የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” 22 በኡስታዝ አቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
308 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
7. አፍራሽ ተግባራት፡-
2. ኩፍር (ክህደት)፡-
ለ. የ‹‹ኩፍር›› አይነቶች፡-
2. ትንሹ ኩፍር ‹‹ኩፍሩን አስገር፡-
ንግግሩና ተግባሩ ‹‹ኩፍር›› የሚል ስያሜ የሚሰጠው ሆኖ፡ ነገር ግን ባለቤቱን ከኢስላም አጥር የማያስወጣው፡ ስራን ሁሉ የማያበላሸው፡ ነገር ግን ለአላህ ቅጣትና ዛቻ አሳልፎ የሚሰጠው ተግባር ትንሹ ኩፍር ‹‹ኩፍሩን አስገር›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ለምሳሌ ያህል ፡-
ሀ. ሙስሊምን መጋደል፡- ያለ-ምንም ሸሪዓዊ ምክንያት ሙስሊም ወንድሞችንና እህቶችን መጋደል ሐራም ነው፡፡ ከትንሹ ኩፍርም የሚመደብ የኃጢአት ተግባር ነው፡፡ ሙስሊምን መግደል ይበቃል ብሎ ካመነ ግን ሙሉ በሙሉ ከኢስላም አጥር የሚያስወጣ የትልቁ ኩፍር ተግባር ነው፡፡ ሐራም መሆኑን በልቡ ከማመኑ ጋር፡ በሰራውም ስራ ኃጢአተኛ መሆኑን አምኖ ከመቀበሉ ጋር፡ በስሜት ተከታይነትና በጥላቻ ስሜት በወንድሙ ላይ የግድያ እርምጃ የሚወስድ ሰው ትንሹን ኩፍር ፈጸመ ይባላል፡፡ ወንድሙን ስለገደለ ከኢስላም አጥር ወጣ፡ ትልቁ ኩፍር ላይ ወደቀ አይባልም፡፡ ምክንያቱም ጌታችን አላህ የሚገዳደሉትን ‹‹ሙእሚኖች›› ብሎ ጠርቷቸዋልና፡፡ ካፊር ብሎ አልሰየማቸውም፡፡ ይህ የሚያመላክተው፡ ግድያው ከታላላቅ ወንጀሎች የሚመደብ እንጂ ከኢስላም አጥር የሚያስወጣ ተግባር እንዳልሆነ ነው፡፡ ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-
” ﻭَﺇِﻥْ ﻃَﺎﺋِﻔَﺘَﺎﻥِ ﻣِﻦَ ﺍﻟْﻤُﺆْﻣِﻨِﻴﻦَ ﺍﻗْﺘَﺘَﻠُﻮﺍ ﻓَﺄَﺻْﻠِﺤُﻮﺍ ﺑَﻴْﻨَﻬُﻤَﺎ ﻓَﺈِﻥْ ﺑَﻐَﺖْ ﺇِﺣْﺪَﺍﻫُﻤَﺎ ﻋَﻠَﻰ ﺍﻟْﺄُﺧْﺮَﻯ ﻓَﻘَﺎﺗِﻠُﻮﺍ ﺍﻟَّﺘِﻲ ﺗَﺒْﻐِﻲ ﺣَﺘَّﻰ ﺗَﻔِﻲﺀَ ﺇِﻟَﻰ ﺃَﻣْﺮِ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻓَﺈِﻥْ ﻓَﺎﺀَﺕْ ﻓَﺄَﺻْﻠِﺤُﻮﺍ ﺑَﻴْﻨَﻬُﻤَﺎ ﺑِﺎﻟْﻌَﺪْﻝِ ﻭَﺃَﻗْﺴِﻄُﻮﺍ ﺇِﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻳُﺤِﺐُّ ﺍﻟْﻤُﻘْﺴِﻄِﻴﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺤﺠﺮﺍﺕ 9
“ከምእምናንም የሆኑ ሁለት ጭፍሮች ቢጋደሉ በመካከላቸው አስታርቁ፤ ከሁለቱ አንደኛይቱም በሌላይቱ ላይ ወሰን ብታልፍ ያችን ወሰን የምታልፈውን ወደ አላህ ት እዛዝ እስክትመለስ ድረስ ተጋደሉ፤ ብትመለስም በመካከላቸው በትክክል አስታርቁ፤ በነገሩ ሁሉ አስተካክሉም፤ አላህ አስተካካዩችን ይወዳልና።” (ሱረቱል ሑጁራት 9)፡፡ በዚህ አንቀጽ ውስጥ የሚገዳደሉትን ሰዎች ‹‹ከምእመናን የሆኑ›› በማለት ሙስሊምነታቸውን ይጠቅሳል፡፡ ይህም ግድያ ከታላላቅ ኃጢአት የሚቆጠር እንጂ ከኢስላም የሚያስወጣ ተግባር አለመሆኑን ያስረዳል፡፡
