የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” 20 በኡስታዝ አቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
365 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
7. አፍራሽ ተግባራት፡-
2. ኩፍር (ክህደት)፡-
ለ. የ‹‹ኩፍር›› አይነቶች፡-
ኩፍርም እንደ ሺርክ ሁለት ቦታ ይከፈላል፡፡ ‹‹ኩፍሩን አክበር›› (ትልቁ ኩፍር) እና ‹‹ኩፍሩን አስገር›› (ትንሹ ኩፍር) በመባል፡፡
ትልቁ ኩፍር የሚባለው፡- ስራን በጠቅላላ የሚያበላሽ፡ ከኢስላም አጥር የሚያስወጣ፡ ባለቤቱንም ያለ ተውበት ከሞተ፡ ዘላለም ለጀሀነም እሳት የሚዳርግ፡ ምንም አይነት ምሕርት (ሸፋዐም ሆነ ይቅርታ) የማያስገኝ ሲሆን፡-
ትንሹ ኩፍር ደግሞ፡- ተግባሩ ወይም ንግግሩ ኩፍር የሚሰኝ ሆኖ፡ ነገር ግን ባለቤቱን ከኢስላም አጥር የማያስወጣ፡ ያለ ተውበት ከሞተ ደግሞ ለአላህ ቅጣት የሚዳርግ፡ ያም ሆኖ አላህ ከፈለገ ከራሱ በመነጨ ምሕረት (ራሕማህ) ወይንም በነቢያችን ሸፋዐህ ኃጢአቱን ይቅር ለማለት የሚያስችል ሲሆን፡ ከታላላቅ ወንጀሎች የሚመደብ ነው፡፡
ሐ. እንዴት ይከሰታል?
ትልቁ ኩፍርና ትንሹ ኩፍር የሚከሰትባቸውን መንገዶች፡ በትልቁ ኩፍርና በትንሹ ኩፍር ውስጥ የሚመደቡትን ድርጊቶችና ንግግሮች ለናሙና ያክል የተወሰኑትን እናያቸዋለን፡፡ ከዛ በፊት መረዳት ያለብን ነገር፡- ማንኛውም ድርጊትም ሆነ ንግግር ‹‹ትልቁ ሺርክ›› ውስጥ የሚመደብ ከሆነ፡ በዛው መልኩ እሱም ‹‹ትልቁ ኩፍር›› እንደሆነ ልናውቅ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ባለፈው ትንታኔውን እንዳየነው፡ ማንኛውም ሙሽሪክ ካፊር ነው የሚል ነበር፡፡ ስለዚህ ትልቁን ሺርክ የፈጸመ ሰው ሁሉ ትልቁ ኩፍር ውስጥም እንደገባ ልናውቅ ይገባል፡፡ አሁን ትልቁ ኩፍርና ትንሹ ኩፍር የሚከሰትባቸውን መንገዶች እንመልከት፡-
1. ትልቁ ኩፍር ‹‹ኩፍሩን አክበር››፡-
ሀ. በእንቢተኝነትና በኩራት፡- ሰዎችን ኩፍር (ክህደት) ውስጥ ከሚከታቸው አንዱ ኩራትና እንቢተኝነት ነው፡፡ ከአላህና ከመልከተኛው ዘንድ የመጣላቸውን ትእዛዝ አውቀውና ተረድተው ሲያበቁ ያለ ምንም ስንፍና በትእቢት፡ በኩራትና በእንቢተኝነት ለመቀበልና ለመታዘዝ ካልፈለጉ፡ ከፈሩ (ካዱ) ማለት ነው፡፡ ይህ አይነቱ ባሕሪ የቀንደኛው ጠላታችን የኢብሊስ ባሕሪ ነው፡፡ ጌታ አላህ መላእክትንና እሱን ለአደም የአክብሮት ስግደትን (ሱጁድ) እንዲወርዱ አዟቸው ነበር፡፡ መላእክት በመላ ለጌታቸው ትእዛዝ ታዛዥ በመሆን የታዘዙትን ሲፈጽሙ፡ ኢብሊስ ግን ለመስገድ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ጌታችንም ለምን አልሰገድክም? በማለት የወቀሳ ጥያቄ ሲያቀርብለት፡ የኢብሊስ መልስም፡- እንዳይሰግድ የከለከለው ዑዝር (ሸሪዐዊ ምክንያት) ሳይሆን፡ የራሱን ማንነት፡ አደም (ዐለይሂ ሰላም) ከተፈጠረበት ማንነት አብልጦ በመመልከቱና አደምንም የበታች አድርጎ በማየቱ ምክንያት፡ በኩራትና በእንቢተኝነት አሻፈረኝ ማለቱን ገለጸ፡፡ በዚህም ምክንያት ከነበረበት የድሎት ዓለም ወደ ውርደት፡ ከአላህ ራሕመት ወደ ዘላለማዊ እርግማንና ቁጣ ተሸጋገረ፡፡ ከካሀዲያንም ጎራ ተመደበ፡፡ አላህ ከኩራትና ከትእቢት ይጠብቀን፡-
” ﻭَﺇِﺫْ ﻗُﻠْﻨَﺎ ﻟِﻠْﻤَﻠَﺎﺋِﻜَﺔِ ﺍﺳْﺠُﺪُﻭﺍ ﻟِﺂﺩَﻡَ ﻓَﺴَﺠَﺪُﻭﺍ ﺇِﻟَّﺎ ﺇِﺑْﻠِﻴﺲَ ﺃَﺑَﻰ ﻭَﺍﺳْﺘَﻜْﺒَﺮَ ﻭَﻛَﺎﻥَ ﻣِﻦَ ﺍﻟْﻜَﺎﻓِﺮِﻳﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺒﻘﺮﺓ 34
“ለመላእክትም «ለአደም ስገዱ» ባልን ጊዜ (አስታውስ) ፡፡ ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ፤ ኢብሊስ (ዲያብሎስ) ብቻ ሲቀር እምቢ አለ፤ ኮራም ከከሓዲዎቹም ኾነ፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 34)፡፡
” ﻭَﻟَﻘَﺪْ ﺧَﻠَﻘْﻨَﺎﻛُﻢْ ﺛُﻢَّ ﺻَﻮَّﺭْﻧَﺎﻛُﻢْ ﺛُﻢَّ ﻗُﻠْﻨَﺎ ﻟِﻠْﻤَﻠَﺎﺋِﻜَﺔِ ﺍﺳْﺠُﺪُﻭﺍ ﻟِﺂﺩَﻡَ ﻓَﺴَﺠَﺪُﻭﺍ ﺇِﻟَّﺎ ﺇِﺑْﻠِﻴﺲَ ﻟَﻢْ ﻳَﻜُﻦْ ﻣِﻦَ ﺍﻟﺴَّﺎﺟِﺪِﻳﻦَ * ﻗَﺎﻝَ ﻣَﺎ ﻣَﻨَﻌَﻚَ ﺃَﻟَّﺎ ﺗَﺴْﺠُﺪَ ﺇِﺫْ ﺃَﻣَﺮْﺗُﻚَ ﻗَﺎﻝَ ﺃَﻧَﺎ ﺧَﻴْﺮٌ ﻣِﻨْﻪُ ﺧَﻠَﻘْﺘَﻨِﻲ ﻣِﻦْ ﻧَﺎﺭٍ ﻭَﺧَﻠَﻘْﺘَﻪُ ﻣِﻦْ ﻃِﻴﻦٍ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻷﻋﺮﺍﻑ 11-12
“በእርግጥ ፈጠርናችሁ፤ ከዚያም ቀረጽናችሁ፤ ከዚያም ለመላእክቶች ለአደም ስገዱ አልን ወዲያውም ሰገዱ፤ ኢብሊስ (ዲያቢሎስ) ሲቀር ከሰጋጆቹ አልሆነም። (አላህ) ባዘዝኩህ ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ? አለው፤ እኔ ከርሱ የበለጥኩ ነኝ፤ ከእሳት ፈጠርከኝ፤ እሱን ግን ከጭቃ ፈጠርከው አለ።” (ሱረቱል አዕራፍ 11-12)፡፡
እኛም ብንሆን፡ ከአላህና ከመልክተኛው ዘንድ የመጣልንን ትእዛዝ ላለመተግበር የከለከለን ይኸው ኩራትና እንቢተኝነት ከሆነ፡ ከከሀዲያንና ከኢብሊስ ጎራ የማንሰለፍበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ አላህና መልክተኛው ያዘዙትን ነገር በስንፍናና በስሜት ተከታይነት መተው ኃጢአት ቢሆንም፡ በኩራትና በእንቢተኝነት መመለሱ ግን እጅግ የከፋ ኃጢአት ብሎም ኩፍር ነው፡፡
