የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” 25 በአቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
420 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
8. የሺርክ መከሰትና መስፋፋት ምክንያቶች፡-
በቁጥር ሰባት ስር ለተከታታይ ጊዜያት የ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ››ን እምነት አፍራሽ የሆኑ ተግባራትን (ሺርክ፣ ኩፍር፣ ኒፋቅ) ስንመለከት ቆይተናል፡፡ ዛሬ ደግሞ በሰዎች መሐል የ ‹‹ሺርክ›› እና የ ‹‹ኩፍር›› ስራዎች እንዲስፋፉ ምክንያት ከሆኑ ነገሮች የተወሰኑትን እንመለከታለን ኢንሻአላህ፡-
ሀ. የዕውቀት ማነስ፡-
አንዱና ዋነኛው ምክንያት ሸሪዓዊ ዕውቀት አለመኖሩ ነው፡፡ ሰዎች ስለ ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› መልእክት እና ትርጓሜ ትክክለኛ ፍቺ ባለማግኘታቸውና ባለመማራቸው፡ የሺርክ ተግባር ላይ ሊወድቁ ችለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የሚሰሯቸው የሺርክ ተግባራት ከ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› ጋር እንደሚጋጭባቸው አያውቁም፡፡ እነሱ ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ››ን የሚረዱት፡- የአላህን ፈጣሪነት የሚገልጽ መሆኑ ላይ ብቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዒባዳን ለፍጡር አሳልፈው ሲሰጡ ከዚህ ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› ከሚለው እምነታቸው ጋር እንደተጋጨ አይረዱም፡፡
አላህ ፈጣሪ መሆኑን ማመን አንድ ነገር ነው፡፡ ይህ ግን ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ አላህ ብቻውን ፈጣሪ ከሆነ ለምንስ ብቻውን አይመለክም? የሚለውንም ማሰብ አለብን፡፡ አንድ ሰው ሶላት ለመስገድ ጡሀራ እንዴት ማድረግ እንዳለበት ማወቁ ብቻ ሶላቱን አያስተካክለውም፡፡ በዛው ተቃራኒ ጡሀራን የሚያፈርሱ ነገሮችን ማወቅ አለበት፡፡ ጡሀራን የሚያፈርሱ ነገሮችን እየፈጸመ፡ እሱ ግን ባለማወቁ ስራውን ሊያበላሽ ይችላል፡፡ ከሺርክ አደጋ ለመጠበቅም የ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ››ን ትክክለኛ ፍቺና አፍራሽ ነገራትንም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በፊትም እንዳየነው ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› በሁለት መሰረታዊ ነገሮች ላይ ነው የሚመሰረተው፡፡
1. ማንኛውንም የአምልኮ አይነት (በልብ፣ በምላስ፣ በሰውነት የሚፈጸሙትን) በጠቅላላ ለአንድ አላህ ብቻ ማድረግ ሲሆን፡-
2. ከአላህ ውጪ የሚመለኩ አካላት በጠቅላላ (መላእክት፣ ነቢያት፣ ጻድቃን፣ ሰማእታት፣ ሙታን፣ ሰይጣናት፣ ግኡዛን ነገራት) ሁሉ አምልኮ የማይገባቸው መሆናቸውን በማመን፡ እነሱን ከማምለክ እራስን ማራቅና በነሱ አምልኮ መካድ፣ እንዲሁም ከአላህ ውጪ ያለን አካል የሚያመልኩ ሰዎች ሙሽሪኮች መሆናቸውን አምነን እራሳችንን ከነሱ ማግለልና አለመተባበር ማለት ነው፡፡ በጥቅሉ ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› በአላህ ማመንና ከአላህ ውጭ ባለ ነገር ሁሉ መካድ ማለት ነው፡፡ ከአላህ ውጭ ላለ ነገር የሚቀርብ አምልኮ ሁሉ የጣኦት አምልኮ ተብሎ ይጠራል፡-
” ﻟَﺎ ﺇِﻛْﺮَﺍﻩَ ﻓِﻲ ﺍﻟﺪِّﻳﻦِ ﻗَﺪْ ﺗَﺒَﻴَّﻦَ ﺍﻟﺮُّﺷْﺪُ ﻣِﻦَ ﺍﻟْﻐَﻲِّ ﻓَﻤَﻦْ ﻳَﻜْﻔُﺮْ ﺑِﺎﻟﻄَّﺎﻏُﻮﺕِ ﻭَﻳُﺆْﻣِﻦْ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻓَﻘَﺪِ ﺍﺳْﺘَﻤْﺴَﻚَ ﺑِﺎﻟْﻌُﺮْﻭَﺓِ ﺍﻟْﻮُﺛْﻘَﻰ ﻟَﺎ ﺍﻧْﻔِﺼَﺎﻡَ ﻟَﻬَﺎ ﻭَﺍﻟﻠَّﻪُ ﺳَﻤِﻴﻊٌ ﻋَﻠِﻴﻢٌ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺒﻘﺮﺓ 256
