የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” 14 በ ኡስታዝ አቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
373 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
7. አፍራሽ ተግባራት፡-
1. ሺርክ (ማጋራት)
ሀ. ትልቁ ሺርክ፡-
5. ፍጡራንን እንደ አላህ መታዘዝ፡-
የአላህን ትእዛዝ በሚቃረን መልኩ ፍጡራንን መታዘዝ፡ እነሱን ማምለክ ማለት ስለሆነ ‹‹ሺርክ›› ነው፡፡ ይህም ማለት፡- አላህ የፈቀደውን ነገር እርም ነው ሲሉን፣ እሱ የከለከለውን ነገር የተፈቀደ ነው ሲሉን፡ አሚን ብለን ተስማምተን ከተቀበልን ተገዛናቸው ማለት ነው፡፡ አንድን ነገር ሐራምም ይሁን ሐላል ማለት የአላህ መብት ብቻ ነው፡፡ ህግን ማውጣትና መደንገግ ከአላህ የጌትነት መገለጫዎቹ አንዱ ነው፡፡ ስለሆነም ከአላህ ዲን ተቃራኒ የሆነን ነገር፡ ፍጡርን መታዘዝ የለም፡፡ ጌታ አላህ በቅዱስ ቃሉ እንዲህ ይላል፡-
” ﺍﺗَّﺨَﺬُﻭﺍ ﺃَﺣْﺒَﺎﺭَﻫُﻢْ ﻭَﺭُﻫْﺒَﺎﻧَﻬُﻢْ ﺃَﺭْﺑَﺎﺑًﺎ ﻣِﻦْ ﺩُﻭﻥِ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻭَﺍﻟْﻤَﺴِﻴﺢَ ﺍﺑْﻦَ ﻣَﺮْﻳَﻢَ ﻭَﻣَﺎ ﺃُﻣِﺮُﻭﺍ ﺇِﻟَّﺎ ﻟِﻴَﻌْﺒُﺪُﻭﺍ ﺇِﻟَﻬًﺎ ﻭَﺍﺣِﺪًﺍ ﻟَﺎ ﺇِﻟَﻪَ ﺇِﻟَّﺎ ﻫُﻮَ ﺳُﺒْﺤَﺎﻧَﻪُ ﻋَﻤَّﺎ ﻳُﺸْﺮِﻛُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺘﻮﺑﺔ 31
“ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለዉን አንድን አምላክ ሊገዙ እንጂ ያልታዘዙ ሲሆኑ ሊቃውንቶቻቸውንና መነኮሳታቸዉን የመርየምን ልጅ አልመሲሕንም ከአላህ ሌላ አማልክት አድርገው ያዙ፤ ከሚያጋሩት ሁሉ የጠራ ነው።” (ሱረቱ-ተውባህ 31)፡፡
ኢስላምን የተቀበለው ዐዲይ ኢብኑ አቢ-ሓቲም (ረዲየላሁ ዐንሁ) ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ሱረቱ-ተውባን ሲቀሩ አዳመጣቸው፡፡ እዚህኛው አንቀጽ ላይ ደርሰው ሲያነቡት፡ እሱም፡- ‹‹እኛ አልተገዛናቸውም እኮ!›› አላቸው፡፡ እሳቸውም፡- ‹‹አላህ ሐራም ያደረገባችሁን ነገር እነሱ ሲፈቅዱላችሁ የምትጠቀሙበት፣ አላህ ሐላል ያደረገላችሁን ነገር እነሱ እርም ሲያደርጉባችሁ ተከትላችሁ እርም ታደርጉ አልነበረምን?›› ሲሉት፡ እሱም፡- ‹‹እንዴታ! ይህማ አልለ›› አላቸው፡፡ እሳቸውም፡- ‹‹እነሱን መገዛት ማለት እኮ ይህ ነው!›› አሉት፡፡ (ቲርሚዚይና ሌሎችም)፡፡
