የአላህን ቃላት ለዋጭ የላቸውም!

900 Views

 

በአቡ ሀይደር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡

” وَلَقَدْ كُذِّبَتْ رُسُلٌ مِنْ قَبْلِكَ فَصَبَرُوا عَلَى مَا كُذِّبُوا وَأُوذُوا حَتَّى أَتَاهُمْ نَصْرُنَا وَلَا مُبَدِّلَ لِكَلِمَاتِ اللَّهِ وَلَقَدْ جَاءَكَ مِنْ نَبَإِ الْمُرْسَلِينَ ” سورة الأنعام 34
“ከበፊትህም መልክተኞች በእርግጥ ተስተባበሉ፡፡ በተስተባበሉበትም ነገርና በተሰቃዩት ላይ እርዳታችን እስከመጣላቸው ድረስ ታገሱ፡፡ የአላህንም ንግግሮች ለዋጭ የለም፡፡ ከመልክተኞቹም ወሬ (የምትረጋጋበት) በእርግጥ መጣልህ፡፡” (ሱረቱል አንዓም 6፡34)፡፡

” وَاتْلُ مَا أُوحِيَ إِلَيْكَ مِنْ كِتَابِ رَبِّكَ لَا مُبَدِّلَ لِكَلِمَاتِهِ وَلَنْ تَجِدَ مِنْ دُونِهِ مُلْتَحَدًا ” سورة الكهف 27
“ከጌታህም መጽሐፍ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ፡፡ ለቃላቶቹ ለዋጭ የላቸውም፡፡ ከእርሱም በቀር መጠጊያን በፍጹም አታገኝም፡፡” (ሱረቱል ከህፍ 18፡27)፡፡

በነዚህ ሁለት የቅዱስ ቁርኣን ጥቅሶች መሠረት ‹‹የአላህን ቃላት ለዋጭ የለም›› ተብሎ ተነግሯልና፡ ተውራትና ኢንጂልም የአላህ ቃላት ናቸውና አልተለወጡም ማለት እንችላለን፡፡ እናንተ ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟል ስትሉ ከዚህ የቅዱስ ቁርኣን ሀሳብ ጋር አትጋጩም ወይ? የሚል ጥያቄ ከካፊሮች በኩል ቀርቧል፡፡ እኛም ለጥያቄዎቹ የሚኖረን መጠነኛ ምላሽ እንደሚከተለው ይቀርባል ኢንሻአላህ፡-

1ኛ/ ጥቅላዊ ምላሽ፡-

የአላህ ቃል ተብሎ ሲጠቀስ ‹‹ቃል›› የሚለው ኃይለ-ቃል ሁለት ነገራትን እንደሚያቅፍ በቅድሚያ ማወቁ ለመልሱ አጋዥ ይኾናል፡፡ የመጀመሪያው ‹‹ከሊማቱላህ አል-ከውኒያህ›› ሲኾን፡ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹ከሊማቱላህ አሽ-ሸርዒያህ›› የተሰኘው ነው፡፡

‹‹ከሊማቱላህ አል-ከውኒያህ›› ማለት፡- አላህ አስቀድሞ ከጥንቱ የወሰነውና የፈረደው የውሳኔ ቃል፣ ለነቢያቱና አማኝ ባሪያዎቹ መልካም የተስፋ ቃል-ኪዳንን የገባላቸው ቃል፣ በከሀዲያንና አመጸኞች ላይ በቁጣውና በጀሀነም እሳት የዛተባቸው፡ የማስፈራራሪያ ቃል ማለት ነው፡፡ ይህንን ቃል(ውሳኔ) ማንም ፍጥረት ለመሻር፣ ለመለወጥ፣ ለማስቀየር አይችልም፡ አቅሙም የለውም፡፡

