የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” 23 በኡስታዝ አቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
392 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
7. አፍራሽ ተግባራት፡-
3. ኒፋቅ (አስመሳይነት)፡-
ሌላኛው የ”ላ ኢላሀ ኢልለሏህ”ን እምነት ከሚያፈርሱት ውስጥ አንዱ ‹‹ኒፋቅ›› ነው፡፡ ሙናፊቅ ማለት ቀጥታ ፍቺው፡- አስመሳይ ማለት ነው፡፡ ያም ማለት፡- ከውጭ ኢስላማዊ ገጽታን እያሳዩ በልብ ክህደትን አምቆ መያዝ ማለት ነው፡፡ ውጪያዊ ተግባሩ የሙስሊሞች አይነት ሆኖ፡ ልቡ ግን ከከሀዲያን ጋር ያደረ ማለት ነው፡፡ ሙናፊቅ፡ ከሙሽሪክና ከካፊር የበለጠ የሙስሊሞች ጠላትና አደጋ ነው፡፡ ምክንያቱም፡- ካፊሮችና ሙሽሪኮች ጠላትነታቸው በይፋ የሚታይ በመሆኑ ለመጠንቀቅ ይረዳል፡፡ ሙናፊቅ ግን የልቡን በልቡ ይዞ በውጪያዊ ማንነቱ ካንተ ጋር ተመሳስሎ የሚውል በመሆኑ መለየት አይቻልም፡፡ ወንድም መስሎ በመቅረብ ሚስጥርን በማውጣት ለጠላት አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ቅዱስ ቁርኣን በሱረቱል በቀራህ መግቢያ ላይ ከ2-20 ባለው 19 አንቀጽ ውስጥ፡ ስለ ሙእሚኖች 4፣ ስለ ካፊሮች 2፣ ስለ ሙናፊቆች ደግሞ 13 አንቀጾችን አውርዷል፡፡ ይህም የሚያሳየው፡- ሙናፊቆች ለኢስላም ምን ያህል ጠንቅ እንደሆኑ ነው፡፡
ሀ. አይነቶቹ፡-
ኒፋቅም እንደ ወንድሞቹ ኩፍርና ሺርክ በሁለት ይከፈላል፡፡ እነሱም፡-
– ኒፋቁን አክበር (ትልቁ ኒፋቅ)፡- ይህ ማለት፡ ከላይ አማኝ መስሎ በልብ የሚፈጸም የክህደት ስራ፡ ባለቤቱን ከኢስላም አጥር የሚያስወጣ፡ ስራን በጠቅላላ የሚያበላሽ፡ ያለ ተውበት ከሞተም ለዘላለም እሳት የሚዳርግ ማለት ነው፡፡
– ኒፋቁን አስገር (ትንሹ ኒፋቅ)፡- ይህ ማለት፡ ሰውየው በልቡ አማኝ ሆኖ፡ በንግግሩና በተግባሩ የመናፍቃንን ባሕሪ የሚያንጸባርቅ፡ ስራው ከኢስላም ባያስወጣውም አላህ በራሕመቱ ወይም በነቢያችን ሸፋዐህ ካልታረቀው በስተቀር ለቅጣት የሚዳርገው፡ ከተቀጣም ለዘላለም በእሳት የማይዘወትርበት የሆነ ተግባር ማለት ነው፡፡
ለ. የመናፍቃን ባሕሪ በቅዱስ ቁርኣን፡-
1. አማኞችን ማታለል፡- አማኝ ሳይሆኑ ያመኑ መስለው በመቅረብ፡ ከሙእሚኖች ጎራ እንደሆኑ ሆኖ ለመታየት የአላህ ባሪያዎችን ለማታለል ይሞክራሉ፡፡ በሐቂቃው ግን እያታለሉ ያሉት ነፍሳቸውን እንጂ አማኞችን አይደለም፡፡
