የኢስላም መልእክት “ላ ኢላሀ ኢልለሏህ” ክፍል -2

ሼር ያድርጉ
416 Views

በኡስታዝ አቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

2. ትርጓሜው፡-

ባለፈው ስለ ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› ትምሕርት ጀምረን፡ በውስጡም የላ ኢላሀ ኢለሏህ አስፈላጊነትን ተመልክተናል፡፡ ዛሬ ደግሞ አላህ ፈቃዱ ከሆነ የላ ኢላሀ ኢልለሏህ ትርጉም እና ይዘት ምን እንደሆነ እንመለከታለን፡፡

“ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” ማለት በቀጥታ ፍቺው፡- ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም ማለት ነው፡፡ አንድ ሙስሊም “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” ካለ፡ አላህን በብቸኝነት ሊያመልክ፡ ከሱ ውጪ ማንንም ምንንም ላይገዛ ቃል ገብቷል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ይህን የ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” ምስክርነት የሰጠ አንድ ሙስሊም፡ በህይወት ዘመኑ በጠቅላላ በችግርና በደስታ፣ በሐብት እና በድህነት፣ በሀገርና በስደት፣ በሰላምና በጦርነት ጊዜ አላህን ብቻ ሊያመልክ ይገባዋል ማለት ነው፡፡ ከአላህ ውጪ ያለው በጠቅላላ አምልኮ የማይገባው የሃሰት አማልክት መሆኑን ዐውቆ ከማምለክ መቆጠብ ይኖርበታል፡፡

‹‹ላ›› የሚለው ፊደል፡ አፍራሽ ፊደል ነው፡፡ የለም! በማለት ይቃወማል፡፡ ምን የለም? የሚል ጥያቄ ከተነሳም፡ መልሱ፡- ‹‹ኢላሀ›› የሚል ይሆናል፡፡ ‹‹ኢላህ›› ማለት የሚመለክ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም አምልኮ የሚገባው የለም ብሎ ይቃወምና፡ በመቀጠልም ‹‹ኢልለሏህ›› ይላል፡፡ ትርጉሙም፡- አላህ ብቻ ሲቀር ማለት ነው፡፡ አላህ በሰማይም ሆነ በምድር ብቻውን የሚመለክ እውነተኛ አምላክ በመሆኑ ‹‹ኢላህ›› ተብሎ ይጠራል፡-

” ﻭَﻫُﻮَ ﺍﻟَّﺬِﻱ ﻓِﻲ ﺍﻟﺴَّﻤَﺎﺀِ ﺇِﻟَﻪٌ ﻭَﻓِﻲ ﺍﻟْﺄَﺭْﺽِ ﺇِﻟَﻪٌ ﻭَﻫُﻮَ ﺍﻟْﺤَﻜِﻴﻢُ ﺍﻟْﻌَﻠِﻴﻢُ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺰﺧﺮﻑ 84
“እርሱም ያ በሰማይ ውስጥ ሊገዙት የሚገባው፣ በምድርም ውስጥ ሊገዙት የሚገባው አምላክ ነው፤ እርሱም ብልሀተኛው ዐዋቂው ነው።” (ሱረቱ-ዙኽሩፍ 84)፡፡

‹‹በእውነት›› የሚለው ቃል ትርጉሙ ውስጥ መካተቱ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት፡- ለአላህ የሚቀርበውን እውነተኛ አምልኮ፡ ለፍጡራን ከሚቀርበው የሃሰት አምልኮ ለመለየት ነው፡፡ እውነተኛ አምልኮ የሚባለው ለእውነተኛው አምላክ ለአላህ የሚቀርበው ሲሆን፡ የሃሰት አምልኮ የሚባለው ደግሞ ከአላህ ውጪ አምላክ ሳይሆኑ ለተመለኩ ነገሮች ሁሉ የሚቀርበውን አምልኮ ነው፡፡ ይህንን ጌታችን አላህ እራሱ በቅዱስ ቃሉ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡-

