የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” 21 በኡስታዝ አቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
366 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
7. አፍራሽ ተግባራት፡-
2. ኩፍር (ክህደት)፡-
ለ. የ‹‹ኩፍር›› አይነቶች፡-
ትላንት የኩፍር አይነቶች ውስጥ ሶስቱን እንደ ናሙና ተመልክተናቸው ነበር፡፡ አልሐምዱሊላህ፡፡ ዛሬ አላህ ፈቃዱ ከሆነ ደግሞ ቀሪውን ነጥብ እንመለስበታለን ኢንሻአላህ፡፡
መ. በጥርጣሬና በመዋለል፡- ደግሞም እንዲህ አይነት ሰው አለ፡፡ ወይ በያዘው እምነት ተረጋግቶ ቀጥ አይል፡፡ ወይ የለየለት ከሀዲ አይሆን!:: ነገር ግን በዚህ መሀል በጥርጣሬ ይመላለሳል፡፡ ይሄ ነገር እውነት ይሆን ወይስ ሀሰት? እያለ እራሱን ይጠይቃል፡፡ እንዲህ አይነቱ ሰው ካፊር ተብሎ ይጠራል፡፡ ምክንያቱም አላህ ከባሪያዎቹ በእምነታቸው እርግጠኝነትን እንጂ ጥርጣሬን አይፈልግም፡፡ እርግጠኝነት የአማኞች ባሕሪ ነው (ሱረቱል በቀራህ 4፣ አል ሑጁራት 15)፡፡ መጠራጠር ደግሞ የከሀዲያንና የመናፍቃን ባሕሪ ነው፡፡ ስለዚህ በእምነት ጉዳይ እርግጠኝነት እንጂ ጥርጣሬ ተቀባይነት የለውም፡-
” ﻭَﺩَﺧَﻞَ ﺟَﻨَّﺘَﻪُ ﻭَﻫُﻮَ ﻇَﺎﻟِﻢٌ ﻟِﻨَﻔْﺴِﻪِ ﻗَﺎﻝَ ﻣَﺎ ﺃَﻇُﻦُّ ﺃَﻥْ ﺗَﺒِﻴﺪَ ﻫَﺬِﻩِ ﺃَﺑَﺪًﺍ * ﻭَﻣَﺎ ﺃَﻇُﻦُّ ﺍﻟﺴَّﺎﻋَﺔَ ﻗَﺎﺋِﻤَﺔً ﻭَﻟَﺌِﻦْ ﺭُﺩِﺩْﺕُ ﺇِﻟَﻰ ﺭَﺑِّﻲ ﻟَﺄَﺟِﺪَﻥَّ ﺧَﻴْﺮًﺍ ﻣِﻨْﻬَﺎ ﻣُﻨْﻘَﻠَﺒًﺎ * ﻗَﺎﻝَ ﻟَﻪُ ﺻَﺎﺣِﺒُﻪُ ﻭَﻫُﻮَ ﻳُﺤَﺎﻭِﺭُﻩُ ﺃَﻛَﻔَﺮْﺕَ ﺑِﺎﻟَّﺬِﻱ ﺧَﻠَﻘَﻚَ ﻣِﻦْ ﺗُﺮَﺍﺏٍ ﺛُﻢَّ ﻣِﻦْ ﻧُﻄْﻔَﺔٍ ﺛُﻢَّ ﺳَﻮَّﺍﻙَ ﺭَﺟُﻠًﺎ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻜﻬﻒ 35-37
“እርሱም ነፍሱን በዳይ ሆኖ ወደ አትክልቱ ገባ፤ ይህች ዘለዓለም ትጠፋለች ብዬ አልጠረጥርም፣ አለ። ሰዓቲቱንም ቋሚ (ኋኝ) ናት ብዬ አልጠረጥርም፤ (እንደምትለው) ወደ ጌታዬም ብመለስ ከርሷ የበለጠን መመለሻ በእርግጥ አገኛለሁ፥ (አለው)።ጓደኛው፥ (አማኙ)፣ እርሱ ለርሱ የሚመላለሰው ሲሆን ፦ በዚያ ከዐፈር ከዚያም ከፍቶት ጠብታ በፈጠረህ፣ ከዚያም ሰው ባደረገህ፥ (አምላክ) ካድህን? አለው።” (ሱረቱል ከህፍ 35-37)፡፡

ሠ. በቸልተኝነት የሚከሰት፡- ይህ ማለት ግለሰቡ ከአላህና ከመልክተኛው የመጣለትን ነገር እውነት ነው ብሎ አይቀበልም፡ ሀሰት ነው ብሎም አያስተባብልም፡፡ ነገር ግን በቸልተኝነት ከመታዘዝ ፊቱን ያዞራል፡፡ በጌታው አንቀጽ በተመከረና በተገሰጸ ጊዜ ሳያስተባብልና እውነት ነው ብሎም ሳይቀበል ጀርባ የሰጠ ሆኖ ይሸሻል፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ኩፍር የሚወስድ ባሕሪ ነው፡-
