነው፡፡ አላህ በጥሩ እንዲቀበላቸው፡ ቀብራቸውንም እንዲያሰፋላቸው፡ ጥፋታቸውንም ይቅር እንዲላቸው ዱዓእ ማድረግ ነው፡፡
” ﻭَﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﺟَﺎﺀُﻭﺍ ﻣِﻦْ ﺑَﻌْﺪِﻫِﻢْ ﻳَﻘُﻮﻟُﻮﻥَ ﺭَﺑَّﻨَﺎ ﺍﻏْﻔِﺮْ ﻟَﻨَﺎ ﻭَﻟِﺈِﺧْﻮَﺍﻧِﻦَﺍ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﺳَﺒَﻘُﻮﻧَﺎ ﺑِﺎﻟْﺈِﻳﻤَﺎﻥِ ﻭَﻟَﺎ ﺗَﺠْﻌَﻞْ ﻓِﻲ ﻗُﻠُﻮﺑِﻨَﺎ ﻏِﻠًّﺎ ﻟِﻠَّﺬِﻳﻦَ ﺁﻣَﻨُﻮﺍ ﺭَﺑَّﻨَﺎ ﺇِﻧَّﻚَ ﺭَﺀُﻭﻑٌ ﺭَﺣِﻴﻢٌ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺤﺸﺮ 10
“እነዚያም ከበኋላቸው የመጡት ጌታችን ሆይ ለኛም ለነዚያም በ እምነት ለቀደሙን ወንድሞቻችን ምሕረት አድርግ። በልቦቻችንም ውስጥ ለነዚያ ለአመኑት (ሰዎች) ጥላቻን አታድርግ። ጌታችን ሆይ! አንተ ርኅሩኅ አዛኝ ነህና ይላሉ።” (ሱረቱል ሐሽር 10)፡፡