የኢስላም መልእክት “ላ-ኢላሀ ኢልለሏህ” 10 በኡስታዝ አቡ ሀይደር

ሼር ያድርጉ
360 Views

በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
7. አፍራሽ ተግባራት፡-
1. ሺርክ (ማጋራት)
ሀ. ትልቁ ሺርክ፡-
1. “አድ-ዱዓእ” (ተማጽኖ)፡- ከአላህ ውጭ ያለ አካልን በሩቁ መማጸን (የሞቱ አካላትን) ወይም በቅርቡ ያሉ (በህይወት ያሉትን) አካላት በማይችሉት ነገር ላይ መማጸን ‹‹ሺርክ›› ነው፡፡ ይህ ተግባር ‹ሺርክ› መሆኑን በደንብ ለመረዳት ቅድሚያ ‹‹ዱዓእ›› የዒባዳ አካል መሆኑን እንመልከት፡-
“ዱዓእ” ልብ ከመላስ ጋር በመጣመር ከሚፈጸሙ የዒባዳ ዘርፎች ውስጥ የሚመደብና ተቀዳሚ ተግባርም ነው፡፡
” ﻭَﻗَﺎﻝَ ﺭَﺑُّﻜُﻢُ ﺍﺩْﻋُﻮﻧِﻲ ﺃَﺳْﺘَﺠِﺐْ ﻟَﻜُﻢْ ﺇِﻥَّ ﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﻳَﺴْﺘَﻜْﺒِﺮُﻭﻥَ ﻋَﻦْ ﻋِﺒَﺎﺩَﺗِﻲ ﺳَﻴَﺪْﺧُﻠُﻮﻥَ ﺟَﻬَﻨَّﻢَ ﺩَﺍﺧِﺮِﻳﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﻏﺎﻓﺮ 60 1 .
“ጌታችሁም አለ፦ ለምኑኝ እቀበላችኋለሁና፤ እነዚያም እኔን ከመገዛት የሚኮሩት ተዋራጆች ሆነው ገሀነምን በእርግጥ ይገባሉ።” (ሱረቱ ጋፊር 60)፡፡
በዚህ አንቀጽ ላይ ጌታችን ይቀበለን ዘንድ እንድለምነው ካዘዘን በኋላ፡ ጀሐነምን ግን እኔን ከመገዛት ለኮሩት ነች አለ እንጂ፡ እኔን ከመለመን ለኮሩት አላለም፡፡ ይህም አላህን መለመን እርሱን መገዛት መሆኑን ፍንትው አድርጎ ያስረዳናል፡፡ ስለሆነም ዱዓእ የአምልኮ አካል ነው፡፡ በተለይ ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ የሚያደርገው ተከታዩ የነቢያችን (ዐለይሂ ሶላቱ ወስ-ሰላም) ሐዲሥ ነው፡-
ኑዕማን ኢብኑ በሺር (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዳስተላለፈልን የአላህ መልክተኛ እንዲህ አሉ፡- “ዱዓእ እራሱ ዒባዳህ ነው፡፡” ከዛም ይህን አንቀጽ አነበቡ፡ ‹‹”ጌታችሁም አለ፦ ለምኑኝ እቀበላችኋለሁና፤ እነዚያም እኔን ከመገዛት የሚኮሩት ተዋራጆች ሆነው ገሀነምን በእርግጥ ይገባሉ››” (አሕመድ 18933፣ቲርሚዚይ 3247፣ አቡ ዳዉድ 1479፣ኢብኑ ማጀህ 3828፣ሐኪም አል-ሙስተድረክ 1802)፡፡
ታዲያ ዱዓእ አምልኮ ከሆነ፡ ልንማጸንና ልንለምን የሚገባው አንዱንና ብቸኛውን አምላክ አላህን መሆን ይኖርበታል፡-