‹‹ከሊማቱላህ አሽ-ሸርዒያህ›› ማለት ደግሞ፡- ጌታ አላህ በነቢያቱና በመልክተኞቹ አማካኝነት፡ ለባሪያዎቹ የሕይወት መመሪያ ይኾን ዘንድ ያወረዳቸው መለኮታዊ መጽሐፍቱ ማለት ነው፡፡ እነዚህ መለኮታዊ መጽሐፍት የአላህ ቃል ይባላሉ፡፡ ቃሉም ኾነ መልእክቱ የርሱ በመኾናቸው፡፡ እነዚህን ‹የአላህ ቃል› የተሰኙ መለኮታዊ መጽሐፍት፡ በውስጣቸው ያለውን የህግ አንቀጾች፡ አላህ እራሱ በሌላ የህግ አንቀጽ በመተካት የፈለገውን ሊሽረውና ሊሰርዘው ይችላል (ሱረቱል በቀራህ 2፡106፣ ሱረቱ-ነሕል16፡101)፡፡ እንዲሁም መጽሐፍቶቹን ለመጠበቅ (ልክ እንደ ቁርኣን) ቃል ካልገባላቸው ሰዎችም እነዚህ መጻሕፍት ላይ እጃቸውን በማስገባት፡ መጨመርና መቀነስ፣ መሰረዝና መደለዝ ይችላሉ ማለት ነው፡፡

ከዚህ ገለጻ በመነሳት፡- ‹ወገኖቻችን› የአላህ ቃላት እንደማይለወጥ ያቀረቧቸው ጥቅሶች፡ አላህ አስቀድሞ ለባሪዎቹ ቃል የገባላቸውን፣ በከሀዲያን ላይ ደግሞ የዛተባቸውን የውሳኔ ቃሉን ለማመልከት፣ ወይንም ደግሞ ለዓለማት ሕዝቦች የሕይወት መመሪያ ይኾን ዘንድ የተወረደውን የመጨረሻውን መለኮታዊ መጽሐፍ ቅዱስ ቁርኣንን ለመግለጽ ካልኾነ በስተቀር፡ እነሱ ዘንድ ያለውን ‹መጽሐፍ ቅዱስ›ን በፍጹም ሊገልጽ አይችልም፡፡ ይህንንም በደንብ ለማሳየት በዚህ ዙሪያ የተነገሩ የቁርኣን ክፍሎችን በጠቅላላ በዝርዝር እናቀርባቸዋለን ኢንሻአላህ፡፡

ሀ. ሱረቱል አንዓም 6፡34፡-

” وَلَقَدْ كُذِّبَتْ رُسُلٌ مِنْ قَبْلِكَ فَصَبَرُوا عَلَى مَا كُذِّبُوا وَأُوذُوا حَتَّى أَتَاهُمْ نَصْرُنَا وَلَا مُبَدِّلَ لِكَلِمَاتِ اللَّهِ وَلَقَدْ جَاءَكَ مِنْ نَبَإِ الْمُرْسَلِينَ ” سورة الأنعام 34
“ከበፊትህም መልክተኞች በእርግጥ ተስተባበሉ፡፡ በተስተባበሉበትም ነገርና በተሰቃዩት ላይ እርዳታችን እስከመጣላቸው ድረስ ታገሱ፡፡ የአላህንም ንግግሮች ለዋጭ የለም፡፡ ከመልክተኞቹም ወሬ (የምትረጋጋበት) በእርግጥ መጣልህ፡፡” (ሱረቱል አንዓም 6፡34)፡፡

ይህ አንቀጽ እያናገረ ያለው ነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነው፡፡ ቃሉም፡- ለሳቸው በወገኖቻቸው በኩል በሚደርስባቸው ማስተባበልና ክህደት ሀዘን እንዳይሰማቸው ማጽናኛን እየሰጠ ነው፡፡ ይህ ነቢያትን የማሰቃየትና የማስተባበል ተግባር ከሳቸው በፊት በነበሩት ነቢያትም ላይ የተፈጸመ ነገር መኾኑን በማውሳት፡ አዲስ እንዳልኾነ በመግለጽና፡ እነዚያም ነቢያት የአላህ እርዳታ (በጠላት ላይ ድልን መጎናጸፍ) እስኪመጣላቸው ድረስ በደረሰባቸው ችግር እንደታገሱ በመግለጽ፡ እሳቸውም እንዲታገሱ ያስተምራል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ‹‹የአላህንም ንግግሮች ለዋጭ የለም፡፡›› በማለት የተናገረው፡፡ ይህም አላህ ነቢያቱንና አማኝ ባሪያዎቹን እንደሚረዳና የበላይ እንደሚያደርግ ከጥንቱኑ ቃል የገባለት ጉዳይ በመኾኑ፡ ይህን ቃል ማንም ሊለውጠው እንደማይችል ተናገረ፡፡ ታዲያ ይህ ቃል በምን መልኩ ነው ከቀደምት መለኮታዊ መጽሐፍት ጋር የሚገናኘውና፡ እነሱም እንደማይለወጡ የሚያሳየው?