” ﻭَﻣِﻦَ ﺍﻟﻨَّﺎﺱِ ﻣَﻦْ ﻳَﻘُﻮﻝُ ﺁﻣَﻨَّﺎ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻭَﺑِﺎﻟْﻴَﻮْﻡِ ﺍﻟْﺂﺧِﺮِ ﻭَﻣَﺎ ﻫُﻢْ ﺑِﻤُﺆْﻣِﻨِﻴﻦَ * ﻳُﺨَﺎﺩِﻋُﻮﻥَ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻭَﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﺁﻣَﻨُﻮﺍ ﻭَﻣَﺎ ﻳَﺨْﺪَﻋُﻮﻥَ ﺇِﻟَّﺎ ﺃَﻧْﻔُﺴَﻬُﻢْ ﻭَﻣَﺎ ﻳَﺸْﻌُﺮُﻭﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺒﻘﺮﺓ 8-9
“ከሰዎችም «በአላህና በመጨረሻው ቀን አምነናል» የሚሉ አልሉ፤ እነርሱም አማኞች አይደሉም፡፡ አላህንና እነዚያን ያመኑትን (ሰዎች) ያታልላሉ፤ የማያውቁ ሲኾኑ ነፍሶቻቸውን እንጅ ሌላን አያታልሉም፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 8-9)::
” ﺇِﻥَّ ﺍﻟْﻤُﻨَﺎﻓِﻘِﻴﻦَ ﻳُﺨَﺎﺩِﻋُﻮﻥَ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻭَﻫُﻮَ ﺧَﺎﺩِﻋُﻬُﻢْ ﻭَﺇِﺫَﺍ ﻗَﺎﻣُﻮﺍ ﺇِﻟَﻰ ﺍﻟﺼَّﻠَﺎﺓِ ﻗَﺎﻣُﻮﺍ ﻛُﺴَﺎﻟَﻰ ﻳُﺮَﺍﺀُﻭﻥَ ﺍﻟﻨَّﺎﺱَ ﻭَﻟَﺎ ﻳَﺬْﻛُﺮُﻭﻥَ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﺇِﻟَّﺎ ﻗَﻠِﻴﻠًﺎ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻨﺴﺎﺀ 142
“መናፍቃን አላህን ያታልላሉ፤ እርሱም አታላያቸው ነው፤ (ይቀጣቸዋል)፤ ወደ ሶላትም በቆሙ ጊዜ ታካቾች ሰዎችን የሚያሳዩ ሆነው ይቆማሉ፤ አላህንም ጥቂትን እንጂ አያወሱም።” (ሱረቱ-ኒሳእ 142)፡፡
2. ውሸተኝነት፡- መልክተኛው ዘንድ በመምጣት፡- እኛ እኮ አንተ የአላህ መልክተኛ መሆንህን እንመሰክራለን! በማለት በልባቸው የሌለውን ሲያወሩ፡ ጌታችን ውሸታሞች መሆናቸውን መሰከረ፡-
” ﺇِﺫَﺍ ﺟَﺎﺀَﻙَ ﺍﻟْﻤُﻨَﺎﻓِﻘُﻮﻥَ ﻗَﺎﻟُﻮﺍ ﻧَﺸْﻬَﺪُ ﺇِﻧَّﻚَ ﻟَﺮَﺳُﻮﻝُ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻭَﺍﻟﻠَّﻪُ ﻳَﻌْﻠَﻢُ ﺇِﻧَّﻚَ ﻟَﺮَﺳُﻮﻟُﻪُ ﻭَﺍﻟﻠَّﻪُ ﻳَﺸْﻬَﺪُ ﺇِﻥَّ ﺍﻟْﻤُﻨَﺎﻓِﻘِﻴﻦَ ﻟَﻜَﺎﺫِﺑُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻤﻨﺎﻓﻘﻮﻥ 1