ለ. በማስተባበል፡- ይህ ደግሞ፡- ከአላህና ከመልክተኛው የመጣን መልእክት ከመነሻው እውነት ነው ብሎ በልብ አለመቀበልና መካድ ማለት ነው፡፡ አላህ የሚልካቸውን መልክተኞቹን በጠቅላላ በማኀበረሰቡ እንዳይስተባበሉበት ከአሳማኝ ማስረጃዎች ጋር ነው አብሮ የሚልካቸው (አል-ሐዲድ 25)፡፡ ከዚህ በኋላ ሰዎች ሆን ብለው ማስተባበልና አሻፈረኝ ብሎ አለመቀበል ካልሆነ በቀር ምንም ምክንያት የላቸውም፡፡ በዚህ አይነት መልኩ የአላህንና የመልክተኛውን ትእዛዝ ያስተባበሉና ያስዋሹ በሙሉ ከሀዲያን ተብለው ይጠራሉ፡፡ ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-
” ﻭَﻣَﻦْ ﺃَﻇْﻠَﻢُ ﻣِﻤَّﻦِ ﺍﻓْﺘَﺮَﻯ ﻋَﻠَﻰ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻛَﺬِﺑًﺎ ﺃَﻭْ ﻛَﺬَّﺏَ ﺑِﺎﻟْﺤَﻖِّ ﻟَﻤَّﺎ ﺟَﺎﺀَﻩُ ﺃَﻟَﻴْﺲَ ﻓِﻲ ﺟَﻬَﻨَّﻢَ ﻣَﺜْﻮًﻯ ﻟِﻠْﻜَﺎﻓِﺮِﻳﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻌﻨﻜﺒﻮﺕ 68
“በአላህ ላይም ውሸትን ከቀጣጠፈ ሰው ወይም እውነቱ በመጣለት ጊዜ ከአስዋሽ ይበልጥ በዳይ ማነው? በገሀነም ውስጥ ለከሐዲዎች መኖሪያ የለምን?” (ሱረቱል ዐንከቡት 68)፡፡ እኛም ከአላህና ከመልክተኛው የመጣልንን ነገር በጠቅላላ፡ ከስሜታችንና ከፍላጎታችን ጋር ገጠመም አልገጠመም ልናስተባብልና ልናስዋሽ አይገባንም፡፡ ካልሆነ በድርጊታችን ሰበብ ካፊር እንሆናለንና፡፡
ሐ. በመካድና በመቃወም፡- ይህ አይነቱ ክህደት ደግሞ ከሁለተኛው የሚለየው፡- የነገሩን እውነተኝነት በልቡ ዐውቆና ተረድቶ፡ ነገር ግን በምላሱ የሚቃወምና የሚክድ ማለት ነው፡፡ እንደ ፊርዐውንና ሹማምንቶቹ አይነቶች፡፡ ሙሳ (ዐለይሂ ሰላም) በግልጽ ተአምራት እነሱ ዘንድ መልክተኛ ሆኖ ተላከ፡፡ እነሱም ተአምራቱን በማየት ከአላህ ዘንድ የተላከ መሆኑን በውስጣቸው አወቁ፡፡ ነገር ግን ላለመቀበል በምላሳቸው አሻፈረኝ አሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ከካፊሮች ጎራ ተመደቡ፡-
” ﻓَﻠَﻤَّﺎ ﺟَﺎﺀَﺗْﻬُﻢْ ﺁﻳَﺎﺗُﻨَﺎ ﻣُﺒْﺼِﺮَﺓً ﻗَﺎﻟُﻮﺍ ﻫَﺬَﺍ ﺳِﺤْﺮٌ ﻣُﺒِﻴﻦٌ * ﻭَﺟَﺤَﺪُﻭﺍ ﺑِﻬَﺎ ﻭَﺍﺳْﺘَﻴْﻘَﻨَﺖْﻫَﺎ ﺃَﻧْﻔُﺴُﻬُﻢْ ﻇُﻠْﻤًﺎ ﻭَﻋُﻠُﻮًّﺍ ﻓَﺎﻧْﻈُﺮْ ﻛَﻴْﻒَ ﻛَﺎﻥَ ﻋَﺎﻗِﺒَﺔُ ﺍﻟْﻤُﻔْﺴِﺪِﻳﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻨﻤﻞ 13-14
“ታምራታችንም ግልጽ ሆና በመታቻቸው ጊዜ ግልጽ ድግምት ነው፤ አሉ። ነፍሶቻቸው ያረጋገጧት ሲሆኑ ለበደልና ለኩራት በርሷ ካዱ፤ የአመጸኞችም ፈጻሜ እንዴት እንደ ነበረ ተመልከት።” (ሱረቱ-ነምል 13-14)፡፡
ለዛሬ ሶስቱን እንደ ምሣሌ ከተመለከትናቸው፡ ቀሪዎቹን ደግሞ በአላህ ፈቃድ በቀጣዩ አንመለስበታለን ኢንሻአላህ፡፡