የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” 12 በኡስታዝ አቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
379 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
7. አፍራሽ ተግባራት፡-
1. ሺርክ (ማጋራት)
ሀ. ትልቁ ሺርክ፡-
3. ተወኩል “በፍጡር መመካት”፡-
ተወኩል ማለት ቀጥታ ትርጉሙ፡- መመካት፣መጠጋት ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት፡- በዱንያም ሆነ በዲን ጉዳይ ላይ የሚጠቅመንን ነገር ለማግኝትና የሚጎዳንን ነገር ለማራቅ፣ ደካማነታችንን በመግለጽ ነገሩን ሊያሳካልን ወደሚችል ኃይል (አላህ) ልባችንን ማዞርና: በርሱ ላይ ተስፋ በማድረግ መመካትና፡ እሱም በሚረዳንና በሚወስንልን ነገር ወዶ መቀበል ማለት ነው፡፡
‹‹ተወኩል›› የልብ ስራ ከሆነ፡ ለማንም አሳልፎ መስጠት አይበቃም፡፡ በፍጡር ላይ መመካት አይቻልም፡፡ ፍጡር የአቅሙን ያህል እገዛ ሊጠየቅ ይችላል እንጂ በሱ ላይ ሊመኩበት አይገባም፡፡ ስለሆነም ‹በአላህና በአንተ ተመካሁ!› አይባልም፡፡ መመካት በአላህ ብቻ ነው፡፡ ልቡን ሙሉ በሙሉ በፍጡር ላይ ያሳካልኛል ብሎ ያንጠለጠለ ሰው በርግጥም አሻርኳል፡፡ አል-ኢማም ኢብኑል-ቀዪም (ረሒመሁላህ)፡- ተወኩል የዲን ግማሹ ሲሆን ኢናባህ (በተውበት ወደ አላህ መመለስ) ደግሞ የቀረው ግማሽ ይሆናል በማለት ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ አባባላቸውም ነቢዩላህ ሹዐይብ (ዐለይሂ-ሰላም) የተናገረውን ተከታዩን አንቀጽ ይጠቅሳሉ፡-
“ሕዝቦቼ ሆይ! ንገሩኝ፤ ከጌታዬ በሆነ አስረጅ ላይ ብሆንና ከርሱም የሆነን መልካም ሲሳይ ቢሰጠኝ፣ (በቅጥፈት ልቀላቅለው ይገባልን?) ከርሱ ወደ ከለልኳችሁም ነገር ልለያችሁ (እናንተን ከልክዬ እኔ ልፈጽመው) አልሻም፤ በተቻለኝ ያክል ማበጀትን እንጂ አልሻም፤ (ለደግ ሥራ) መገጠሜም በአላህ እንጂ በሌላ አይደለም፤ በርሱ ላይ ተመካሁ፤ ወደርሱም እመለሳለሁ፤ አላቸው።” (ሱረቱ ሁድ 88)፡፡