” ﺫَﻟِﻚَ ﺑِﺄَﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻫُﻮَ ﺍﻟْﺤَﻖُّ ﻭَﺃَﻥَّ ﻣَﺎ ﻳَﺪْﻋُﻮﻥَ ﻣِﻦْ ﺩُﻭﻧِﻪِ ﻫُﻮَ ﺍﻟْﺒَﺎﻃِﻞُ ﻭَﺃَﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻫُﻮَ ﺍﻟْﻌَﻠِﻲُّ ﺍﻟْﻜَﺒِﻴﺮُ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺤﺞ 62
“ይህ አላህ እርሱ እውነት በመሆኑ ከርሱም ሌላ የሚገዙት ነገር እርሱ ፍጹም ውሽት በመሆኑ አላህም እርሱ የሁሉ በላይ ታላቅ በመሆኑ ነው።” (ሱረቱል ሐጅ 62)፡፡

” ﺫَﻟِﻚَ ﺑِﺄَﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻫُﻮَ ﺍﻟْﺤَﻖُّ ﻭَﺃَﻥَّ ﻣَﺎ ﻳَﺪْﻋُﻮﻥَ ﻣِﻦْ ﺩُﻭﻧِﻪِ ﺍﻟْﺒَﺎﻃِﻞُ ﻭَﺃَﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻫُﻮَ ﺍﻟْﻌَﻠِﻲُّ ﺍﻟْﻜَﺒِﻴﺮُ ” ﺳﻮﺭﺓ ﻟﻘﻤﺎﻥ 30
“ይህ፣ አላህ እርሱ እውነት፣ ከርሱም ሌላ የሚገዙት (ጣዖት) ውሸት በመሆኑና አላህም እርሱ የበላይ ታላቅ በመኾኑ ነው።” (ሱረቱ ሉቅማን 30)፡፡

አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ስለ “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” ትርጉም ተጠይቀው ሲናገሩ፡- አላህ አንድ ነው፣ ከአላህ ሌላ ፈጣሪ የለም… መልስ ይሰጣሉ፡፡ እርግጥ ነው ጌታችን አላህ አንድ ነው፡፡ ሁለት ወይም ሶስት ወይም ሌላ አይደለም፡፡ ደግሞም ከርሱ ሌላ ፈጣሪ የለም፡ ሊኖርም አይችልም፡፡ ስህተቱ ግን ዋናው “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” ያዘለው መልእክት ይህንን ብቻ አድርጎ ማሰቡ ላይ ነው፡፡

አንድ ሙስሊም ጌታው አላህ አንድ እንደሆነ አምኖ፡ ከሱም ውጭ ሌላ ፈጣሪ እንደሌለ ቢመሰክርና ነገር ግን ይህን ጌታውን በአምልኮ (በሶላት፣ በዱዓእ…) ባይገዛለት ምን ይጠቅመዋል? ወይንም ደግሞ የአላህን አንድነት አምኖ፡ ከሱ ውጪ ፈጣሪም እንደሌለ ተቀብሎ፡ አላህንም እየተገዛ፡ ነገር ግን ከአላህ ሌላ ያሉትንም አካላት ቢያመልካቸው ወይም የተወሰነ የአምልኮ ክፍልን ቢሰጣቸው ስራው አልተበላሸምን? በመሆኑም “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” የአላህን አንድነትና ብቸኛ ፈጣሪነቱን ማመን ብቻም ሳይሆን ብቸኛ ተመላኪነቱንም ማመን እና መተግበርንም ይጠይቃል፡፡
ስለዚህም ትክክለኛ ትርጓሜው፡- ‹‹ላ መዕቡደ ቢሐቂን ኢልለሏህ›› (ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም) ማለት ነው፡፡ ይህን ትርጉም ከተጠቀሙ የቅዱስ ቁርኣን ሙፈሲሮች መካከል የተወሰኑትን ስማቸውን ልጥቀስ፡-