” ﻭَﺃَﻥَّ ﺍﻟْﻤَﺴَﺎﺟِﺪَ ﻟِﻠَّﻪِ ﻓَﻠَﺎ ﺗَﺪْﻋُﻮﺍ ﻣَﻊَ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﺃَﺣَﺪًﺍ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺠﻦ 18
“እነሆ መስጊዶችም የአላህ ብቻ ናቸው፣ (በውስጣቸው) ከአላህ ጋር አንድንም አትገዙ” (ሱረቱል ጂን 18)፡፡
” ﻓَﺎﺩْﻋُﻮﺍ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻣُﺨْﻠِﺼِﻴﻦَ ﻟَﻪُ ﺍﻟﺪِّﻳﻦَ ﻭَﻟَﻮْ ﻛَﺮِﻩَ ﺍﻟْﻜَﺎﻓِﺮُﻭﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﻏﺎﻓﺮ 14
“አላህንም ከሐዲዎች ቢጠሉም ሃይማኖትን ለርሱ አጥሪዎች ሆናችሁ ተገዙት።” (ሱረቱ ጋፊር 14)፡፡
” ﻫُﻮَ ﺍﻟْﺤَﻲُّ ﻟَﺎ ﺇِﻟَﻪَ ﺇِﻟَّﺎ ﻫُﻮَ ﻓَﺎﺩْﻋُﻮﻩُ ﻣُﺨْﻠِﺼِﻴﻦَ ﻟَﻪُ ﺍﻟﺪِّﻳﻦَ ﺍﻟْﺤَﻤْﺪُ ﻟِﻠَّﻪِ ﺭَﺏِّ ﺍﻟْﻌَﺎﻟَﻤِﻴﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﻏﺎﻓﺮ 65
“እርሱ ብቻ (ሁል ጊዜ) ሕያው ነው፤ ከርሱ ሌላ አምላክ የለም፤ ሃይማኖትንም ለርሱ ያጠራችሁ ስትሆኑ፣ ምስጋና ለዓለማት ጌታ ለአላህ ይሁን፣ የምትሉ ሆናችሁ ተገዙት” (ሱረቱ ጋፊር 65)፡፡
አላህን ብቻ መማጸን የሚያዋጣ ተግባር መሆኑን በወቅቱ የነበሩ ዐረብ ጣኦታውያኖች እንኳ የተረዱት ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም በጀልባ ተሳፍረው ሲጓዙ ከባሕሩ ማዕበልና ከመስጠም ያድናቸው ዘንድ፡ ሲያመልኳቸው የነበሩትን የሀሰት አማልክቶች በመተው ፊታቸውን ወደ ጌታ አላህ ያዞሩ ነበር፡፡ ችግራቸው ግን ወደ የብሱ በሰላም መውጣታቸውን ሲያረጋግጡ ወደነበሩበት ሽርክ መመለሳቸው ነው-
” ﻫُﻮَ ﺍﻟَّﺬِﻱ ﻳُﺴَﻴِّﺮُﻛُﻢْ ﻓِﻲ ﺍﻟْﺒَﺮِّ ﻭَﺍﻟْﺒَﺤْﺮِ ﺣَﺘَّﻰ ﺇِﺫَﺍ ﻛُﻨْﺘُﻢْ ﻓِﻲ ﺍﻟْﻔُﻠْﻚِ ﻭَﺟَﺮَﻳْﻦَ ﺑِﻬِﻢْ ﺑِﺮِﻳﺢٍ ﻃَﻴِّﺒَﺔٍ ﻭَﻓَﺮِﺣُﻮﺍ ﺑِﻬَﺎ ﺟَﺎﺀَﺗْﻬَﺎ ﺭِﻳﺢٌ ﻋَﺎﺻِﻒٌ ﻭَﺟَﺎﺀَﻫُﻢُ ﺍﻟْﻤَﻮْﺝُ ﻣِﻦْ ﻛُﻞِّ ﻣَﻜَﺎﻥٍ ﻭَﻇَﻨُّﻮﺍ ﺃَﻧَّﻬُﻢْ ﺃُﺣِﻴﻂَ ﺑِﻬِﻢْ ﺩَﻋَﻮُﺍ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻣُﺨْﻠِﺼِﻴﻦَ ﻟَﻪُ ﺍﻟﺪِّﻳﻦَ ﻟَﺌِﻦْ ﺃَﻧْﺠَﻴْﺘَﻨَﺎ ﻣِﻦْ ﻫَﺬِﻩِ ﻟَﻨَﻜُﻮﻧَﻦَّ ﻣِﻦَ ﺍﻟﺸَّﺎﻛِﺮِﻳﻦَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﻳﻮﻧﺲ 22
“እርሱ (አላህ) ያ በየብስና በባሕር የሚያስኬዳችሁ ነው፡፡ በመርከቦችም ውስጥ በሆናችሁና በእነርሱም (በተሳፋሪዎቹ) በመልካም ነፋስ በርሷ የተደሰቱ ኾነው (መርከቦቹ) በተንሻለሉ ጊዜ ኀይለኛ ነፋስ ትመጣባታለች፡፡ ከየስፍራውም ማዕበል ይመጣባቸዋል፡፡ እነሱም (ለጥፋት) የተከበቡ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ (ያን ጊዜ) አላህን ከዚህች (ጭንቀት) ብታድነን በእርግጥ ከአመስጋኞቹ እንሆናለን ሲሉ ሃይማኖትን ለርሱ ብቻ ያጠሩ ሆነው ይለምኑታል፡፡” (ሱረቱ ዩኑስ 22)፡፡
ስለ ዱዓእ በተወሰነ መልኩ ከተመለከትን እንዲሁም የዒባዳ አንድ አካል መሆኑን ካወቅን፡ ሌላው ልንረዳ የሚገባው ነገር ዱዓን ከአላህ ውጭ ለሆነ አካል አሳልፈን መስጠት እንደሌለብን ነው፡፡ ዒባዳ የሆነን ነገር ከአላህ ውጪ ላለ ነገር አሳልፎ መስጠት ሺርክ (ማጋራት) ውስጥ ይከታልና፡፡ ከአላህ ውጭ ያለን አካል መማጸን ደግሞ ሽርክ መሆኑን የሚያመላክቱ መረጃዎችን እንመልከታቸው፡-
” ﻗُﻞْ ﺃَﺭَﺃَﻳْﺘَﻜُﻢْ ﺇِﻥْ ﺃَﺗَﺎﻛُﻢْ ﻋَﺬَﺍﺏُ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﺃَﻭْ ﺃَﺗَﺘْﻜُﻢُ ﺍﻟﺴَّﺎﻋَﺔُ ﺃَﻏَﻴْﺮَ ﺍﻟﻠَّﻪِ ﺗَﺪْﻋُﻮﻥَ ﺇِﻥْ ﻛُﻨْﺘُﻢْ ﺻَﺎﺩِﻗِﻴﻦَ * ﺑَﻞْ ﺇِﻳَّﺎﻩُ ﺗَﺪْﻋُﻮﻥَ ﻓَﻴَﻜْﺸِﻒُ ﻣَﺎ ﺗَﺪْﻋُﻮﻥَ ﺇِﻟَﻴْﻪِ ﺇِﻥْ ﺷَﺎﺀَ ﻭَﺗَﻨْﺴَﻮْﻥَ ﻣَﺎ ﺗُﺸْﺮِﻛُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻷﻧﻌﺎﻡ 40-41
“የአላህ ቅጣት ቢመጣባችሁ ወይም ሰዓቲቱ (ትንሣኤ) ብትመጣባችሁ ከአላህ ሌላን ትጠራላችሁን እውነተኞች እንደ ኾናችሁ ንገሩኝ በላቸው፡፡ አይደለም እርሱን ብቻ ትጠራላችሁ፡፡ ቢሻም ወደርሱ የምትጠሩበትን ነገር ያስወግዳል፡፡ የምታጋሩትንም ነገር ትተዋላችሁ (በላቸው)፡፡” (ሱረቱል አንዓም 40-41)፡፡
ይህ የቅዱስ ቁርኣን አንቀጽ የሚያስረዳን፡- ጌታ አላህ ለአጋሪዎች ስራቸው ከንቱ መሆኑን በምክንያት ሲያስረዳቸው፡- ቅጣት ቢመጣባችሁ ወይም ሰዓቲቷ ብትመጣ ከአላህ ሌላ በእውነት የምትጠሩት ማን ሊኖር ይችላል? እነዚያ የምትጠሯቸው በዚህ ጭንቅ ጊዜ እንደማይደርሱላችሁ እናንተም ስለምታውቁ የዛኔ አላህን ብቻ ትጠሩና የምታጋሩትን ትረሳላችሁ አላቸው፡፡ የምትጠሩትን ትረሳላችሁ ሳይሆን የምታጋሩትን ትረሳላችሁ ማለቱ፡- ከአላህ ሌላ ያለን አካል መጥራትና መማጸን በርሱ ላይ ማሻረክ እንደሆነ የሚገልጽ ነው ማለት ነው፡፡