‹‹የአላህንም ንግግሮች ለዋጭ የለም›› የሚለውን ሀሳብ የቅዱስ ቁርኣን ተንታኞች (ሙፈሲሮች) በጠቅላላ በአንድ ድምጽ ‹አላህ የወሰነውን መለኮታዊ ውሳኔና ፍርድ፣ ለአማኝ ባሪያዎቹ የገባላቸውን የተስፋ ቃል-ኪዳን ማለት እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ከነዚህም መካከል፡-

ሀ/ ኢማሙል ቁርጡቢይ (አል-ጃሚዑ ሊአሕካሚል-ቁርኣን).
ለ/ ኢማሙል በገዊይ (መዓሊሙ-ተንዚል ፊ-ተፍሲር ወት-ተእዊል).
ሐ/ ጀላሉዲን አስ-ሲዩጢይ (ተፍሲሩል-ጀላለይን).
መ/ አል-ሓፊዝ ኢብኑ ከሢር (ተፍሲር አል-ቁርኣኒል ዐዚም).
ሠ/ አል-ኢማም አሽ-ሸውካኒይ (ፈትሑል ቀዲር)›

ለ. ሱረቱል አንዓም 6፡115፡-

” وَتَمَّتْ كَلِمَتُ رَبِّكَ صِدْقًا وَعَدْلًا لَا مُبَدِّلَ لِكَلِمَاتِهِ وَهُوَ السَّمِيعُ الْعَلِيمُ ” سورة الأنعام 115
“የጌታህም ቃላት እውነተኛና ትክክለኛ ስትኾን ተፈጸመች፡፡ ለቃላቱ ለዋጭ የለም፡፡ እርሱም ሰሚው ዐዋቂው ነው፡፡” (ሱረቱል አንዓም 6፡115)፡፡

ይህም አንቀጽ ከላይኛው ጋር መልእክቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁለቱም በአንድ ሱራ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ መልእክቱንም የቁርኣን ሙፈሲሮች በሁለት ጎን ነው ያዩት፡፡ እሱም፡-

‹‹የጌታህም ቃላት›› የሚለውን ቁርኣን በሚለው ይገልጹትና ሲያብራሩት፡- ቁርኣን በትምሕርቶቹና በዜናዎቹ ፍጹም እውነተኛ፡ እንዲሁም በፍርዱና በውሳኔው ፍጹም ትክክል የኾነ ማለት ነው ይላሉ፡፡

‹‹የጌታህም ቃላት›› የሚለውን የአላህን መለኮታዊ ውሳኔ በማለት በሌላ ጎኑ ይተረጉሙትና ደግሞ ሲያብራ

ሩት፡- አላህ በነቢያት በኩል በገባው ቃል መሰረት እውነትን የበላይ በማድረግ፡ ሀሰትን ደግሞ በማንኮታኮት የተስፋ ቃሉን ሞላልን/ፈጸመልን፡፡ ትክክለኛ ፍርዱንም ፈጸመልን ማለት ነው ብለዋል፡፡ በሁለቱም መልኩ ብናየው መልእክቱ ጤናማ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ ‹‹የአላህን ቃላት›› የሚለውን ግን ወደ ቀደምት መለኮታዊ መጻሕፍት በመውሰድ የተረጎመው የለም፡፡ ይልቁኑ ‹ፈትሑል በያን› በተሰኘው ተፍሲር ላይ ‹‹የጌታህም ቃላት›› ሚለውን ቁርኣን በሚለው ከፈታው በኋላ ሲያብራራው እንዲህ ይላል፡- ‹‹በተውራትና በኢንጂል ላይ የሰው እጅ እንደገባበት ሁሉ፡ ማንም ሰው በቁርኣን ላይ እጁን እንዳያስገባበት በኃይሉ በመጠበቅ እውነተኛና ትክክለኛ አደረገው›› ይላሉ፡፡