በአላህ ላይ በትክክል የሚመካ ሰው፡ አላህ ሲሳዩን ኃላፊነት ወስዶ እንደሚችለውና ሁሉንም ጉዳዮቹን ሊያሟላለት እንደሚችል ያውቃል፡፡ ያ በመሆኑም ሌሎች ነገሮች ላይ መደገፍን ትቶ ሰጪና ከልካይ፣ ጠቃሚና ጎጂ፣ለጋሽና ያዥ በሆነው አላህ ላይ ብቻ ይመካል፡፡ በአላህ ላይ መመካት ፍላጎታችን እንዲሳካ ሊያግዙን የሚችሉ የሆኑ ምክንያቶችን ከመጠቀም ጋር የሚጋጭ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ ይልቁኑ አብሮ የሚሄድና የሚዛመድ ህግ ነው፡፡ የሚጋጨው አጋዥ ነገሮችን ከምክኒያታዊነታቸው በዘለለ መልኩ ውጤትም ናቸው ብሎ ማመን ነው፡፡ የዱንያ ነገራት ምክንያት ሲሆኑ ውጤቱና ፈጻሚው ግን ጌታችን አላህ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ያለ አላህ ፈቃድ ምንም ነገር ሊሳካ አይችልምና፡፡ ሃሳቡ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆን አንድ ምሳሌ እንመልከት፡-
ከመኖሪያ ቤትህ 5 ኪሎ ሜትሮችን ያህል ርቆ የሚገኘው መስጂድ ለመሔድና ሶላትን በጀመዓ ለመስገድ የመኪናህን ሞተር አስነስተህ ከቤት ወጣህ፡፡ በቃ አሁን አንተ መስጂድ እንደምትደርስ እርግጠኛ ነህ ማለት ነው? በፍጹም! እንዴት በማለት የምትከራከር ከሆነ ቀጥሎ ያሉትን ጥያቄዎች በደንብ አስተውል፡-
1. ከቤትህ እስከ መስጂዱ የ10 ደቂቃ ጉዞ ይፈጃል ብለን ብንገምት፡ ቢያንስ አንተ መስጂዱ ለመድረስ የ10 ደቂቃ life time ሊኖርህ ግድ ነው፡፡ ታዲያ ይህን የ10 ደቂቃ እድሜ ማን ሊሰጥህ ይችላል? አላህ ያንተ እድሜ እዚህ ጋር ይብቃ ቢልህ እኮ ሄደህ ከመስገድ ይልቅ፡ ሞተህና ጀናዛ ሁነህ ታጥበህ ይሰገድብሃል ማለት ነው፡፡ ተግባባን ወንድም?
2. እንደው አላህ አይግደልህና አልሞትክም እንበል፡፡ ነገር ግን በዚህ 10 ደቂቃ ውስጥ አንተ መስጂድ ለመድረስ ቢያንስ ጤናማ መሆንህ ግድ ነው፡፡ ታዲያ አላህ ጤናህን ቢይዘውና የሰውነት ብልቶችህ ለመንቀሳቀስ አንታዘዝም! ቢሉህ እዛው መኪናህ ስር ከመቀመጥ ውጪ ምን ማድረግ ትችላለህ? እጅና እግሮችህን እንዲንቀሳቀሱ የሚያዘው የሰውነት ሴሎችህ ከሆኑ እነሱንስ የሚያንቀሳቅሳቸው አዛዣቸው ማን ይመስልሀል? አሁንስ የተሻለ ተግባባን ወንድም?
3. አሁንም አላህ ይጠብቅህና ሰውነትህም ጤነኛ ነው እንበል፡፡ ግን ወደ መስጂዱ ለመሔድ የተጠቀምክባቸው 10 ደቂቃዎች ውስጥ በመሬት ጀርባ ላይ ሁነህ እንጂ ራስህን ችለህ እንዳልነበር አትርሳ፡፡ ታዲያ አላህ መሬትን አመጸኛ አድርጓት በመሬት መንቀጥቀጥም ሆነ በእሳተ ጎመራ አንተን መሸከም በቃኝ አልፈልግህም ብላ አፏን ብትከፍት እንዴት ሆነህ ወደ መስጂዱ ትደርሳለህ? ከሷስ ወዴት ትሸሻለህ? አሁን በደንብ ተግባባን ወንድም?