“… ﺫَﻟِﻜُﻢُ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﺭَﺑُّﻜُﻢْ ﻟَﻪُ ﺍﻟْﻤُﻠْﻚُ ﻭَﺍﻟَّﺬِﻳﻦَ ﺗَﺪْﻋُﻮﻥَ ﻣِﻦْ ﺩُﻭﻧِﻪِ ﻣَﺎ ﻳَﻤْﻠِﻜُﻮﻥَ ﻣِﻦْ ﻗِﻄْﻤِﻴﺮٍ * ﺇِﻥْ ﺗَﺪْﻋُﻮﻫُﻢْ ﻟَﺎ ﻳَﺴْﻤَﻌُﻮﺍ ﺩُﻋَﺎﺀَﻛُﻢْ ﻭَﻟَﻮْ ﺳَﻤِﻌُﻮﺍ ﻣَﺎ ﺍﺳْﺘَﺠَﺎﺑُﻮﺍ ﻟَﻜُﻢْ ﻭَﻳَﻮْﻡَ ﺍﻟْﻘِﻴَﺎﻣَﺔِ ﻳَﻜْﻔُﺮُﻭﻥَ ﺑِﺸِﺮْﻛِﻜُﻢْ ﻭَﻟَﺎ ﻳُﻨَﺒِّﺌُﻚَ ﻣِﺜْﻞُ ﺧَﺒِﻴﺮٍ ” ﺳﻮﺭﺓ ﻓﺎﻃﺮ 13-14
“…ይሃችሁ ጌታችሁ አላህ ነው፤ ንግሥናው የርሱ ብቻ ነው፤ እነዚያም ከርሱ ሌላ የምትግገዟቸው የተምር ፍሬ ሺፋን እንኳ አይኖራቸውም።ብትጠሩዋቸው ጥሪያችሁን አይሰሙም፤ ቢሰሙም ኖሮ ለናንተ አይመልሱላችሁም፤ በትንሣኤም ቀን (እነርሱን በአላህ( ማጋራታችሁን ይክዳሉ፤ እንደ ውስጠ አዋቂው ማንም አይነግርህም።” (ሱረቱ ፋጢር 13-14)፡፡
በዚህም አንቀጽ ላይ ተመሳሳይ ሀሳብ እናገኛለን፡፡ በዚህ ምድር ላይ ከርሱ ሌላ ሲጥጠሩና ሲለመኑ የነበሩ የሀሰት አማልክቶች መስማት የማይችሉ፡ ቢችሉ እንኳ ለጥሪያችሁ መልስ መስጠት የማይችሉ ናቸው ይልና በመጨረሻው ቀን ደግሞ በማጋራታችሁ ይክዳሉ አለ፡፡ እነሱን በመጥራታችሁ ይክዳሉ ሳይሆን ያለው “በማጋራታችሁ ይክዳሉ” ነው ያለው፡፡ ይህ የሚያሳየው ከአላህ ሌላ ያለን መጥራት በአላህ ላይ ማጋራት መሆኑን ነው፡፡
” ﻓَﺈِﺫَﺍ ﺭَﻛِﺒُﻮﺍ ﻓِﻲ ﺍﻟْﻔُﻠْﻚِ ﺩَﻋَﻮُﺍ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻣُﺨْﻠِﺼِﻴﻦَ ﻟَﻪُ ﺍﻟﺪِّﻳﻦَ ﻓَﻠَﻤَّﺎ ﻧَﺠَّﺎﻫُﻢْ ﺇِﻟَﻰ ﺍﻟْﺒَﺮِّ ﺇِﺫَﺍ ﻫُﻢْ ﻳُﺸْﺮِﻛُﻮﻥَ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﻌﻨﻜﺒﻮﺕ 65
“በመርከቦች ውስጥ በተሳፈሩ ጊዜም፣ አላህን መግገዛትን ለርሱ ብቻ ያጠሩ ኾነው ይጠሩታል፣ ወደ የብስ (በማውጣት) ባዳናቸው ጊዜም ውዲያውኑ እነርሱ (ጣዖትን) ያጋራሉ።” (ሱረቱል ዐንከቡት 65)፡፡
” ﻭَﺇِﺫَﺍ ﻏَﺸِﻴَﻬُﻢْ ﻣَﻮْﺝٌ ﻛَﺎﻟﻈُّﻠَﻞِ ﺩَﻋَﻮُﺍ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻣُﺨْﻠِﺼِﻴﻦَ ﻟَﻪُ ﺍﻟﺪِّﻳﻦَ ﻓَﻠَﻤَّﺎ ﻧَﺠَّﺎﻫُﻢْ ﺇِﻟَﻰ ﺍﻟْﺒَﺮِّ ﻓَﻤِﻨْﻬُﻢْ ﻣُﻘْﺘَﺼِﺪٌ ﻭَﻣَﺎ ﻳَﺠْﺤَﺪُ ﺑِﺂﻳَﺎﺗِﻨَﺎ ﺇِﻟَّﺎ ﻛُﻞُّ ﺧَﺘَّﺎﺭٍ ﻛَﻔُﻮﺭٍ ” ﺳﻮﺭﺓ ﻟﻘﻤﺎﻥ 32