“በሃይማኖት ማስገደድ የለም፡፡ ቅኑ መንገድ ከጠማማው በእርግጥ ተገለጠ፡፡ በጣዖትም የሚክድና በአላህ የሚያምን ሰው ለርሷ መበጠስ የሌላትን ጠንካራ ዘለበት በእርግጥ ጨበጠ፡፡ አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 256)፡፡
በዚህ የቁርኣን አንቀጽ ስር፡ ትክክለኛውን የ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› ጠንካራ ዘለበት የጨበጠው፡ ሁለት ነገሮችን ያሟላ ሰው ብቻ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ እነሱም፡-
– ‹‹በጣኦት የሚክድ›› ይህ ማለት ከአላህ ውጭ የሚመለኩ ነገራት በጠቅላላ የጣኦት አምልኮ መሆኑን በማመን፡ ራስን ከጣኦት አምልኮ ማራቅና በጣኦትም መካድ ሲሆን፡
– ‹‹በአላህም የሚያምን›› ሲል ደግም፡ አምልኮን ለአንድ አላህ ብቻ የሚያደርግና እሱንም ብቻ የሚገዛ ማለት ነው፡፡
” ﻭَﺇِﻟَﻰ ﻋَﺎﺩٍ ﺃَﺧَﺎﻫُﻢْ ﻫُﻮﺩًﺍ ﻗَﺎﻝَ ﻳَﺎ ﻗَﻮْﻡِ ﺍﻋْﺒُﺪُﻭﺍ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻣَﺎ ﻟَﻜُﻢْ ﻣِﻦْ ﺇِﻟَﻪٍ ﻏَﻴْﺮُﻩُ ﺃَﻓَﻠَﺎ ﺗَﺘَّﻘُﻮﻥَ … ﻕَﺍﻟُﻮﺍ ﺃَﺟِﺌْﺘَﻨَﺎ ﻟِﻨَﻌْﺒُﺪَ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻭَﺣْﺪَﻩُ ﻭَﻧَﺬَﺭَ ﻣَﺎ ﻛَﺎﻥَ ﻳَﻌْﺒُﺪُ ﺁﺑَﺎﺅُﻧَﺎ ﻓَﺄْﺗِﻨَﺎ ﺑِﻤَﺎ ﺗَﻌِﺪُﻧَﺎ ﺇِﻥْ ﻛُﻨْﺖَ ﻣِﻦَ ﺍﻟﺼَّﺎﺩِﻗِﻴﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻷﻋﺮﺍﻑ 65-70
“ወደ ዓድም ወንድማቸውን ሁድን ላክን፤፦ ወገኖቼ ሆይ! አላህን ተገዙ፤ ከርሱ ሌላ ምንም አምላክ የላችሁም፤ (የአላህን ቅጣት) አትፈሩምን? አላቸ…አላህን አንድ ብቻውን እንድንገዛ አባቶቻችንም ይግገዙት የነበረውን (አማልክት) እንድንተው መጣህብን? ከውነተኞች ከሆንክ የምታስፈራራብንን (ቅጣት) አምጣብን አሉ።” (ሱረቱል አዕራፍ 65.70)፡፡
ሁድ (ዐለይሂ ሰላም) ወገኖቹን ወደ ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› ጥሪ አደረገላቸው፡፡ እነሱም ከሱ ጥሪ የተረዱት ሁለት ነገር ነበር፡፡ የመጀመሪያው፡- ‹‹አላህን አንድ ብቻውን እንድንገዛ›› የሚለው ቃላቸው፡ አምልኮን ለአላህ ብቻ አሳልፎ መስጠት እንዳለባቸው ሲሆን፡- ሁለተኛው ደግሞ፡- ‹‹አባቶቻችንም ይግገዙት የነበረውን (አማልክት) እንድንተው መጣህብን?›› የሚለው ደግሞ፡ ከአላህ ውጪ የሚመለኩ የሃሰት አማልክቶችን መተውና መራቅ እንዳለባቸው መሆኑን ነው፡፡
” ﻭَﻟَﻘَﺪْ ﺑَﻌَﺜْﻨَﺎ ﻓِﻲ ﻛُﻞِّ ﺃُﻣَّﺔٍ ﺭَﺳُﻮﻟًﺎ ﺃَﻥِ ﺍﻋْﺒُﺪُﻭﺍ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻭَﺍﺟْﺘَﻨِﺒُﻮﺍ ﺍﻟﻄَّﺎﻏُﻮﺕَ ” … ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻨﺤﻞ 36
“በየሕዝቡም ሁሉ አውስጥ አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ፤ በማለት መልክተኛን በእርግጥ ልከናል…” (ሱረቱ-ነሕል 36)፡፡
በዚህም አንቀጽ መሰረት አላህ ነቢያትን ወደ ህዝቦቻቸው ሲልካቸው፡ ሁለት ነገርን እንዲያስተምሩ ነው፡፡ እሱም፡- ሰዎች አላህን በብቸኝነት እንዲገዙት ጥሪ ማቅረብና፡ ከአላህ ውጪ የሚመለኩ ነገራት በጠቅላላ ጣኦት ስለሆኑ ከነሱ አምልኮ እራሳቸውን እንዲያርቁ ነው፡፡ በጥቅሉ ለሺርክ መስፋፋት አንዱና ዋነኛው ምክንያት የዒልም ማነስ በመሆኑ፡ ሁላችንም ትኩረት ሰጥተን ልንማረው ይገባል፡፡ ከ ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› መስፈርቶች ውስጥ አንዱ ‹‹ዕውቀት›› መሆኑንም ልብ ልንል ይገባል፡፡ አላህ ስለ ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› ትክክለኛ ዕውቀትና እምነት፡ እንዲሁም ተግባር ተውፊቁን ይለግሰን፡፡