1. ኢብኑ-ጀሪር አጥ-ጠበሪ (310 ሒጅ.)፡- በሱረቱል አንዓም ቁ 106 ላይ ያለውን የ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” ቃል በዚህ መልክ ተንትነውታል፡፡ እንዲሁም በሱረቱ ሁድ ቁ. 14 ላይ ያለውንም ተመሳሳይ ትርጉም ሰጥተውታል፡፡ (ጃሚዑል በያን፡ ሱረቱል አንዓም 106፣ ሱረቱ ሁድ 14)፡፡

2. አቡ ጀዕፈር አን-ነሐስ (338 ሒጅ.)፡- በሱረ- ጡር 43 ላይ ያለውን እንደዚሁ ገልጸውታል፡፡ (ኢዕራቡል ቁርኣን፡ ሱረቱ-ጡር 43)፡፡

3. አቡል መዝፈር አስ-ሰምዓኒይ (489 ሒጅ.) በሱረቱ ጣሀ ቁ. 14 ላይ ያለውን እንደዚሁ ገልጸውታል፡፡ (ተፍሲር አስ-ሰምዓኒ፡ ሱረቱ ጣሀ 14)፡፡

4. ጀላሉዲን አስ-ሲዩጢይ (911 ሒጅ.) በሱረቱል በቀራህ ቁ. 255 ላይ ያለውን የአየተል ኩርሲይን አንቀጽ ሲያብራሩ የ “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ”ን ትርጉም በተመሳሳይ መልኩ ተርጉመውታል፡፤ (ተፍሲሩል ጀላለይን፡ ሱረቱል በቀራህ 255)፡፡

በጥቅሉ በ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” ውስጥ ሁለት መሰረታዊ ማእዘናት አሉ፡፡ የመጀመሪያው፡- አምልኮን በጠቅላላ ለአንድ አላህ ማድረግና እሱን በብቸኝነት አምልኮ መገኘት ሲሆን፡ ሁለተኛው ደግሞ፡- ከአላህ ውጪ የሚመለኩ ነገሮችን ሁሉ ከማምለክ መራቅና በነሱም አምልኮ መካድ ማለት ነው፡፡ ይህ በዐረብኛው ‹‹ነፍይ›› እና ‹‹ኢሥባት›› ተብሎ ይጠራል፡፡

‹‹ነፍይ›› ማለት፡- ማራቅና ማግለል ውድቅ ማድረቅ ማለት ነው፡፡ አምልኮን ከአላህ ውጭ ካለ አካል ላይ በማራቅና በማግለል እንዲሁም ውድቅ በማድረግ የሚገኝ ሲሆን፡- ‹‹ኢሥባት›› ማለት፡- ማጽደቅና ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡ ማንኛውንም አይነት የአምልኮ ዘርፍ ለአንድ አላህ ብቻ በማድረግና እሱንም ብቻ በማምለክ የሚገኝ ማለት ነው፡፡ የ”ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” መልእክት እነዚህን ሁለት መሰረታዊ ማእዘናት እንደያዙ የሚያመላክቱ ቅዱስ ቁርኣናዊ አንቀጾችን እንመልከት፡-

” ﻟَﺎ ﺇِﻛْﺮَﺍﻩَ ﻓِﻲ ﺍﻟﺪِّﻳﻦِ ﻗَﺪْ ﺗَﺒَﻴَّﻦَ ﺍﻟﺮُّﺷْﺪُ ﻣِﻦَ ﺍﻟْﻐَﻲِّ ﻓَﻤَﻦْ ﻳَﻜْﻔُﺮْ ﺑِﺎﻟﻄَّﺎﻏُﻮﺕِ ﻭَﻳُﺆْﻣِﻦْ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻓَﻘَﺪِ ﺍﺳْﺘَﻤْﺴَﻚَ ﺑِﺎﻟْﻌُﺮْﻭَﺓِ ﺍﻟْﻮُﺛْﻘَﻰ ﻟَﺎ ﺍﻧْﻔِﺼَﺎﻡَ ﻟَﻬَﺎ ﻭَﺍﻟﻠَّﻪُ ﺳَﻤِﻴﻊٌ ﻋَﻠِﻴﻢٌ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺒﻘﺮﺓ 256
“በሃይማኖት ማስገደድ የለም፡፡ ቅኑ መንገድ ከጠማማው በእርግጥ ተገለጠ፡፡ በጣዖትም የሚክድና በአላህ የሚያምን ሰው ለርሷ መበጠስ የሌላትን ጠንካራ ዘለበት በእርግጥ ጨበጠ፡፡ አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 256)፡፡

