የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” 19 በኡስታዝ አቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
419 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
7. አፍራሽ ተግባራት፡-
2. ኩፍር (ክህደት)፡-
ሰሞኑን በተከታታይ ትምህርታችን የ‹‹ላ ኢላሀ ኢለሏህ››ን እምነት አፍራሽ ከሆኑት ውስጥ አንዱ የሆነውን ሺርክን ምንነቱን ስንመለከት ቆይተናል አልሐምዱ ሊላህ፡፡ በውስጡም ስለ ትርጉሙና ስለ አይነቶቹ መጠነኛ ዳሰሳ አድርገናል፡፡
ለዛሬ ደግሞ የምንመለከተው ሌላው የ‹‹ላ ኢላሀ ኢለሏህ››ን እምነት ከሚያፈርሱት ውስጥ አንዱ የሆነውን የኩፍር ተግባር ነው፡፡ በ‹‹ኩፍር›› እና በ‹‹ሺርክ›› መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ፡ ቅድሚያ የ‹‹ኩፍር››ን ምንነትና ትርጉሙን በመጠኑ እንየው፡-
‹‹ኩፍር›› የሚለው ቃል ቋንቋዊ ፍቺው፡- አንድን ነገር መደበቅና መሸሸግ ማለት ነው፡፡ አንድን ነገር የደበቀና የሸሸገ ሰው ካፊር ብለህ በቋንቋ ህግ ልትጠራው ትችላለህ፡፡ ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-
” ﺍﻋْﻠَﻤُﻮﺍ ﺃَﻧَّﻤَﺎ ﺍﻟْﺤَﻴَﺎﺓُ ﺍﻟﺪُّﻧْﻴَﺎ ﻟَﻌِﺐٌ ﻭَﻟَﻬْﻮٌ ﻭَﺯِﻳﻨَﺔٌ ﻭَﺗَﻔَﺎﺧُﺮٌ ﺑَﻴْﻨَﻜُﻢْ ﻭَﺗَﻜَﺎﺛُﺮٌ ﻓِﻲ ﺍﻟْﺄَﻣْﻮَﺍﻝِ ﻭَﺍﻟْﺄَﻭْﻟَﺎﺩِ ﻛَﻤَﺜَﻞِ ﻏَﻴْﺚٍ ﺃَﻋْﺠَﺐَ ﺍﻟْﻜُﻔَّﺎﺭَ ﻧَﺒَﺎﺗُﻪُ ﺛُﻢَّ ﻳَﻬِﻴﺞُ ﻓَﺘَﺮَﺍﻩُ ﻣُﺼْﻔَﺮًّﺍ ﺛُﻢَّ ﻳَﻜُﻮﻥُ ﺣُﻄَﺎﻣًﺎ ﻭَﻓِﻲ ﺍﻟْﺂﺧِﺮَﺓِ ﻋَﺬَﺍﺏٌ ﺷَﺪِﻳﺪٌ ﻭَﻣَﻐْﻔِﺮَﺓٌ ﻣِﻦَ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻭَﺭِﺿْﻮَﺍﻥٌ ﻭَﻣَﺎ ﺍﻟْﺤَﻴَﺎﺓُ ﺍﻟﺪُّﻧْﻴَﺎ ﺇِﻟَّﺎ ﻣَﺘَﺎﻉُ ﺍﻟْﻐُﺮُﻭﺭِ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺤﺪﻳﺪ 20
“ቅርቢቱ የሕይወት ጨዋታና ዛዛታ፣ ማጌጫም፣ በመካከላችሁም መፎካከሪያ በገንዘቦችና በልጆችም መፎካከሪያ በገንዘቦችና በልጆችም ብዛት መበላለጫ ብቻ መሆንዋን ዕወቁ፤ (እርሷ) በቃዩ ገበሬዎችን እንደሚያስደስት ዝናም ከዚያም በቃዩ እንደሚደርቅናም ገርጥቶ እንደምታየው፣ ከዚያም የተሰባበረ እንደሚሆን ብጤ ናት፤ በመጨረሻዪቱም ዓለም ብርቱ ቅጣት ከአላህም ምሕረትና ውዴታ አልለ፤ የቅርቢቱም ሕይወት የመታለያ ጥቅም እንጅ ሌላ አይደለችም።” (ሱረቱል ሐዲድ 20)፡፡