4. በድጋሚ አላህ አያምጣብህና የተሸከመችህም መሬት ሰላም ነች እንበል፡፡ ታዲያ ወደ መስጂድ በምታደርገው ጉዞህ ላይ ካንተ አይነት ሌላ መኪና ከያዘ ሰው አደጋ ደርሶብህ ወይም አንተ ራስህ በሌላ መኪና ወይም በህይወት ላይ አደጋ አድርሰህ ከጉዳይህ እንደማትሰናከልስ ምን ዋስትና አለህ? አሁን የተማመንን ይመስለኛል፡፡
ስለዚህ የኛ ድርሻ ሰበቡን ማሟላትና እንዲሳካ ደግሞ በአላህ ላይ ተስፋ ማድረግ ነው፡፡ man proposes and ALLAH disposes (ሰው ያስባል አላህ ይፈጽማል) አይደል የሚባለው፡፡ አንድ ሙስሊም የአላህ ባሪያ አቅሙ የቻለውን ያህል ሰበቦችን እያሟላ የፍላጎቱን መሳካት ግን በአላህ ላይ አንጠልጥሎና ተስፋ አድርጎ ሊኖር ይገባል፡፡ በአላህ ላይ መመካት እንዳለብን ከሚናገሩ አንቀጾች ውስጥ ከፊሉን እነሆ፡-
” ﻭَﻗَﺎﻝَ ﻣُﻮﺳَﻰ ﻳَﺎ ﻗَﻮْﻡِ ﺇِﻥْ ﻛُﻨْﺘُﻢْ ﺁﻣَﻨْﺘُﻢْ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻓَﻌَﻠَﻴْﻪِ ﺗَﻮَﻛَّﻠُﻮﺍ ﺇِﻥْ ﻛُﻨْﺘُﻢْ ﻣُﺴْﻠِﻤِﻴﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﻳﻮﻧﺲ 84
“ሙሳም አለ፡- «ሕዝቦቼ ሆይ! በአላህ አምናችሁ እንደ ሆነ በርሱ ላይ ተጠጉ፡፡ ታዛዦች እንደ ሆናችሁ (በአላህ ላይ ትመካላችሁ)፡፡»” (ሱረቱ ዩኑስ 84)፡፡
” ﻭَﺍﺗَّﺒِﻊْ ﻣَﺎ ﻳُﻮﺣَﻰ ﺇِﻟَﻴْﻚَ ﻣِﻦْ ﺭَﺑِّﻚَ ﺇِﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻛَﺎﻥَ ﺑِﻤَﺎ ﺗَﻌْﻤَﻠُﻮﻥَ ﺧَﺒِﻴﺮًﺍ * ﻭَﺗَﻮَﻛَّﻞْ ﻋَﻠَﻰ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻭَﻛَﻔَﻰ ﺑِﺎﻟﻠَّﻪِ ﻭَﻛِﻴﻠًﺎ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻷﺣﺰﺍﺏ 2-3
“ከጌታህም ወደ አንተ የሚወርደውን ተከተል፤ አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነውና። በአላህም ላይ ተመካ፤ መመኪያም በአላህ በቃ።” (ሱረቱል አሕዛብ 2-3)፡፡
” ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻟَﺎ ﺇِﻟَﻪَ ﺇِﻟَّﺎ ﻫُﻮَ ﻭَﻋَﻠَﻰ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻓَﻠْﻴَﺘَﻮَﻛَّﻞِ ﺍﻟْﻤُﺆْﻣِﻨُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺘﻐﺎﺑﻦ 13
“አላህ ከርሱ በቀር አምላክ የለም፤ በአላህም ላይ አማኞቹ ይመኩ።” (ሱረቱ-ተጋቡን 13)፡፡ በአላህ ላይ መመካት የእውነተኛ ሙእሚኖች ባህሪ ነው፡-
” ﺇِﻧَّﻤَﺎ ﺍﻟْﻤُﺆْﻣِﻨُﻮﻥَ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﺇِﺫَﺍ ﺫُﻛِﺮَ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻭَﺟِﻠَﺖْ ﻗُﻠُﻮﺑُﻬُﻢْ ﻭَﺇِﺫَﺍ ﺗُﻠِﻴَﺖْ ﻋَﻠَﻴْﻬِﻢْ ﺁﻳَﺎﺗُﻪُ ﺯَﺍﺩَﺗْﻬُﻢْ ﺇِﻳﻤَﺎﻧًﺎ ﻭَﻋَﻠَﻰ ﺭَﺑِّﻬِﻢْ ﻳَﺘَﻮَﻛَّﻠُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻷﻧﻔﺎﻝ 2
“ፍጹም ምእምናን፣ እነዚያ አላህ በተወሳ ጊዜ ልቦቻቸው የሚፈሩት፤ በነሱም ላይ አንቀጾቻችን በተነበቡ ጊዜ እምነትን የሚጨምሩላቸው፣ በጌታቸው ላይ ብቻ የሚመኩት ናቸው።” (ሱረቱል አንፋል 2)፡፡
በአላህ ላይ በመመካት ነቢያት ለኛ ቀዳሚ አርአያዎቻችን ናቸው፡፡
” ﻗَﺎﻟَﺖْ ﻟَﻬُﻢْ ﺭُﺳُﻠُﻬُﻢْ ﺇِﻥْ ﻧَﺤْﻦُ ﺇِﻟَّﺎ ﺑَﺸَﺮٌ ﻣِﺜْﻠُﻜُﻢْ ﻭَﻟَﻜِﻦَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻳَﻤُﻦُّ ﻋَﻠَﻰ ﻣَﻦْ ﻳَﺸَﺎﺀُ ﻣِﻦْ ﻋِﺒَﺎﺩِﻩِ ﻭَﻣَﺎ ﻛَﺎﻥَ ﻟَﻨَﺎ ﺃَﻥْ ﻧَﺄْﺗِﻴَﻜُﻢْ ﺑِﺴُﻠْﻄَﺎﻥٍ ﺇِﻟَّﺎ ﺑِﺈِﺫْﻥِ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻭَﻋَﻠَﻰ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻓَﻠْﻴَﺘَﻮَﻛَّﻞِ ﺍﻟْﻤُﺆْﻣِﻨُﻮﻥَ * ﻭَﻣَﺎ ﻟَﻨَﺎ ﺃَﻟَّﺎ ﻧَﺘَﻮَﻛَّﻞَ ﻋَﻠَﻰ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻭَﻗَﺪْ ﻫَﺪَﺍﻧَﺎ ﺳُﺒُﻠَﻨَﺎ ﻭَﻟَﻨَﺼْﺒِﺮَﻥَّ ﻋَﻠَﻰ ﻣَﺎ ﺁﺫَﻳْﺘُﻤُﻮﻧَﺎ ﻭَﻋَﻠَﻰ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﻓَﻠْﻴَﺘَﻮَﻛَّﻞِ ﺍﻟْﻤُﺘَﻮَﻛِّﻠُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺇﺑﺮﺍﻫﻴﻢ 11-12
“መልክተኞቻቸው ለነርሱ አሉ፦ እኛ ብጤያችሁ ሰው እንጂ ሌላ አይደለንም፤ ግን አላህ ከባሮቹ በሚሻው ሰው ላይ ይለግሳል፤ እኛም በአላህ ላይ ፈቃድ እንጂ ልናመጣላችሁ አይገባንም፤ በአላህም ላይ ምእመናኖች ይጠጉ።መንገዳችንን በእርግጥ የመራን ሲሆን በአላህ ላይ የማንመካ ለኛ ምን አለን? በማሰቃየታችሁም ላይ በእርግጥ እንታገሣለን፤ በአላህም ላይ ተመኪዎች ሁሉ ይመኩ።” (ሱረቱ ኢብራሂም 11-12)፡፡
ከጌታ አላህ ስሞች መሐከል አንዱ “አል-ወኪል” የሚለው ነው፡፡ ትርጓሜውም፡- መጠጊያ፣ ዋቢ፣ መመኪያ ማለት ነው፡፡ የባርያዎቹን ሁኔታ ባማረ መልኩ ያበጃል፡፡ አንዳንዴ በህይወታችን ውስጥ ችግር ይገጥማል፡፡ ሲሳይ ይጎድላል፣ በትምሕርት መውደቅ አለ፣ በቤተሰቡ ውስጥ ከአላህ የራቁ ልጆች ይኖራሉ፣ በትዳር አለመስማማት ይከሰታል፡፡ ለነዚህና መሰል ችግሮች መፍትሔ የሚሰጠን፡ ስንቀርበው ይበልጥ የሚያስጠጋን መመኪያ ያስፈልገናል፡፡ አላህ በሰው ላይ አንድን በር ሲዘጋበት ሌሎች ብዙ በሮችን ይከፍትለታል፡፡ ይህቺ ዓለም ለጊዜው ብታጨልምብህ “አል-ወኪል” የሆነው አላህ ሌሎች የሚያስደስቱህ መንገዶችን ሊከፍትልህ እንደሆነ እወቅ፡፡ ስለሆነም አላህ ምንም ነገር ከልክሎህ አያውቅም ሌላ የተሻለ ሊሰጥህ ቢሆን እንጂ!