” ﻳَﺎ ﺃَﻳُّﻬَﺎ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﺁﻣَﻨُﻮﺍ ﻛُﺘِﺐَ ﻋَﻠَﻴْﻜُﻢُ ﺍﻟْﻘِﺼَﺎﺹُ ﻓِﻲ ﺍﻟْﻘَﺘْﻠَﻰ ﺍﻟْﺤُﺮُّ ﺑِﺎﻟْﺤُﺮِّ ﻭَﺍﻟْﻌَﺒْﺪُ ﺑِﺎﻟْﻌَﺒْﺪِ ﻭَﺍﻟْﺄُﻧْﺜَﻰ ﺑِﺎﻟْﺄُﻧْﺜَﻰ ﻓَﻤَﻦْ ﻋُﻔِﻲَ ﻟَﻪُ ﻣِﻦْ ﺃَﺧِﻴﻪِ ﺷَﻲْﺀٌ ﻓَﺎﺗِّﺒَﺎﻉٌ ﺑِﺎﻟْﻤَﻌْﺮُﻭﻑِ ﻭَﺃَﺩَﺍﺀٌ ﺇِﻟَﻴْﻪِ ﺑِﺈِﺣْﺴَﺎﻥٍ ﺫَﻟِﻚَ ﺗَﺨْﻔِﻴﻒٌ ﻣِﻦْ ﺭَﺑِّﻜُﻢْ ﻭَﺭَﺣْﻤَﺔٌ ﻓَﻤَﻦِ ﺍﻋْﺘَﺪَﻯ ﺑَﻌْﺪَ ﺫَﻟِﻚَ ﻓَﻠَﻪُ ﻋَﺬَﺍﺏٌ ﺃَﻟِﻴﻢٌ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺒﻘﺮﺓ 178
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በተገደሉ ሰዎች ማመሳሰል በናንተ ላይ ተጻፈ፡፡ ነጻ በነጻ ባሪያም በባሪያ ሴትም በሴት (ይገደላሉ)፡፡ ለእርሱም (ለገዳዩ) ከወንድሙ (ደም) ትንሽ ነገር ምሕረት የተደረገለት ሰው (በመሓሪው ላይ ጉማውን) በመልካም መከታተል ወደርሱም (ወደ መሓሪው) ገዳዩ በመልካም አኳኋን መክፈል አለባቸው፡፡ ይህ ከጌታችሁ የኾነ ማቃለልና እዝነት ነው፡፡ ከዚህም በኋላ ሕግን የተላለፈ ሰው ለርሱ አሳማሚ ቅጣት አለው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 178)፡፡
በዚህም ቅዱስ አንቀጽ ላይ፡- የገደለን አካል በተመሳሳይ ቅጣት መግደል ጥቅላዊ ህግ መሆኑን ከደነገገ በኋላ፡ ነገር ግን ከተገዳይ ቤተሰብ በኩል ለገዳይ ይቅርታን የማድረግ አዝማሚያ (በካሳ ክፍያ) ቢያሳዩ ስርአቱ እንዴት መሆን እንዳለበት ሲያብራራ፡ እግረ መንገዱን የተገዳይ ቤተሰቦችን ለገዳዩ ‹‹ወንድም›› ብሎ ጠርቷቸዋል፡፡ ይህም የተፈጸመው ግድያ በ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› የተገነባውን ኢስላማዊ ወንድማማችነት ሊያፈርሰው እንደማይችልና፡ ገዳይንም ከኢስላም አጥር እንደማያስወጣው መረዳት ይቻላል፡፡
አቡ በክራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ሲሉ ሰማሁ አለ፡- “ሁለት ሙስሊሞች በሰይፋቸው ከተገናኙ (ከተገዳደሉ) ገዳይም ተገዳይም የእሳት ናቸው…” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
በዚህም ሐዲሥ ላይ፡- ሰይፍ የተማዘዙትን ሁለቱንም (ገዳይንም ተገዳይንም) ሙስሊም ብሎ ሲጠራቸው እንመለከታለን፡፡ በመሆኑም የነፍስ ግድያ ከታላላቅ ኃጢአት የሚመደብ እንጂ ከኢስላም አጥር የሚያስወጣ እንዳልሆነ ለመረዳት ብዙም አይከብድም፡፡ ነገር ግን ይህ ተግባር (የነፍሱ ግድያ) ትንሹ ኩፍር ውስጥ እንደሚከት ቀጣዩ ሐዲሥ ያስረዳል፡-
ዐብዱላህ ኢብኒ መስዑድ(ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ሙስሊምን መሳደብ አመጸኝነት ነው፡፡ መጋደሉ ደግሞ ኩፍር ነው” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