“መናፍቃን በመጡህ ጊዜ አንተ የአላህ መልክተኛው መሆንህን በእርግጥ (ምለን) እንመሰክራለን ይላሉ፤ አላህም አንተ በ እርግጥ መል ዕክተኛ መሆንህን ያውቃል፤ አላህም መናፍቃን (ከልብ እንመሰክራለን በማለታቸው) ውሸታሞች መኾናቸውን ይመሰክራል።” (ሱረቱል ሙናፊቁን 1)፡፡
3. በአማኞች ማሾፍ፡- ሙእሚኖች ላይ በመጠቋቆም ማሾፍና መቀለድ ዋና መለያቸው ነው፡፡ የሙስሊሞችንም እምነት እንደ ቂል ይመለከቱታል፡-
” ﻭَﺇِﺫَﺍ ﻗِﻴﻞَ ﻟَﻬُﻢْ ﺁﻣِﻨُﻮﺍ ﻛَﻤَﺎ ﺁﻣَﻦَ ﺍﻟﻨَّﺎﺱُ ﻗَﺎﻟُﻮﺍ ﺃَﻧُﺆْﻣِﻦُ ﻛَﻤَﺎ ﺁﻣَﻦَ ﺍﻟﺴُّﻔَﻬَﺎﺀُ ﺃَﻟَﺎ ﺇِﻧَّﻬُﻢْ ﻫُﻢُ ﺍﻟﺴُّﻔَﻬَﺎﺀُ ﻭَﻟَﻜِﻦْ ﻟَﺎ ﻳَﻌْﻠَﻤُﻮﻥَ * ﻭَﺇِﺫَﺍ ﻟَﻘُﻮﺍ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﺁﻣَﻨُﻮﺍ ﻗَﺎﻟُﻮﺍ ﺁﻣَﻨَّﺎ ﻭَﺇِﺫَﺍ ﺧَﻠَﻮْﺍ ﺇِﻟَﻰ ﺷَﻴَﺎﻃِﻴﻨِﻬِﻢْ ﻗَﺎﻟُﻮﺍ ﺇِﻧَّﺎ ﻣَﻌَﻜُﻢْ ﺇِﻧَّﻤَﺎ ﻧَﺤْﻦُ ﻣُﺴْﺘَﻬْﺰِﺋُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺒﻘﺮﺓ 13-14
“ለነሱም «ሰዎቹ እንዳመኑ እመኑ» በተባሉ ጊዜ «ቂሎቹ እንዳመኑ እናምናለን?» ይላሉ፡፡ አዋጅ ንቁ እነርሱ ቂሎቹ እነርሱው ናቸው፤ ግን አያውቁም፡፡ እነዚያንም ያመኑትን በተገናኙ ጊዜ «አምነናል» ይላሉ፡፡ ወደ ሰይጣኖቻቸውም ባገለሉ ጊዜ «እኛ ከናንተ ጋር ነን፤ እኛ (በነሱ) ተሳላቂዎች ብቻ ነን» ይላሉ፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 13-14)፡፡
4. ከሀዲያንን መወዳጀት፡- እነሱ ዘንድ ከሙስሊሞች ጋር ወዳጅ መሆን በፍጹም አይታሰብም፡፡ የነሱ የልብ ወዳጆች ካፊሮችና ሙሽሪኮች በጠቅላላ የኢስላም ጠላቶች ናቸው፡-
” ﺑَﺸِّﺮِ ﺍﻟْﻤُﻨَﺎﻓِﻘِﻴﻦَ ﺑِﺄَﻥَّ ﻟَﻬُﻢْ ﻋَﺬَﺍﺑًﺎ ﺃَﻟِﻴﻤًﺎ * ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﻳَﺘَّﺨِﺬُﻭﻥَ ﺍﻟْﻜَﺎﻓِﺮِﻳﻦَ ﺃَﻭْﻟِﻴَﺎﺀَ ﻣِﻦْ ﺩُﻭﻥِ ﺍﻟْﻤُﺆْﻣِﻨِﻴﻦَ ﺃَﻳَﺒْﺘَﻐُﻮﻥَ ﻋِﻨْﺪَﻫُﻢُ ﺍﻟْﻌِﺰَّﺓَ ﻓَﺈِﻥَّ ﺍﻟْﻌِﺰَّﺓَ ﻟِﻠَّﻪِ ﺟَﻤِﻴﻌًﺎ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻨﺴﺎﺀ 138-139
“መናፍቃንን፣ ለነርሱ አሳማሚ ቅጣት ያላቸው መሆኑን አብስራቸው። እነዚያ ከምእመናን ሌላ ከሐዲዎችን ወዳጆች አድርገው የሚይዙ፣ እነሱ ዘንድ ልቅናን ይፈልጋሉን? ልቅናም ሁሉ ለአላህ ብቻ ነው።” (ሱረቱ-ኒሳእ 138-139)፡፡