ሐ. ሱረቱ ዩኑስ 10፡62-64፡-

” أَلَا إِنَّ أَوْلِيَاءَ اللَّهِ لَا خَوْفٌ عَلَيْهِمْ وَلَا هُمْ يَحْزَنُونَ * الَّذِينَ آمَنُوا وَكَانُوا يَتَّقُونَ * لَهُمُ الْبُشْرَى فِي الْحَيَاةِ الدُّنْيَا وَفِي الْآخِرَةِ لَا تَبْدِيلَ لِكَلِمَاتِ اللَّهِ ذَلِكَ هُوَ الْفَوْزُ الْعَظِيمُ ” سورة يونس 64-62
“ንቁ! የአላህ ወዳጆች በእነሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነሱም አያዝኑም፡፡ (እነሱም) እነዚያ ያመኑትና ይፈሩት የነበሩ ናቸው፡፡ ለእነሱ በቅርቢቱ ሕይወትም በመጨረሻይቱም ብስራት አላቸው፤ የአላህ ቃላት መለወጥ የላትም፤ ይህ እርሱ ታላቅ ዕድል ነው፡፡” (ሱረቱ ዩኑስ 10፡62-64)፡፡

እውነተኛ የአላህ ወዳጆች ማለት፡- በጌታቸው አላህ ያመኑ ኾነው የትም ስፍራ ላይ ቢኾኑ፡ ይህን ጌታቸውን በንግግራቸውም ኾነ በተግባራቸው እንዲሁም በልቦናቸው ሚፈሩት ናቸው፡፡ እነዚህ አማኝ ባሪያዎች፡ ከሞት በኋላ ምን ይገጥመናል የሚል ስጋትም ኾነ፡ ባሳለፉት ምድራዊ ሕይወት ትካዜ አይገጥማቸውም፡፡ እንደውም ገና በቅርቢቱ (ምድራዊ) ሕይወታቸው፡ በህልም አማካኝነት ወይም ሊሞቱ ሲሉ መልካም ብስራት፣ በመጨረሻው ዓለም ደግሞ ጀነት አለላቸው፡፡ ይህ አላህ ለነሱ የገባው ቃል-ኪዳን ነውና፡ የአላህ ቃል ደግሞ በፍጹም አትለወጥም ነው፡፡

የቅዱስ ቁርኣን ተርጓሚዎች ‹‹የአላህ ቃላት›› የሚለውን ከአንቀጹ ላይና ታች ያሉ ተያያዥ ሀሳቦች ጋር በማገናኘት የፈቱት ‹‹የአላህን የተስፋ ቃል-ኪዳን›› በሚለው ነው፡፡

መ. ሱረቱል ከህፍ 18፡27፡-

” وَاتْلُ مَا أُوحِيَ إِلَيْكَ مِنْ كِتَابِ رَبِّكَ لَا مُبَدِّلَ لِكَلِمَاتِهِ وَلَنْ تَجِدَ مِنْ دُونِهِ مُلْتَحَدًا ” سورة الكهف 27
“ከጌታህም መጽሐፍ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ፤ ለቃላቶቹ ለዋጭ የላቸውም፤ ከርሱም በቀር መጠጊያን በፍጹም አታገኝም።” (ሱረቱል ከህፍ 18፡27)፡፡