በዚህ አንቀጽ ላይ ‹‹ገበሬዎች›› ለሚለው የአማርኛ ትርጉም በዐረብኛው የተቀመጠው ቃል ‹‹ኩፋር›› የሚል ነው፡፡ ገበሬ ‹‹ካፊር›› የሚል ስም የተሰጠው፡ ዘሮቹን ከአፈር በታች በመዝራት በአፈሩ ስለሚደብቃቸው ነው፡፡
ሃይማኖታዊ ፍቺው ደግሞ፡- በእምነት የካደ፡ ያስተባበለና ከመቀበል የኮራ ማለት ነው፡፡ በአላህ መካድ ብቻ ሳይሆን፡ በማንኛውም የእምነት ዘርፎች ማመን ሲገባው፡ ካላመነና ከካደ ‹‹ካፊር›› ሆነ ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ፡- ሙስሊም ያልሆነ በጠቅላላ ማለት ነው፡፡ የኢስላምን ሃይማኖት የማይከተልና ሙስሊም ያልሆነ በጠቅላላ ካፊር ተብሎ ይጠራል፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ከሃይማኖት አንጻር በሁለት ነው የሚከፈሉት፡፡
1ኛ፡- በአላህና በመልክተኛው ያመኑት፡- እነዚህ ሙስሊሞች፣ ሙእሚኖች ሲባሉ፡-
2ኛ፡- ከዚህ ውጭ ያሉት በጠቅላላ፡- ሌላ ሃይማኖት ኖራቸውም አልኖራቸውም ካፊር ተብለው ይጠራሉ፡፡ ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-
” ﻫُﻮَ ﺍﻟَّﺬِﻱ ﺧَﻠَﻘَﻜُﻢْ ﻓَﻤِﻨْﻜُﻢْ ﻛَﺎﻓِﺮٌ ﻭَﻣِﻨْﻜُﻢْ ﻣُﺆْﻣِﻦٌ ﻭَﺍﻟﻠَّﻪُ ﺑِﻤَﺎ ﺗَﻌْﻤَﻠُﻮﻥَ ﺑَﺼِﻴﺮٌ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺘﻐﺎﺑﻦ 2
“እርሱ ያ የፈጠራችሁ ነው፤ ከናንተም ከሐዲ አለ፤ ከናንተም አማኝ አለ፡፡ አላህም በምትሠሩት ሁሉ ተመልካች ነው።” (ሱረቱ-ተጋቡን 2)፡፡
የኩፍርን ትርጓሜ በዚህ መልኩ ከተረዳን፡ አሁን በ‹‹ሺርክ›› እና በ‹‹ኩፍር›› መካከል›› ያለውን ልዩነት እንመለከታለን፡፡ ‹‹ኩፍር›› እና ‹‹ሺርክ›› ሁለቱም ባለቤቱን ከኢስላም አጥር የሚያስወጡ፡ ስራን በጠቅላላ የሚያበላሹ፡ ሰውየው ያለ ተውበት ከሞተም ለዘላለም ክስረት የሚዳርጉ የኃጢአት ሁሉ ቁንጮ ስለሆኑ፡ ከሑክም (ከሃይማኖታዊ ብይን) አንጻር ሁለቱም አንድ ናቸው፡፡ ምክንያቱም፡- ሙሽሪክ ሆኖ ሙስሊም የሚባል ሰው እንደሌለው ሁሉ፡ ካፊር ሆኖም ሙስሊም የሚባልም የለም፡፡ ሁለቱም ድርጊታቸው ባለቤቱን ከኢስላም አጥር ያስወጣልና፡፡ ከትርጉማቸው አንጻርና ከሚከሰቱበት ሁኔታ አንጻር ግን በሁለቱ መሀል ልዩነቶች እንዳሉ መረዳት ይቻላል፡፡ እሱም፡-
– ‹‹ሺርክ›› የሚባለው፡- በአላህ ማንነት እና መብት ላይ ተጋሪን የማበጀት ስራ ሲሆን፡ ‹‹ኩፍር›› የሚባለው ደግሞ፡- በእምነት ጉዳዮች ላይ የሚፈጸም ክህደትና እምቢተኝነት ማለት ነው፡፡
