የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” 17 በኡስታዝ አቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
404 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
7. አፍራሽ ተግባራት፡-
1. ሺርክ (ማጋራት)
ለ. ትንሹ ሺርክ፡-
4. በገድ ማመን
‹‹አት-ተጠዩር››፡- በገድ ማመን ማለት፡- በምናየው ወይም በምንሰማው ነገር ላይ ተመርኩዘን፡ በቃ ሊቀናኝ ነው ወይም ሊከፋኝ ነው የሚል አስተሳሰብና ድምዳሜ ላይ መድረስ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- አሜሪካኖች 13 ቁጥርን አይወዱትም፡፡ ከመቶ አመታት በፊት የተከሰተ ክስተትን በማንሳት ዛሬም በቀኑ ላይ መጥፎ ጥርጣሬ አላቸው፡፡ ፎቆቻቸውን ስትቆጥሩ 12 ይልና 14 ነው ቀጣዩ፡፡ 13ትን ይዘሉታል፡፡ 13 ቁጥር ያለበት ቤት እንኳ ገዢ የለውም፡፡ ወደ ሆቴል ስትሄዱ 13 ቁጥር ሆቴል የለም፡፡ እስኪ ቆም ብላችሁ አስቡ፡፡ ቁጥር እና ቀን ሰውን ምን ማድረግ ይችላሉ? ይሄ ሁሉ በገድ የማመን ውጤት ነው፡፡
ጥንት ዐረቦች ወደ ሌላ ሀገር ለስራ ለመውጣት ካሰቡ አንዲት በራሪ ላይ ድንጋይ ይወረውራሉ፡፡ ያቺ ወፍ ወደ ቀኝ ተነስታ ከበረረች ይቀናኛል በማለት ጉዞውን ይቀጥላሉ፡፡ ወደ ግራ ከበረረች ደግሞ ዛሬ ዕድሌ መጥፎ ነው አይቀናኝም በማለት ከጉዞ ይመለሳሉ፡፡ ይሄ ሁሉ የነገሮችን ሰበብ ወደ ገድ ማስጠጋት ነው፡፡ ይህ የተሳሳተ እምነት ነው፡፡ የኛ ገዳችን አላህ ዘንድ እንጂ ማንም ጋር አይደለም፡፡ ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡-
” ﻓَﺈِﺫَﺍ ﺟَﺎﺀَﺗْﻬُﻢُ ﺍﻟْﺤَﺴَﻨَﺔُ ﻗَﺎﻟُﻮﺍ ﻟَﻨَﺎ ﻫَﺬِﻩِ ﻭَﺇِﻥْ ﺗُﺼِﺒْﻬُﻢْ ﺳَﻴِّﺌَﺔٌ ﻳَﻄَّﻴَّﺮُﻭﺍ ﺑِﻤُﻮﺳَﻰ ﻭَﻣَﻦْ ﻣَﻌَﻪُ ﺃَﻟَﺎ ﺇِﻧَّﻤَﺎ ﻃَﺎﺋِﺮُﻫُﻢْ ﻋِﻨْﺪَ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻭَﻟَﻜِﻦَّ ﺃَﻛْﺜَﺮَﻫُﻢْ ﻟَﺎ ﻳَﻌْﻠَﻤُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻷﻋﺮﺍﻑ 131
“ደጊቱም ነገር (ምቾት) በመጣላችሁ ጊዜ ይህች ለኛ (ተገቢ) ናት፣ ይላሉ፤ ክፋትም ብታገኛቸው በሙሳና አብረውት ባሉት ገደቢስነት ያመካኛሉ፤ ንቁ፤ ገደቢስነታቸው አላህ ዘንድ ብቻ ነው፤ ግን አብዛኛዎቻቸው አያውቁም።” (ሱረቱል አዕራፍ 131)፡፡
ይህ አንቀጽ የሚነግረን፡- የፊርዐውን ህዝቦች የኑሮ ውድነት፡ ድርቅና ችግር በሚገጥማቸው ጊዜ፡- ይሄ ሁሉ በሙሳና በሀሩን ሰበብ የመጣብን በማለት እንደሚናገሩና፡ አላህም፡- ነገሩ እነሱ እንዳሉት ሳይሆን ቀድሞ በተወሰነባቸው የቀዷ ወል-ቀደር ውጤት መሆኑን፡ ለዚያም ምክንያቱ የነሱ ክህደትና አመጽ መሆኑን ያብራራል፡፡ ሆኖም ግን አብዝኃኛዎች ሰዎች አያውቁም ይለናል፡፡