በዚህ የቁርኣን አንቀጽ ስር፡ ትክክለኛውን የላ ኢላሀ ኢለሏህ ጠንካራ ዘለበት የጨበጠው፡ ሁለት ነገሮችን ያሟላ ሰው ብቻ እንደሆነ እንረዳልን፡፡ እነሱም፡-

– ‹‹በጣኦት የሚክድ›› ይህ ማለት ከአላህ ውጭ የሚመለኩ ነገራት በጠቅላላ የጣኦት አምልኮ መሆኑን በማመን ራስን ከጣኦት አምልኮ ማራቅና በጣኦትም መካድ ሲሆን፡
– ‹‹በአላህም የሚያምን›› ሲል ደግም፡ አምልኮን ለአንድ አላህ ብቻ የሚያደርግና እሱንም ብቻ የሚገዛ ማለት ነው፡፡

” ﻭَﺇِﻟَﻰ ﻋَﺎﺩٍ ﺃَﺧَﺎﻫُﻢْ ﻫُﻮﺩًﺍ ﻗَﺎﻝَ ﻳَﺎ ﻗَﻮْﻡِ ﺍﻋْﺒُﺪُﻭﺍ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻣَﺎ ﻟَﻜُﻢْ ﻣِﻦْ ﺇِﻟَﻪٍ ﻏَﻴْﺮُﻩُ ﺃَﻓَﻠَﺎ ﺗَﺘَّﻘُﻮﻥَ … ﻕَﺍﻟُﻮﺍ ﺃَﺟِﺌْﺘَﻨَﺎ ﻟِﻨَﻌْﺒُﺪَ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻭَﺣْﺪَﻩُ ﻭَﻧَﺬَﺭَ ﻣَﺎ ﻛَﺎﻥَ ﻳَﻌْﺒُﺪُ ﺁﺑَﺎﺅُﻧَﺎ ﻓَﺄْﺗِﻨَﺎ ﺑِﻤَﺎ ﺗَﻌِﺪُﻧَﺎ ﺇِﻥْ ﻛُﻨْﺖَ ﻣِﻦَ ﺍﻟﺼَّﺎﺩِﻗِﻴﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻷﻋﺮﺍﻑ 65-70
“ወደ ዓድም ወንድማቸውን ሁድን ላክን፤፦ ወገኖቼ ሆይ! አላህን ተገዙ፤ ከርሱ ሌላ ምንም አምላክ የላችሁም፤ (የአላህን ቅጣት) አትፈሩምን? አላቸ…አላህን አንድ ብቻውን እንድንገዛ አባቶቻችንም ይግገዙት የነበረውን (አማልክት) እንድንተው መጣህብን? ከውነተኞች ከሆንክ የምታስፈራራብንን (ቅጣት) አምጣብን አሉ።” (ሱረቱል አዕራፍ 65.70)፡፡

ሁድ (ዐለይሂ ሰላም) ወገኖቹን ወደ ላ ኢላሀ ኢልለሏህ ጥሪ አደረገላቸው፡፡ እነሱም ከሱ ጥሪ የተረዱት ሁለት ነገር ነበር፡፡ የመጀመሪያው፡- ‹‹አላህን አንድ ብቻውን እንድንገዛ›› የሚለው ቃላቸው፡ አምልኮን ለአላህ አሳልፎ መስጠት እንዳለባቸው ሲሆን፡- ሁለተኛው ደግሞ፡- ‹‹አባቶቻችንም ይግገዙት የነበረውን (አማልክት) እንድንተው መጣህብን?›› የሚለው ደግሞ፡ ከአላህ ውጪ የሚመለኩ የሃሰት አማልክቶችን መተውና መራቅ እንዳለባቸው መሆኑን ነው፡፡

” ﻭَﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﺍﺟْﺘَﻨَﺒُﻮﺍ ﺍﻟﻄَّﺎﻏُﻮﺕَ ﺃَﻥْ ﻳَﻌْﺒُﺪُﻭﻫَﺎ ﻭَﺃَﻧَﺎﺑُﻮﺍ ﺇِﻟَﻰ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻟَﻬُﻢُ ﺍﻟْﺒُﺸْﺮَﻯ ﻓَﺒَﺸِّﺮْ ﻋِﺒَﺎﺩِ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺰﻣﺮ 17
“እነዚያም ጣዖታትን የሚግገዟት ከመሆን የራቁ ወደ አላህም የዞሩ ለነርሱ ብስራት አላቸው፤ ስለዚህ ባሮቼን አብስር።” (ሱረቱ-ዙመር 17)፡፡

በዚህም አንቀጽ መሰረት፡ ከጌታችን የሆነውን መልካም ብስራት ማግኘት የምንችለው፡- በጣኦታት ስንክድና በአላህ ስናምን የሆነ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ የአላህ መልክተኞች በጠቅላላ ወደ ህዝቦቻቸው ሲላኩ ስተማሩትም፡ አንድ አላህን በብቸኝነት አምልኩ የሚለውንና ከአላህ ውጭ ያሉ ነገራትን ማምለክ ጣኦት ነውና፡ ጣኦታትን ከማምለክ ተቆጠቡ በማለት ነው፡-

” ﻭَﻟَﻘَﺪْ ﺑَﻌَﺜْﻨَﺎ ﻓِﻲ ﻛُﻞِّ ﺃُﻣَّﺔٍ ﺭَﺳُﻮﻟًﺎ ﺃَﻥِ ﺍﻋْﺒُﺪُﻭﺍ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻭَﺍﺟْﺘَﻨِﺒُﻮﺍ ﺍﻟﻄَّﺎﻏُﻮﺕَ ﻓَﻤِﻨْﻬُﻢْ ﻣَﻦْ ﻫَﺪَﻯ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻭَﻣِﻨْﻬُﻢْ ﻣَﻦْ ﺣَﻘَّﺖْ ﻋَﻠَﻴْﻪِ ﺍﻟﻀَّﻠَﺎﻟَﺔُ ﻓَﺴِﻴﺮُﻭﺍ ﻓِﻲ ﺍﻟْﺄَﺭْﺽِ ﻓَﺎﻧْﻈُﺮُﻭﺍ ﻛَﻴْﻒَ ﻛَﺎﻥَ ﻋَﺎﻗِﺒَﺔُ ﺍﻟْﻤُﻜَﺬِّﺑِﻴﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻨﺤﻞ 36
“በየሕዝቡም ሁሉ አውስጥ አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ፤ በማለት መልክተኛን በእርግጥ ልከናል፤ ከነሱም ውስጥ አላህ ያቀናው ሰው አልለ፤ ከነሱም ውስጥ አላህ በርሱ ላይ ጥመት የተረጋገጠበት ሰው አለ፤ በምድርም ላይ ኺዱ፤ የአስተባባዮችም መጨረሻ እንዴት እንደ ነበረ ተመልከቱ።” (ሱረቱ-ነሕል 36)፡፡

አላህ ሆይ! አንተ ብቻህን እውነተኛ አምላክ ነህ! ከአንተ ውጪ ሊመለክ የሚገባው ሌላ አምላክ የለም! እኛም አንተን ብቻ አምልከው ባንተ ሳያጋሩ ሙስሊም ሆነው ከሚሞቱ ባሮችህ አድርገን፡፡

Shortlink http://q.gs/Ey5xM