የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” 16 በኡስታዝ አቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
400 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
7. አፍራሽ ተግባራት፡-
1. ሺርክ (ማጋራት)
ለ. ትንሹ ሺርክ፡-
3. በአላህና በአንተ ሰበብ ማለት:-
ሌላው ትንሹ ሺርክ ውስጥ ከሚካተቱት ጉዳዮች አንዱ የ‹ማጣመር› ጉዳይ ነው፡፡ ማጣመር ማለት፡- ለአንድ ሰው፡ አንተን መልካም ነገር ለማግኘትህም ሆነ መጥፎ ነገርን ካንተ ለመከላከል ሰበብ በሆነው ነገር ላይ የአንተ አጸፋዊ ምላሽ፡- ‹‹አላህና አንተ ባትረዱኝ ኖሮ፣ አላህና አንተ ባትደርሱልኝ ኖሮ›› ማለትህ ነው፡፡ ይህ አባባል የሺርክ ቋንቋ ነው፡፡ የአላህን ሰጪነትና ከክፋት ተከላካይነት ከፍጡሩ ሰበብ መሆን ጋር ተያይዞ በ‹‹እና›› ሊገለጽ አይገባም፡፡ ማለት እንኳ ካለብህ፡- ‹‹አላህ ባይረዳኛ ከዛም አንተ ሰበብ ባትሆነኝ፣ አላህ ባይደርስልኝ ከዛም አንተ ባታግዘኝ ኖሮ›› ነው ማለት ያለብህ፡፡
‹‹እና›› በሚለውና ‹‹ከዛም›› በሚለው ቃላት መካከል ትልቅ የትርጉም ልዩነት አለ፡፡ እሱም፡- ‹‹እና›› የሚለው አያያዥ ቃል እኩልነትን እና አብሮነትን አመላካች ቃል ነው፡፡ ሙሐመድ እና አሕመድ መስጂድ ሄዱ ቢባል፡ የሚያስተላልፈው መልእክት፡ ሁለቱም ያለመቀዳደም በእኩልነት መስጂድ መሄዳቸውን ነው፡፡ ግን መሐመድ ከዚያም አሕመድ ወደ መስጂድ ሄዱ ቢባል፡ ወደ መስጂድ ቀዳሚው መሐመድ ተከታዩ ደግሞ አሕመድ መሆኑን እንረዳለን እንጂ አብረው እንደሄዱ አንረዳም፡፡
ወደ ነጥባችን ስንመለስ፡- በምድራዊ ህይወታችን ሳለን ለምናገኛቸው መልካም ነገሮች፣ ለምንከላከላቸው መጥፎ ሁኔታዎች ሰዎች ሰበብ ከመሆን የዘለለ ምንም ሚና የላቸውም፡፡ አድራጊና ፈጻሚው ግን ጌታችን አላህ ነው፡፡ አላህ እነዚያን ሰዎች ሰበብ አድርጎ አንተ እንድትጠቀም፡ ወይም ሊመጣብህ የነበረውን ክፉ ነገር ከላይህ ላይ እንዲከላከሉልህ ባይፈቅድና ባይወስን ኖሮ፡ ሰዎች በምን ኃይላቸው አንተን መርዳት ይችላሉ? እነሱም እኮ እንዳንተው የጌታቸው ጥገኛ፡ ራሳቸውን ያልቻሉ ድኃዎች ናቸው፡፡ ታዲያ አላህ ተውፊቁ ሆኖ ሰዎችን ሰበብ በማድረግ ላደረገልህ መልካም ነገር ‹‹አሽኩሩኩም ባዕደ ሹክሪላሂ ዐዝዘ ወጀል›› (ከጌታዬ ምስጋና ቀጥሎ እናንተን አመሰግናለሁ) ማለት ሲገባህ፡ ‹‹አላህ እና እናንተ ስለረዳችሁኝ›› በማለት እንዴት ከጌታህ ጋር በአንድ ታቆራኛቸዋለህ?
