የአያሙል–ቢድ ደንበኞች ለኾናችሁ!

ሼር ያድርጉ
286 Views

በአቡ ሀይደር

በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2) ፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

1/ የሙስሊሞች ፆም የነፍስ–ወከፍ ግዴታ በሆነው የረመዷን ፆም ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። ሙስተሐብ (ግዴታ ያልሆነ ተወዳጅ ተግባር) የሆኑ የሱንና ፆሞች ብዙ አልሉ። ከነዚህም ውስጥ አንዱ በየወሩ ሶስት ቀን መፆም የሚሰኘው ነው። አንድ መልካም ሥራ: ቸርና አዛኝ የኾነው አላህ ዘንድ በአሥር እጥፍ ተባዝቶ ነው ለሠሪው የሚከፈለው። ይህ ማለት የሶስት ቀን ፆም እንደ ሰላሳ ቀን ፆም ወይም እንደ አንድ ወር ፆም ይቆጠራል ማለት ነው። ወሩን እየጠበቀ በአሥራ ሁለቱም ወራት ውስጥ ሶስት ሶስት ቀን የሚፆም ሙስሊም አመቱን ሙሉ እንደፆመ ተቆጥሮለት አጅርን ከጌታው ይረከባል ማለት ነው። የአላህ ቃል እንዲህ ይላል:–

“مَنْ جَاءَ بِالْحَسَنَةِ فَلَهُ عَشْرُ أَمْثَالِهَا ۖ وَمَنْ جَاءَ بِالسَّيِّئَةِ فَلَا يُجْزَىٰ إِلَّا مِثْلَهَا وَهُمْ لَا يُظْلَمُونَ” سورة الأنعام 160

“በመልካም ሥራ የመጣ ሰው ለእርሱ ዐሥር ብጤዎችዋ አሉት፡፡ በክፉ ሥራም የመጣ ሰው ብጤዋን እንጅ አይመነዳም፡፡ እነርሱም አይበደሉም፡፡” (ሱረቱል አንዓም 6:160)።

2/ አያሙል–ቢድ በመባል የሚታወቁት ቀናቶች በእስልምናው አቆጣጠር የወሩ 13ኛ, 14ኛ እና 15ኛ ቀናት ናቸው። በየወሩ ሶስት ቀናትን በመፆም ከጌታቸው እጥፍ ድርብ የኾነ መልካም ምንዳን የሚከጅሉ ሙስሊም የአላህ ባሪያዎች: በብዛት ለፆም የሚያውሉት እነዚህን የአያሙል–ቢድ ቀናት ነው። አሁን ያለንበት 12ኛው የዙል–ሒጃህ ወር 13ኛው ቀን የአያሙ–ተሽሪቅ ቀን ነው። አያሙ ተሽሪቅ በመባል የሚጠሩት የዙል–ሒጃህ 11ኛ, 12ኛ እና 13ኛ ቀናት ደግሞ የሙስሊሞች ዒድ በመኾናቸው: በነዚህ ቀናት አይፆምም። በመኾኑም አያሙል–ቢድን በፆም የሚያሳልፉ አንዳንድ እሕቶች የነገውን 13ኛ ቀን ምን እናድርገው? በማለት ጥያቄን አቅርበዋል። ለዚህ የሚሰጠው መጠነኛ ምላሽም:–

ሀ/ በየወሩ ሶስት ቀናትን የሚፆም የአላህ ባሪያ: እነዚህን ሶስት ቀናት ለመፆም የግድ የወሩን 13ኛ, 14ኛ እና 15ኛ ቀናት መጠበቅ የለበትም። ዋናው ነገር የገባው ወር ተጠናቅቆ ከመውጣቱና ሌላ ቀጣዩ ወር ከመምጣቱ በፊት ሶስት ቀናትን መርጦ መፆሙ ነው። አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተናገው:– “ወዳጄ (ረሱል ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እስክሞት ድረስ በየወሩ ሶስት ቀናትን በመፆም፣ ሶላተ–ዱሓን በመስገድ፣ ዊትርን ከሰገድኩ በኋላ መተኛትን እንዳዘወትርና እንዳልተዋቸው መክረውኛል” ይለናል (ቡኻሪና ሙስሊም)።

ሙዐዘቱል–ዐደዊያ (ረሒመሃላህ) እናታችንን ዓኢሻን (ረዲየላሁ ዐንሃ) :– የአላህ መልክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በየወሩ ሶስት ቀናትን ይፆሙ ነበርን? በማለት ጠየቀቻት። እናታችንም “አዎን!” በማለት መለሰች። እሷም:– “ከወሩ የትኞቹን ቀናት ነበር?” ብላ ስትጠይቃት: እናታችንም:– “እሳቸው የሚፆሟቸውን የወሩን ቀናት (መምረጥ) ግድ አይላቸውም” ነበር በማለት መለሰችላት። (ሙስሊም 1160)።

ለ/ እነዚህ የወሩ ሶስት ቀናቶች ደግሞ የግድ ተከታታይ መኾን የለባቸውም። የፈለገ ሰው ሶስቱንም ቀናት አከታትሎ፣ የፈለገ ደግሞ ቀናቱን አለያይቶና አፈራርቆ ወሩ ከመውጣቱ በፊት መፆም ይችላል። ሐዲሡም የሚናገረው “ሶስት ቀናትን ስለመፆም” እንጂ: እነዚህን ቀናት ስለማከታተል አይደለም። የኢስላም ሊቃውንትም እነዚህን ቀናት በማፈራረቅ መፆም እንደሚቻል ፈትዋ ሰጥተዋል። (ኢብኑ ዑሠይሚን: መጅሙዕ ፈታዋ ወረሳኢል ሸይኽ ኢብኑ ዑሠይሚን: ጥራዝ 20: ኪታቡ–ሲያም: ጥያቄ ቁ· 376)።

ሐ/ እነዚህን ሶስት የፆም ቀናት በአያሙል–ቢድ ማድረጉ ግን በላጭና ተወዳጅ ነው። አቢ ዘር (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል:– “የአላህ መልክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉኝ:– ከወሩ ውስጥ የተወሰነ ቀናትን ከፆምክ: 13ኛውን, 14ኛውንና 15ኛውን ቀን ፁም” (ቲርሚዚይ 761፣ ነሳኢይ 2424፣ አልባኒይ: ሶሒሑ ተርጚብ ወት–ተርሂብ 1038)።

ሆኖም እነዚህን አያመል–ቢድ መፆም ያስለመደ የአላህ ባሪያ በሐይድ ወይም በህመም እና መሰል ዑዝር ሰበብ ቀናቶቹ ቢያመልጡት: ወሩ ከመጠናቀቁ በፊት በቀሪዎቹ 15 ቀናት ውስጥ መፆም ይችላል። ወላሁ አዕለም።

3/ ሌላው ማወቅ የሚገባን ነገር: በወሩ ውስጥ ሶስት ቀናትን መርጦ መፆም ሲባል: የወር አቆጣጠሩ ኢስላማዊውን የሂጅሪ ካላንደር መሠረት ያደረገ እንጂ: የአውሮፓውያንን ወይም ሀገር ቤት ያለውን የቀን አቆጣጠር የተረመኮዘ አለመሆኑን ነው። አንደኛው ወር ተጠናቅቆ ቀጣዩ ወር መግባቱን የምናውቀው በሒጅራው አቆጣጠር ብቻ ነው። ይህን ለማወቅ እንዲረዳችሁ በሞባይላችሁ ላይ Hijri calander የሚለውን አፕ በማውረድ ይጠቀሙ።

Shortlink http://q.gs/EwihU