” ﻭَﻣَﻦْ ﺃَﻇْﻠَﻢُ ﻣِﻤَّﻦْ ﺫُﻛِّﺮَ ﺑِﺂﻳَﺎﺕِ ﺭَﺑِّﻪِ ﺛُﻢَّ ﺃَﻋْﺮَﺽَ ﻋَﻨْﻬَﺎ ﺇِﻧَّﺎ ﻣِﻦَ ﺍﻟْﻤُﺠْﺮِﻣِﻴﻦَ ﻣُﻨْﺘَﻘِﻤُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺴﺠﺪﺓ 22
“በጌታቸውም አንቀጾች ከተገሠጸና ከዚያም ከተዋት ሰው ይበልጥ በደለኛ ማነው? (የለም)፤ እኛ ከተንኮለኞቹ ተበቃዮች ነን።” (ሱረቱ-ሰጅዳህ 22)፡፡
” ﻭَﻣَﻦْ ﺃَﻇْﻠَﻢُ ﻣِﻤَّﻦْ ﺫُﻛِّﺮَ ﺑِﺂﻳَﺎﺕِ ﺭَﺑِّﻪِ ﻓَﺄَﻋْﺮَﺽَ ﻋَﻨْﻬَﺎ ﻭَﻧَﺴِﻲَ ﻣَﺎ ﻗَﺪَّﻣَﺖْ ﻳَﺪَﺍﻩُ ﺇِﻧَّﺎ ﺟَﻌَﻠْﻨَﺎ ﻋَﻠَﻰ ﻗُﻠُﻮﺑِﻬِﻢْ ﺃَﻛِﻨَّﺔً ﺃَﻥْ ﻳَﻔْﻘَﻬُﻮﻩُ ﻭَﻓِﻲ ﺁﺫَﺍﻧِﻬِﻢْ ﻭَﻗْﺮًﺍ ﻭَﺇِﻥْ ﺗَﺪْﻋُﻬُﻢْ ﺇِﻟَﻰ ﺍﻟْﻬُﺪَﻯ ﻓَﻠَﻦْ ﻳَﻬْﺘَﺪُﻭﺍ ﺇِﺫًﺍ ﺃَﺑَﺪًﺍ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻜﻬﻒ 57
“በጌታውም አንቀጾች ከተገሠጸና ከርሷ ከዞረ እጆቹም ያስቀደሙትን ነገር ከረሳ ሰው፣ ይበልጥ በዳይ ማነው? እኛ በልቦቻቸው ላይ እንዳያውቁት ሺፋኖችን፥ በጆሮዎቻቸውም ውስጥ ድንቁርናን አደረግን፤ ወደ መመራትም ብትጠራቸው ያንጊዜ ፈጽሞ አይመሩም።” (ሱረቱል ከህፍ 57)፡፡
ረ. በአስመሳይነት የሚከሰት፡- ሌላው ትልቁ ኩፍር ከሚከሰትባቸው መንገዶች አንዱ አስመሳይ (ሙናፊቅ) መሆን ነው፡፡ ይህ ማለት ሰውየው በልቡ የካደ ሆኖ በምላሱና በተግባሩ ግን ያመነ ለመምሰል የሙስሊሞችን ስራ የሚሰራና የነሱን ንግግር የሚናገር ይሆናል፡፡ ይህ ሰው ምንም በምላሱ አመንኩ ቢልም፡ በአካሉ የሙስሊሞችን ዒባዳ (ሶላት፣ ጾም፣ ሐጅ…) ቢተገብርም፡ በልቡ አምኖ እስካልተቀበለ ድረስ ካፊር ነው፡፡ ከሙስሊሞች ጎራ አይመደብም፡፡ ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡-
” ﻭَﻣِﻦَ ﺍﻟﻨَّﺎﺱِ ﻣَﻦْ ﻳَﻘُﻮﻝُ ﺁﻣَﻨَّﺎ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻭَﺑِﺎﻟْﻴَﻮْﻡِ ﺍﻟْﺂﺧِﺮِ ﻭَﻣَﺎ ﻫُﻢْ ﺑِﻤُﺆْﻣِﻨِﻴﻦَ * ﻳُﺨَﺎﺩِﻋُﻮﻥَ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻭَﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﺁﻣَﻨُﻮﺍ ﻭَﻣَﺎ ﻳَﺨْﺪَﻋُﻮﻥَ ﺇِﻟَّﺎ ﺃَﻧْﻔُﺴَﻬُﻢْ ﻭَﻣَﺎ ﻳَﺸْﻌُﺮُﻭﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺒﻘﺮﺓ 8-9
“ከሰዎችም «በአላህና በመጨረሻው ቀን አምነናል» የሚሉ አልሉ፤ እነርሱም አማኞች አይደሉም፡፡ አላህንና እነዚያን ያመኑትን (ሰዎች) ያታልላሉ፤ የማያውቁ ሲኾኑ ነፍሶቻቸውን እንጅ ሌላን አያታልሉም፡፡ ” (ሱረቱል በቀራህ 8-9)፡፡