ﻭﻓﻲ ﺍﻟﺼَّﺤﻴﺢ : ﺃﻥَّ ﺭﺳﻮﻝ ﺍﻟﻠﻪ – ﺻﻠﻰ ﺍﻟﻠﻪ ﻋﻠﻴﻪ ﻭﺳﻠﻢ – ﻛﺎﻥ ﻳﻘﻮﻝ : )) ﺍﻟﻠﻬﻢ ﻟﻚ ﺃﺳﻠﻤْﺖ، ﻭﺑﻚ ﺁﻣﻨْﺖ، ﻭﻋﻠﻴﻚ ﺗﻮﻛﻠْﺖ، ﻭﺇﻟﻴﻚ ﺃﻧﺒْﺖ، ﻭﺑﻚ ﺧﺎﺻﻤْﺖ، ﺍﻟﻠﻬﻢ ﺇﻧِّﻲ ﺃﻋﻮﺫ ﺑﻌﺰﺗﻚ ﻻ ﺇﻟﻪ ﺇﻻ ﺃﻧﺖ ﺃﻥ ﺗﻀﻠﻨﻲ، ﺃﻧﺖ ﺍﻟﺤﻲ ﺍﻟﺬﻱ ﻻ ﻳﻤﻮﺕ، ﻭﺍﻹﻧﺲ ﻭﺍﻟﺠﻦ ﻳﻤﻮﺗﻮﻥ (( ؛ ﺭﻭﺍﻩ ﻣﺴﻠﻢ .
የአላህ መልክተኛ እንዲህ ይሉ ነበር፡- “አላህ ሆይ! ላንተ ታዘዝኩ፣ ባንተም አመንኩ፣ ባንተም ላይ ተመካሁ፣ ወደ-አንተም ተመለስኩ፣ ባንተም (ዲን) ተከራከርኩ፣ አላህ ሆይ! ካንተ በስተቀር ሌላ አምላክ የለምና እንዳታጠመኝ እኔ በእልቅናህ እጠበቃለሁ፣ አንተ ህያውና የማትሞት ነህ፣ ሰዎችና ጂኒዎች ይሞታል” (ሙስሊም)፡፡
ﻓﺎﻹﻣﺎﻡ ﺳﻌﻴﺪ ﺑﻦ ﺟﺒﻴﺮ ﻛﺎﻥ ﻳﺪﻋﻮ ﻓﻴﻘﻮﻝ : ” ﺍﻟﻠﻬﻢ ﺃﺳﺄﻟﻚ ﺻﺪﻕ ﺍﻟﺘﻮﻛﻞ ﻋﻠﻴﻚ، ﻭﺣﺴﻦ ﺍﻟﻈَّﻦ ﺑﻚ ” ، ﻭﻛﺎﻥ ﻳﻘﻮﻝ : ” ﺍﻟﺘﻮﻛُّﻞ ﻋﻠﻰ ﺍﻟﻠﻪ ﺟﻤﺎﻉ ﺍﻹﻳﻤﺎﻥ ” ؛ ” ﻧﺰﻫﺔ ﺍﻟﻔﻀﻼﺀ “.
ከሰለፍ ሊቃውንት ውስጥ አንዱ የነበሩት “ሰዒድ ኢብኑ ጁበይር” (ረሒመሁላህ) እንዲህ በማለት ዱዓ ያደርጉ ነበር፡- “አላህ ሆይ! ባንተ ላይ እውነተኛ የሆነ መመካትንና ጥሩ የሆነ ጥርጣሬን እለምንሀለሁ” እንዲሁም፡- “በአላህ ላይ መመካት ጠቅላይ እምነት ነው” ይሉ ነበር፡፡
በአላህ ላይ መመካት በተለይ ቀጥሎ ባሉት ሁኔታዎች ላይ በጣም ተወዳጅ ነው፡-
1. በጠላት ላይ ድልን መቀዳጀት ስንፈልግ፡- “አላህ ቢረዳችሁ ለእናንተ አሸናፊ የለም፡፡ ቢያዋርዳችሁም ያ ከርሱ(ማዋረድ) በኋላ የሚረዳችሁ ማነው? በአላህም ላይ ብቻ ምእምናን ይመኩ” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 160)፡፡
2. ጠላት ኃይሉን አሰባስቦ ሙስሊሙ ላይ ችግር ለመፍጠር ሲያስብ፡- “እነዚያ መቁሰል ካገኛቸዉ በኋላ ለአላህና ለመልክተኛዉ የታዘዙትን ከነሱ ለነዚያ በጐ ለሠሩትና ለተጠነቀቁት ታላቅ ምንዳ አላቸዉ። እነዚያ ሰዎች ለነርሱ ፡- ሰዎች ለናንተ (ጦርን) አከማችተዋልና ፍሩዋቸዉ ያሉዋቸዉና (ይህም) እምነትን የጨመረላቸዉ በቂያችንም አላህ ነዉ፥ ምን ያምርም መጠጊያ! ያሉ ናቸዉ።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 172-173)፡፡