እናት አዲስ የተወለደ ህጻን ልጇን አቅፋ ወደ ጡቷ ማስጠጋቷና ለማጥባት መሞከሯ ሰበብ ነው፡፡ የህጻኑን አፍ በመክፈት፡ ጡቱን እንዲጠባ በማሳወቅ፡ የወተቱ ሪዝቅ በጉሮሮው በኩል ወደ መላ ሰውነቱ እንዲዳረስ መላክና ማቀናጀት ግን የአላህ ቸርነት ነው፡፡ ታዲያ ሰበብና ውጤት እንዴት በአንድ ቃል ውስጥ በ‹‹እና›› ይያያዛሉ? በመሆኑም በንግግራችን ላይ ጥንቃቄ እናድርግ፡፡ በአላህና ባንተ በረካ ከማለት እንቆጠብ፡፡ ማለት ካለብንም፡- በአላህ በረካ ከዛም ባንተ ሰበብ መሆን ተረዳሁኝ፣ ታገዝኩኝ…እንበል፡፡ ‹‹እና›› በሚለው አያያዥ ቃል የሰዎችን ሰበብ መሆን ብቻ፡ ውጤት ከሆነው የጌታችን ተውፊቅ ጋር በአንድ ቅርጫት አናስቀምጠው፡፡
ዐብዱላህ ኢብኒ ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንዲህ ይላል፡- “አንድ ሰው ወደ አላህ ነቢይ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ዘንድ በመምጣት በሆነ ነገር ላይ ካናገራቸው በኋላ፡ ‹‹ማሻአላሁ ወሺእተ›› (አላህና እርሶ የፈለጉት ነገር ሆነ) አላቸው፡፡ እሳቸውም፡- ለአላህ ብጤ አደርግኸኝን? ‹አላህ የሻው ብቻ ሆነ› በል! በማለት አስተካከሉት” (ነሳኢይ፡ ሱነኑል ኩብራ 10825)፡፡
የአዒሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) በእናቷ በኩል ወንድም የሆነው ጡፈይል (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- “(በህልሜ) ወደ አይሁዶች ጎራ ስመጣ አየሁኝ፡፡ ከዛም፡- እናንተ እኮ ዑዘይር የአላህ ልጅ ነው ባትሉ ኖሮ ጥሩ ህዝቦች ነበራችሁ አልኳቸው፡፡ እነሱም፡- እናንተም እኮ፡- ማሻአላሁ ወሻአ-ሙሐመድ (አላህና ሙሐመድ የፈለጉት ነገር ሆነ) ባትሉ ኖሮ ጥሩ ህዝቦች ነበራችሁ አሉኝ፡፡ ከዛም ወደ ክርስቲያን ጀመዓዎች መጣሁኝና፡- እናንተ እኮ አል-መሲሕ የአላህ ልጅ ነው ባትሉ ኖሮ ጥሩ ህዝቦች ነበራችሁ አልኳቸው፡፡ እነሱም፡- እናንተም እኮ፡- ማሻአላሁ ወሻአ-ሙሐመድ (አላህና ሙሐመድ የፈለጉት ነገር ሆነ) ባትሉ ኖሮ ጥሩ ህዝቦች ነበራችሁ አሉኝ፡፡ ባነጋሁም ጊዜ ህልሜን መንገር ለፈለኩት ሰው ተናገርኩኝ፡፡ ከዛም ወደ አላህ ነቢይ በመምጣት ነገርኳቸው፡፡ እሳቸውም፡- ለሌላ ሰው ነግረሀልን? አሉኝ፡፡ አዎን! አልኳቸው፡፡ እሳቸውም አላህን አመሰገኑ፣ እርሱንም አወደሱትና እንዲህ አሉ፡- ጡፈይል ህልምን አይቷል፡፡ ከመሀከላችሁም ለነገረው ሰው ነግሯል፡፡ …ከአሁን በኋላ አላህና ሙሐመድ የሻው ሆነ! አትበሉ፡፡ ነገር ግን አላህ ብቻ የሻው ሆነ በሉ በማለት አስተማሩ” (ኢብኑ ማጀህ)፡፡ ጌታ አላህም በቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-
” ﻭَﻣَﺎ ﺗَﺸَﺎﺀُﻭﻥَ ﺇِﻟَّﺎ ﺃَﻥْ ﻳَﺸَﺎﺀَ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﺭَﺏُّ ﺍﻟْﻌَﺎﻟَﻤِﻴﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺘﻜﻮﻳﺮ 29
“የዓለማት ጌታአላህ ካልሻም አትሹም።” (ሱረቱ-ተክዊር 29)፡፡