ለ. በዘር መሳደብ፡- አንድ ሙስሊም የሌላን ሰው ዘር መሳደቡና ማንቋሸሹ፡ ከታላላቅ ኃጢአትና ከትንሹ ኩፍር የሚመደቡ ተግባራቶች ናቸው፡፡ ሰዎችን በዘርና በጎሳ ከፋፍሎ የፈጠራቸው አላህ ነው፡፡ ይህም የጥበቡ መገለጫ ነው፡፡ ዓላማውም እንድንተዋወቅበትና እንድንግባባ እንጂ እንድንናቆርበት አይደለም፡፡ ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡-
” ﻳَﺎ ﺃَﻳُّﻬَﺎ ﺍﻟﻨَّﺎﺱُ ﺇِﻧَّﺎ ﺧَﻠَﻘْﻨَﺎﻛُﻢْ ﻣِﻦْ ﺫَﻛَﺮٍ ﻭَﺃُﻧْﺜَﻰ ﻭَﺟَﻌَﻠْﻨَﺎﻛُﻢْ ﺷُﻌُﻮﺑًﺎ ﻭَﻗَﺒَﺎﺋِﻞَ ﻟِﺘَﻌَﺎﺭَﻓُﻮﺍ ﺇِﻥَّ ﺃَﻛْﺮَﻣَﻜُﻢْ ﻋِﻨْﺪَ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﺃَﺗْﻘَﺎﻛُﻢْ ﺇِﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻋَﻠِﻴﻢٌ ﺧَﺒِﻴﺮٌ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺤﺠﺮﺍﺕ 13
“እላንተ ሰዎች ሆይ እኛ ከወንድና ከሴት ፈጠርናችሁ፤ እንድትተዋወቁም ጎሳዎችና ነገዶች አደረግናችሁ፤ አላህ ዘንድ በላጫችሁ፣ በጣም አላህን ፈሪያችሁ ነው፤ አላህ ግልጽን ዐዋቂ፣ ውስጥንም ዐዋቂ ነው።” (ሱረቱል ሑጁራት 13)፡፡
ይህን ህግ በመጣስ የዘር ጥላቻንና ስድብን የሚያስፋፋ ሰው የኩፍር ተግባር ፈጸመ ይባላል፡፡ ተግባሩ ‹‹ኩፍር›› የተሰኘው፡ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ላይ የሚታዩት ካፊሮች በመሆናቸው ምክንያት ነው፡፡
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ሁለት ነገሮች በሰዎች ላይ ኩፍር (የከሃድያን ስራ) ናቸው፡፡ በዘር መናቆርና በሟች ላይ ድምጽን ከፍ አድርጎ መጮህ (ማልቀስ)” (ሙስሊም)፡፡
ሀዘን የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ባሕሪ ነው፡፡ አጠገቡ ያለውን፡ የተላመደውንና የሚወደውን ሰው ሲያጣ ማዘኑ አይቀርም፡፡ ሊያለቅስም ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ በኢስላም አልተወገዘም፡፡ ነገር ግን ከልክ ባለፈ መልኩ የሟችን መልካም ተግባር እያነሱ፡ ድምጽን ከፍ አድርጎ መጮህና ማልቀስ የአላህን ውሳኔ (ቀደር) ወዶአለመቀበል ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ተግባር ደግሞ የከሀዲያን ስራ ነው፡፡ እኛ ለሟች እንዲህ የምንሆንለት ከፈጠረው አላህ የበለጠ አዝነንለት ነው እንዴ? ስለዚህም ሀዘናችን ገደብ ይኑረው፡፡
በአላህ ፈቃድ ሁለተኛውን የ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ››ን እምነት አፍራሽ ተግባር የሆነውን የኩፍርን ምንነት በመጠኑ ተመልክተናል፡፡ ኢንሻአላህ በቀጣዩ ፕሮግራማችን ደግሞ ሶስተኛውን አፍራሽ ተግባር እንመለከታለን፡፡