ይህ አንቀጽ እየተናገረ ያለው ስለ ቁርኣን ነው፡፡ ‹‹ከጌታህም መጽሐፍ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ›› በማለት የሚያናግረው ነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነው፡፡ ወደሳቸው የወረደው መጽሐፍ ደግሞ ‹ቅዱስ ቁርኣን› ነው፡፡ ይህን መጽሐፍ እንዲያነቡ ካዘዛቸው በኋላ፡ ‹‹ለቃላቶቹ ለዋጭ የለውም›› በማለት፡ ይህ ቁርኣን ማንም ሰው ሊለውጠው እንደማይችል ተናገረ ማለት ነው፡፡ የቁርኣኑ ተርጓሚዎችም አቋም ይህ ነው ወላሁ አዕለም፡፡

ሀሳቡን ጠቅለል ለማድረግ፡- ከላይ ባየናቸው አራት የቅዱስ ቁርኣን አንቀጾች ውስጥ ‹‹የአላህ ቃላት›› ተብሎ የተጠቀሰው፡ አላህ አስቀድሞ የወሰነውና የፈረደው መለኮታዊ ቃሉን፣ ለነቢያቱና ለአማኝ ባሪያዎቹ የገባላቸውን መልካም የተስፋ ቃል-ኪዳኑን፣ በከሀዲንና በአመጸኞች ላይ የተዛተባቸውን የቅጣት ቃሉን የሚገልጽ ነው፡፡ በተጨማሪም ለሰው ልጆች የሕይወት መመሪያ ይኾን ዘንድ በነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ አለይሂ ወሰለም) በኩል የተወረደውን ቅዱስ ቁርኣን የሚገልጽ ነው እንጂ፡ ስለ ቀደምት መለኮታዊ መጽሐፍት የሚናገር አይደለም የሚለውን ድምዳሜ መያዝ እንችላለን ማለት ነው፡፡

እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ፡- ቀደምት መለኮታዊ መጽሐፍት (ተውራት. ዘቡር. ኢንጂልና የነቢያት መጻሕፍት) የአላህ ቃል አይደሉም ወይ? የሚል ከኾነም፡ መልሱ፡- አዎን የአላህ ቃል ናቸው! ብለን እንመልሳለን፡፡ ጥያቄውም ይቀጥልና፡- እነዚያ መጻሕፍትም የአላህ ቃል ከኾኑ፡ ለምን እነሱንም ‹‹የአላህ ቃላት መልለወጥ የላትም›› የሚለው ውስጥ አብረው አልተካተቱም? ካሉን ደግሞ ምላሻችን እንደሚከተለው ይቀርባል፡-

1ኛ/ የቅዱስ ቁርኣንን ሀሳብ ለመረዳት አንደኛው መንገድ ሲያቅ (ኮንቴክስት) ማየትና ከግምት ማስገባት ነው፡፡ የአንቀጹን መልእክት ከላይና ከታች ከተጠቀሱት ጋር በማመሳከር ስለምን እየተነገረ እንደኾነ መረዳት ይቻላል፡፡ የቅዱስ ቁርኣን የተፍሲር ሊቃውንትም በጉዳዩ ላይ የሰጡትን ትንተና ማየቱ ለመረዳት የበለጠ ያግዛል፡፡ ከዚህ በመነሳት በአራቱም አንቀጾች ላይ ያሉትን ሀሳቦች ወደ ላይ ወደ ታች ብትመለከቱ፡ እንዲሁም የተፍሲር ሊቃውንትን ሀሳብ ብትመለከቱ፡ ስለ ቀደምት መለኮታዊ መጻሕፍት የሚያወራ ነገር አታገኙም፡፡ ስለዚህ እኛም ከሊቃውንቱ ሀሳብ የወጣ ነገር አይኖረንም ማለት ነው፡፡