5. ከአላህ ሸሪዓህ መሸሽ፡- በፍጹም በአላህ ህግ መዳኘትን አይፈልጉም፡፡ እሱን የሚፈልጉት ምናልባት ሐቅ ሲኖራቸው ብቻ ነው፡፡ ከዛ በተረፈ የነሱ ምርጫ የጣኦት ህግ ነው፡-
” ﺃَﻟَﻢْ ﺗَﺮَ ﺇِﻟَﻰ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﻳَﺰْﻋُﻤُﻮﻥَ ﺃَﻧَّﻬُﻢْ ﺁﻣَﻨُﻮﺍ ﺑِﻤَﺎ ﺃُﻧْﺰِﻝَ ﺇِﻟَﻴْﻚَ ﻭَﻣَﺎ ﺃُﻧْﺰِﻝَ ﻣِﻦْ ﻗَﺒْﻠِﻚَ ﻳُﺮِﻳﺪُﻭﻥَ ﺃَﻥْ ﻳَﺘَﺤَﺎﻛَﻤُﻮﺍ ﺇِﻟَﻰ ﺍﻟﻄَّﺎﻏُﻮﺕِ ﻭَﻗَﺪْ ﺃُﻣِﺮُﻭﺍ ﺃَﻥْ ﻳَﻜْﻔُﺮُﻭﺍ ﺑِﻪِ ﻭَﻳُﺮِﻳﺪُ ﺍﻟﺸَّﻴْﻄَﺎﻥُ ﺃَﻥْ ﻳُﻀِﻠَّﻬُﻢْ ﺿَﻠَﺎﻟًﺎ ﺑَﻌِﻴﺪًﺍ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻨﺴﺎﺀ 60
“ወደ እነዚያ፣ እርሱ ባንተ ላይ በተዋረደውና ከአንተ በፊትም በተወረደው አምነናል ወደሚሉት አላየህምን? በርሱ እንዲክዱ በእርግጥ የታዘዙ ሲሆኑ ወደ ጣዖት መፋረድን ይፈልጋሉ፤ ሰይጣንም (ከውነት) የራቀን መሳሳት ሊያሳስታቸው ይፈልጋል።” (ሱረቱ-ኒሳእ 60)፡፡
6. ባለ ሁለት ፊት መሆናቸው፡- ሙስሊሞች በአላህ እርዳታ ድልን ሲጎናጸፉና በጠላታቸው ላይ ሲርረዱ፡ መናፍቃን ይመጡና እኛም እኮ ከናንተ ጋር ነበርን ይላሉ፡፡ ሙስሊሞች በወንጀላቸው ወይም አንድነታቸውን ባለመጠበቃቸው ሰበብ አላህ ከሀዲያንን ሲሾምባቸው ደግሞ፡ መናፍቃን በሌላኛው ፊታቸው ወደነሱ በመሄድ፡- እኛ እኮ ከናንተ ጋር ነበርን፡፡ ሙስሊሞቹም እንዳያጠቋቹ ስንከላከል ነበርን ይላሉ፡-
” ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﻳَﺘَﺮَﺑَّﺼُﻮﻥَ ﺑِﻜُﻢْ ﻓَﺈِﻥْ ﻛَﺎﻥَ ﻟَﻜُﻢْ ﻓَﺘْﺢٌ ﻣِﻦَ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻗَﺎﻟُﻮﺍ ﺃَﻟَﻢْ ﻧَﻜُﻦْ ﻣَﻌَﻜُﻢْ ﻭَﺇِﻥْ ﻛَﺎﻥَ ﻟِﻠْﻜَﺎﻓِﺮِﻳﻦَ ﻧَﺼِﻴﺐٌ ﻗَﺎﻟُﻮﺍ ﺃَﻟَﻢْ ﻧَﺴْﺘَﺤْﻮِﺫْ ﻋَﻠَﻴْﻜُﻢْ ﻭَﻧَﻤْﻨَﻌْﻜُﻢْ ﻣِﻦَ ﺍﻟْﻤُﺆْﻣِﻨِﻴﻦَ ﻓَﺎﻟﻠَّﻪُ ﻳَﺤْﻜُﻢُ ﺑَﻴْﻨَﻜُﻢْ ﻳَﻮْﻡَ ﺍﻟْﻘِﻴَﺎﻣَﺔِ ﻭَﻟَﻦْ ﻳَﺠْﻌَﻞَ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻟِﻠْﻜَﺎﻓِﺮِﻳﻦَ ﻋَﻠَﻰ ﺍﻟْﻤُﺆْﻣِﻨِﻴﻦَ ﺳَﺒِﻴﻠًﺎ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻨﺴﺎﺀ 141