– ‹‹ሺርክ›› የሚከሰተው በአላህ ላይ ባላንጣን ያበጀህ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ከሱ ውጪ ያለን አካል መገዛት፣ ለፍጡሩ የአምላካዊ ባህሪን ማላበስ… ላይ ሲሆን፡ ‹‹ኩፍር›› ግን የሚከሰተው በየትኛውም የእምነት ጉዳዮች ላይ ያላመነ፡ የኮራና ያስተባበለን ሁሉ ነው፡፡ ከሞት በኋላ ህይወት (ቂያማህ) መኖሩን አላምንም ያለ ሰው፡ ካፊር ይባላል እንጂ ሙሽሪክ አትለውም፡፡ በፈጣሪ መኖር አላምንም ያለ አንድ ፈላስፋ ካፊር ይባላል እንጂ ሙሽሪክ አትለውም፡፡ በነቢዩ ሙሐመድ ነቢይነት ያላመነ ሰው ካፊር ተብሎ ይጠራል እንጂ ሙሽሪክ አይባልም፡፡ በአላህ ላይ ፍጡርን ያጋራ ሰው ግን ሙሽሪክም ካፊርም ተብሎ ይጠራል፡፡ ዒሳ ጌታ ነው ብሎ በአላህ ጌትነት ላይ ሌላ ጌታን ያጋራ ሰው ሙሽሪክም ካፊርም ይባላል፡፡
ከዚህ ትርጓሜ በመነሳት በሁለቱ ዙሪያ ያለውን ልዩነት ቀለል ባለ ቋንቋ እንዲህ ብለን ልንገልጸው እንችላለን፡- ‹‹ፈኩልሉ ሙሽሪኪን ካፊር፣ ወለይሰ ኩልሉ ካፊሪን ሙሽሪክ›› (ሁሉም ሙሽሪኮች ካፊሮች ሲሆኑ ሁሉንም ካፊሮች ግን ሙሽሪክ አይደሉም) የሚል ነው፡፡ ለምን? ምክንያቱም፡- ድርጊታቸው በኩፍር ላይ ብቻ የተገደበ፡ በአላህ ላይ ሌላን አካል ያላጋሩ ሊኖሩ ስለሚችሉ፡፡ ለምሳሌ፡-
ሀ. ኢብሊስ፡- ኢብሊስ በጌታችን ቃል ውስጥ ውስጥ ‹‹ካፊር›› ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ምክንያቱም የጌታውን ትእዛዝ በትእቢትና በኩራት ባለመፈጸሙ፡፡ ነገር ግን ‹‹ሙሽሪክ›› አልተባለም፡፡ እሱ በአላህ ላይ በማጋራት የሚገዛውና የሚያመልከው ሌላ አካል የለምና፡፡ ለ. እምነት አልባዎች፡- ከስሜት ህዋሳት ውጭ በሆኑ ነገሮች ላይ ማመን አንችልም በማለት፡ በአይን የማይታዩትን ( አላህ፣ ጀነት፣ ጀሀነም፣ መላኢካህ…) አናምንባቸውም ያሉ ፈላስፋዎች፡ በኢስላም ቋንቋ ካፊር ይባላሉ፡፡ በእምነት በመካዳቸው ሰበብ፡፡ ሙሽሪክ ግን ለማለት በማን ላይ ማንን አጋርተው? የሚል ጥያቄ መነሳቱ ግድ ነውና፡፡ ታዲያ በዛው መልኩ፡- ካፊር ሆነው ሙሽሪክ ያልሆኑ አሉ ካልን፡ ለምን ሙሽሪክ ሆነው ካፊር ደግሞ ያልሆኑ አሉ ለማለት ምን ይከለክለናል? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ መልሱም፡- ካፊር ማለት፡- በእምነት የካደ፡ በትእቢትና በኩራት የታዘዘውን ያልተቀበለ ነው በሚለው ከተስማማን መልሱን ለማግኘት ቀላል ይሆናል፡፡ ታዲያ አንድ ሰው በአላህ ላይ በማጋራት ሙሽሪክ ሆነ ሲባል፡ ይህ ሰው የአላህን ግላዊ መብት ካደ ማለት አይደለም እንዴ? አላህን በብቸኝነት መገዛት እኮ፡ ዒባዳህ የሱ ግላዊ መብት መሆኑን ማመን ማለት አይደል እንዴ? ታዲያ ይሄን መብት ለፍጡር አሳልፎ ሲሰጥ ሰውየው ማሻረክ ብቻ ሳይሆን የአላህ ግላዊ መብት በሆነውም ነገር ካደ ማለት እኮ ነው፡፡ ስለዚህ ሙሽሪክ ሁሉ ካፊር ሲባል፡ ካፊር ሁሉ ሙሽሪክ አይባልም፡፡ ወላሁ አእለም፡፡
ለዛሬ ስለ ኩፍር ጥቅላዊ የቃላት ፍቺውን በመጠኑ ከተረዳን፡ በቀጣዩ ደግሞ አላህ ፈቃዱ ከሆነ፡ ወደ አይነቶቹ በመግባት በዝርዝር እንመለከተዋለን፡፡ ኢንሻአላህ፡፡