2ኛ/ ከቅዱስ ቁርኣን በፊት የነበሩት ቀደምት መለኮታዊ መጻሕፍት፡ ለዘልዓለሙ ተጠብቀው እንዲቆዩ አምላካዊ ዋስትና አልተሰጣቸውም፡፡ የመጽሐፍቶቹም ኾነ የነቢያቱ ተልእኮ በጊዜና በቦታ የተገደበ እንጂ ዘላለማዊና ዘውታሪ አልነበረም፡፡ ከነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በፊት የነበረ መልክተኛ የሚላከው ለሕዝቦቹ እንጂ፡ ለዓለማት አልነበረም፡፡ መልእክቱም ተልእኮውም በሕዝቦቹ ላይ ብቻ የተገደበ ነበር፡፡ ደግሞም ነቢይ በሞተ ቁጥር፡ ወዲያውኑ ሌላ ነቢይ በማስነሳት ይተካላቸው ስለነበር፡ ትምሕርቱ ቢጠፋ እንኳ ያ ከኋላ የተነሳው ነቢይ ያድስላቸው ነበር ማለት ነው፡፡

ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐሌሂ ወሰለም) ግን የተላኩት በየትኛውም ዘመንም ኾነ በየትኛውም ስፍራ ለሚኖር የሰው ዘር በጠቅላላ በመኾኑ (4፡79፣ 7፡158፣ 21፡107፣ 34፡28) ቁርኣንም የወረደው እንደዛው ለዓለማት ሕዝቦች የሕይወት መመሪያ እንዲሆን ስለኾነ (6፡90፣ 25፡1፣ 68፡52) ትንሳኤ/ቂያማ እስኪመጣና እስኪከሰት ድረስ ጌታ አላህ ‹‹እኔው እንዳወረድኩት እኔው እጠብቀዋለሁ›› በማለት ቃል ገባለት (ሱረቱል-ሒጅር 15፡9)፡፡

ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐሌሂ ወሰለም) የነቢያት መደምደሚያ በመኾናቸውና ከሳቸው በኋላ ከአላህ ዘንድ የሚላክ ነቢይ ባለመኖሩ ሰበብ፡ አላህ የኢስላምን መልእክት እስከመጨረሻው ዘመን ማብቂያ ድረስ ሊጠብቀው ቃል ገባ፡፡ ቃል በገባለት መሰረትም፡ ዲኑ እስካሁን ሳይበረዝና ሳይደለዝ አልለ ማለት ነው፡፡ ቀደምት መጻሕፍት ግን ምንም በውስጣቸው የአላህ ቃላት ቢኖሩም የሰው ሀሳብና ስህተቶችንም አብረው አቅፈዋል፡፡ ስለዚህ ‹‹መልለወጥ የላትም›› የሚለው ውስጥ መካተት የሚችለው ቁርኣን ነው፡፡

3ኛ/ በብዙ የቅዱስ ቁርኣን ክፍሎች ላይ ቀደምት መለኮታዊ መጽሐፍት የሰው እጅ እንደገባባቸውና እንደተበረዙ ተገልጾአል፡፡ ከዚህ በመነሳትም ‹‹የአላህ ቃላት መልለወጥ የላትም›› የሚለውን ለቀደምት መለኮታዊ መጻሕፍት መተርጎሙ የሚያስኬድ አይደለም ማለት ነው፡፡ ከነዚህም የቁርኣን ክፍሎች ውስጥ አንዱ እንዲህ ይላል፡-

” فَوَيْلٌ لِلَّذِينَ يَكْتُبُونَ الْكِتَابَ بِأَيْدِيهِمْ ثُمَّ يَقُولُون

َ هَذَا مِنْ عِنْدِ اللَّهِ لِيَشْتَرُوا بِهِ ثَمَنًا قَلِيلًا فَوَيْلٌ لَهُمْ مِمَّا كَتَبَتْ أَيْدِيهِمْ وَوَيْلٌ لَهُمْ مِمَّا يَكْسِبُونَ ” سورة البقرة 79
“ለነዚያም መጽሐፉን በእጆቻቸው ለሚጽፉና ከዚያም በርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት «ይህ ከአላህ ዘንድ ነው» ለሚሉ ወዮላቸው፡፡ ለነርሱም ከዚያ እጆቻቸው ከጻፉት ወዮላቸው፡፡ ለነሱም ከዚያ ከሚያፈሩት (ኃጢኣት) ወዮላቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡79)፡፡