“እነዚያ በእናንተ (የጊዜን መዘዋወር) የሚጠባበቁ ናቸው፤ ለናንተም ከአላህ የሆነ አሸናፊነት ቢኖራችሁ ከናንተ ጋር አልነበርንምን? ይላሉ፤ ለከሐዲዎችም ዕድል ቢኖር (ከአሁኑ በፊት) በናንተ ላይ አልተሾምንምን? (እና አልተውናችሁምን?) ከምእመናንም አደጋ አልከለከልናችሁምን? ይላሉ። አላህም በትንሣኤ ቀን በመካከላችሁ ይፈርዳል፤ አላህም ለከሐዲዎች በምእመናን ላይ መንገድን በፍጹም አያደርግም።” (ሱረቱ-ኒሳእ 141)፡፡
7. በመጥፎ ማዘዝና ከመልካም መከልከል፡- የምእመናን ባሕሪ፡- ሰዎችን በጥሩ ማዘዝና ከመጥፎ መከልከል ሲሆን፡ መናፍቃን ግን ከዚህ በተቃራኒ በመቆም ሰዎችን በመጥፎ ማዘዝና ከመልካም መከልከል እንዲሁም ለመልካም ነገር እጃቸውን ከመለገስ መሰብሰብና አላህን ከማውሳት መዘንጋት ነው፡-
” ﺍﻟْﻤُﻨَﺎﻓِﻘُﻮﻥَ ﻭَﺍﻟْﻤُﻨَﺎﻓِﻘَﺎﺕُ ﺑَﻌْﻀُﻬُﻢْ ﻣِﻦْ ﺑَﻌْﺾٍ ﻳَﺄْﻣُﺮُﻭﻥَ ﺑِﺎﻟْﻤُﻨْﻜَﺮِ ﻭَﻳَﻨْﻬَﻮْﻥَ ﻋَﻦِ ﺍﻟْﻤَﻌْﺮُﻭﻑِ ﻭَﻳَﻘْﺒِﻀُﻮﻥَ ﺃَﻳْﺪِﻳَﻬُﻢْ ﻧَﺴُﻮﺍ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻓَﻨَﺴِﻴَﻬُﻢْ ﺇِﻥَّ ﺍﻟْﻤُﻨَﺎﻓِﻘِﻴﻦَ ﻫُﻢُ ﺍﻟْﻔَﺎﺳِﻘُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺘﻮﺑﺔ 67
“መናፍቃንና መናፍቃት ከፊሎቻቸው ከከፊሉ ናቸው፤ በመጥፎ ነገር ያዛሉ፤ ከደግም ነገር ይከለከላሉ፤ እጆቻቸዉንም (ከልግስና) ይሰበስባሉ፤ አላህን ረሱ ስለዚህ (እርሱ) ተዋቸዉ፤ መናፍቃን አመጠኖቹ እነሱ ናቸዉ።” (ሱረቱ-ተውባህ 67)፡፡
8. የሂዳያ እንቅፋት መሆን፡- መናፍቃን ወደ አላህና መልክተኛው መንገድ ኑ ተብለው በተጠሩ ጊዜ፡ ለጥሪው ተገቢውን ምልሽ በመስጠት እንኳን ሊመጡ ሌላውንም ሰው እንዳይመጣ እንቅፋት በመሆን በር ሲዘጉ ታገኛቸዋለህ፡-
” ﻭَﺇِﺫَﺍ ﻗِﻴﻞَ ﻟَﻬُﻢْ ﺗَﻌَﺎﻟَﻮْﺍ ﺇِﻟَﻰ ﻣَﺎ ﺃَﻧْﺰَﻝَ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻭَﺇِﻟَﻰ ﺍﻟﺮَّﺳُﻮﻝِ ﺭَﺃَﻳْﺖَ ﺍﻟْﻤُﻨَﺎﻓِﻘِﻴﻦَ ﻳَﺼُﺪُّﻭﻥَ ﻋَﻨْﻚَ ﺻُﺪُﻭﺩًﺍ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻨﺴﺎﺀ 61
“ለነርሱም፦ አላህ ወደ አወረደው (ቁርአን)ና ወደ መልክተኛው ኑ፣ በተባሉ ጊዜ መናፍቃን ከአንተ መሸሽን ሲሸሹ ታያቸዋለህ።” (ሱረቱ-ኒሳእ 61)፡፡
አላህ ከኒፋቅና ከሙናፊቆችይጠብቀን፡፡