ሰ. ሶላትን መተው፡- ከትልቁ ኩፍር ውስጥ ከሚመደቡት ተግባራቶች ውስጥ አንዱ ሶላትን መተው ነው፡፡ አንድ ሰው ሶላትን ከተወ (ካልሰገደ) ካፊር እንጂ ሙስሊም አይባልም፡፡ ሶላት የኢስላም ምሶሶ ነው፡፡ አንድ ሙስሊም ነኝ የሚል ሰው፡ ሶላትን ተወ ማለት የኢስላምን ምሰሶ ናደ ማለት ነው፡፡ ታዲያ ምሰሶው ከተናደ ከቤቱ ምን ቀረ? ሶላትን የተወ ሰው ካፊር መሆኑን የሚያመላክቱ ማስረጃዎችን ቀጥለን እንመልከታቸው፡-
ጃቢር ኢብኒ-ዐብዲላህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ሲሉ ሰማሁ አለ፡- “በሰውየውና በኩፍር መሐከል ያለው ነገር ቢኖር ሶላት መተዉ ብቻ ነው” (ሙስሊም)፡፡
የሐዲሡ መልእክት ሶላትን የተወ ሰው ወደ ኩፍር ለመግባት ምንም የሚቀረው ነገር የለም ነው፡፡ የተወ ጊዜ ከፈረ ማለት ነው፡፡ በሌላ ሐዲሥ ላይ ደግሞ መልክተኛው (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ይላሉ፡- “በኛና በነሱ (በሙሽሪኮች) መሐከል ያለው የቃል-ኪዳን ምልክት ሶላት ነው፡ የተዋትም ሰው በርግጥ ከፈረ” (ቲርሚዚይ)፡፡
ዐብዱላህ ኢብኑ-ሸቂቅ አል-ዑቀይሊይ (ረሒመሁላህ) እንዲህ አለ፡-“የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ባልደረቦች ሳይሰሩት መተውን እንደ ኩፍር የሚመለከቱት ነገር ከሶላት ውጪ ሌላ ነገር አልነበረም” (ቲርሚዚይ 2622)፡፡
ሌላው ልናስተውል የሚገባን ነገር ቢኖር፡- ኢብሊስ ከነበረበት የድሎት ዓለም የተባረረው፡ አላህ ያዘዘውን አንድ ሱጁድ በትእቢትና በኩራት አልሰግድም በማለቱ መሆኑን ነው፡፡ ነገ የውሙል ቂያም የባሮች ስራ በትክክለኛ ሚዛን ሲመዘን መጀመሪያ የሚመዘነው ከስራ ሶላት ነው፡፡ ሶላቱ ከተስተካከለ ሌላው ስራው ሁሉ ይስተካከላል፡፡ ሶላቱ ከተበላሸ ሌላው ስራ ሁሉ ይበላሻል፡፡ ይህ በመሆኑም ሶላት ላይ ልዩ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ማለት ነው፡-
ዐብዱላህ ኢብኑ መስዑድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- ‹‹የውሙል ቂያም አላህ ሰዎችን ከስራቸው መጀመሪያ የሚተሳሰባቸው ሶላታቸውን ነው፡፡›› (አቡ ዳዉድ 864)፡፡
ዑመርኢብኑል ኸጣብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- “ሶላትን የተወ ሰው በኢስላም ውስጥ ምንም እጣ የለውም” (አል-ኢማን፡ ኢብኑ አቢ ሸይባህ 103)፡፡
ዛሬ ስለ ትልቁ ኩፍር‹‹ኩፍሩን አክበር›› ሰባት ምሳሌዎችን በአላህ ፈቃድ ተመልክተናል አልሐምዱ ሊላህ፡፡ በቀጣዩ ደግሞ በአላህ ፈቃድ ስለ ትንሹ ኩፍር‹‹ሺርኩን አስገር›› የተወሰነ እንመለከታለን፡፡ አላህ ከሁሉም አይነት የኩፍር መንገዶች በራሕመቱ ይጠብቀን አሚን፡፡