በዚህ የቅዱስ ቁርኣን አንቀጽ ላይ ታዋቂው የቁርኣን ተንታኝና ሊቅ የኾነው ታላቁ ሶሓቢይ ዐብዱላህ ኢብኑ ዐብባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንዲህ ይላል፡-

عَنْ عَبْدِ اللَّهِ بْنِ عَبَّاسٍ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُمَا، قَالَ: ” يَا مَعْشَرَ المُسْلِمِينَ، كَيْفَ تَسْأَلُونَ أَهْلَ الكِتَابِ، وَكِتَابُكُمُ الَّذِي أُنْزِلَ عَلَى نَبِيِّهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ أَحْدَثُ الأَخْبَارِ بِاللَّهِ، تَقْرَءُونَهُ لَمْ يُشَبْ، وَقَدْ حَدَّثَكُمُ اللَّهُ أَنَّ أَهْلَ الكِتَابِ بَدَّلُوا مَا كَتَبَ اللَّهُ وَغَيَّرُوا بِأَيْدِيهِمُ الكِتَابَ، فَقَالُوا: هُوَ مِنْ عِنْدِ اللَّهِ لِيَشْتَرُوا بِهِ ثَمَنًا قَلِيلًا، أَفَلاَ يَنْهَاكُمْ مَا جَاءَكُمْ مِنَ العِلْمِ عَنْ مُسَاءَلَتِهِمْ، وَلاَ وَاللَّهِ مَا رَأَيْنَا مِنْهُمْ رَجُلًا قَطُّ يَسْأَلُكُمْ عَنِ الَّذِي أُنْزِلَ عَلَيْكُمْ ” رواه البخاري 2685.7522.7523
ዐብዱላህ ኢብኑ-ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንዲህ ይላል፡- “እናንተ ሙስሊሞች ሆይ! በነቢዩ ላይ የተወረደላችሁ መጽሐፍ (ቁርኣን) ከአላህ ዘንድ የመጣ አዲስ (ያላረጀ) ሆኖ ሳለ፡ እናንተም ያልተበረዘና የሰው እጅ ያልገባበት ሆኖ እያነበባችሁት፡ የመጽሐፉን ሰዎች (አይሁዶችና ክርስቲያኖች) እንዴት ትጠይቃላችሁ? አላህም (በቁርኣኑ) የመጽሐፉ ሰዎች መጽሐፉን በእጃቸው እንደበረዙትና እንደቀየሩት፣ ከዛም የተበረዘውን ጥቂትን ምድራዊ ዋጋ ለመሸመት፡ ይህ ከአላህ ዘንድ የመጣ ነው እንዳሉ ነግሯቹኋል፡፡ እንግዲያውስ ወደናንተ የመጣላችሁ ዕውቀት እነሱን ከመጠየቅ አይከለክላችሁምን? በአላህ ይሁንብኝ! ከነሱ ውስጥ አንድም ሰው ወደናንተ ስለወረደው ሲጠይቁአችሁ በፍጹም አላየንም (ታዲያ እናንተ እነሱን እንዴት ትጠይቃላችሁ?)” (ቡኻሪይ 2685፣ 7522፣ 7523)፡፡

4ኛ/ ወገኖቻችን እንደሚሉት ‹‹የአላህ ቃላት መለወጥ የልላትም›› የሚለው እነሱ ዘንድ ያለውን መጽሐፍ ‹መጽሐፍ ቅዱስ›ንም የሚጨምር ከኾነ፡ እንግዲያውስ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ለምን አንድ ወጥ አልኾነም? ለምን ሁላችሁም የምትይዙት አንድ አይነት አልኾነም? የአንደኛው ግሩፕ በውስጡ 66 መጻሕፍት ያሉት፣ የሌላኛው ደግሞ 73 መጻሕፍትን በውስጡ የያዘ፣ ሶስተኛው ደግሞ 81 መጻሕፍትን ያቀፈ መጽሐፍ ለምን ኾነ? ይህ በራሱ ለመጽሐፉ መለወጥ በቂ ማስረጃ አይሆንምን? በማለት ልንጠይቃችሁ እንወዳለን፡፡