የአዲስ ኪዳን የእጅ ጹሁፎችን/Manuscripts/ አስመልክቶ

733 Views

ጥቂት መግቢያ

የአዲስ ኪዳንም ሆነ ሌሎች ጥንታዊ ጹሁፎች በድሮ ጊዜያት የሚጻፉት ልክ እንዳሁኑ በወረቀት ላይ አልነበረም። የተለያዩ የመጻፍያ ቁሳቁሶች ቢኖሩም በዋናነት ግን የሚጠቀሙት ብራና ነበር። ብራና ደግሞ በተፈጥሮው ጥበቃ ካልተደረገለት በስተቀር በቀላሉ የመውደም ባህርይ ያለው ነው።ለሀዋርያት ዘመን ይቀርባሉ ተብለው የሚታሰቡት የመጀመሪያዎቹ የአዲስ ኪዳን የእጅ ጹሁፍ የሆኑት p66 እና p75 ሲሆኑ እነዚህ ጥንታዊ መጽሀፍትም በተለያዩ ጊዜያት ምሁራን በሚያደርጓቸው ጥናቶች የቀን ጊዜያቸው እየተራዘመ መጥቶ አሁን ላይ ከእየሱስ ልደት ከ4ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ እንደተጻፉ በምሁራን እየተገለጸ ነው። ይህ ደግሞ ለክርስትናው ዓለም መጥፎ ዜና ነው። ሁለቱ አስፈላጊ የሆኑ ማኑስክሪፕቶች p66 እና p75 በተለምዶ ተጽፈዋል ተብለው የሚታሰቡት በ2ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው።

ችግሩ ምንድን ነው?

የጥንት አዲስ ኪዳን ጹሁፎች የዘመን ርዝማኔያቸው የሚለካው ፓሊዮግራፊክ በሆነ መንገድ ነው። ፓልዮግራፊ ማለት የጹሁፉን ይዘት መሰረት በማድረግ እድሜውን የመገመት ሳይንሳዊ አካሄድ ነው። ይህ ማለት በዚህ ቀን ተጽፏል ተብሎ እንቅጩን የምንናገርለት የአዲስ ኪዳን ማኑስክሪፕት የለም ማለት ነው። አንዳንድ የክርስቲያን አቃቤ እምነቶች የማኑስክሪፕቶችን እድሜ ሲገልጹ እቅጩን የሆነ አመት ሲጠቅሱ እናስተውላለን። ይህ ግን ስህተት ነው። ማኑስክሪፕቶች በአመታት መካከል ያለ የጊዜ መጠን ተገልጾ ከ – እስከ ተብለው ይገለጻሉ እንጅ የሆነ የተወሰነ አመት ተጠቅሶ አይገለጹም። ለአብነት አንዳንድ አፖሎጂስቶች ከላይ የጠቀስናቸውን ማኑስክሪፕቶች አስመልክቶ ሲናገሩ በ125 ዓ/ል የተጻፉ እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህ ከላይ እንደጠቀስነው ከሰዎቹ አላዋቂነት የሚመነጭ እንጅ በዛ መልኩ የሚገለጽ አይደለም።
በዚህም ምክንያት እነዚህ የእጅ ጹሁፎች በ2ተኛው ክፍል ዘመን ገደማ ተጽፈዋል ተብሎ ይታመን የነበረ ሲሆን አሁን ላይ የሚወጡ ጥናቶች ግን የእጅ ጹሁፎቹ ወደ 4ተኛው ክፍለ ዘመን የተጠጉ እንደሆ እየገለጹ ነው። ክርስቲያኖች በአብዛኛው የሚተማመኑባቸው ሁለቱ ኮዴክሶች (ኮዴክስ ሲናይታከስ እና ኮዴክስ ቫቲካነስ) በተመሳሳይ የአራተኛው ክፍለ ዘመን ጹሁፎች እንደሆኑ ይታወቃል።

ጠቅለል ስናደርገው

ይህ ማለት በሀዋርያትና በመጀመሪያው የአዲስ ኪዳን ጹሁፍ መካከል ባሉት 400 ዓመታት ውስጥ ምንም አይነት የምናመሰክረው የአዲስ ኪዳን ጹሁፍ የለም ማለት ነው። ለ400 ዓመት ምን አስመልክቶ ተጽፎ ነበር ለሚለው ምንም አይነት ምላሽ የለንም። በ400 ዓመታት ውስጥ መጽሀፉ ምን እንደገጠመው በተመሳሳይ የምናውቅበት ምንም መንገድ የለም።.
ይህንን አስመልክቶ በዘርፉ ታዋቂ የሆኑት ምሁራን ዶ/ር ብሬንት ኖንግበሪ እና ደ/ር ኦርሲኒ ሳይቀር የገለጹ ሲሆን ደ/ር ብሬንት ይህንን አስመልክቶ የራሱን ጥናት ይፋ አድርጓል። እነዚህ አዳዲስ ግኝቶች ደግሞ ለአብዛኛው ክርስቲያን ወዳጆቻችን አሳሳቢ አንደሚሆኑባቸው ግልጽ ነው።
የአዲስ ኪዳን እና የብሉይ ኪዳን ማኑስክሪፕቶችን አስመልክቶ ኢንሻአላህ በሰፊው በምጽፋቸው ተከታታይ ጹሁፎቼ የምንገናኛ ይሆናል።

የተለያዩ የመረጃ ምንጮቼ

የወንድም ኢጃዝ አህመድ ስራዎችና የራሱ የዶ/ር ብሬንት ጹሁፎች ሲሆኑ የዶ/ሩን ስራዎች በዚህ የግል ጦማሩ ማግኘት ትችላላችሁ።

The Date of P66 (P. Bodmer II): Nongbri’s New Argument

A Challenge to the Dating of P75

Orsini on Bodmer Biblical Papyri

(የሕያ ኢብኑ ኑህ)