3. ከሀዲያንን ወደ ኢስላም ጋብዘናቸው ማመናቸውን ተስፋ ስንቆርጥ፡- “ከሐዲዎችንና መናፍቃንንም አትታዘዛቸው፤ ማሰቃየታቸውንም (ለአላህ) ተው፤ በአላህም ላይ ተጠጋ፤ መጠጊያም በአላህ በቃ።” (ሱረቱል አሕዛብ 48)፡፡
4. ሰዎች ካንተ ችላ ብለው ከዞሩ፡- “ቢያፈገፍጉም አላህ በቂዬ ነው፤ ከርሱ ሌላ አምላክ የለም፤ በርሱ ላይ ተጠጋሁ፤ እርሱም የታላቁ ዐርሽ ጌታ ነው በላቸው።” (ሱረቱ-ተውባህ 129)፡፡
5. ጠላት ወደ እርቅ በተመለሰ ጊዜ፡- “ወደ ዕርቅም ቢያዘነብሉ ወደ እርሷ አዘንብል፤ በአላህም ላይ ተጠጋ፤ እነሆ እርሱ ሰሚ ዐዋቂ ነውና።” (ሱረቱል አንፋል 61)፡፡
6. ጠላት ሙስሊሙን ለማታለል ሲሞክር፡- “ሊያታልሉህም ቢፈልጉ በቂህ አላህ ነው፤ እርሱ ያ በርዳታውና በምመናን ያበረታህ ነው።” (ሱረቱል አንፋል 62)፡፡
7. መከራና ችግር ሲገጥም፡- “አላህ ለኛ የጻፈልን (ጥቅም) እንጂ ሌላ አይነካንም እርሱ ረዳታችን ነው በአላህ ላይም ምእምናን ይመኩ በላቸዉ።” (ሱረቱ-ተውባህ 51)፡፡ ዐብደላህ ኢብኑ ዐባስ(ረዲየላሁ ዐንሁ)፡- ኢብራሂም(ዐለይሂ-ሰላም) ወደ እሳት ሲወረወሩ ‹ሐስቢየላሁ ወኒዕመል ወኪል› (አላህ በቂዬ ነው ምንኛ ያማረ መመኪያም ነው!) ብለዋል በማለት ይነግረናል፡፡ (ቡኻሪይ 4563)፡፡
8. በአንድ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ላይ ስትደርስ፡- “በነገሩም ሁሉ አማክራቸዉ። ቁርጥ ሐሳብም ባደረግህ ጊዜ በአላህ ላይ ተመካ። አላህ በራሱ ላይ ተመኪዮችን ይወዳልና” (ሱረቱ አለ-ዒምራን 159)፡፡
9. ከቤትህ ስትወጣ፡- “ቢስሚላህ፣ ተወከልቱ ዐለላህ፣ ላሐውለ ወላ-ቁወተ ኢልላ-ቢላህ” (በአላህ ስም፡ በአላህ ላይ ተመካሁ፣ በአላህ ፈቃድ ቢሆን እንጂ መንቀሳቀስም ሆነ ችሎታ የለም) (አቡ ዳዉድና ነሳኢይ የዘገቡት)፡፡
10. ሲሳይን ስንፈልግ፡- “እናንተ በአለህ ላይ እውነተኛ የሆነ መመካትን ብትመኩ ኖሮ አእዋፋትን እንደሚረዝቀው እናንተንም ያለ ድካም በረዘቃችሁ ነበር፡፡ (አእዋፋት ጠዋት ከጎጆአቸው) በባዶ ሆድ ይወጣሉ፡ ሲመሽ ጠግበው ይመለሳሉ” (ቲርሚዚና አሕመድ የዘገቡት)፡፡ አላህ አውቀው ከሚሰሩት ያድርገን፡፡