“እንደ ጥላዎችም የኾነ ማዕበል በሸፈናቸው ጊዜ አላህን ሃይማኖትን ለርሱ ብቻ ያጠሩ ሆነው ይጠሩታል፤ ወደ የብስም ባዳናቸው ጊዜ ከነሱ ትክክለኛም አለ፤ (ከነሱ የሚክድም አለ)፤ በአንቀጾቻችንም አታላይ ከዳተኛ ሁሉ እንጂ ሌላው አይክድም።” (ሱረቱ ሉቅማን 32)፡፡
” ﻗُﻞْ ﺇِﻧَّﻤَﺎ ﺃَﺩْﻋُﻮ ﺭَﺑِّﻲ ﻭَﻟَﺎ ﺃُﺷْﺮِﻙُ ﺑِﻪِ ﺃَﺣَﺪًﺍ ” ﺳﻮﺭﺓ ﺍﻟﺠﻦ 20
“እኔ የምግገዛው ጌታየን ብቻ ነው፤ በርሱም አንድንም አላጋራም በል።” (ሱረቱል ጂን 20)፡፡
ሃይማኖታዊ ዕውቀት ፈልገን ዑለማዎችን፣ ለችግራችን ማሟያ ገንዘብ አጥሮን ለጋሶችን፣ ለምንሰራው ስራ ጉልበት አንሶን ጠንካሮችን እንዲተባበሩን ብንማጸናቸው ግን፡ ሺርክ ሰራን አይባልም፡፡
አንደኛ፡- የተለመኑት ነገር እነሱ ያላቸውና የሚችሉት ነገር ስለሆነ፡-
ሁለተኛ፡- የሚለመኑት አካላት በህይወት ያሉና ልመናችንንም በቅርቡ መስማትና መረዳት የሚችሉ በመሆናቸው ነው፡፡ እኛም ግን እዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን፡ ከላይ የተጠቀሱትን አካላት የምንማጸነው ሰበብ ይሆናሉ ብለን እንጂ ሙሉ በሙሉ በነሱ ተስፋ አድርገን አይደለም፡፡ እነሱን ሰበብ በማድረግ ፍላጎታችን እንዲሟላ ለመፍቀድም ሆነ ለመከልከል ሙሉ ስልጣኑ የአላህ ነውና!! በቅርብ የተገኘና የሚሰማ ሁሉ ደግሞ፡ የማይችለውን ነገር መለመንም የለብንም፡፡ ገንዘብ ከሌለው ሰው ዘንድ ብር እንዲረዳን እንደማንጠይቀው ሁሉ፡ ጠንቋይ ዘንድ ወይም መጽሐፍ ገላጭ ነኝ ባይ ጋር ሂደን የባለቤቴን ማህጸን እንዲፈታና ልጅ እንድትወልድ፣ ምቀኛ ጎረቤቶቼን አደብ እንዲያስዪዛቸው፣ የተሰረቀውን ንብረቴን እንዲያስመልስልኝ መጠየቅም ሐራም ነው፡፡ አንድ ክስተት ልንገራችሁና በዚሁ ልቋጨው፡- ሴትየዋ ጠንቋይ ሁሉን ያውቃል ብላ የወደፊት እጣዋን ለመጠየቅ ወደቤቱ ታመራለች፡፡ በሩ ላይ እንደደረሰችም ወደ ግቢው ለመግባት ማንኳኳት ጀመረች፡፡ ጠንቋዩም ከውስጥ ሆኖ፡- ማነው? ሲል፡ ወዲያው የውስጥ አይኗ (ልቦናዋ) ተከፈተላትና እንዲህ አለችው፡- እኔ ሁሉን ታውቃለህ ብዬ ስለ ወደፊት እጣዬ ላማክርህ እመጣለሁ፡ አንተ ግን ከውስጥ ሆነህ እንኳ በር የሚያንኳኳውን ሰው መለየትህ አቅቶህ ማነው? ትላለህ፡ ብላ በመገረም ተመለሰች፡፡ አላህን ብቻ አምልከን እሱኑ ብቻ ተማጽነን በዚሁ እምነታችን የምንሞት ባሪያው ያድርገን አላሁመ አሚን፡፡ ይቀጥላል