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ባስተላለፈው ሐዲሥ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “በራሱ ፈቃድ የሚተላለፍ በሽታ፣ በገድ ማመን፣ በቡማ ማመን፣ ሰፈር የሚባል ነገር የለም” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
የአላህ መልክተኛ(ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በዚህ ንግግራቸው አራት ቁም ነገሮችን አስተምረውናል፡፡ እነሱም፡-
ሀ. ዐድወ፡- በሽታ በአላህ ፈቃድና ይሁንታ ካልሆነ በስተቀር ከአንድ ህመምተኛ ላይ ተነስቶ ወደ ሌላ ሰው በገዛ ፈቃዱ ሊዛመድ አይችልም፡፡ ከቀዷ ወል-ቀደር ውጪ ሊሆን የሚችል ነገር የለምና፡፡
ለ. ገድ፡- በምንሰማውና በምናየው ነገር ላይ ብቻ በመመርኮዝ፡- በቃ ዛሬ ገዴ ተስተካክሏል ወይንም ዛሬ ላይቀናኝ ነው የሚል ዕምነት ከንቱ መሆኑን፡፡
ሐ. ሀምማህ፡- ቡማህ በመባል የምትታወቅ አንዲት በራሪ አለች፡፡ ካረፈችበት ስፍራ ላይ ወደሷ ድንጋይ በመወርወር የምትበርበትን አቅጣጫ በማየት የሚደርሰንን ወይም የሚደርስብንን ዕድል ለማወቅ መሞከር የተሳሳተ አመለካከት መሆኑን፡፡
መ. ሰፈር፡- ለዚህ ቃል ከተሰጡት ትርጓሜዎች አንዱ፡ በዐረብኛ ሁለተኛውን ወር ነው፡፡ እናም ቅድመ ጃሂሊያ በዚህ ወር ገድ በማመናቸው ሰበብ ጋብቻን እንኳ አይፈጽሙም ነበር፡፡ ልክ እንደ ሃገራችን ግንቦት ወር ማለት ነው፡፡ ይህ ግን ከንቱና የተወገዘ አስተሳሰብ ነው፡፡
ከኢብኑ መስዑድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) በተላለፈው ሐዲሥ ላይ ደግሞ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “በገድ ማመን ሺርክ ነው፡፡ በገድ ማመን ሺርክ ነው፡፡ ከዛም ኢብኑ መስዑድ፡- ከኛ ውስጥ የዚህ አስተሳሰብ በመጠኑም ቢሆን ያለበት እንጂ ማንም የለም፡፡ ግን አላህ በተወኩል ሰበብ ያስወግደዋል አሉ፡፡” (አቡ ዳዉድና ቲርሚዚይ)፡፡
ዑርወት ኢብኑ-ዓሚር (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ አለ፡- “የአላህ መልክተኛ ዘንድ ስለ ገድ ተወራ፡፡ እሳቸውም፡- የተሻለው መልካም ንግግር ነው፡፡ ገድ ሙስሊምን ከሃሳቡ አትመልሰውምና፡፡ ከናንተ አንዳችሁ የሚጠላውን ነገር ካየ፡- አላህ ሆይ! ጥሩ ነገርን አንተ እንጂ ማንም ሊያመጣው አይችልም፡፡ መጥፎ ነገርንም ካንተ ውጪ ማንም ሊመልሰው አይችልም፡፡ ብልሐትና ችሎታም በአንተ ፈቃድ ካልሆነ በቀር የለም ይበል አሉ” (አቡ ዳዉድ 3719)፡፡
እስኪ የሃገራችንንና የቤታችንንም ተጨባጭ እናጢነው፡፡ የዚህ ሰለባ የሆነ ሰው ይጠፋልን? ጥቁር ድመት ካየሁ አይቀናኝም፣ ከመሰላል(ሊፍት) ስር አልወጣም አልወርድም… የመሳሰለ አስተሳሰብ ያለው? እስኪ እናንተስ ልታካፍሉንና ልትነግሩን ከፈቀዳችሁ የምታውቁትና ምን የገጠማችሁ ነገር አለ? አላህ ከዚህ ሁሉ ነጃ ይበለን፡፡