” ﻭَﻟَﺎ ﺗَﺄْﻛُﻠُﻮﺍ ﻣِﻤَّﺎ ﻟَﻢْ ﻳُﺬْﻛَﺮِ ﺍﺳْﻢُ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻋَﻠَﻴْﻪِ ﻭَﺇِﻧَّﻪُ ﻟَﻔِﺴْﻖٌ ﻭَﺇِﻥَّ ﺍﻟﺸَّﻴَﺎﻃِﻴﻦَ ﻟَﻴُﻮﺣُﻮﻥَ ﺇِﻟَﻰ ﺃَﻭْﻟِﻴَﺎﺋِﻬِﻢْ ﻟِﻴُﺠَﺎﺩِﻟُﻮﻛُﻢْ ﻭَﺇِﻥْ ﺃَﻃَﻌْﺘُﻤُﻮﻫُﻢْ ﺇِﻧَّﻜُﻢْ ﻟَﻤُﺸْﺮِﻛُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻷﻧﻌﺎﻡ 121
“በእርሱም ላይ የአላህ ስም ካልተጠራበት ነገር አትብሉ፡፡ እርሱም በእርግጥ አመጽ ነው፡፡ ሰይጣናትም ወደ ወዳጆቻቸው (በክትን በመብላት) ይከራከሯችሁ ዘንድ ያሾከሹካሉ፡፡ ብትታዘዙዋቸውም እናንተ በእርግጥ አጋሪዎች ናችሁ፡፡” (ሱረቱል አንዓም 121)፡፡
በዚህ አንቀጽም መሰረት፡- አላህ ለኛ ሐላል ያደረገልን እርድ፡ በስሙ የታረደውን ብቻ ነው፡፡ ሌላውን (የአህሉል ኪታብ ሲቀር) መብላት አመጸኝነት ነው፡፡ ሰይጣናት ደግሞ በወዳጆቻቸው አማካኝነት አላህ የከለከለንን ምግቦች (ሱሙ ያልተወሱበትን እርድ) እንድንመገብ ይከራከሩናል፡፡ እሺ ብሎ በፈቃደኝነት የሚታዘዛቸውም ‹‹ሙሽሪክ›› በአላህ አጋሪ እንደሆነ ተገልጾአል፡፡
6. በመልካም ስራችን ዱንያን ብቻ መከጀል፡-
አንድ ሙስሊም በሚፈጽማቸው መልካም ተግባራቱ በመላ የአላህ ፊት ፈልጎና ተስፋ አድርጎ እንጂ ምድራዊ ጥቅምን ሽቶ መሆን የለበትም፡፡ በዚህ ፍላጎቱ ላይ የዱንያን ጌጦች ፈልጎ ከሆነ መልካም ተግባራትን የሚያደርገው፡ በጌታው ላይ የዱንያን ጌጦች አጋራ ‹‹ሙሽሪክ ሆነ›› ማለት ነው፡፡ በአኼራም እጣ ፈንታ የለውም፡-
” ﻣَﻦْ ﻛَﺎﻥَ ﻳُﺮِﻳﺪُ ﺍﻟْﺤَﻴَﺎﺓَ ﺍﻟﺪُّﻧْﻴَﺎ ﻭَﺯِﻳﻨَﺘَﻬَﺎ ﻧُﻮَﻑِّ ﺇِﻟَﻴْﻬِﻢْ ﺃَﻋْﻤَﺎﻟَﻬُﻢْ ﻓِﻴﻬَﺎ ﻭَﻫُﻢْ ﻓِﻴﻬَﺎ ﻟَﺎ ﻳُﺒْﺨَﺴُﻮﻥَ * ﺃُﻭﻟَﺌِﻚَ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﻟَﻴْﺲَ ﻟَﻬُﻢْ ﻓِﻲ ﺍﻟْﺂﺧِﺮَﺓِ ﺇِﻟَّﺎ ﺍﻟﻨَّﺎﺭُ ﻭَﺣَﺒِﻂَ ﻣَﺎ ﺻَﻨَﻌُﻮﺍ ﻓِﻴﻬَﺎ ﻭَﺑَﺎﻃِﻞٌ ﻣَﺎ ﻛَﺎﻧُﻮﺍ ﻳَﻌْﻤَﻠُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﻫﻮﺩ 15-16
“ቅርቢቱን ሕይወትና ጌጧን የሚሹ የሆኑትን ሰዎች ሥራዎቻቸውን (ምንዳዋን) በርሷ ውስጥ ወደነሱ እንሞላላቸዋለን፤ እነሱም በርሷ ውስጥ ምንም አይጎደልባቸውም። እነዚያ እነርሱ በመጨረሻይቱ ዓለም ለነርሱ ከእሳት በቀር የሌላቸው ናቸው፤ የሠሩትም ሥራ በርሷ ውስጥ ተበላሸ፤ (በቅርቢቱ ዓለም) ይሠሩት የነበሩትም በጎ ሥራ ብልሹ ነው።” (ሱረቱ ሁድ 15-16)፡፡
በአላህ ፈቃድ እስካሁን በትልቁ ሺርክ ዙሪያ ስድስት ነጥቦችን አንስተን ተመልክተናል፡፡ በቀጣዩ ደግሞ በትንሹ ሺርክ ዙሪያ የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡ ኢንሻአላህ።